Saturday, 23 March 2024 20:21

የማህፀን ግድግዳ ካንሰር

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 “ከ100 ሴቶች መካከል 3 ሴቶች በማህፀን ግድግዳ ካንሰር ይጠቃሉ”
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት ኦላና
የማህፀን ግድግዳ ካንሰር (endometrial cancer) በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶችን ከሚያጠቁ የካንሰር አይነቶች መካከል በ6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በ1 ዓመት ውስጥ በካንሰሩ የሚያዙ ሴቶች ቁጥር ከ4 መቶ ሺ በላይ ነው። የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት ኦላና እንደተናገሩት ከ100 ሴቶች መካከል 3 ሴቶች በህይወት ዘመናቸው ውስጥ በማህፀን ግድግዳ ካንሰር የመጠቃት እድል አላቸው።

ለማህፀን ግድግዳ ካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች (ምክንያቶች)
ከመጠን ያለፈ ውፍረት
ደም ግፊት፣ ስኳር እና ተያያዥ በሽታዎች
ያልወለዱ እና መውለድ የማይችሉ የሆኑ እናቶች
እድሜያቸው የገፋ እናቶች (ከ60 ዓመት በላይ)
በማህፀን ግድግዳ የተጠቃ ቤተሰብ መኖር
በዓለምአቀፍ ደረጃ ካንሰር ላይ ጥናት የሚያደርገው ተቋም [International agency for research on cancer] እንዳስቀመጠው ሰሜን አሜሪካ (ዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ) በማህፀን ግድግዳ ካንሰር ተጠቂዎች ብዛት ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች። እንደ አጠቃላይ ያደጉ ሀገራት ካላደጉ ሀገራት አንፃር በማህፀን ግድግዳ ካንሰር ይበልጥ ተጠቂ ናቸው። እ.ኤ.አ በ2018 በተደረገ ጥናት መሰረት በአፍሪካ የማህፀን ግድግዳ ካንሰር ከሌሎች የካንሰር አይነቶች ጋር ሲነፃፀር በ20ኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው። ነገር ግን እንደየ ሀገሩ የስርጭት እና የጉዳቱ እንዲሁም የማገገም ሁኔታው የተለያየ ነው።
የማህፀን ግድግዳ ካንሰር ምልክቶች
የወርአበባ ኡደት መዛባት
የወርአበባ ኡደት (መምጣት) ካቆመ በኋላ ደም መኖር
ሽታ ያለው ፈሳሽ መኖር
ማህፀን አከባቢ ህመም መኖር

በየዓመቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ በማህፀን ግድግዳ ከተጠቁ ሴቶች መካከል ወደ 23.5 በመቶ የሚሆኑ በካንሰሩ ሳቢያ ህይወታቸው እንደሚያልፍ ይገመታል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በማህፀን ግድግዳ ካንሰር ከተጠቁ ሴቶች መካከል ደረጃው ከፍ ሳይል ምርመራ እና ህክምና ያደረጉ ታካሚዎች 90 በመቶ እንዲሁም የበሽታው ደረጃ ከፍ ሲል ደግሞ ከ75 እስከ 80 በመቶ ለ5 ዓመታት በህይወት የመቆየት እድል እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

የማህፀን ግድግዳ ካንሰር ደረጃዎች
ደረጃ አንድ; ካንሰሩ የማህፀን ግድግዳ እና አከባቢ (የማህፀን ጡንቻ) ላይ ብቻ ይገኛል።
ደረጃ ሁለት; በሽታው ከግድግዳ አልፎ ወደ ማህፀን ጫፍ ከደረሰ ደረጃ 2 ይባላል።
ደረጃ ሦስት; ማህፀን አከባቢ ያሉ የሰውነት ክፍሎችን ካንሰሩ ያጠቃል።
ደረጃ አራት; ይህ ደረጃ ከማህፀን ውጪ ያሉ የሰውነት ክፍሎች እንደ ሳንባ እና ጉበት ያሉ ክፍሎች የሚጠቁበት ነው።
የማህፀን ግድግዳ ካንሰር ካለው 4 ደረጃ በተጨማሪ በ2 አይነት (type) ይከፈላል። ይህም የበሽታው አይነት የተከፈለው ጉዳት የሚያደርስ ሆኖ ከፍተኛ ያልሆነ (ሲነፃፀር የቀነሰ) እና ጉዳቱ ከፍተኛ የሆነ (aggressive) በሚል ነው። እንደ ህክምና ባለሙያው ንግግር የመጀመሪያው አይነት ቅድመ ካንሰር በሚባለው ደረጃ ላይ ከታወቀ መታከም እና መዳን ይችላል። ሁለተኛው አይነት ደግሞ እድሜያቸው በገፋ እና ሌላ ተጓዳኝ በሽታ በሌለባቸው ሴቶች ላይ የሚስተዋል እንዲሁም ቶሎ የመሰራጨት ባህሪ ያለው ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሁለተኛው አይነት ከህክምና በኋላም መልሶ የመምጣት (የማገርሸት) ሁኔታ እንደሚኖረው ዶ/ር መሰረት ኦላና ተናግረዋል። የመጀመሪያው አይነት (type one) መንስኤው የታወቀ እንዲሁም ሁለተኛ አይነት (type two) መነሻ ምክንያቱ የማይታወቅ መሆኑን ባለሙያው አክለዋል።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት ኦላና “ካንሰር በመኖሩ ብቻ ጉዳት ይኖራል። ነገር ግን እንደ ደረጃው ጉዳቱ ይለያያል” በማለት ተናግረዋል። እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር ደረጃው ከፍተኛ የሆነ የማህፀን ግድግዳ ካንሰር ህክምና ከተደረገለት በኋላ ተመልሶ የመምጣት (የማገርሸት) ሁኔታ ሊኖረው ይችላል። እንዲሁም ታካሚዎች በህይወት የሚቆይበት ጊዜ (እድሜ) እንደ በሽታው ደረጃ ይለያያል።

የማህፀን ግድግዳ ካንሰር ህክምና
ቀዶ ጥገና; የማህፀን ማምረቻ፣ ማህፀን ሙሉበሙሉ እና ሌሎችም በሽታው የተሰራጨባቸው (ሊሰራጭ የሚችልበት) የሰውነት ክፍሎችን በቀዶ ጥገና ህክምና እንዲወጣ ይደረጋል።
የሆርሞን ህክምና; ልጅ መውለድ የምትችል (የምትፈልግ) ከሆነ ከቀዶ ጥገና ይልቅ ይህ ህክምና ይሰጣል።
የኬሞቴራፒ ህክምና
የጨረር ህክምና

የማህፀን ግድግዳ ካንሰር መከላከያ መንገዶች
ከመጠን ያለፈ ውፍረት መቀነስ
የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ
የስኳር እና የደም ግፊት በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል
የወርአበባ ኡደት ከቆመ በኋላ የሚሰጥ የሆርሞን ህክምና የሚወስዱ ሴቶች የህክምና ባለሙያ ማማከር
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት (የወሊድ መቆጣጠሪያ) አጠቃቀም ላይ የህክምና ባለሙያ ማማከር
በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ልጅ መውለድ
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት ከሆኑት ዶ/ር መሰረት ኦላና እንደተናገሩት የወርአበባ ኡደት ከቆመ በኋላ ደም መኖር (ትንሽም ቢሆን) ጤናማ አይደለም። ወር አበባ ከቆመ በኋላ ደም ካለ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህም ይወርአበባ ኡደት መዛባት ሲኖር የህክምና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል። ስለሆነም ለማህፀን ግድግዳ ካንሰር የሚያጋልጥ መንስኤ (ምክንያት) ሲኖር ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ህክምና ማድረግ እንደሚያስፈልግ  የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት ኦላና ተናግረዋል።

Read 273 times