Saturday, 30 March 2024 20:26

በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ተባብሶ ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በአማራ ክልልና በትግራይጊዜያዊ አስተዳደር መካከል የተከሰተው ውዝግብ ተባብሶ ቀጥሏል። ሁለቱም ወገኖች በየፊናቸው ማስጠንቀቂያና መግለጫ እያወጡ ነው፡፡
የአማራ ክልል  ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሀገሪቱን ና ሁለቱን ክልሎች ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራቱ  እንዲቆጠብ አስጠንቅቋል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር  ያወጣው መግለጫ ጠብ አጫሪ  እንደሆነም ገልጿል። ክልሉ ባወጣው በዚሁ መግለጫው፤  “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር  መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ  የአካባቢው ነዋሪዎችን በመግደልና በማሰቃየት ላይ ይገኛል” ሲል ከስሷል።
የአማራ ክልል በመግለጫው፤ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከመማሪያ መጽሐፍ ካርታ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ላይ ጥቃት ከመፈጸም የማይመለስ መሆኑን የሚገልጽ የጠብ አጫሪ መግለጫ ማውጣቱ ካለፉት ድርብርብ ውድቀቶች ትምህርት አለመውሰድን ከማሳየት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም” ብሏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለሀገሪቱ ቋሚ ቀውስ ምንጭ ከሚያደርጉት ተግባራት እንዲታቀብና ሀገሪቱንና ሁለቱን ክልሎች ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራት እንዲቆጠብም የአማራ ክልል መንግስትአስጠንቅቋል።  በተጨማሪም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከለመደው አጓጉል የካርታ ፖለቲካ ጨዋታ እንዲወጣና የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩር ክልሉ  መክሯል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ በበኩሉ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫው፤ “የአማራ ክልል መንግሥት የትግራይ መሬቶችን የግዛቱ አካል በማድረግ፣ በክልሉ ካርታ ላይ አስፍሯል፤ የትግራይ ክልል መሬቶች የሰፈሩበትን ካርታ በትምህርት ካሪኩለሙ በማካተት እያስተማረበት እንደሚገኝ ተረድቻለሁ” ብሏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፣ የአማራ ክልል በመማሪያ መጽሐፍት ላይ ያወጣውን የተሳሳተ ካርታ በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ በመግለጫው  ያስጠነቀቀ ሲሆን፤ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን “ይህን ተከትሎ ለሚመጣው ነገር ሁሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው የአማራ ክልል መሆኑን ልናሳውቅ እንወዳለን” ብሏል።


Read 1099 times