Saturday, 30 March 2024 19:32

የአዲስ አበባ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ አሶሴሽን 3ኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠና እየሰጠ ነው

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

የአዲስ አበባ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ አሶሴሽን 3ኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠና እየሰጠ ነው


      የአዲስ አበባ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ አሶሴሽን፣ የ2016 ዓ.ም 3ኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠናና ዓለማቀፍ የፕሮ ቴኳንዶ የመጀመሪያ ራስን መከላከል ኮርስ በወወክማ  አዳራሽ ውስጥ እየሰጠ ነው። ከመጋቢት 14 እስከ መጋቢት  29 ቀን 2016 ዓ.ም ለ15 ቀናት ይዘልቃል በተባለው በዚህ ሥልጠና ላይ ከ35 በላይ ሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ማስተር ሃይለየሱስ ፍስሃ ከትላንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ አሁን በመሰጠት ላይ የሚገኘው 3ኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠና፣ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የሠጠው የመጀመሪያ ኮርስ ነው ብለዋል።
ሥልጠናውም በአምስት የሌጀንድ አሰልጣኞች፣ ከ35 በላይ ለሚሆኑ ከአዲስ አበባና የተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ ተሳታፊዎች የሚሰጥ ነው ብለዋል- ማስተር ሃይለየሱስ።
ሌጀንድ ኢንተርናሽናል፤ ከአዲስ አበባ ውጭ በሁለት ክልሎች ላይ ስልጠና መጀመሩንና በ8 ክልሎች ፈቃድና ዕውቅና ማግኘቱንም ማስተር ሃይለየሱስ ፍስሃ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ ፌደሬሽን መስራች ግራንድ ማስተር ሔኖክ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ፤ እኛ ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው አገራችን በማርሻል አርት ኮሪያና ጃፓን የደረሱበት ደረጃ ላይ ለማድረስ  ነው ብለዋል።
በ8 ክልሎች ፌደሬሽን መሥርተን እየሰራን ነው ያሉት ማስተር ሔኖክ፤ ዓላማቸው ሙያተኛው ትክክለኛ ሙያና ብቃት እንዲኖረው በማስተማር፣ የተሻለ አገር መገንባት መሆኑን ገልፀዋል። ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ከተመሰረተ አንስቶ የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠሙት መሆኑን ያልደበቁት መሥራቹ፤ ”ተግዳሮቱን ተሸንፈን ነው የምናሸንፈው” ብለዋል።
የሌጀንድ ኢንተርናሽናል ዋና መ/ቤቶች በአሜሪካ፤ ጀርመንና ኮሪያ እንደሚገኙ የጠቀሱት ማስተር ሄኖክ፤ በዓለም ላይ ከሚሰሩ 7 ፌደሬሽኖችም ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታችን በፊት በ34 አገራት ውስጥ ነበር የምንሰራው ያሉት የሌጀንድ ኢንተርናሽናል መሥራች፤ አሁን ግን ወደ 56 አገራት አድርሰነዋል ሲሉም ተናግረዋል። በአፍሪካ ከ200ሺ በላይ ተከታዮች እንዳሏቸውም አውስተዋል።

Read 221 times