Saturday, 20 April 2024 11:10

አባቱ ማነው?

Written by  በተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ (ዶ/ር)
Rate this item
(3 votes)

ክፍል አንድ
በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2005 ዓ.ም (2012)፣ በሰሜኑ ኢትዮጵያ፣ በትግራይ ምዕራባዊ አስተዳደር፣ የሽሬ እንደሥላሴ ነዋሪዎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነበሩ፡፡ በርካታ ሰዎች መነሾው ባልታወቀ የጉበት በሸታ አልጋ

ላይ ውለዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ሕይወታቸው ዐልፏል፡፡ የበሽታው መንስኤ አለመታወቅ ችግሩን አባብሶት የሚያዘው የሚጨበጠው ግራ ገብቶ ነበር፡፡ በዚኽም መነሻነት ነበር መንስኤው እንዲታወቅና ተገቢው ሳይንሳዊ

ምርምርና ጥናት እንዲደረግ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የ“እርዱኝ” ጥሪ ያቀረበው፡፡ ለዚኹ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ስፍራው ከተጓዙት ባለሙያዎች አንዱ ነበርኩኝ።
 ለጥናቱ የበኩሌን ድርሻ ለማበርከት ከምሠራበት መሥሪያ ቤት በተሰጠኝ ኃላፊነት መሰረት እቃዬን  ሸክፌ፣ ከሦስት የሥራ ባልደረቦቼ ጋር ከአሜሪካ፣ አትላንታ ከተማ ረጅሙን ጉዞ ተያያዝነው። አውሮፕላኑ፣

ሰዉንም ሻንጣውንም አጭቆ በመንደርደሪያ ቍጥር ዐራት፣ በመነሻ አቅጣጫ 007 አፍንጫውን አሰግጎ ለማኮብከብ ተዘጋጅቷል። የበረራ አስተናጋጆቹ መንገደኞች ቀበቷችንን በተገቢው መንገድ ማሠራችንን

አረጋግጠው፣ እነሱም ከወንበራቸው ጋር ተጣብቀዋል።
በመጠኑ ይጮህ የነበረው የአውሮፕላኑ ድምጥ ተቀይሮ፣ ከባድ ጭነት እንደተከመረበት መኪና ያጓራ ጀመር። አከታትሎም ሯጮች ፊሽካ ሲነፋላቸው እንደሚወነጨፉት፣ አውሮፕላኑም ከማማው ፊሽካ የተነፋለት

ይመስል፣ ተንደርድሮ ተስፈነጠረ። የፊት ጎማዎቹ ከምድር መልቀቅ ሲጀምሩ፣ መሬት ላይ ዕቃ የቀረን ይመስል፣ ልቤ ቍልቍል ትጎተት ጀመር። አውሮፕላኑ ሽቅብ፣ የእኔ ልብ ቍልቍል! ከዚኹ ጋር ተያይዞ በመጠኑም

ጆሮ የመደፈንና አንጀት የመንጠልጠል ዐይነት ስሜቶች ተሰሙኝ። 10‚000 ጫማ ከፍታ ላይ እንደ ደረስን፣ መንቀሳቀስ እንደሚቻል መልእክት ተላለፈ፡፡ ከዚኽ በኋላ ያለው ጉዞ፣ “እየበሉ እየጠጡ ዝም፣ የጋን

ወንድም” ኾኖ ከደመናው በላይ መክነፉን ተያያዝነው፡፡
በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ከደመናው በላይ እንቅልፍ ወሰድ፣ መለስ ሲያደርገኝ አሰላስል የነበረው፣ ቀደም ባሉት የሽሬ ጉዞዎቼ ያየኋቸው ሕፃናትንና አዛውንቶችን በራሳቸው ታሪክ የሚናገሩ ገጽታዎችን ነበር፡፡ በተጨማሪም

ስለ ሕመማቸው መንስኤ የማወቅ ጉጉትና ጭንቀታቸው ለአዕምሮዬ ዕረፍት ሳይሰጠው፣ አትላንታን ከለቀቅን ከስምንት ሰዐት ከሠላሳ ደቂቃ በረራ በኋላ፣ በመጀመሪያዋ መዳረሻችን በጀርመኗ ፍራንከፈርት ከተማ

ዐረፍን። የኹለት ሰዐት ቆይታ አድርገንም፣ አውሮፕላን ቀይረን፣ ቅዳሜ ዕለት ከምሽቱ ኹለት ሰዐት ተኩል አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ደረስን።
የጉዞ ሰነድና የመግቢያ ፈቃዳችን ተፈትሾ አልፈንና ምርመራውን ለማካኼድ ይዘን የመጣናቸው ብዛት ያላቸው ዕቃዎችን የፍተሻ ውጣ ውረድ ጨርሰን፣ ከምሽቱ ዐምስት ሰዐት ማረፍያ ሆቴላችን አዲስ አበባ ሂልተን

ገባን።
እሑድ ጠዋት ጉዞ ከሽሬ 62 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው አክሱም ከተማ ኾነ። ፎከር አውሮፕላናችን ዐምሳ መንገደኞችን አሳፍራ ስድስት ሰዐት ላይ አክሱም ደረሰን። ዕቃዎቻችንን ኹሉ ይጠብቁን በነበሩት

ላንድኩሩዘር መኪናዎች ጭነን፣ ጉዞ ወደ ሽሬ እንዳሥለሴ ከተማ ኾነ፡፡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ምልክት የኾኑትን የአክሱም ሐውልቶች በስተቀኝ እያየን ጥቂት እንደተጓዝን፣ የታላቋ ንግሥት ሳባን ቤተ

መንግሥት ፍርስራሸ ግንብ ዐልፈን፣ ተራራማ መንገዱን ተያያዝነው። ትኵረት እንዳልተሰጠው የሚያሳብቀውን የንግሥት ሳባ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ እያየሁ ቍጭት ሲጎነትለኝ ተሰማኝ፡፡ “ሌሎች አገራት ይኼ

ቢኖራቸው ኖሮ--!”
ጠመዝማዛና ቀጥ ያሉ መንገዶች እየተፈራረቁብን ስንጓዝ፣ በዐይነ ኅሊናዬ የሚመጡብኝ፣ እነኛ ስለ ሕመማቸው ኹኔታ ቍርጡን ለማወቅ የሚጓጉት አዛውንቶች፣ እናቶች፣ ልጆች፣ የጠመጠሙ ቄሶች፣ ዲያቆናት  ነበሩ።

እኛ ጭንቀታቸውን ተረድተንላቸዋል፡፡ እነሱ ግን የእኛን ጭንቅት  የሚያውቁልን አልመሰለኝም። ባለሙያዎችን ሳይቀር ግራ ያጋባው፣ ለዐሥር ዓመት ገደማ የታማሚዎችን ሆድ እያሳበጠ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈው

 ስም አልባ በሽታ መንስኤው  ምን ይኾን? እስከዚያን ጊዜ ድረስ ስለ መንስኤው ምንም ፍንጭ ባይኖርም፣ የአካባቢው ሕዝብና ሕሙማኑ ግን እኛን ከእግዚአብሔር በታች ኹሉንም ያወቃሉ ብለው

ስለሚገምቱ፣ እየመጣን መኾናችንን ሲያወቁ፣ ቍርጣቸውን ለመስማት ምን ያኽል እንደሚጓጉ ሳስበው፣ እጅጉን ያስጨንቀኝ ጀመር፡፡  
በሽሬ ከተማ ከውጭ የመጣነው የምርምር ቡድን አባላት፣ ከአገር ውስጥ ከተውጣጡ ባለሙያ ጠበብቶች ጋር ተገናኝተን፣ ዐሳብ ከተለዋወጥን በኋላ፣ የጋራ የሥራ ዕቅዳችንን አወጣን። ዕቅዱም በድጋሚ ሕሙማኑ

በብዛት የሚገኙባቸውን መንደሮች መጎብኘት፣ የደም ናሙና ከሰዎችም ከቤት እንስሶችም መውሰድ፣ እንዲኹም የተወሰኑ ሕፃናትና አዋቂ ሕሙማንን ወደ ሽሬ ሆስፒታል አምጥተን  ከጉበታቸው በመርፌ ናሙና

ቆንጥበን መውሰድ ሲሆን በተጨማሪም  የተለያዩ እህሎችን፣ ማር፣ ወተት ከሕሙማን ቤት፣ ከጎረቤት፣ ከሽሬ ገበያ ማሰባሰብን ያካትታል። በቆየንባቸው ዐምስት ቀናት በዕቅዳችን መሰረት ሁሉንም   ፈጽመን

ቅዳሜ አዲስ አበባ ተመለስን።
 በጉዞ ወቅት እነኛ፤ “ንገሩን፣ ችግሩ ምንድነው?” የሚሉት ዐይኖች፣ በመቧረቂያቸው ሰዐት ሆዳቸው አብጦ ለመሮጥ የሚቸገሩት ሕፃናት በዐይነ ኅሊናዬ እየተመላለሱብኝ ተጨነቅሁ፡፡ አዲሰ አበባ ደርሰን ወደ ማረፍያ

ሆቴላችን ገባን። ዳግም እነኛን ልጆች ሳስታውስ፣ እኔም የልጆች አባት ነኝና እንባ ይተናነቀኝ ነበር። በክፍሌ ውስጥ ታዛቢ በሌለበት እስኪወጣልኝ ድረስ አነባሁ፡፡ በተለይ ያነሳኋቸውን ፎቶግራፎች አስተውዬ ስመለከት፣

ሕይወት እንደ ሻማ ሲቀልጥ፣ ምክንያቱ  እስከሚታወቅና መፍትሔው እስከሚገኝ ድረስ የሚያልፈው ሕይወት በርካታ እንባ አስለቃሸ ጢሶች በአዕምሮም፣ በልብም ውስጥ እያፈነዱ በሲቃ ሰቅዘው ይይዛሉ። የጨለማ

ውስጥ ሲቃ!
በአዲስ አበባ ቆይታዬ ከሽሬ ካመጣነው ጥራጥሬና እህል በተጨማሪ፣ ለንጥጥር ይረዳን ዘንድ እዛው ከተማው ውስጥ ከሚገኘው ግዙፉና ከመላው ኢትዮጵያ እህል ወደ ሚመጣበት አማኑኤል እህል በረንዳ ዘልቄ፣

የቻልኩትን ያኽል እህል በናሙናነት ገዛሁ። ዐርፈንበት በነበረው አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴልም በአንደኛችን ክፍል ያሰባሰብናቸውን ናሙናዎች በአግባቡ አሸግናቸው። ከአገር ውስጥ መውጫ ፍቃድ፣ አሜሪካን አገር

የመግቢያ ፈቃድ፣ ልዩ መግለጫ ምልክቶች እንዲኹም የአያያዝ መመሪያ ወረቀቶችን ለጣጥፈን፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ተቋም ላብራቶሪ ውስጥ ያስቀመጥነውን የደምና ጉበት ናሙና በደረቅ በረዶ

(ከካርበን ሞኖክሳይድ ሠርተን) በልዩ መያዣዎች አሽገን፣ ከሽሬ በገባን በኹለተኛው ቀን ቦሌ ለሚገኘው አንዱ ዕቃ አስተላላፊ ወኪል ተገቢውን ክፍያ ከፍለን አስረከብን። ከሠላሳ ስድስት የበረራ ሰዓታት በኋላም፣

በደቡብ አፍሪካ በኩል አድርጎ ወደ መዳረሻው የምርምራ ማዕከል እንደሚደርስ አረጋግጠውልን ተመለስን። እኛም ምሽቱን ከአዲስ አበባ ተነስቶ፣ በፍራንክፈርት በኩል አትላንታ የሚደርሰውን በረራ ለመያዝ፣

ዝግጅታችንን ቀጠልን።
ከውጣ ውረዱ በኋላም፣ አዲስ አበባን ከረገጥኩ ሳልቀምሳት የማልመለሰውን የቶሞካ ቡና ፉት ለማለት፣ ከቦሌ በቀጥታ ያመራሁት፣ ወደ ካቴድራል ትምህርት ቤት አካባቢ ነው። በቤተሰብ መኪና ቸርችል ጎዳናን

ሽቅብ ወጥተን፣ ባንኮ ዲሮማ አጠገብ ያለው የትራፊክ መብራት ጋ ስንደርስ፣ ወደ ግራ ታጥፈን ከመንገድ በስተቀኝ መጀመሪያ ላይ ያለችው ታሪካዊ ሕንጻ ጋ ደረስን። በዐምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ዘመን

ተከፍታ እስከ አኹን ጠጪውንም ኾነ ዐላፊ አግዳሚውን በቡና ስታጥን የምትኖረው፣ ዝናዋ በርካታ ጎብኝዎች ልብ ውስጥ የናኘው ቶሞካ፤  መኪና ማቆሚያም ኾነ በርከት  ያለ ሰው ማስተናገጂያ  በቂ ቦታ

የላትም። ቶሞካ ውስጥ ያዘዝኩትን  ቡና እንደወረደ ፉት ለማለት ስዘጋጅ፣ የእጅ ስልኬ አንቃጨለች። “ሃሎ፣ ጤና ይስጥልኝ፣ ማን ልበል?” አልኹ።
“ሃሎ ዶክተር… ሰላም ዋሉ?” አለኝ፣ የማላውቀው ድምጥ፡፡
“እንዲላክ ቦሌ ያስገባችሁት ዕቃ ነበር።”
“አዎን ጌታዬ፡፡ ተጫነ?” አልኹት፣ እንደተጫነ እርግጠኛ በመኾን። አላስጨረሰኝም!
“አይ፣ ይኼ ነገር እኮ ችግር አለው። ከአገር ውስጥ መውጣት አይችልም። እላዩ ላይ ‘ሊቨር ዲዚዝ (የጉበት በሽታ)’ ስለሚል፣ በሽታ ደግሞ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ አገር ያስወቅሳል፣ ወንጀልም ነው!

ስለዚኽ መጥታችሁ ውሰዱ” አለ፣ እየነገረኝ ሳይኾን እያዘዘኝ።
ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ። ስልኬን ሳልዘጋው ይዤ ከጠባቧ ቡና ቤት ወደ መንገዱ ወጣሁ።
“ለመኾኑ አንተ ማነህ? የተለጣጠፉትን የፈቃድ ወረቀቶች አታነብም! ነው ወይስ ትርጕሙ አይገባህም?” አልኹት፣ እልሄ ሰውነቴን እያርገፈገፈው፡፡
 በአካል ፊት ለፊቱ ብኾን ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አላውቅም። ምናልባትም ዶቃ ማሰሪያው ድረስ…።
 “ይስሙ ዶክተር፣ በእኔ በኩል ባለው መመሪያ መሠረት ተናግሬያለሁ! ይምጡና ዕቃችሁን ይውሰዱ” አለ፣ ግትር ባለ አባባል።
“ስማ፣ ወይ ናሙናው ኤክስፖርት ይደረጋል፣ ወይም አንተ ከቢሮህ ትወጣታለህ!” አልኩትና ስልኩን ጠረቀምኩት። የሐረር ልጅነቴ መጣብኝ! “ኢጆሌ ጉርሱም ፉኛን ቢራ! ለፍቶ መና!” ያ ኹሉ ድካም

በእንደዚኽ ያለ ሰው ሜዳ ላይ ሊቀር!
ሰዐቱ 10፡30 ይላል፡፡ መፍትሔ ከተገኘ ብዬ ችግር ሲገጥመኝ በማንቀሳቅሰውና እንደ ሸረሪት በተዘረጋው መረቤ በአቶ መስፍን ተፈራ በኩል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሕክምና ክፍል ኀላፊ ዶ/ር ዓይናለም

ገብረማርያም ጋር ተደዋወልን። እሱም ዕቃው በመንገደኞች ሳይኾን በጭነት ክፍል በኩል ስለ ኾነ፣ በእሱ በኩል ምንም ሊረዳን እንደማይችል አስረዳኝ። ተስፋ ልቆርጥ አፋፍ ላይ ደርሼ ሳለሁ፤ “ምንጊዜም ተስፋ

አትቁረጥ!” የምትል በአንድ ፈረንሳዊ የተሳለች ስዕል ትዝ አለችኝ። ሲቸግረኝ ከፊቴ ድቅን የምትለውን የዳክዬዋን አንገት አንቃ የምትንፈራገጠውን እንቍራሪትም አስታወሰኩ፡፡ የመጨረሻ ሙከራ። የሞት ሽረት ጥረት!

ይኼ ዕቃ ወይ ይወጣል፣ ወይ ይቃጠላታል!
በወቅቱ የኢትዮጵያ ጤናና ሥነ ምግብ ምርምር ማዕከል  ምክትል ዋና ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ዳዲ ጅማ ዘንድ ደወልኩላቸው፡፡  የድረሱልን ጥሪ ማለት ይቀላል፡፡ በውስጤ “ስብሰባ ላይ ይኾኑ ይኾን?” የሚል

ሥጋት ነበረብኝ፡፡
ከኹለት ጥሪ በኋላ ስልካቸውን አነሱልኝ።
“ሰላም ዶክተር” አሉኝ፤ “ኹሉም ነገር ተሳካ?”
“ምን ይሳካል! ያልጠበቅነው፣ ከየት የመጣ አለቃ እንደ ኾነ አላውቅም ቦሌ ላይ ይፎክራል። የደወልኩት ወይ መፍትሔ እንድትሰጡን፣ ወይ እኔ ያልተሳካ ተልእኮ ችግር ያዘለ ዘገባዬን ለላከን መሥሪያ ቤት

ልስደድና ያኔ ማን እንደሚወቀስ ይታያል!” አልኳቸው  ጠበቅ አድርጌ። ቃላቶቹን አልወረወርኳቸውም፣ እንደ ጥይት አንጣጣኋቸው እንጂ፡፡ ትንፋሼ ቍርጥ፣ ቍርጥ እያለ በየመኻሉ ይገባል፡፡
“ግድየለም፣ ለእኔ ተወው፡፡ ምንም መልእክት እንዳትልክ! እኔ የጤና ምክትል ሚንስትር ዶ/ር ከበደ ወርቁ ዘንድ አኹኑኑ እደውላለሁ። ሠላሳ ደቂቃ ብቻ ስጠኝ፡፡ ግድየለም ዶክተር፣ ተረጋጋ” በማለት ለማረጋጋት

ሞከሩ።
በተምታታ ስሜት ወደ ቶሞካ  ተመለስኩኝ፡፡ ‘አኹንስ በዛ! ይኼ ኹሉ ሥቃይና መከራ፣ ቢሮክራሲ! በምን ዕዳችን ሥራቸውን ሳያውቁ ወንበር ላይ በተቀመጡ ከንቱዎች እንሰቃይ?’ እያልኁ እያጉረመረምኩኝ ወደ

ቡና ስኒዬ ተመለሰኩኝ። የምወዳት ቡና ቀዝቅዛ ኖሮ እንደገና አስሙቄ ተጎነጨሁ፣ አላረካችኝም። ድጋሚ አዘዝኩና ይዤው የምኼደውን ዐምስት ኪሎ የተፈጨ ቡና ገዝቼ፣ ኹለተኛ ስኒ ቡናዬን እያገባደድኩ ሳለ

ስልኬ አንቃጨለች፡፡   “ሄሎ ዶክተር፣ ዳዲ ነኝ፡፡ በጣም ይቅርታ። አንዳንድ አሉ መቼም… እንዲኽ ናቸው  ለማለት የሚከብዱ። ነገሩ ተቃሏል! ችግሩ ተፈቷል። ከማስጠንቀቂያ ጋር አስቸኳይ ትእዛዝ ተሰጥቷል።

ዕቃውም ተጭኗል። መልካም መንገድ ይኹንላችሁ። ውጤቱን ቶሎ እንደምትልኩልን እንተማመናለን” ሲሉ አበሰሩኝ።
“እኔም አመሰግናለሁ፡፡ ም/ሚኒስትሩን አመስግኑልኝ” አልኳቸው፡፡ከስጋት ወጥቼ  ትንሽ ተንፈስ አልኹ፡፡ ተመስገን! ብዬ  ጉዞ ወደ ሻንጣ ሽከፋ አደረግኹ!
አገር ቤት ተኺዶ ባዶ እጅ መመለስ የለምና የገዛሁትን የቶሞካ ቡና፣ ቤተሰብ ያዘጋጀውን ሽሮና በርበሬ ወዘተ… አሣሥሬ ከምሽቱ ዐራት ሰዐት ከአዲስ አበባ ተነስቶ በፍራንክፈርት በኩል የሚበረውን የሉፍታንዛ አየር

መንገድ ተሳፍሬ፣ ጉዞ ቀጠልኩ። ይኼኛው ጉዞ የዐሳብ ውጣ ውረድ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ከነበረው ከመብዛቱ በቀር፣ ብዙም የተለየ አይደለም። በጉዞው ወቅትም በዐሳቤ ከሚመላለሱት ሕሙማን በተጨማሪ፣

‘የላክናቸው የምርመራ ናሙናዎች በሰላም ይደርሱ ይኾን? ነው ወይንስ ይበላሹ? ከነአካቴውም ይጠፉ ይኾን?’ የሚሉት ዐሳቦች እጅጉን ያስጨንቁኝ ነበር። በተለይም በስንት መከራ የተዘጋጀው የጉበት ናሙና

ከጠፋ ወይም ከተበላሸ ለፍቶ መና መኾናችንን ሳስብ ደግሞ ጭንቀቴ ይብስበታል፣ መፍትሔ የሌለው ጭንቀት!  (ይቀጥላል)

Read 1172 times