Saturday, 23 March 2024 19:58

ኢትዮጵያ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ናት ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  -  ባለፈው ዓመት 7 ሺህ የሚጠጉ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገዋል
ኢትዮጵያ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነታቸው ከፍ ካሉ ሀገራት  መካከል አንዷ እንደሆነችና የሳይበር ጥቃቶቹ  የፋይናንስና የፀጥታ ተቋማትን፣ ባንኮችን፣ እንደ ቴሌኮምና መብራት ሃይል ያሉ  ተቋማትን፣ መሰረተ ልማቶችንና  ቁልፍ የመንግስት ተቋማትን  ኢላማ ያደረጉ እንደሆኑ  ታዋቂው የሳይበር ደህንነት ተቋም ሲዮን ገልጿል።
ተቋሙ ከትናንት በስቲያ  ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤  ዓለማችን በኢንተርኔት መተሳሰሯና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ጥገኝነቷ በፍጥነት እያደገ መሄዱን ተከትሎ የሳይበር ጥቃትም ፈተና ሆኖባታል። ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ከ340 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ተጎጂ ያደረጉ የሳይበር ጥቃቶች ተፈጽመዋል ።
ግለሰቦችን፣ ተቋማትን እና የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ኢላማ ባደረጉ የሳይበር ጥቃቶች፣ በ2023 ብቻ ከ8 ትሪሊየን ዶላር በላይ የሚገመት ጉዳት ደርሷል።
የሳይበር ጥቃት የትኛውንም ሀገር ወይም ተቋም ለይቶ እንደማይተው የሚገልጸው ታዋቂው የሳይበር ደህንነት ተቋም ሲዮን፥ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ህግና ቴክኖሎጂ ያላቸው ሀገራት አደጋውን መቀነስ መቻላቸውን ገልጿል።
በአንጻሩ ደካማ የሳይበር ደህንነት ህግ ያላቸው አልያም ከነጭራሹ የሌላቸውና ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመመከት የሚጠቀሟቸው ቴክኖሎጂዎች ከፈጣኑ የዲጂታል አለም ጋር አብሮ በማይሄድባቸው ሀገራት አደጋው እንደሚከፋም ጠቁሟል።
በዚህም መሰረት ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭነታቸው ከፍ ያሉ ናቸው በሚል  በተቋሙ  ከተጠቀሱ ሀገራት መካከል  ኢትዮጵያ የምትገኝ ሲሆን፤ አገሪቱ  ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ በመሆን ከአለማችን  በ8ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች  ብሏል።
ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ የሳይበር ምህዳሩን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ፣ በግለሰቦችና ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን ጨምሮ በሀገሪቱ  ቁልፍ የመንግስት መሰረተ-ልማቶች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች የብሄራዊ ደህንነት ስጋት መሆናቸውን የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ  የሚታወስ ሲሆን፤  ባሳለፍነው ዓመት 2015 ዓ.ም  ከ 6 ሺ 959 በላይ  የሳይበር ጥቶች መፈጸማቸውንም ጠቁመዋል።
ከሳይበር ጥቃቶቹ ውስጥም 2 ሺ 559 ያህሉ በድረ ገጽ ላይ የተፈጸሙ ሲሆኑ፤ 1 ሺህ 295 ያህሉ ደግሞ የማልዌርና የፒሺግ መሆናቸው ተጠቁሟል። እንዲሁም 603 በመሰረተ ልማት ቅኝት፣ 1 ሺህ 493 መሰረት ልማት የማቋረጥ (አብዛኛው የፋይናንስ ተቋማትን ኢላማ ያደረገ)፣ 695 ሰርጎ የመግባት ሙከራ እና 145 ሌሎች የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተደርገዋል።
የሳይበር ጥቃቶቹ የፋይናንስና የፀጥታ ተቋማትን፣ እንደ ቴሌኮምና መብራት ያሉ ቁልፍ ተቋማት መሰረተ ልማቶችንና  ቁልፍ የመንግስት ተቋማትን  ኢላማ ያደረጉ ነበሩ ተብሏል። በ2015 የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን መከላከል በመቻሉም፣ በሀገር ላይ ሊደርስ የነበረ 23.2 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማዳን መቻሉን የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ማስታወቃቸው አይዘነጋም ።

Read 796 times