Tuesday, 02 April 2024 20:45

የመሪዎቻችን ፖለቲካዊ ከባቢ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

የሕዝብ መሪ እንደ አንድ ጎጆ ጉልላት ላይ ተሰቅሎ፣ ለሚያልፍ ለሚያገድመው ጌጥ መሥሎና ተቆልሎ ቢታይም፤መነሻውና ሥሩ ግን የቆመበት መሬት ነው። መሬቱን ደግሞ እንደ ሠፊው ሕዝብ፤ወጋግራዎቹን በየደረጃው መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉት ባለሥልጣናት ሊሆኑ ይችላል። ታዲያ ሁሌም የመሪዎች መነሻና መሠረት ሕዝብ ስለሆነ፣ተቀላቅለው ከኖሩት ማኅበረሰብ ይዘዋቸው የሚወጡት ቀለማት ይኖራሉ።
ከሰዎች መካከል ተወልደው፣ ከሰዎች ጋር አድገው፣አብረው ተምረው፣ ወደ ሥልጣን ይውጡ እንጂ ልባቸው ራዕይ የሚያረግዘው፣ሥዕል የሚያበጀው፣ መንበረ ሥልጣን ላይ ከመውጣታቸው ቀደም ብሎ በታሪካቸው ማለዳ፣በልጅነታቸው ጀንበር ነው። ከእናት ከአባት ጓዳና እልፍኝ አስተዳደግ፣እስከ ማኅበረሰባዊ ተቋማት፣ባሕል ሥነ-ልቡናና፣አኗኗር ይዘው የሚወጡት መልክና ቁመና አለ።
እንደ ቤተሰብ ከሚያዳብሩት አስተሳሰብና መስተጋብር በተጨማሪ፣ ወደ ማኅበረሰብ ሲዘልቁ ከትምህርት ቤት፣ ከተለያዩ ማኅበራዊ ክንውኖች የሚዘግኑት ነገር አለ። መሪነትን ነጥለን ስንመለከት በተለይ በአምባገነናዊ ሥርዐቶች፣ማለትም በኋላ ቀሩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዐት ውስጥ ወደ ሥልጣን መምጣት የሚቻለው በደምና አጥንት፣ በዝምድና በመሆኑ በአጋጣሚ የሥልጣን ኮርቻ ላይ መፈናጠጥ አይቻልም። ይልቅስ፣ በቤተሰብ መካከል ተኮትኩቶ ታጭቶና ተዘጋጅቶ የሚመጣ በመሆኑ ድንገቴነት አይከሰትም።
ሥርዐቱ የሚወልዳቸውም መሪዎች አንዳንዱ ቀና ሌላው ጠማማ፤አንዳንዱ ችኩል፣ሌላው የተረጋጋ፣ አንዳንዱ ጨካኝ ሌላኛው ለሕዝብ አሳቢ ይሆናል። በሶሻሊስታዊውና በአብዮት ሥልጣን ከያዙት ውስጥ እንኳ አንዱ ከአንዱ ይለያል። ለምሳሌ፣ስታሊንን ከሚያክል አምባገነን ትይዩ ሚካኤል ጎርባቾቭን የመሠለ ዴሞክራት ይወጣል። ስታሊን በፊውዳሉ ሥርዐት ሥር አድጎ፣የአርሶ አደር ወላጆቹ ሕይወት መርሮት ልቡ ለአብዮት ተመቻችቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሴሚነሪ ሲሸፍት፣ሚካኤል ጎርባቾቭ ደግሞ በሶሻሊስቱ ሥርዐት አርሶ አደር ቤተሰቦቹ ሀብታቸው ሲነጠቅና ሀብት ማፍራታቸው ወንጀል ሆኖ “ኩላክ”እየተባሉ ሲረሸኑ ባየው ቁጭት ሌላ አብዮት አምጥቶ፣ የዐለም አብዮተኞች ማዕከል የሆነችውን ሶቪየት ኅብረት ቀለሟንና ታሪኳን ቀይሯል።
ዋይት ሀውስን በድምቀቱና በሰብዐዊነቱ ጉድ ያሰኘው ዴላኖ ሩዝቬልት በበቀለባትና በነገሠባት ምድር፣ ታፍትን የመሰለ ፈዛዛና ሰው ናቂ ይቀመጣል። ወደ እኛ ሀገር ስንመጣም፣ ዐፄ ቴዎድሮስን የመሠለ ቁጡ በነገሠባት ምድር፣ ምኒልክን የመሠለ የተረጋጋ ንጉሥ ይኖራል።
የዘመኑ ሳይንስ በአብዛኛው መሪነት ከሌላ መሪ የሚጋባ ነው እያለ ቢያስተምርም፣ አንዳንዶቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ የመሪነት ዝንባሌ ስለሚኖራቸው ነገሩ ያከራክራል። ለምሳሌ ያህል ከአሜሪካ መሥራች አባቶች አንዱ የሆነው ቤንጃሚን ፍራንክሊን በዕድሜ እኩዮቹንና የሚበልጡትን ያስከትልና ይመራ እንደነበር የሕይወት ታሪኩ ይነግረናል።
የፖለቲካ ማኅበራዊነት ሳይንስን ያጠኑ ምሁራን እንደሚሉት፤ ሰዎች ለፖለቲካ ማኅበራዊነት የሚጋለጡበት የዕድሜ አንጓ ልጅነትና በጥቂቱ ደግሞ ወጣትነት ነው። ስለዚህ ብዙ ጊዜ በፖለቲከኞች ከባቢ ውስጥ ልጅነታቸውን ያሳለፉ ሰዎች ወደ ፖለቲካውና መሪነቱ ያዘነብላሉ።
ወደራሳችን ነገሥታት ስንመለስ፣ዐፄ ምኒልክ በልጅነታቸው የቴዎድሮስ ምርኮኛ ሆነው በንጉሡና ባለሟሎቻቸው ከባቢ አድገዋል። ስለዚህም በልባቸው የጻፉትን፣በቃላቸው የያዙትን መርምረው የተሻለውን ለማድረግ በዘመናቸው ሠርተዋል። የቴዎድሮስ ችኮላ ያደረሱባቸውን አደጋ አጢነው፣ሕልማቸው ሲከሽፍ ልብ ብለው፣በተረጋጋ መንፈስ ወዳጆቻቸውንና ጠላቶቻቸውን አስተናግደዋል። እንደ ቴዎድሮስ የማይነኩ ነገሮችን ሳይነኩ፣የማይደፈሩ ቅጥሮችን ሳይደፍሩ፣ቴዎድሮስ ልብ ውስጥ ይነድድ የነበረውን የአንድነትና የሥልጣኔ ፋና በጥንቃቄ ይዘው ዘልቀዋል።
ከነጮቹም ጋር ቶሎ ጦር ከመስበቅ ይልቅ፣በዘዴና በማግባባት ለጋራ ጥቅም ለመሥራት ሞክረው በአብዛኛው ተሳክቶላቸዋል። የዐደዋው ጦርነት እንኳ በጣሊያኖች ራስን ያለልክ ሰቅሎ የማየት ስካር የተፈጠረ እንጂ በምኒልክ ጦረኝነት የተደረገ  አልነበረም።
ሌላኛው የፖለቲካ ማኅበራዊነትን በልጅነቱ ተጠምቀውበት የወጡት ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ናቸው። ኀይለሥላሴ፣ሥልጣኔ የገባቸውና ሳይንስ የተጠሙ ምርጥ ዲፕሎማት የነበሩት የራስ መኮንን ልጅ ናቸው። ልዑል መኮንን የዐፄ ምኒልክ ቀኝ እጅ፣ብርቱ አማካሪና አገረ ገዢ ነበሩ። እኒህ ሰው በቅርባቸው በርካታ ባለሟሎች ያሏቸው ሲሆን፣ ቀዳማዊ ኀይለሥላሴም የአስተዳደር ሥርዐቱንና ወግና ደንቡን ጥንቅቅ አድርገው ስላዩ፣ጊዜያቸው ደርሶ ሥልጣን ላይ ሲወጡ አባታቸው ላይ ይታዩ የነበሩ መልካም ነገሮችን አሳይተዋል።
ራስ መኮንን ጦርነትን ሳይሆን፣ ሥልጣኔን፤ ድኽነትን ሳይሆን ብልፅግናን ለማምጣት ከተለያዩ ሀገራትና ከሰለጠኑ ሀገራት ግለሰቦች ጋር ሳይቀር ኅብረት ያደርጉ እንደነበረ ሁሉ ልጃቸውም ያንኑ ሀዲድ ተከትለዋል። ይህ እንግዲህ የልጅነት ከባቢ ያሳረፈባቸው አሻራ ውጤት ነው።
መለስ ብለን ከሀገራችን የጦር አዛዦች ጎራ ስንቃኝ፣ ራስ አሉላ አባነጋ ተመሳሳይ የልጅነት ጊዜ አሻራ እንደነበራቸው ልብ እንላለን። በመጀመሪያ ባሻ ፈረንጃይ የተባሉት አጎታቸው ዘወትር ጧት፣ጧት ፀሐይ እየሞቁ፣ሰናድር ጠመንጃቸውን እየፈታቱ ይገጥሙ ነበር።አሉላ ደግሞ በበኩላቸው፣ ጧት ጧት ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ሲሄዱ አጎታቸው ዘንድ  ጎራ እያሉ ጠመንጃውን ይፈታትሹና ይሞካክሩ ነበር። የቄስ ተማሪም ሳሉ፣አጎታቸው እንዴት አድርገው ማነጣጠር እንዳለባቸው ያሳዩዋቸውና ያስተምሯቸው እንደ ነበር የሕይወት ታራካቸው ያስረዳል።
ተኩስ ከተለማመዱ በኋላም ደጃዝማች አርኣያ ቤት በፍቃዳቸው ታጣቂ ሆነው ገብተው፣ የዒላማ ተኩስ ችሎታቸውን ያዩት ደጃዝማች አርኣያ፤  ዐፄ ዮሐንስ ዘንድ ታጣቂ እንዲሆኑ አድርገዋቸው፣ በንጉሥ ሥርዐትና ከባቢ ውስጥ አድገዋል። በሌላ በኩል፤ የአሉላ ወላጅ አባት ባሻ ቁምቢም ያለወታደር ሰው ያለ የማይመስላቸው፣ያለነፍጥ ሕይወት ትርጉም የማይሰጣቸው ነበሩ፡፡  የአሉላ የክርስትና ስም ገብረሚካኤል መሆኑን ያልወደዱትም፣ ከዚሁ ከጀግና ፍቅር ጋር በተያያዘ ባደረባቸው ዝንባሌ ነበር።
ባሻ እንግዳ፣ገብረሚካኤል የሚለውን ስም ወደ ወልደ ገብርኤልነት እንዲቀየር ያደረጉት፣ ሚካኤል ገራገርና ለስላሳ ነው፤ ገብርኤል ግን ተፈሪ፣ ቁጡ፣ ኀይለኛና ኮስታራ፣ ቀልጣፋና ግርማ ሞገሥ ያለው ነው በሚል እምነት ነው። ይህ የሚያሳየው አባት፣ልጃቸው ለስላሳ ሳይሆን ኮስታራ እንዲሆን መፈለጋቸውን  ነው።
እንግዲህ ”አሉላ ለምን በጠላቶቻቸው ላይ ነብር ሆኑ?...” ለሚል መልሱ ያለው እዚህ ውስጥ መሆኑን መገመት አያዳግትም። እንግዲህ ከላይ እንዳየነው፣የከፍተኛም ሆነ የመካከለኛ መሪዎችን ታሪክ ስናጠና፣ መሪዎች ካደጉበት ከባቢ ጋር የተዛመደና የተጋመደ ማንነት እንዳላቸው እንረዳለን።
በዚህ መሠረት ታሪካችን ውስጥ የብረት ዐምድ ሆነው ከቆሙት መካከል መሠል የሕይወት ገጠመኝ ያላቸውን እናገኛለን። ለምሳሌ፡- በፖለቲካ ማኅበራዊነት ቅርጽ አበጅተው፣አደባባይ ከወጡ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የምኒልክ የጦር ሚኒስትር ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ይመጡብናል። በታሪክ ወደኋላ ተመልሰን ልጅነታቸውን ስናይ፣ ሀብተጊዮርጊስ በራስ ጎበና ዳጬ በሚመራው ሀገር አቅኚ ጦር፣ፈሊጦ በምትባል ቦታ የተማረኩት ገና በ11 ዓመታቸው ነበር።በኋላ  ወደ አገረ ገዢነት የመጡት ዝም ብለው ሳይሆን፤ ጋረደው አባተምሰስ በተባለ ጅሩዬ  የጦር ሰው ሠልጥነው፣ከዚያም ወደ ምኒልክ ገብተው፣ ከዚያም ለአንኮበር ገዢ ለአዛዥ ወልደጻዲቅ ተሰጥተው ነው ለመሪነት ቁመና የበቁት። በመሆኑም ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ሚና የነበራቸውና ወሳኝ ሰው ለመሆን በቅተው ነበር።
ወደ ቅርቡ የአገራችን ታሪክ ስንመጣ፣በዚህ አይነት ፖለቲካዊ ማኅበራዊነት መልክ አግኝተዋል ለማለት የሚያስደፍሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም  ናቸው። የእኒህ መሪ  የታሪክ መልክ ያን ያህል በገነነ ሁኔታ ባይሆንም፣ ከፈረንሳዩ የጦር ጀኔራልና አገር መሪ ናፖሊዮን ቦናፓርት ጋር በጥቂቱ ተመሳሳይነት አለው።
ናፖሊዮን ገና በልጅነቱ ወታደርነት የናፈቀውና ጦር አካዳሚ ለመግባት የተጣደፈው፣በኋላም ጦርነት የጠማው በዋዛ አልነበረም። ይልቅስ የነፃነት ተዋጊ ከሆኑት እናትና አባቱ፣እንዲሁም ከማኅበረሰቡ በወረሰው የሕይወት ቀለም ነው። ስለዚህም በልጅነቱ የጦር መኮንን ሆኖ፣ልክ እንደኛ ሀገሩ ኮሎኔል መንግስቱ  የዘመኑን ኩነቶች በተከተለ አጋጣሚ ባገኘው ሽንቁር ወደ ሥልጣን መጥቷል። ከመጣ በኋላም ከአገር መሪነቱ ይልቅ ጀኔራልነቱ አመዝኖበት፣አገሩ በርካታ ጦርነቶችን እንድታሳልፍ ሰበብ ሆኗል።
የኛ መንግሥቱም ከዚህ የተለዩ አልነበሩም፤ዕድሜያቸውን ወታደር ቤት አሳልፈው ጠመንጃ ወዳድ ሆነው ኖረዋል። የአገር አስተዳዳሪነታቸውም ወታደራዊ ኀይል የመጠቀም ዝንባሌ ያመዘነበት ስለነበረ አገሪቱ በበርካታ ጦርነቶች ውስጥ ለማለፍ ተገድዳለች።
የሰው ልጅ ከሞላ ጎደል የአካባቢው ውጤት በመሆኑ፣የልጅነት ዘመኑ ቀለም አገር ለማሳመርም ሆነ፣ለማጨለም ወሳኝ ሚና ይኖረዋል የሚለው እምነት እውነትነት ያለው ይመስላል።
    ከአዘጋጁ፡-
 ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አያሌ መጣጥፎችን አስነብቧል፡፡ በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ትንተና አቅርቧል፡፡ ደረጀ በላይነህ ገጣሚና አርታኢም ነው፡፡ 12 ያህል መጻሕፍትን አሳትሞ  ለአንባቢያን አድርሷል፡፡

Read 590 times