Tuesday, 09 April 2024 20:32

የምንሞትለትና የምንሟሟትለት ምን?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አንዳንድ ጥቅስ ከእግረሙቅ ይከፋል፤ ጠፍሮ ሲይዝ፣ ሳምንት እራሴ ጠቅሼ ተወስውሼ ሳልወድ በግድ አብሬው የከረምኩት የKarl marx ንግግር ነው፤ እንዲህ ይላል፡-
“Man’s Most Preeious treasure, his greatest wealth; is man himself” (የሰው ልጅ የከበረ ሀብቱ ሆነ ታላቅ ንብረቱ እራሱ ሰው ነው)
ይሄን ጥቅስ ይዘን በሃሳብ ስንነጉድ ይሄን ዘመን፣ ይሄን ሀገርና ይሄን ሰው አገኘን…
… እንደው ለመሆኑ፤
የዚህ ዘመንና የዚህ ሀገር ሰው የሚሞትለትና የሚሟሟትለት  የህይወት ግቡ ምንድን ነው? ሀገር?.... ብሔር?… ገንዘብ?...ጥበብ?... ሥርዓት?... እምነት?… ነጻነት ?-....ዕውቀት?....ጸሎት?.... ዕውነት?--ወይስ ምን?...
    Karl Marx እንዳለው ነው? የዚህ ዘመንና ሀገር ነዋሪ የከበረ ሀብቱ ሆነ ታላቅ ንብረቱ፣ እራሱ ሰው ነው?...እዚህ ላይ ሳንቆርጥ ወደ ተናጋሪው Marx እንዙር…
… የMarx የህወይት ግብ፣ እዚህ ጥቅስ ውስጥ ተጠቅልላ ትገኛለች። የተራበው፣ የተጎሳቆለው፣ ቤተሰቡን ችግር ላይ የጣለው፣ ልጁ ስትሞት ምንም ማድረግ ሳይችል የቀረው፣ የተሰደደው… ለዚች የህወት ግቡ ነው። ርዕዮተ ዓለም እስከመሆን የደረሰው  ፍልስፍናው፤ የዚች ህይወት ግቡ ማስፈጸሚያ አቋሙ ብቻ ነው። ሰውን ሁሉ የሰው ብቸኛ ሀብት አድርጎ በመመልከቱ የዓለም አድሏዊነት ላይ ነው የዘመተው። ጨቋኝ፣ ተጨቋኝ ስለምን ይኖራል? ነው ያለው። ዓለም የሁሉም ሰው ከሆነች፣ ሁሉም ሰው ለመኖር ከተፈጠረ፣ እንዴት በዝባዥና ተበዝባዥ ይሆናል? አንዲት እናት ልጆቿን እንደከበረ ሀብቷ እንደ ታላቅ ንብረቷ የምትመለከት ከሆነ፣ በመካከላቸው ጨቋኝና ተጨቋኝ፤ በዝባዥና  ተበዛባዥ እንዲኖር ትፈቅዳለች? የማርክስ ፍልስፍና ለልጆች የወረደ የእናት ማኒፌስቶ ነው። የተገኘውን ሥራ ሆነ ያፈሩትን ሀብት በእኩልነት የሚከፋፈሉበት የእናት መተዳደሪያ ደንብ ነው።
እሺ!
    … የዚህ ዘመንና የዚህ ሀገር ሰዎች፤ በፍልስፍና የምንደግፈው፣ በሥቃይና በሞትም ቢሆን የምንጸናው ለየትኛው የህይወት ግብ ነው? ፍቅር? ህብር? ጥበብ? ወይስ ገንዘብ?...
… ገንዘብ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን!! የህይወታቸውን ግብ እንደገመሬ ዝንጀሮ ገንዘብ ክምር ላይ ፊጥ ማለት አድርገው የተለሙ አሜሪካኖች ብዙ አስተምህሮቶች አሏቸው። አንዱ የገንዘብ ነብይ ነበረው Napoleon Hill ገንዘብ ለማግኘት እራስን መሸጥ እንደሚገባ ያስተምራል። እራስን የሚሸጠው “የሽያጭ ሠራተኛ” በመሆን ነው ይላል። ከምናምንቴ ጋር የተነካካውን የህይወት ግብ፣ የተቀደሰ ለማድረግ የታሪክ ጠገግ ሲፈልግለት እንዲህ ይላል…
“….ቄሳር፣ ታላቁ አሌክሳንደር፣ ናፖሊዮን እና መሰሎቻቸው የተዋጣላቸው የሽያጭ ሰራተኞች መሆናቸው ይታወቃል።… ጦርነትን ሸጠዋል፣ አቅርበዋል። ጦርነቱ ደግሞ የሰዎችን ደም እንባና መከራ ያስከፈለ ነበር። “ ይልሃል።”
“እ…ሺ” ስትለው፤ ይሄን ሃሳብ ጉያህ ውስጥ ይሸጉጠዋል።
“ይህን አስታውስ! በሽያጭ የተካንኩ ነኝ የምትል ሁሉ ድንጋይም፣ ጦርም ሰውም ይሁን እባብ ሽጥ!” አለ የገንዘብ ነብይ የሆነው Napoleon፡-
“ሰው ማለት፣ ሰው የሚሆን ሰው የጠፋ ዕለት” የምትለው የነተበች መፈክር፣ በ”ዘመኑ” ሰው ወርዳ በሌላ ተተክታለች።
“ሰው ማለት ሸቀጥ የሚሆን ሸቀጥ የጠፋ ዕለት” ተብሏል። ሰው፣ ሰውን ሸቀጥ አድርጎ መዳረሻው የት ነው? ግቡስ? ሰው ተሸጦ የተከማቸ ሀብት፣ለየትኛው ህይወት? ዘመኑ እዚህ ላይ ይተጋል። ህሊና የሌለው የሽያጭ ሠራተኛ ማብዛት፣ ሻጭን እራሱን ለገበያ ከማቅረብ የሚጀምር፣ የማያማርጥ መሸጥ በመልመዱ እናቱን፣ ልጁን፣ ሀገሩን የሚያስማማ…
… የዚህ ዘመን ሳይሆን “የዚያ ሰው” የነበሩት ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ፤ ስለ ሽያጭ ሠራተኛ (ነጋዴ) እንዲህ በማለት እራሳቸውን ይጠይቃሉ።
    “ነጋዴስ ደክሞ የሚያመጣው ወረት፣ ቀማኝነት የሌለበት እውነተኛ ገንዘብ አይደለምን?” እራሳቸው ሲመልሱ…
“ነጋዴም ቢሆን ምንም የመንገድ ድካም ቢኖርበት ወይም ሲገዛ፣ ወይም ሲሸጥ ማታለል የግድ የስራው ስለሆነ ከሚያታልለው ሰው ላይ የማይገባውን ሳይወስድ አይቀርምና ከንግድ ገንዘብ ውስጥ እንደ ቅሚያ ያለ ገንዘብ በግድ መቀላቀሉ የማይቀር ነው።”
ሁለተኛው ጥያቄ ከራሳቸው ከልዑል መብሰልሰል ውስጥ ይወጣል፡-
“የንግድ ገንዘብ ቅሚያ ያልተቀላቀለበት ጥሩ እንዲሆን ምን መስራት ይሻላል?”
መልሱ…
“… ከንግዱ ጎዳና አስቀድሞ መንፈሳዊነትና የዕውቀታችን  ጎዳና ይዞ ደከመውን ጉልበቱን በቅን የሚገዛ ባለምንዳ ልክ እያሰላ ዐርፎ ተድላ ደስታ ያደረባቸውን ቀኖች እየተወ ለመግዣና ለመንገድ ያወጣውን ገንዘቡን ዋና አድርጎ በጉልበቱ ልክ ትርፍን እየገመተ የሚሸጥ፣ በጉልበቱ ዋጋ ላይ ያልዋሸ እንደሆነ ሌብነት ያልተቀላቀለበት ገንዘብ ይንለታልና ቢያስቀምጠው ንፉግ ብቻ እንጂ ቀሚ አያሰኘውም።”
የዚህ ዘመንና የዚህ ሀገር ሰው ውጤቱ Napoleon Hill እንጂ የዚያ ዘመን ሰው፤ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ አይደሉም። ከምክራቸው የለም። በብዛ የሚደመጠው ሰውን ስለገንዘብ ለውጡ የሚለው የዘመኑ ዋሾ ነብይ ነው።
እንደው ለመሆኑ…
… የዚህ ዘመንና የዚህ ሀገር ሰው ለልጆቹ እንዲሞቱለት ወይም እንዲሟሟቱለት የሚነግራቸው የህይወት ግብ አለ? ምንድነው? ሀገር?...ብሄር?... ህዝብ?… ጥበብ?...ወይስ ምን??
    “የዚህ ዘመን ሰው” ማለቴ “የዚያ ዘመን ሰው” የህይወት ግቡን መሳት እና ለህይወት ግቡ ሞቶ ስላለፈ ነው። የዚያ ዘመን ሰው ሀገሩን አስቀድሞ፣ ትግሉን በድል ደምድሞ፣ ለሀገሩ እምነት፣ ለእምነቱ እውነትን አስከትሎ፣ የመወጣውን ሁሉ በመቀበል አልፏል።
    ብላታ ወልደጊዮርጊስ ይሄን ምሳሌ አኑረውልና። ምሳሌው አራት መከራ የደረሰባቸው ሰዎች የተወያዩት ነው። የመጀመሪያው ሰው የደረሰበት መከራ ጠላው በድንገት ተነስቶ ጦርነት ያደረሰበት ሰው ነው አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆኖ ነፍሱን ቢከላከልም ተዘፍፏል፤ ተገፍፏል፣ ከብቱ ተነድቷል ይሁንና በሀገር እርዳታ አንሰራርቷል፡፡
ሁለተኛው መከ
ረቃልሎ ይጀምራል “ወንድ ልጅ እጁ ካልተጨበጠ፣ የሚበላው ካጣ፣ በዋሻ በጥሻ፣ በገደል በቅጠል፣ በዱር በፈረፈር… እያለ ተከላክሎ አንድ እድል ሳይገጥመው አይቀርም፡፡” ይላል በእሱ ላይ የደረሰውን መከራ የሚያሰፋው በዱር በገደል ቢሉ ማምለጥ የማይቻው ‘ክፉ ባላጋራ ማለት ረሃብ ነው’ ብሎ ይደመድማል፡፡
ሶስተኛው ሰው የሁለቱን መከራ አጣጥሎ ጦርነትም ረሃብም ከባድ ቢሆኑም፣ መከላከያ ላይሆንለት አይቀርም በማለት የራሱን ጭንቅ ከፍ፣ ከፍ ያደርጋል፡፡ በዚህ ሰው ላይ የደረሰው በሙያ ቢስነት የሚመጣ መከራ ነው፡፡ ጭንቁ መከላከያ አልቦ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
ሦስቱን በፀጥታ ሲያዳምጥ የቆየው ሰው እንዲህ ይላል፡፡ “መጠቃት ማለት አጥቂ ይመጣና ተከላክሎ ለመዳን ሳይቻል ቀርቶ ያገር ሰንደቅ አላማ ሲረገጥ፣ አርማዎች ሲገፈፋ፣ የንጉስ ትንፋሾች ሲጠፋ፣ አባቶች ሲሰደቡ፣ ትውልዶች ሲደበደቡ፣ ሥም ሲ ረክስ፣ ታሪክ ሲደመሰስ፣ ለመሳቂያ ሲምታቱ፣ የተቀደሱ ልማዶች ሲረክሱ፣ እርስቶች ሲወረሱ፣ የሰው ጀርባና ደረት፣ ግንባርና፣ አንገት የጥይት ጌጤዎች ሲሆኑ፣ አቤት ቢሉ ዳኛ፣ ቢሸሹ መደኛ ሲታጣ፣መሣሪያዎች ከእጅ ተፈልቅቀው ሲወሰዱ፣ የነፃነት ዘፈኖች በለቅሶ ሲለወጡ፣ ዓይኖች በዕንባ ሲሞጨመጩ፣ ጆሮዎች በጥፍ ሲደነቁሩ፣ አካላቶች በጫማ ሲረገጡ፣ እሬሳዎች መቃብር ሲነፈጉ፣ አምሮቶችና ናፍቆቶች ፍቅሮችና ትዝታዎች ጥቅጥቅ ባለ ሀዘናዊ ጉም ውስጥ ሲዘጉ፣ የአምላክ ስፍራዎና የሀይማኖት አባቶች ሲጎሳቆሉ፣ ጥርሶች ስጋቸው ያለቀ አስከሬኖች ሲመለሱ ይህንና ይህን የመሰለው የግፍ ግፍ በነፃነትና በነፃ ህዝብ ላይ ሲደረግ ከጭንቀቶ ሁሉ የበለጠ ጭንቅ ከዚህ በቀር ምንም የለም፡፡”
 በዚህ አራቱም ይስማማሉ፡፡
            አየህ!!
የዚህ ዘመንና የዚህ ሀገር ሰው ግራ የሚገባህ እዚህ ላይ ነው፡፡ ጠላት በወረራ የሚያደርገውን ሁሉ በራሱ ላይ አድርጓል፡፡ የራሱን ሰንደቅ አላማ እራሱ ረግጧል፣ የራሱን አርማዎች እራሱ ገፍፏል፣ የራሱን አባቶ እራሱ ሰድቧል፣ የራሱን ትውልዶች እራሱ ደብድቧል፣ የራሱን ሥም እራሱ አርክሷል፤ የራሱን ታሪክ እራሱ ደምስሷል፣ የራሱን መታሰቢያ እራሱ አፍርሷል የራሱን የምራቅ ጢቅታዎች በራሱ ፊቶ ላይ ተፍቷል ፤የራሱ ፉጨት ለራሱ መሳቂያ አምጥቷል፣ የራሱን የተቀደሰ ልማድ እራሱ አርክሷል፣ ከራሱ እርስት እራሱን ነቅሏል…ራሱን እራሱ አሳዷል፣ አቤት ቢል ዳኛ፣ ቢሽሽ መዳኛ አጥቷል፡፡ የራሱን ሬሳዎች እራሱ መቃብር ነፍጓል፣ የራሱን የአምላክ ስፍራዎን የራሱን የኃይማኖት አባቶች እራሱ አጎሳቁሏል፡፡
አየህ የዚህ ዘመንና የዚህ ሀገር ሰው የህይወት ግቡ ምንድነው? ተብሎ የሚጠየቀው፤ ይሄ ድርጊቱ ግራ ስለሚያጋባ ነው፡፡ ለመሆኑ የሚሞትለት ሳይሆን የሚሟሟትለት አላማስ አለው?
***
ከአዘጋጁ፡-
ጋዜጠኛ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ ከአሥር በላይ መጻህፍትን ለህትመት ያበቃ የብዕር ሰው ሲሆን፤ የሚበዙት የህትመት ውጤቶቹ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው - ልብወለዶች፡፡ የጋዜጠኝነት ልምድና ተሞክሮ ያካበተው አለማየሁ ገላጋይ፤በሥነጽሁፍ ሃያሲነቱም በእጅጉ ይታወቃል፡፡ ማህበራዊ ሃያሲም ነው፡፡


Read 552 times