Thursday, 18 April 2024 21:03

የማቲዎስ ወንዱ - የካንሰር ሶሳይቲ የ20 ዓመት ጉዞ

Written by  ትዕግስቱ በለጠ-
Rate this item
(0 votes)
• ከመሪር ሃዘን ውስጥ የተወለደ በጎነትና ብርታት
 
ማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ፤ መሪር ሃዘንን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር፣ በልጅ ፍቅር ሳቢያ የተቋቋመ የካንሰር ድርጅት ሲሆን፤ ማህበሩ ከተመሰረተ ሁለት አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል። በአሁኑ ሰዓትም ማህበሩ የተመሰረበትን የ20ኛ ዓመት ክብረ በዓል እያከበረ ነው።
ማቲዎስ ወንዱ፤ የአቶ ወንዱ በቀለና የወ/ሮ አምሳለ በየነ ሦስተኛ ተወዳጅ ልጃቸው ነበር - የአብራካቸው ክፋይ፡፡ ከአንድ ወር ዕድሜው ጀምሮ የማቲዎስ ሞግዚት የነበረችው ይፍቱሥራ ስለህጻኑ ስትናገር፤ "… ቆንጆ፣ ደስተኛ፣ ንቁና ጤናማ ልጅ ነበር። ዕድገቱም እንዲሁ ነው። ከዕድሜው በላይም ፈጣን- ያየው ሁሉ የሚገረምበት። እያደገ ሲመጣ ደግሞ የበለጠ ተወዳጅ እየሆነ የመጣ…" ትላለች፡፡
ህጻኑ የሁለተኛ ዓመት ልደቱን ባከበረ ማግስት ግን ማንም ባልጠበቀው ከባድ ህመም ተያዘ። የሆነው ሁሉ ለቤተሰቡ ዱብዳ ነበር። ሃኪሞች ህፃኑ በደም ካንሰር መታመሙን አሳወቁ። "ያን ቀን ቤተሰቡ ውስጥ የተፈጠረው ድንጋጤ መቼም አይረሳኝም። እኔ ካንሰር ሲባል የእኛ ሃገር ህመም አይመስለኝም ነበር። እንዴት ሊሆን ይችላል? በተለይ እናቱ የሆችውን አሁን ሳስበው ለራሴም ይከብደኛል።" ትላለች የህፃኑ ሞግዚት፡፡
ማቲዎስ ለሁለት አመት ያህል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተል መቆየቱን ቤተሰቦቹ ይናገራሉ፡፡ ከህመሙ እንደሚድን ተስፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ህመሙ አገርሽቶበት ወደ ውጭ አገር ሄዶ ህክምና ካላገኘ በስተቀር እዚህ አገር ተስፋ እንደሌለው የተናገራቸው ወላጆች ቤታቸውን ሸጠው ልጃቸውን ለማሳከም ይዘጋጃሉ፡፡ ማቲዎስ ዕድለኛ ሆኖ ግን ወላጆቹ ቤታቸውን ከመሸጣቸው በአሜሪካ የነጻ ህክምና ማግኘት ቻለ፡፡ ቤተሰብ ለአሜሪካ የህክምና ጉዞ ዝግጅቱን ጀመረ፡፡ ሆኖም ግን ከጉዞው በፊት የ4 ዓመቱ ተወዳጅ ህጻን ማቲዎስ ወንዱ ከዚህ ዓለም በሞት ተሰናበተ፡፡ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ሞግዚቱና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ክትትል ታደርግለት የነበረችውን ነርስ ጨምሮ መሪር ሃዘን ውስጥ ገቡ፡፡ ብዙ አዘኑ፡፡ ብዙ አለቀሱ፡፡
"ማቲዎስ ወንዱ በካንሰር ህመም ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ምክንያት ቤተሰቡ ላይ የደረሰውን እጅግ መራር ሃዘን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር፣ ማቲዎስን ማዳን ባይቻለን እንኳን፣ እጅግ ብዙ ማቲዎሶችን ለማዳን እንችላለን በማለት በ15 መሥራች አባላት የተመሰረተው ሶሳይቲያችን፣ 20ኛ ዓመቱን ለማክበር በቅቷል።" ብለዋል፤ትላንት ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም በማርዮት ሆቴል መግለጫ የሰጡት የማቲዎስ አባትና የማህበሩ መሥራች አቶ ወንዱ በቀለ።
የማህበሩ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሰቢ ዶ/ር የትናየት አበበ በበኩላቸው፤ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት መሪር ሃዘን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር በተጀመረው ጉዞ፣ ዛሬ ሶሳይቲያችን ከ1ሺ 400 በላይ አባላት፣ ከ500 በላይ በጎ ፈቃደኞች እንዲሁም 300 ቋሚ ሰራኞችን በመያዝ፣ 8 ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ ይገኛል።" ብለዋል።
የማህበሩን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በታተመው "ፍርቱና" የተሰኘ መጽሄት ላይ የሶሳይቲው ዋና ዋና ዓላማዎች ተዘርዝረዋል። አንደኛው፤ የተሳሳተውን የካንሰር ገፅታ በመቀየር፣ ህብረተሰቡ ትክክለኛውን የካንሰር ምንነት፣ የመከላከያና መታከሚያ አማራጮቹን እንዲያውቅ ማድረግ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በአገራችን የካንሰር ህክምና ተሟልቶ የሚሰጥበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠር፣ እንዲሁም አቅሙ ለሌላቸው አስፈላጊውን የሞራልና ማቴሪያል ድጋፍ መስጠት ሲሆን፤ ሦስተኛው፣ በአገራችን የሚገኙ የህክምናና የትምህርት ተቋማት በካንሰር ላይ ምርምር እንዲያደርጉ ማበረታታት የሚሉ ናቸው።
ከሁለት አስርት ኣመታት በፊት በማቲዎስ ወንዱ መኖሪያ ቤት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ፣ በአሁኑ ወቅት ለካንሰር ህሙማንና ቤተሰቦቻቸው ትርጉም ያለው ትብብርና ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል። ማህበሩ እስካሁን ድረስ ከ3ሺ በላይ የካንሰር ህሙማንና ቤተሰባቸውን መርዳቱ የተጠቆመ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት 175 የካንሰር ህሙማንና ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት ላይ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።
ማህበሩ ለህሙማኑና ቤተሰባቸው ከሚሰጣቸው ድጋፎች መካከል ከአገራቸው የሚመጡበትና የሚመለሱበት ሙሉ የትራንስፖርት ወጪ፤ ሆስፒታሎች የማይሰጧቸውን ወድሃኒቶች ከግል መድሃኒት ቤቶች እንዲገዙ ሲደረግ ሙሉ ወጪውን መሸፈን፤ የላቦራቶሪና ምርመራ አገልግሎቶች በግል ተቋማት ሲያሰሩ ሙሉ ወጪውን መሸፈ እንዲሁም ሆስፒታል ለህክምና በሚተኙ ወቅት ለጥቃቅን ወጪ መሸፈኛ በወር 1ሺ ብር መስጠትና ሌሎችም ይገኙበታል- ተብሏል።
የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ዘላለም መንግስቱ እንደሚገልፁት፤ ከ2006 ዓ.ም በኋላ የማህበሩ የፕሮጀክት ሥራዎች እየሰፉ የመጡ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የአሜሪካ ካንሰር ሶሳይቲ ፕሮጀክትን ይጠቅሳሉ። ካምፔይን ፎር ቶባኮ ፍሪ ኪድስ CFK) ከተባለው ድርጅት ጋር በመተባበር፣ በኢትዮጵያ የትምባሆ ቁጥጥር ህግ እንዲወጣ ማህበሩ እንቅስቃሴ ማድረጉንም አቶ ዘላለም ያወሳሉ።
"አሁን ስማችን ብቻ ነው ካንሰር ላይ ያለው" የሚሉት የፕሮግራም ዳይሬክተሩ፤ ከኮቪድ በኋላ ሙሉ በሙሉ ስትራቴጂያችንን ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ላይ አድርገን ላቅ ያሉ ስራዎችን መስራት ችለናል ብለዋል። የሳንባ ካንሰር ፕሮጀክታችን ሌላ የካንሰር ህመም ዓይነት ላይ እንድንሰራ አስችሎናል ሲሉም አክለዋል- ዳይሬክተሩ።
አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሱት የማይተላለፉ ህመሞች፣ በአገራችን ከሚከሰት ሞት ውስጥ 52 በመቶውን የሚወክሉ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ማህበሩ በትኩረት እየሰራበት እንደሚገኝ ተነግሯል። በዚህም መሰረት ከግሎባል ኸልዝ አድቮኬ ሲ ኢንኩቤተር (GHAI) በተገኘ የገንዘብና ቴክኒክ ድጋፍ፤ ጠንካራ የሆነ ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች ቁጥጥር አዋጅ በኢትዮጵያ እንዲፀድቅ ድጋፍ የሚሰጥ ፕሮጀክት ላይ እየሰራ ነው ተብሏል፡፡
ምንም እንኳን ማቲዎስ ወንዱ- የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ከተቋቋመ 20 አመታትን ቢያስቆጥርም፣ የዕድሜውንና እንቅስቃሴውን ያህል እንደማይታወቅ የሚናገሩት የማህበሩ የቦርድ አመራሮች፤ በዚህም ሳቢያ በብዙ ነገር መበደሉን ይገልጻሉ። አንዳንድ ማህበራትና ተቋማት በተመሰረቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ መሬት እያገኙ የራሳቸውን ህንጻ እንደሚገነቡ በማንሳትም፣ ማህበሩ ግን ለህመምተኞችና ቤተሰቦቻቸው መኖሪያ የቤት ኪራይ በዓመት ብዙ ሚሊዮን ብሮች በመክፈል ለህመምተኞች ድጋፍ ይውል የነበረ ገንዘብ ለኪራይ እያወጣ መሆኑን በቅሬታ ተናግረዋል - አመራሮቹ፡፡ በዚህ አጋጣሚም መንግሥት በተለይም የከንቲባ አዳነች አበቤ ቢሮ፣ ማህበሩ እየሰራ ያለውን በጎ ተግባር ገምግሞ ቦታ እንዲሰጠው ተማጽነዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ማህበሩ ብዙ ተግዳሮቶችና ውጣ ውረዶች እንደገጠሙት እሙን ነው፡፡ የዚያኑ ያህልም በተለይ ባለፉት 5 ዓመታት ከተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት በትንሹ 7 የሚደርሱ ሽልማቶችን ማግኘቱንም የሶሳይቲው መሥራች አቶ ወንዱ በቀለ ባለፈው ረቡዕ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡
በ4 ዓመት የጨቅላ ዕድሜው በካንሰር ህይወቱ ባለፈው ህጻን ማቲዎስ ወንዱ ስም የተቋቋመው ማህበር፤ የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት በዓል የሚያከብረው ለመተግበር በእጅጉ የሚፈታተኑ ትላልቅ ህልሞችና ፕሮጀክቶችን ከፊቱ ደርድሮ ነው -ከእነዚህም አንዱ የልህቀት ማዕከል ማቋቋሚያ ፕሮጀክት የሆነው "ጤናማ አፍሪካ- Healthy Africa" የተሰኘ ፕሮጀክት ነው ተብሏል፡፡
Read 253 times