Monday, 25 March 2024 21:05

ሰውን ሰው ያደረገው ወሬ ነው? (ነገረ ወሬ)

Written by  -ዓለማየሁ ገላጋይ-
Rate this item
(2 votes)

 ስብሃት፣ መስፍን ዓለማየሁና ደምሴ ፅጌ (የሦስቱን ነፍስ ይማርልንና) አንድ ላይ ሆነው እያወጉ ነው፡፡ የሁነቱ ዘጋቢ መስፍን ነው፡፡
“….ኢህአዴግ እንደገባ ሰሞን እኔ፣ ስብሃትና ደምሴ ፅጌ ተገናኘንልህ፡፡ እንደተለመደው ፖለቲካውን ወሸከትንና እንግዲህ ሁላችንም ተባራሪ ስራ ከመስራት በቀር ሥራ የለንም፣ ኧረ ሥራ እንስራ አልኩኝ፡፡ ሽማግሌው (ስብሃት) ምን ይለኛል፤ ‘ይሄው እያወራን አይደለም እንዴ? እዚህ አገርኮ ከወሬ የተሻለ ሥራ የለም’ አለ ፍርጥም ብሎ፡፡”
ስብሃት ከዚህ አለም (የወሬ ድካም እንበለው?) ባረፈ ጊዜ ነቢይ መኮንን ይሄን ትውስታ ሲያስነብበን “ነው እንዴ?” አልኩ፡፡ እውነት እዚህ ሀገር ከወሬ የተሻለ ሥራ የለም? የወሬን ስራነት በphysics ለማረጋገጥ አንታትርም፤ በትርጉሙ በኩል አሳብረን ብናልፍ ሳይሻል አይቀርም፡፡
ከሣቴ ብርሃን ተሰማ በአማርኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ወሬን እንዲህ በፍቺ ያሽሞነሙኗታል፡፡
“ሰው ኹሉ በአዕምሮ የሚናገረው፣ የሚአወራው ንግግር፣ ጨዋታ፣ ቡዋልት፣ ታሪክ፣ ወሬ ነው፡፡” ይሉትና አሥር ያህል የወሬ ዘመድ አዝማዶችን ያፍታታሉ፡፡ አንዱ “ወሬ ምሳው” ነው፡፡ “ወሬ ነፍሱ፤ ወሬን የሚወድና የሚጠይቅ ወይም ወዲያም ወዲህ ብሎ ወሬን ሳያገኝና ሳይሰማ የማይውል ወሬ ምሳው ይባላል”
በእዝነ ልቡናችን ስንትና ስንት የ‘ወሬ ምሳው’ ሰራዊት ተሰልፎ አለፈ? እዚያ ውስጥ እኛም ልንኖር እንችላለን፤ መጠርጠር ነው፡፡ ‘ወሬ ምሳውነት’ኮ ለራስ አይታወቅም፡፡
ደግሞ “የወሬ ቋት” አለላችሁ፡፡ “ከአፉ ላይ ወሬ የማይጠፋበት፤ ሁልጊዜ የሚያወራ፤ የወሬ ቋት ይባላል” ይላሉ፤ ከሣቴ ብርሃን ተሰማ፡፡ እነዚህ ወሬ ምሳው እና የወሬ ቋት በብዛት የሚኖሩበት አካባቢ ሳይሆን አይቀርም “የወሬ መንደር” ይባላል፡፡ “ዕውነትና ሐሰት ያልተለየ ወሬ የሚወራበት መንደር ነው፡፡”
“የወሬ መንደር”ን መናገሻው አድርጎና ምላሱን አንፈራጦ (እግር ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላልና) ወሬ እንደ ጥሬ የሚፈለፍል ሥመ-ንግስና አለው፡፡ “የወሬ አባት” ይባላል፡፡ James Bruce የአባይን ምንጭ ፍለጋ እንደተጓዘ ሁሉ፣ የወሬ ዳቦ ተከትሎ ያሰሰ ሰው ምንጩ የወሬ አባት ሆኖ ያገኘዋል፡፡
ከትርጉም ሳንወጣ….
…. ስብሐት በጋዜጠኞች ሲናደድ አጠገቡ ላለ ሰው አዘውትሮ የሚነግረው የራሱ ትርጉም አለው፡፡
“እኛ እንደዚህ ያለውን ጋዜጠኛ ‘ወሬ አሩጥ’ እንለዋለን፡፡ እንግዲህ ስንገምት ገና ልጅ ሳለ ወላጆቹ ‘እነ እከሌ ቤት ሂድና ምን እንደሚያወሩ ሰምተህ ና’ እየተባለ ያደገ ነው፡፡ ይሄ ልጅ እድሉን ካገኘ የሚሆነው ወሬ አሩጥ ጋዜጠኛ ነው፡፡” ይላል፡፡
ስንቀጥል…
… ስብሐት ወሬን ስራ አደረገው እንጂ እንደውም ወሬ የሥራ ጸር ሆኖ ነው የሚታየን፡፡ እዚህ ላይ ‘ቀንጣሽ ሲበዛ ጎመን ጠነዛ’ የሚለውን ተረት እንደዘበት ጣል አድርገን እንለፍ፡፡ ቀንጣሽ ከበዛ ጎመን መጠንዛት ነበረበት? መካከል ላይ ወሬ አለቻ! አንዱ አንድ ሲያመጣ፣ ደሞ ሰው ሲታማ ሥራው አብሮ አልሄድ ይላል፡፡
ሩሲያዊው ደራሲ Anton Chekhov ወደ መጨረሻ ዘመኑ  ላይ እንዲህ ያለ “የቀንጣሾች” ጎርፍ ቤቱን ሞልቶት ነበር አሉ፡፡ ደራሲነቱ ወደ “መጠንዛቱ” አዝምሞ ሳለ እንዲህ ሲል ለራሱ አልጎመጎመ፡፡ “My country house is full of people, they never leave me alone; if only they would go away I could be a good writer.”
“ወሬኛ ሲበዛ ድርሰት ጠነዛ” እንበል ይሆን? እንደ Chekhov ሁሉ በቀንጣሾች መብሰክሰክ የዘወትር ቀለቤ ሆኖ ነበር፡፡ ወሬ ሲሞቅ ሲንተከተክ ቀስ ብዬ ከመካከል እሾልክና ወደ ተከዜ ሆቴል አመራለሁ፡፡ ግቢው፣ ጥላው፣ ፀጥታው… ጥቂት አነብና ወይ እጽፍና እንዳይቆጨኝ ሆኜ እመለሳለሁ፡፡
(ይህ በእንዲህ እንዳለ አለ ዜና አንባቢ)
አንድ መጽሐፍ እጄ ገባ፡፡ ከ Chekhov አገር ሩሲያ፡፡ The Last Days of Pushkin ርዕሱ ነው፡፡ ምንጩ ወሬና ሐሜት ነው፡፡ የፑሽኪን ዘመነኞች ስለ ባለቅኔው የእለት ተዕለት ባህርይና ከገዳዩ d’Anthes ጋር ስለነበረው ቁርሾ የተፃፉ የሀሜት ደብዳቤዎች የተሰባሰቡበት መፅሐፍ፡፡ የካራምዚን (Karamzin) ቤተሰብ Pushkin ከመገደሉ አንድ አመት ቀደም ብሎ (1836) የጀመሩትን የደብዳቤ ሃሜት ለአስራ አራት ወራት ይቀጥሉታል፡፡ የቤተሰቡ ቁንጮ የታሪክ ባለሙያው Nikolai Karamzin ነው፡፡ እንደሚነገረው ከሆነ ይሄ ሰው ባለቅኔው Pushkin በንጉሱ ላይ በማሴር ወንጀል ተከስሶ ወደ ሳይቤሪያ ግዞት እንዲላክ ሲወሰንበት ምህረት እንዲደረግለት በድፍረት ጓደኞቹን ሰብስቦ ንጉሱ ፊት የቀረበ ሰው ነው፡፡ ተሳክቶለት Pushkin ከግዞት ቅጣቱ ሊተርፍ ችሏል፡፡ በዚህም ቤተሰቡ እንደጥበብ መከታ እየታየ ቤቱ በጥበብ ሰዎች ይሞላል፡፡ ታላቁ ደራሲ Alexander Turgenevን ጨምሮ ባለቅኔው Zhukovsky፣ ፀሀፌ ተውኔቱ  Sollogub  እና ሌሎቹም የቤተሰቡ አዘውታሪ እንግዶች ነበሩ፡፡ ታሪክ፣ ጥበብ፣ ባህልና ፖለቲካ የእነዚያ ታላላቅ ሰዎች የመወያያ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡
Nikolai Karamzinን ከሞተ በኋላም ነባሩ ልምድ በባለቤቱና በልጆቹ ቀጥሏል፡፡ በይበልጥ Sophia Karamzin የገጣሚዎቹ  የZhukovsky፣  የLermontov እና የPushkin  የቅርብ ወዳጅ በመሆን ሥሟ ይነሳል፡፡ አብዛኛዎቹ የሐሜት ደብዳቤዎች ሶፊያ ለወንድሟ የፃፈቻቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ስለ Pushkin ስትፅፍ፤ “Pushkin, on the other hand Continues to behave in the most stupid and ridiculous manner.” ትላለች፡፡ ቁጡ ፊቱ የነብር መስሎ፣ ጥርሱን እያፋጨ ሰው ፊት መገተር ልምዱ እንዳደረገ ትገልጻለች፡፡
ሶፊያ የፑሽኪንን ባለቤት እየተከታተለች በማነወር ለወንድሟ ትጽፋለች፡፡ “ፑሽኪን ፊት ጠንቃቃ ትመስላለች፡፡ ዘወር ሲል ግን d’Anthes ላይ አይኗን ሰክታ መንቀል ያቅታታል፡፡ d’Anthes ደግሞ ሳያፍር በድፍረት ወንበር ስቦ  ይቀመጥና ፊቷ ላይ በአይኖቹ ያንዣብባል፡፡”
ለፑሽኪን የፍልሚያ ሞት ያበቃው ይሄ ሁኔታ ነው፡፡ ሶፊያ ብቻ ሳትሆን የእንጀራ እናቷ madame Karamzina ለልጃቸው በሚጽፉት ደብዳቤ ውስጥ ፑሽኪንንና ሁኔታውን የዘገባ ያህል እያረቀቁ ይገልጻሉ፡፡ ፑሽኪን በጥይ ከተመታ በኋላ ሁለት ቀን ተሰቃይቶ መሞቱን በገለፁበት ደብዳቤ ላይ “የተመኘውን ሞት በማግኘቱ፣ መራር ቢሆንም ደስታ ተሰምቶኛል” ይላሉ፡፡
ደብዳቤዎቹ ከመቶ አመታት በኋላ በ1950ዎቹ መጀመሪያ ሲገኙ በሥነፅሁፍ ሙያተኞች፣ “ብዙ ክፍተቶችን የሚሸፍን ግብዓት አግኝተናል” በሚል ተሞካሽቷል፡፡ እውነትም ፑሽኪን በወቅቱ እንደወንጀል በሚቆጠር ፍልሚያ በመሞቱ ግልፅ እና ዝርዝር መረጃ ለማግኘት አልተቻለም ነበርና፣ የሐሜቱ ደብዳቤ ብዙ ክፍተት ሸፍኗል፡፡
የወሬ ስንኩልነቱ ትናንሽ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩና ውሸት መቀላቀሉ ነው፡፡ ስብሐት “ወሬዎች ማማር ይወዳሉ” ይላል፡፡ ወሬዎች በራሳቸው አይኳኳሉም፡፡ እነ የወሬ ቋት፣ እነ ወሬ ምሳው፣ እነ የወሬ አባት…. ይፈሽኗቸዋል እንጂ፡፡
ይሄን የወሬና የወሬኞች ባህርይ የሚረዱት የሩሲያ ስነ ፅሁፍ ተመራማሪዎች፣ የ Karamzin ደብዳቤዎች እንዴት አበጥረዋቸው፣ እንዴት አንፍሰዋቸው ይሆን? እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡
ቆይ! ቆይ! ቆይ!......
…..ስንጀምር ወሬን አነውረን አልነበረም ወይ? ሥነፅሁፍን በማሟላት በኩል እንዴት ቀዳዳ ደፋኝ ሆኖ ተገኘ? ሲቆይ እንደ ወይንጠጅ ትክክለኛ ጣዕሙን ያገኝ ይሆንን? እና ቆይቶም ቢሆን ከጠቀመ ዝም ብለን እንታማ? ዝም ብለን እንማ እንዴ?.....
…. ወደ ሌላ ፀሐፊ ደግሞ ልውሰዳችሁ፡፡ Yuval Noah Harari ይሰኛል፡፡ “Sapiens፡ Homo Deus” እና “21 Lessons from the 21st Century” የተሰኙ የጥናት መጽሐፎች አሉት፡፡   Sapiens ላይ ወሬ፣ ሐሜትና አሉባልታዎች የቋንቋ እድገታችን መሰረቶች ናቸው ይላል፡፡ እንደውም እንደ ንድፈ ሀሳብ ወለዶች “gossip theory” ሲል ለጽንሰ ሀሳብነት ያጨዋል፡፡
Harari “የቋንቋ ዕድገት የተመዘገበው በወሬ፣ በሐሜትና በአሉባልታዎች መስፋፋት ላይ ተመርኩዞ ነው” የሚል አቋምም ያንጸባርቃል፡፡ አዲዮስ!...
… አዲዮስ! ከቋንቋችን ጋር የማሰብና የማውጠንጠን አቅማችን የተያያዘ ስለሆነ Harariን ከተከተልን፣ ሰውን ሰው ያደረገው ሐሜት ነው ብለን ልንደመድም ነው፡፡ ጉድ!!
ከአዘጋጁ፡-
ጋዜጠኛ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ ከአሥር በላይ መጻህፍትን ለህትመት ያበቃ የብዕር ሰው ሲሆን፤ የሚበዙት የህትመት ውጤቶቹ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው - ልብወለዶች፡፡ የጋዜጠኝነት ልምድና ተሞክሮ ያካበተው አለማየሁ ገላጋይ፤በሥነጽሁፍ ሃያሲነቱም በእጅጉ ይታወቃል፡፡ ማህበራዊ ሃያሲም ነው፡፡

Read 1018 times