Monday, 18 March 2024 17:16

ከመርካቶ ሰማይ ሥር

Written by  ብርሃነ ዓለሙ ገሣ-
Rate this item
(2 votes)

”--ምዕራብ ሆቴል የቡና ቤት፣ የመኝታና የሬስቶራንት አገልግሎት ከመስጠቱ በተጨማሪ መነሻና መድረሻ ምልክት
እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ በጊዜው ግዙፍና ዘመናዊ ከሚባሉት ፎቆችም አንዱ ነበር፡፡ በመርካቶ መሃል፣ “ማማ በሰማይ
ላይ!” ሆኖ ለዓመታት ነግሦ ቆይቷል፡፡ ሆቴሉ፦ መቀጣጠሪያ፣ መገናኛ፣ መተዋወቂያ፣ የተቸገረን መርጃ፣ ዕርዳታ
ማሰባሰቢያ፣ የተጣላን ማስታረቂያ፣ የቢዝነስ ሃሳብ ማመንጫ፣ የጋብቻ (የሰርግ) መርሐ ግብር ማውጫ፣ የልማት ምክረ
ሃሳብ ማዘጋጃ፣ ክፉና ደግ ማቀጃና ማቀጣጠያ ወዘተ. ነበር፡፡ --”


በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ፊደል ቆጥሬ ለመጠነ ንባብ ስበቃ፣ “ጂኦግራፊ” የሚባል የትምህርት አይነት ተዋወቅኩ፡፡ ብዙም ሳልቆይ በግሪክ ቋንቋ ጂኦ ማለት ምድር፣ ግራፊ ማለት ደግሞ ጽሑፍ ማለት እንደሆነ ለመረዳት ቻልኩ፡፡ ስለ ምድር መጻፍ፡፡
በወቅቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን እያጠናከርኩ ስሄድ፣ “ምዕራብ ማለት፣ ፀሐይ  የምትጠልቅበት የዓለም ክፍል” እንደሆነም ተረዳሁ፡፡ ከአራቱ አቅጣጫዎች አንዱ መሆኑንም ተገነዘብኩ፡፡ በልጅነት ጊዜዬም አዲስ አበባ (በአካባቢያችን አጠራር ሸዋ)ን ለማየት ዕድል አገኘሁ፡፡ በወቅቱ ዘመዶቼ፣ “ወልቂጤ ወሊሶ ካልተመላለሱ፣ ገንዘብ ከየት ይገኛል ኪስን ካልዳበሱ” ሲሉ ሰምቼ ነበርና አዲስ አበባ ስመጣ የተሰማኝ ደስታ ልክ አልነበረውም፡፡
ወይ አዲስ አበባ የሁሉ ሰው አገር፣ መጠጫው ብርሌ መቀመጫው ወንበር” ተብሎ የተገጠመላት አዲስ አበባ፡፡
ጊዜው ሐምሌ 1964 ዓ.ም ነበር፡፡ ከገጠር እንደመጣሁ በመጀመሪያ ያየሁት መርካቶ የሚገኘው ባለ አራት ወለሉ ምዕራብ ሆቴልን ነበር፡፡ ምዕራብ ሆቴል - የመርካቶ አድባር፡፡
በዕድሜ የሚገዳደሩት እነ አስፋው ወሰን፣ አዲስ አበባ እና አስፋው ተክሌ ሆቴሎች እንደነበሩ አቶ መልስ ጭብሳ ነግረውኛል፡፡
ቆይቶ ቃኘው ሻለቃ፣ አዲስ ከተማ፣ 14ቱ፣ አክሱም፣ የምሥራች፣ አምባሳደር፣ ብሔራዊ፣ ተሰማ፣ ምሥራቅ፣ ጨረቃ፣ ከፋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ዋርካ፣ ነጻነት ጎህ፣ ኬኔዲ፣ ኤርትራ፣ ጎረምስ (ደበበ ተክሌ)፣ መቀሌ፣ ራስ ሥዩም፣ ጎህ፣ ፋሲል፣ ጭላሎ፣ መነን፣ መክሊት፣ ዓባይ ዙሪያ፣ ጭላሎ … ሆቴሎች በመርካቶና ዙሪያው ተከፈቱ፡፡
ምዕራብ ሆቴል የቡና ቤት፣ የመኝታና የሬስቶራንት አገልግሎት ከመስጠቱ በተጨማሪ መነሻና መድረሻ ምልክት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ በጊዜው ግዙፍና ዘመናዊ  ከሚባሉት ፎቆችም አንዱ ነበር፡፡ በመርካቶ መሃል፣ “ማማ በሰማይ ላይ!” ሆኖ ለዓመታት ነግሦ ቆይቷል፡፡ ሆቴሉ፦ መቀጣጠሪያ፣ መገናኛ፣ መተዋወቂያ፣ የተቸገረን መርጃ፣ ዕርዳታ ማሰባሰቢያ፣ የተጣላን ማስታረቂያ፣ የቢዝነስ ሃሳብ ማመንጫ፣ የጋብቻ (የሰርግ) መርሐ ግብር ማውጫ፣ የልማት ምክረ ሃሳብ ማዘጋጃ፣ ክፉና ደግ ማቀጃና ማቀጣጠያ ወዘተ. ነበር፡፡ በመርካቶ ጠፈር ሥር ባለው ምዕራብ ሆቴል ምን ያልተሠራና ያልታቀደ አለ?  
በመርካቶ መሃል - በመርካቶ ሰማይ ሥር፣
ምዕራብ ሆቴል - በበጎ አድራጎት ሲፈጠር
ከዚህ በርሮ - ከዚያ አምልጦ፣
በእንካ ሰላንቲያ ተለጣልጦ - ተፋልጦ
የኑሮን ውል ፈትቶ ለመቋጠር፣
የደረቀን ጉሮሮ ለማርጠብ
የጎደለን ሆድ ለመሙላት
ምዕራብ ጓዳ ገብቶ
ምን ጠፍቶ?
ወፈ ሰማይ ሰው ያርፋል - ተመቻችቶ፡፡
ባለቅኔው ደራሲና ገጣሚ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ “እሳት ወይ አበባ” በሚለው መጽሐፋቸው፣ አይ መርካቶ የሚል ርዕስ በሰጡት ግጥማቸው፣ ምዕራብ ሆቴልን አለማካተታቸው ያንገበግበኛል፡፡
ምዕራብ ሆቴል፣ ከተመሠረተ እነሆ 54 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ መጀመሪያ ሆቴሉን ተከራይተው በ1962 ዓ.ም ሥራ ያስጀመሩት አቶ ነጋ ቦንገር፣ አቶ መልስ ጭብሳና አቶ ወልዴ አሰና መሆናቸውን ከአቶ መልስ ጭብሳ ጋር ባደረግኩት ቃለ ምልልስ ገልጸውልኛል፡፡ ሕንጻውን ያሠራው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት የመርካቶ የገበያ አዳራሾችን፣ አንበሣ የከተማ አውቶቡስ ድርጅትንና ሌሎችንም ያስተዳድር እንደነበር ይታወቃል፡፡
አቶ መልስ፣ ለምዕራብ ሆቴል መጀመሪያ ያወጡለት ሥም ”ማርቲን ሉተር ኪንግ“ (የጥቁሮች መብት ተሟጋች) የነበረ ሲሆን፤ ዳሩ ግን በወቅቱ ከነበሩት የአዲስ አበባ አራቱ ዞኖች መካከል የምዕራብ ዞን የፖሊስ አዛዥ፣ ”ሉተር ኪንግ” የሚለውን ሥም በመተው፣ በሚመሩት ዞን በምዕራብ ሥም እንዲሰየም አድርገዋል፡፡  
እኔ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ፣ በ1964 ዓ.ም አዲስ አበባ እንደመጣሁ አባቴ ካስጎበኘኝ የማልረሳቸው ቦታዎች አንዱ መርካቶ ሲሆን፤ በተለይ ምዕራብ ሆቴል አካባቢ እንደነበር አልረሳሁም፡፡ እዚህ ገጠመኝም አለኝ፡፡ በምዕራብ ሆቴል በር በኩል ከአባቴ ጋር ስናልፍ፣ የኪስ መሃንዲሶች ብር የያዝኩ መስሏቸው ከአባቴ ለይተው አገቱኝ፡፡ አባቴ እንደ ጎሽ ተቆጥቶ ቀንድ አብቅሎ ሊዋጋ ሲዘጋጅ ለቅቀውኝ ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ ጀንበር ሳለች ሩጥ፣ አባት ሳለ አጊጥ እንዲሉ፡፡ ሌላው እዚሁ አካባቢ ስንዞር፣
“አባ!” አልኩት
“አቤት”
“የአዲስ አበባ ሰው አንዱ ጋ ተከማችቶ አይለም እንዴ የሚኖረው?” ጠየቅኩት፤ ፈርጠም ብዬ፡፡ መልሱን ሳይመልስልኝ ከት፣ ከት ብሎ ሳቀ፡፡  የአዲስ አበባ ሕዝብ እንዲህ በየፊናው የሚበታተን ሳይሆን አንዱ ጋ ተከማችቶ የሚኖር ይመስለኝ ነበር- አገር ቤት (ገጠር) እያለሁ፡፡
አዎ ምዕራብ ሆቴል በአእምሮዬ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ታሪክ አለው፡፡ በርካታ የሚያስቁና የሚያሳዝኑ ሁነቶችም ተስተናግደውበታል፡፡ በሰባት ቤት ልክ እንደ አለቃ ገብረሐና አሽሙርና ቀልድ የሚቀናቸው የደቤዎች (ጅገሮች)፣ ምዕራብ ሆቴል ድረስ ዘልቀው ብዙ ቀልደዋል፡፡ ብዙ አሹፈዋል፡፡ ብዙ አስቀው - ጥቂትም ቢሆን ማሳዘናቸው ግን አልቀረም፡፡ ለማንኛውም የደቤዎች እንዳማረባቸው ለዘለዓለም ይኑሩ!
ከዕለታት በአንዱ ቀን ነው አሉ፤ አንዱ ነጋዴ በምዕራብ ሆቴል ይሰበሰብ የነበረው ዕቁብ ይደርሰዋል፡፡ ዕቁብ የደረሰው የፍንጥር ይሰጣልና ውስኪ አወረደ፡፡ መርቅ ተባለ - በዕለቱ በሥፍራው የተገኘው የደቤ (ጅገር)፡፡ በቅኔ የታጀበው ምርቃቱን አዥጎደጎደው፡፡ እንዲህ ብሎ፦
“እናንት ኧዣዎች ወጣችሁ ይጣፍጥ፤ እናንት ጎማረዎች እንደ ማር ጣፍጡ፤ እናንት ቸሃዎች ፊደል ሁኑ፤ እናንት እኖሮች አጥንታችሁ ይመር” ብሎ ቅኔውን አወረደው፡፡ ቅኔው የገባቸው ተቆጡ፡፡ ያልገባቸው ግን ለተወሰኑ ደቂቃዎችም ቢሆን ከልባቸው ሳቁ፡፡  
ኧዣዎች የሆቴል ሥራ ስለሚያዘወትሩ ነው ወጣችሁ ይጣፍጥ ያለው፤ ጎማረዎች በወቅቱ ጠጅ  ይነግዱ ስለነበር ነው፡፡ ቸሃዎች ትምህርት ላይ ቀዳሚ ስለነበሩ፣ እኖሮች ደግሞ በብዛት ሉካንዳ ሥራ ላይ ስለተሰማሩ ነው፡፡
በ“የቡና ቤት ስዕሎች” ድርሰቱ የምናውቀው ጋሽ መስፍን ኃብተማርያም (ነፍስ ይማር)፣ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት፣ “መርካቶ ምዕራብ ጋ ጠብቂኝ” የሚል ርዕስ በሰጠው ገጹ፣ ምዕራብ ሆቴልን መነጋገርያ አድርጎት እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ምዕራብ ሆቴል የዘመኑ ሰዎች እንደልማዳቸው ተነስቶባቸው እናፍርስ ካላሉ ወደፊት ብዙ ገድል፣ ብዙ ታሪክ ይጻፍለታል፡፡
ምዕራብ ሆቴል፣ አሁንም ብዙዎች ተቀጣጥረው ይገናኙበታል፡፡ አገልግሎት በመስጠቱ ረገድ አሁንም ሞቅ እንዳለ ነው፡፡
ሰው ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ምዕራብ ሆቴል በወጣትነት ዘመኑ አምሮና ደምቆ ታይቷል፡፡
ብዙዎች፣ የባላገርነትና የሞኛሞኝነት  ጠባያቸውን ገፍፈውበታል፡፡ ከከተሜዎች ጋር ተገናኝተውበታል፡፡
 በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተተኩሰውበታል፡፡የዘመኑ ቆንጆዎች በምዕራብ ሆቴል አስተናግደዋል፤ ከፍ ሲልም ተንፈላስሰውበታል፡፡
ብዙዎች ደግሞ ነሁልለውበታል፡፡  የምዕራብ ሆቴል አዘውታሪ የነበሩ ደንበኞች፣ በጉራግኛ የተቀኙለት ግጥም የሚከተለው ነበር፡፡ውጨም ኧዢ መርካቶ፣
በኮረንቲ ፎቅ ይወጬ
አንቅፉወ ይጠውጪ
ቴጎዢም ኤብ ይሰጪ
በህም ቦነም - በህም ይቆዢ
የመርካማ አምሳ ይኰሺ
የኖዘነ ሁያ ይኰሺ
ያኽዬ ጄኔራል - በምዕራብ ውቴል ወረጀ ያዢ፡፡
ነጻ ትርጉሙ የሚከተለውን ይመስላል፤
ወጥተሸ እይው መርካቶን፣
በኮረንቲ ፎቅ ይወጣል
ማንኪያ ይያዛል
ሳያረቡ ወተት ይጠጣል
እዚያው ተበልቶ እዚያው ይሸናል
ለቆንጆ 50፣ ለመልከ ጥፉ ብር 20 ይከፈላል
ጄኔራልሽ በምዕራብ ሆቴል በር ላይ ቆሞ ታይቷል፡፡ (በኮረንቲ ፎቅ መውጣት ለአሳንሰሩ ሲሆን፤ ጄኔራል የተባለው ደግሞ የደንብ ልብስ የለበሰው የጥበቃ ሠራተኛ መሆኑ ነው)
ምዕራብ ሆቴል፣ ለ16 ዓመታት ያህል ጊዜ በሶስቱ ጓደኛሞች ሽርክና ሲተዳደር ቆይቶ ቀጥሎ ግን ወደ አቶ ክፍሌ ወልዴ ተዘዋውሮ (አቶ ክፍሌ አሁን በሕይወት ባይኖሩም በልጃቸው ወ. ገነት ክፍሌ) እስከዛሬም ድረስ ሥራው በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ወደ ሆቴሉ ለመግባት ከፊት ለፊት የተነጠፉት መደቦች እክል ስለሚፈጥሩ ሥርአት ሊበጅላቸው ይበጃል፡፡
ከሆቴሉ ወደ ሰባተኛ በሚወስደው መንገድ ግራና ቀኝ ረድፍ ላይ የሚታየው ቆሻሻ ለአካባቢው ገጽታና ጤንነት ፀር ስለሆነ በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
አዲስ አበባ ቆሻሻ ከተማ ናት ለሚሉ ጥሩ ምስክር ይህ ቦታ ነውና አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ መርካቶዎች በጽዳቱ በኩል ነቃ በሉ እንጂ፡፡  
ሆቴሉ፣ የአዛውንትነት ዕድሜ እየተጫጫነው ወገቤን እያለ ስለሆነ አፋጣኝ እድሳት፣ ጽዳትና ጥገና እንደሚፈልግ በቆይታዬ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡
ምዕራብ ሆቴል፣ አዎ የብዙዎች የእንጀራ ማግኛ፣ ማረፊያና ማኅበራዊ ችግር መፍቻ ስለሆነ በአድባርነቱ ይቀጥል ዘንድ የባለድርሻዎች ድጋፍና ትብብር ባይለየው እላለሁ፡፡ ሰላም ሁኑልኝ!     

Read 664 times