Saturday, 20 April 2024 11:04

ከቀዶጥገና ወሊድ በኋላ በምጥ መውለድ.....

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

“ከዚህ ቀደም 1 ጊዜ በቀዶጥገና አማካኝነት የወለዱ እናቶች በቀጣይ በማህፀን ወይም በቀዶ ጥገና የመውለድ እድል (አማራጭ) አላቸው”
የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መብርሃቱ ተኽለ
በዚህ እትም እናቶች በቀዶጥገና ከወለዱ በኋላ በምጥ መውለድ ስለሚችሉበት ሁኔታ አስመልክቶ ልናስነብባችሁ ያሰናዳነውን የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ከሆኑት ከዶ/ር መብርሃቱ ተኽለ ማብራሪያ

አስቀድሞ የ2 እናቶችን ልምድ እናካፍላችሁ።
“ሀረግ እባላለው። የ2 ልጆች እናት ነኝ። ሁለቱንም ልጆቼን በቀዶጥገና ነው የወለድኩት። ለብዙ ጊዜ ቁስሉ ህመም ሆኖብኝ ቆይቷል፣ ክብደቴ ጨምሯል፣ ከብዙ ነገሮኝ ተገድቤያለው እና በምጥ የወለዱ ሴቶች

እድለኛ መሆናቸውን አስባለው። ከዚህ በኋላም በምጥ መውለድ አለመቻሌን ሳስበው በእራሴ አዝናለው። በእርግጥ የመጀመሪያ ልጄን በቀዶጥገና መውለዴ ህይወቴን ታድጎልኛል። ነገር ግን ሁለተኛ ልጄን በምጥ

መውለድ እችል እንደነበር ውጪ ሀገር የምትኖር ጓደኛዬ ስትነግረኝ ቁጭት ተሰማኝ። ባለቤቴ ዋናው በሰላም መገላገልሽ ነው እያለ ይገስፀኛል። እኔ ግን የእናትነትን አምጦ የመውለድ ወግ ማየት ደስ የሚል

ይመስለኛል። እኔ ሁለቱንም ልጆቼን ስወልድ የመውለድ ትርጉሙ (ስሜት) ሳይገባኝ ነው ልጆቼን አቅፌ የተመለስኩት።” ሀረግ ተስፋዬ
“አንድ ልጅ አለኝ። ልጄን የወለድኩት ሆስፒታል ውስጥ በምጥ ነው። ምጥ ከ1 ቀን በላይ ቆይቶብኛል። የነበርኩበት ስፍራ ከልጄ አባት እና ከቤተሰቦቼ ሩቅ ስለነበር ብቻዬን ነበርኩ። ይህ ደግሞ ሁኔታውን

ይበልጥ አባሰብኝ። በህይወቴ ከባድ የምለውን ጊዜ ያሳለፍኩበት ወቅት ነበር። ሆስፒታሉ ገጠር ውስጥ በመሆኑ ይመስለኛል እንጂ በቀዶጥገና መውለድ እንደነበረብኝ አስባለው። የልጄ ክብደት ትልቅ ነበር፣ ምጡ

ረዥም ነበር እና ደግሞ አቅሙም አልነበረኝም። ብቻ ከእግዚአብሔር ጋር ነው በህይወት የተረፍኩት! ከወለድኩም በኋላ የተሰራልኝ ስቲች ተፈቶ ስለነበር ሌላ ህመም ውስጥ ነበርኩ። እግዚአብሔር ፈቅዶ ከዚህ

በኋላ ልጅ ከወለድኩ በቀዶጥገና የምወልድ ይመስለኛል። እናቶች የምጥ ወቅት ይረሳል ይላሉ እኔ ግን እኔንጃ...... አልመሰለኝም።” መሰረት ከድር ከቃሊቲ
የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) መረጃ እንደሚያሳየው በቀዶጥገና የሚወልዱ እናቶች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ልጅ ከሚወልዱ 5 እናቶች ውስጥ 1 እናት በቀዶጥገና

ትወልዳለች። ይህ ቁጥር በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት እየጨመረ እንደሚሄድ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። ድርጅቱ በቀዶጥገና መውለድ አስፈላጊ እና ሕይወት አድን እንደሆነ ገልጾ ነገር ግን አስፈላጊ

ባልሆነበት ወቅት ከተከናወነ እናቶች እንዲሁም ሕፃናት ላይ ለአጭር እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁሟል።
ከዚህ ቀደም በቆዶጥገና የወለዱ እናቶች በቀጣይ በቀዶጥገና መውለድ እንዳለባቸው የሚደነግገው አሰራር ከ30 ዓመታት በፊት ነው መለወጥ የጀመረው። ከዛም አንድ ጊዜ በቀዶጥገና የወለደች እናት በቀጣይ

(ሁልጊዜ) በሆስፒታል ውስጥ መውለድ አለባት በሚል መርህ ተተካ። የአሜሪካ ነፍሰጡር (እርግዝና) ማህበር (American pregnancy association) እንዳስቀመጠው በቀዶ ጥገና ከወለዱ እናቶች

መካከል ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት እናቶች በቀጣይ እርግዝና ስኬታማ በሆነ መልኩ በማህፀን (በምጥ) መውለድ ችለዋል።
የኢትዮጵያ የፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር 32ኛ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ከቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች መካከል በአይደር እና መቐለ ሆስፒታል ከዚህ ቀደም በቀዶጥገና ወልደው የነበሩ እናቶች በቀጣይ እርግዝና

[ወሊድ] ወቅት ስለነበራቸው ሁኔታ የተደረገ ጥናት አንዱ ነው። ጥናቱ ከዚህ ቀደም 1 ጊዜ በቀዶጥገና የወለዱ እናቶች በቀጣይ በማህፀን ወይም በቀዶ ጥገና ለመውለድ ስለሚያስፈልጋቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣

ለእናት እና ለህፃናት ያለው ጥቅም እንዲሁም ጉዳት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ጥናታዊ ፅሁፉን ያዘጋጁት የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መብርሃቱ ተኽለ ናቸው።
“ከዚህ ቀደም 1 ጊዜ በቀዶጥገና አማካኝነት የወለዱ እናቶች በቀጣይ በማህፀን ወይም በቀዶ ጥገና የመውለድ እድል(አማራጭ) አላቸው” ብለዋል ዶ/ር መብርሃቱ ተኽለ። አክለውም ጥናቱ በሁለቱ መንገድ

በወለዱ እናቶች እና በተወለዱ ህፃናት መካከል ስላለው ሁኔታ (ልዩነት) ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል። በአይደር ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንዲሁም በመቐለ ጠቅላላ ሆስፒታል በ5 ወራት ውስጥ

5ሺ 6መቶ 54 እናቶች ወልደዋል። ከእነዚህም ውስጥ 376 እናቶች ከዚህ ቀደም 1 ጊዜ በቀዶጥገና ህክምና የወለዱ ናቸው። እንደ ዶ/ር መብርሃቱ ተክለ ንግግር 300 የሚሆኑ እናቶች በማህፀን መውለድ

(መሞከር) የሚችሉ ነበሩ።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መብርሃቱ ተኽለ እንደተናገሩት በማህፀን (ምጥ) መውለድ ይችላሉ ተብለው ከተለዩት 300 እናቶች ውስጥ ለመሞከር ፍቃደኛ የሆኑት 183 እናቶች ናቸው።

134 እናቶች ያለ ምንም ችግር በማህፀን (ምጥ) መውለድ ችለዋል። የተቀሩት 49 እናቶች ባጋጠማቸው የተለያየ ችግር ምክንያት በድጋሚ በቀዶጥገና እንዲወልዱ ተደርጓል።
ከዚህ ቀደም በቀዶጥገና የወለዱ እናቶች በቀጣይ በማህፀን(ምጥ) ለመውለድ የሚያስፈልጓቸው መስፈርቶች
እናት ላይ ተጓዳኝ በሽታ አለመኖር
ልጅ(ፅንስ) በወሊድ ወቅት በጭንቅላት መምጣት አለበት
ፅንሱ ከ4 ኪሎ ግራም መብለጥ የለበትም
የማህፀን ጫፍ ልጅ ለመውለድ በቂ ስፋት ሊኖረው ይገባል
ከ42 ሳምንት በላይ የሆነ ወይም ከ37 ሳምንት የቀደመ[በታች] እርግዝና መሆን የለበትም
የተፀነሰው ልጅ ሁለት እና ከሁለት በላይ መሆን የለበትም
ምጥ በእራሱ (በተፈጥሯዊ መንገድ) መምጣት አለበት
በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የተሰራው የቀዶጥገና ህክምና አይነት (ቀዶጥገና የተሰራበት ቦታ እና አሰራር) በምጥ ወይም በቀዶ ጥገና ለመውለድ ወሳኝነት አለው። እንዲሁም አንዲት እናት በቀዶጥገና ከወለደች በኋላ

በምጥ የመውለድ እድል የሚኖራት በቀዶጥገና የወለደችው 1 ጊዜ ብቻ ከሆነ ነው። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች እንደ ኢትዮጵያ የሚተገበሩ ናቸው። በተለያዩ ሀገራት እንዲሁም የህክምና ተቋማት የተለያየ የአሰራር

ስርአት አለ።
እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር ያደጉ ሀገራት ባላቸው የህክምና ቁሳቁስ ምክንያትነት ከዚህ ቀደም በቀዶጥገና የወለዱ እናቶች በማህፀን (ምጥ) የመውለድ የተሻለ እድል አላቸው። ከህክምና ቁሳቁስ መካከል

የልጅ(ፅንስ) ልብ ምት ማዳመጫ እና የምጥ ሀይል መለኪያ ተጠቃሽ ነው። ከቁሳቁሶች በተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎች ብዛት (ቁጥር) ከኢትዮጵያ እና መሰል ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር ያደጉ ሀገራት የተሻሉ ናቸው።

“እንደ እንግሊዝ እና አሜሪካ ያሉ ሀገራት የህክምና ተቋማት ጥራት ከፍተኛ ነው። አንድ የህክምና ባለሙያ ለአንድ ታካሚ ብቻ ህክምና (ክትትል) ሊያደርግ ይችላል። በእኛ ሀገር ግን አንድ አዋላጅ ነርስ ለ5

ወይም 6 ታካሚዎች (እናቶች) ነው ክትትል የሚያደርገው” ብለዋል ዶ/ር መብርሃቱ ተኽለ።
ከዚህ ቀደም በቀዶጥገና ወልደው የነበሩ እና በምጥ መውለድ የሚችሉ እናቶች በምጥ እንዲወልዱ ማድረግ በቀዶጥገና ምክንያት የሚከሰቱ ተጓዳኝ ችግሮች እንዲወገዱ ያደርጋል። ስለሆነም እናቶች በምጥ እንዲወልዱ

ማበረታታት እና መደገፍ እንደሚያስፈልግ የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መብርሃቱ ተኽለ ተናግረዋል።

Read 283 times