Friday, 12 April 2024 20:42

ነሕምያ ኦቲዝም ማዕከልን ለመደገፍ የዳንስ ፊትነስ በጎልፍ ክለብ ተዘጋጀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


•  በእሁዱ መርሃ ግብር እስከ 5ሺ የሚደርሱ ደጋግ ሰዎች ይሳተፋሉ

•  ለማዕከሉ እስከ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ  ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዷል

 ነሕምያ ኦቲዝም ማዕከል፣ ከኢትዮ ዳንስ ፊትነስ ጂምና ሰፖ ጋር በመተባበር ከነገ ወዲያ እሁድ ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም  ከጠዋቱ 1:00 ሰዓት ጀምሮ ጦርሀይሎች በሚገኘው ጎልፍ ክለብ የዳንስ ፊትነስ  መዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን ዓለማውም ለማዕከሉ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ ነው ተብሏል፡፡

በእዚህ ዝግጅት ላይ እስከ 5 ሺ  የሚደርሱ ደጋግ ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በዕለቱ ከ5 ሚሊየን ብር ለማሠባሠብ መታቀዱን የሚገልጸው የኢትዮ ዳንስ ፊትነስ መስራችና ባለቤት ቶማስ ኃይሉ (ቶም ኘላስ)፤ ሁላችንም በመተባበር በነሕምያ የሚገኙ ህጻናትን እንድናግዝ ጥሪውን  አስተላልፏል።

ከ10 ዓመት በፊት የተመሠረተው ነሕምያ ኦቲዝም ማዕከል፤ በኦቲዝምና ተዛማጅ ችግሮች የአዕምሮ ዕድገት እከልየገጠማቸውን ህጻናትና ወጣቶችን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ከተጋረጠባቸው ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፣ ስነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ለመታደግ አልሞ የሚሰራ መሆኑን የማዕከሉ መስራች ወይዘሮ ራሄል አባይነህ ገልጸዋል።

በመላው ኢትዮጵያ  እየተከበረ የሚገኘው  የዘንድሮውን የዓለም ኦቲዝም ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የዳንስ ፊትነስ ኘሮግራም ላይ ለመታደም የመግቢያ ዋጋው አምስት መቶ ብር ሲሆን፤ ቲኬቶቹ ቦሌ  ኢትዮ ዳንስ ፊትነስ ጂም እና ሰፖ ፣ ቄራ አልማዝዬ ሜዳ አካባቢ በሚገኘው ነሕምያ ኦቲዝም ማዕከል እንዲሁም በእለቱ ጎልፍ ክለብ መግቢያ በር ላይ እንደሚሸጡ ተገልጿል።

Read 544 times