Sunday, 17 March 2024 20:04

ውድነህ ክፍሌ በሽልማት ዓይኖች!

Written by  ደ.በ-
Rate this item
(1 Vote)

የቱም ሰው በየትኛውም የሕይወት ምህዋር እንጀራውን ይዞ ወዲያ ወዲህ የሚልና በአፀደ ስጋ የሚኖር፣ በዚህ ምድር ላይ በየተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን የራሱ የሰውዬውና የሚኖርበት ከባቢና ቤተሰቡን ጨምሮ ከአካባቢው የወሰዳቸው ማንነቶች የሕይወቱን ዕጣና የርሱንም ማንነት ይወስኑታል።
በተለይ መልካም የሥራ ከባቢ (Good working condition)፣የሚባለው የኑሮውና የውጤቱ መልክ ማያዎችን ማቃናት ይችላል። አብሮዋቸውየሚማሩ ተማሪዎች፣ አብሮዋቸው የሚሠሩ ባልደረቦች በውጤቱ ላይ በጣም ወሳኞችና አሻራ የሚኖራቸው ናቸው።
ሌላው ቀርቶ አመቺ የአየር ጠባይ፣የሚያሠራና የሚያበረታታ አለቃ፣የሚደግፍ/የምትደግፍ የትዳር አጋር ወዘተ ሲመቻች ለተሻለ ትጋትና ላማረ ውጤት ያበቃሉ። በተጨማሪ በየዘመኑና ደረጃው የገጠሙት፣መምህራን ሳይቀሩ  ለኋላ ማንነቱና ውጤቱ ቀላል የማይባለውን ሚና ይጫወታሉ።
ብዙ  ትልልቅ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው፣ ለበጎም ለክፉም አሻራቸው ዕድሜ ዘመን እንደ ጥላ የሚከተል አስተዋጽዖ አላቸው። በግሌ በጥላሁን ገሠሠ ሕይወትና ሥራዎች ላይ በነበረው ውጤትና ማኅበራዊ ምስቅልቅል፣ የሰው ልጅ ጋን ቢሆን እንኳ የተደገፈባት ጠጠር የሕይወቱን አቅጣጫ እንደምትለውጥ ዘከርያ መሐመድ ሸጋ አድሮጎ ከጻፈው የሕይወት ታሪኩ ብዙ ተገንዝቤያለሁ። እንደ ሥነልቡናዊ ምሁራን ትንተናና አተያይ፣ ሌላው በሰው ልጅ ሕይወትና ሰብዕና ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣው ከትዳር አጋር ያለ ግንኙነት ነው። እዚህ የሕይወት ማማ ላይ ለተሳካ ግብ፣ወይም ለተጸነሰ ሕልም መጨንገፍ ምክንያት የሆኑ ክስተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
በአብዛኛው፣አንድ ሰው የተሻለ ውጤት ካሳየ የውጤቱ ምክንያት የትዳር ጓደኛው ትሆናለች ተብሎ ይታመናል፡፡ በተለይ የኪነ ጥበብ ሰው ከሆነ፣ጠባዩን የምትረዳለት፣ጊዜ የምትሰጠውና ክፍተቱን የምትሞላለት ከሆነ፣ ከዕድገቱ ዝንፍ ሳይል ይቀጥላል።
 የዛሬ ዐቢይ ጉዳዬ ትዳርና አካባቢ ሳይሆን፣ በእነዚህ እቅፎች ውስጥ አድጎ በኪነጥበቡ ሰማይ ያበራው ጸሐፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ነው። ውድነህን ብዙዎቻችን ያወቀነው” ነጭ ጥቀርሻ”ን እንዲሁም  ሌሎች በርካታ ቴአትሮችን ይዞ ከመጣ በኋላ ቢሆንም፣ ከዚያ  በፊት  የሚገርም ታሪክ እንዳለው የምናውቅ ጥቂቶች ነን።
አዎ፣ውድነህ ከደራሲነት ይልቅ በአዳጊ ዕድሜው የሚታወቀው በቴሌቪዥን ቴክኒሽያንነትና በልዩ ልዩ የፈጠራ ሥራው ነው። በፈጠራ ሥራው ለሠፈር የሚታይ ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ በቴሌቪዥን ኢንተርቪው የተደረገበትና በጋዜጣ ላይ እንግዳ የሆነበትን ሥራ ሠርቶ ለአደባባይ በቅቷል። ታዲያ የትኛውን የሳይንስ ግኝት ይዞ ይመጣል?...ምን ፈጥሮ ያስደንቀናል የተባለው ወጣት፣ ባልተጠበቀ ሁኔታና መንገድ እንጀራውና ሕይወቱ ቴአትር ቤት ሆኖ ተገኘ።
ይህን ከያኒ በተለያየ አጋጣሚ ቴአትሮቹን በማየትም ሆነ፣በጥበቡ ክበብ አግኝቼም ቀርቤም አይቸዋለሁ። በተለይ ከጋዜጠኛ ተመሥገን በየነ ጋር ያዘጋጁት በነበረው “ሙዳይ” የሬዲዮ ፕሮግራም ምክንያት ብዙ ተቀራርበናል። እኔም ከእነርሱ ጋር በመሥራቴ ”የናፍቆት ጥላዎች” የሚለውንና በደብዳቤ ቅርጽ ያሳተምኩትን ልቦለድ መጽሐፍ ማዘጋጀት ችያለሁ፡፡
ታዲያ በዚህ ቅርርቤ እንዳየሁት እኛ ሀገር በቅርብ ከማውቃቸው ብዙ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች፣ እንዲያውም ከዚያ ክብ ውጭ ካየኋቸው ሁሉ ትዳሩን በእጅጉ የሚያከብርና ትዳሩም እርሱን የሚያከብረው ሰው፣ ጸሐፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ስለዚህም በተለይ ብዙ ሥራዎችን በሠራበትና ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ በነበረበት ጊዜ፣ቤቱ ስለሚመቸው በጣም በጊዜ የሚገባ፣ገብቶም  ለውጤት የሚተጋ  ሰው ስለሆነ፣ በሀገራችን የቴአትር ታሪክ ውስጥ ወደ ሃያ የሚጠጉ የመድረክ ቴአትሮችን፣በርካታ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድራማዎችን ጽፏል። ከዚያም ሌላ “ላማሰበቅታኒ”በሚል ርዕስ አንድ የልቦለድ መጽሐፍ አሳትሟል።
በሚገርም ሁኔታ አንዳንዴ ውድነህ ክፍሌ፣ በከተማው ባሉ ሦስት ቴአትር ቤቶች ውስጥ በአንዴ ሦስት ቴአትሮች ይታዩለታል። ይህ ደግሞ ብዙዎችን የሚያስደንቅና የሙያው ቅርብ ሰዎች እንደሚሉት፣”ውድነት የቴአትር ቤቶቻችን ጉሮሮ እንዳይደርቅና እርሻው ጦም እንዳያድር የማይነጥፍ ምንጭና ባለውለታ ነው።” በሌላ በኩል፤ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ መቸም ሆኖ በማያውቅ ደረጃ “ባቢሎን በሳሎን” የተሠኘና ብዙውቻችን ደጋግመን ያየንለት ቴአትሩ ያለማቋረጥ ለረዥም ዐመታት በመታየት የሀገራችንን ቴአትሮች የመድረክ ዕድሜ ክብረ ወሰን የሰበረ ነው። ይሁን እንጂ ውድነህ የድካሙን ያህል ያላገኘ፣የሥራውን ያህል ያልተዘፈነለት የጥበብ ባለውለታ ነው። የራሱም ዐይነ አፋርነት ተጨምሮበት፣ ስሙ በአደባባዮች ላይ መድመቅ ያለበትን ያህል አልደመቀም። ወይም በበቂ ደረጃ አደባባዮች ላይ አልተሸለመም።
ሌላው ውድነህ፣ከሥራው ባሻገር ሊነገርለት የሚገባ ብዙዎቻችን ለማድረግ የምንቸገርበት ጥሩ ባህርይ አለው። ያም የሚሠሩ ሰዎችን  በወጉ ማበረታታት ነው። እርሱ ግን ለብዙ ዐመታት በተሠማራበት የቴአትር ጽሑፍ ሌሎች ገብተው እንዲጽፉ ሲገፋና ሲያደፋፍር፣ በሙያው ካለው ልበሙሉነት ባሻገር ቅንነቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
እኔ በግሌ ቀደም ሲል በጠቀስኩትና ከተመስገን በየነ ጋር በሚያዘጋጁት ሙዳይ የሬዲዮ ፕሮግራም ጊዜ በነበረን አብሮነት እንዳየሁት፣ውድነህ ሰዎችን ለበጎ ሥራ ቀስቃሽ ነው። በዚህ አጋጣሚ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለጻፍኳቸው  ሦስት የራዲዮ ድራማዎች ጉዳይ ማንሳት እወዳለሁ፡፡ ይህን የማልደፍረውንና የማልሞክረውን ተራራ፣እጄን ጎትቶ ያወጣኝ፣የጻፍኩትን መሥመር ያበጀልኝ፣ማበጀት ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት እንድሠራ የቆሰቆሰኝ ሰው ነው። እኔ ግን ሠፈሬም ዝንባሌዬም ባለመሆኑ ወጣሁ እንጂ እንደ ውድነህ ምኞት፣ ቴአትሮችን የምጽፍ፣ተከታታይ የቴቪ ድራማ የማቀርብ የዘርፉ ሰው ሆኜ ነበር። ውድነህ ከዚህ አለፍ ሲልም፣ በተጣበበ ጊዜው ጽሑፍ “እይልኝ”ሲባል፣ ያለው መልካምነት የሚገርም ነው።እንደ ብዙውቻችን አይታሽም፤በዚያ ላይ ወስዶ አስተያየት ሲሰጥ በፍጥነትና ከልቡ ነው፡፡
ውድነህ ቀና ልብ ስላለው፣በየትኛውም አጋጣሚ፣ ስለማንም  በአሉታዊነት መናገር አይወድድም። እንዲያውም በእኔ ትርጉም፣ ውድነህ ስለ አንድ ሰው አዝኖ ትንሽ ከተናገረ፣”ያ ሰውዬ ምን ያህል አስቸጋሪ ቢሆን ነው?”የሚል ግምት ይሰጠዋል። ስለበደሉት ሰዎች እንኳ አምልጦት አይናገርም። ከተናገረ ግን የቱን ያህል በሰው ላይ ቋጥኝ የሚንድ ሰው ገጥሞት ቢሆን ነው?..የሚል ግምት እንዲሰጠው ያደርጋል።
ታዲያ ከላይ የጠቃቀስኳቸውንና ሌሎችም ማኅበራዊ በጎነቶቹን ስናይ በሥራው ብቻ ሳይሆን፣አንዳንድ ሀገራት ላይ ስለሥነምግባራቸው ሙገሳ እንደሚጠግቡና እንደሚከበሩ የኪነት ሰዎች ሙገሳ መጥገብ የሚገባው ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ባሕላችን ይህንን ስላላዳበረ፣ውድነህ የዚያ ዐይነቱን ዘውድ አልጫነም። ቢሆንም በሥራም ሆነ በሥነምግባር  ለትውልድ አርኣያ የሚሆን ሰው ስለሆነ በዚህም በአደባባይ ሊመሰገን ይገባ ነበር።
እንግዲህ ዛሬ የውድነህን ስምና ሁለንተና ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም፤ከሰሞኑ በአዲስ አበባ አስተዳደር የባሕል፣ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከተካሄደ  የሽልማት ሥነ ሥርዐት ጋር በተያያዘ ማለት የፈለግሁት ጥቂት ነገር ስላለ ነው። እውነት ለመናገር ውድነህን በብዙ ዐመታት አንዴ መሸለም ብርቅ አይደለም። ቢቻል በየዐመቱ መሸለም የነበረበት ሰው ነው። ሌላው ቀርቶ ጉሮሯቸውን ያለማቋረጥ የሚያርስላቸው፣አንጀታቸውን የሚያነሳ መብል የሚያዘጋጅላቸው ቴአትር ቤቶች ሊሸልሙት ይገባ ነበር።...ምክንያቱም ያለማቋረጥ መግቧቸዋልና! ይህ ግን አልሆነም፤ምናልባት ባለማስተዋል አሊያም በግድየለሽነት ተገቢውን ሽልማትና ክብር አላገኘም። ይህ ግን ከመሥራት አላገደውም። ሆኖም አንድም ጥሪው በመሆኑ፣በሌላም በኩል ጥረቱ ታክሎበት ውድነህ ቀጥሏል። ከአፍላ ወጣትነቱ ጀምሮ አሁንም በቅርቡ እንደምናየው የውዴታ ግዴታው ሆኖ ጊዜውን በሚገባ ተጠቅሞ፣እስካሁን የቴአትር ጥማታችንን ለማርካት ነጋ መሸ እየባተለ ነው። በዚህ ሁኔታ ሳለ በቅርቡ የአዲስ አበባ ባሕል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ለውድነህ ክፍሌ ደመቅ ያለ ሥነሥርዐት አዘጋጅቶ፣የሞያ ባልደረቦቹና ሌሎች የሕብረተሰቡ አባላት በተገኙበት በአደባባይ   ሸልሞታል።
 ይህ ሽልማት ብዙዎቻችንን ያስደሰተና ለሌሎችም አርአያነት ያለውና ሊለመድ የሚገባው ነው። በግሌ ስለ ሽልማቱ ሳስብ” እንዴት አድርገው አዩት?..እንዴት መዝዘው አወጡት?..ትክክለኛ ሰው መረጡ”ብዬ አልደነቅም። ምክንያቱም ውድነህን በቴአትር ዘርፍ መርጦ ለመሸለም ሰው ብቻ ሳይሆን የቴአትር ቤት እልፍኞችና አደባባዮች ሳይቀር የሚመሰክሩለት ትጉህ ደራሲ ነው። ይልቅስ ስለዚህ ሽልማት ሲነሳ ትኩረቴን የሳበውና ስሜት የሰጠኝ፣  ገጣሚና ደራሲ ታገል ሠይፉ ሽልማቱን ያየበት መንገድ ነው።
በታገል አባባልና አተያይ (እኔም እስማማበታለሁ)፤ የዚህ ሀገር ሽልማት ባብዛኛው ባለሞያ ወይም ባለተሰጥዖው ከሥራው የመዳከሙ፣ከሜዳው የመገለሉ ማሳያ ተደርጎ እስኪታይ ደርሷል። ምክንያቱም እንደልማድ ተወስዶ ብዙ ሰው የሚሸለመው፣ደክሞ መሥራት ሲያቅተውና ከውድድር ውጭ ሲሆን ወይም ምርኩዝ ሲይዝ ነው። ይህ የሚሆነው ለምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ደስ የማይልና ሥር የሰደደ ክፉ በሽታ ነው፤ምናልባትም ከፍ አድርገን ካየነው መርገም ነው።
ልብ ብለን ካየን በተለይ በፊት በፊት፣የክብር ዶክትሬት እንኳ ከተሰጣቸው ሰዎች አብዛኞቹ፣አንድ እግራቸው መቃብር ከገባ፣ወይም መሥራት ካቆሙ በኋላ የተሰጣቸው ነው።  አሁን አሁን እንኳ የክብር ዶክትሬቱ ትርጉም የሰፈር ፉክክር እስኪመስል ድረስ ትርጉሙ ስለተበላሸና በዚሁ ሰበብ ክብሩም ዝቅ ስላለ፣ ጠለቅ ብለን ባናነሳውና ልባችን ባይደማ እመርጣለሁ።
የዛሬው ዋናው ነገር  ግን በጥሩ ዕድሜ፣በሥራ ላይ፣በሩጫው መም ላይ ያለውን ውድነህ ክፍሌን በመሸለሙ ሸላሚው ወገን በዚህ ሥራው ሊመሰገንና አርአያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ለማለት ነው። ምክንያቱም ሽልማት ለሚሠራ ሰው ጉልበት ይጨምራል፤ልብ ያበረታል። በዚያ ብቻ ሳያበቃ ሌሎች ተተኪዎችን ለመፍጠር መንገድ ይደለድላል። ለሀገር ውለታ የዋሉ ሰዎች ሳይደክሙና ጡረታ ሳይወጡ፣ጉልበታቸው ሳይዝል መሸለም እንዲለምድብንም ሌላ አቅጣጫና ልማድ ያመላክተናል።ስለ ሽልማት ካነሳን አይቀር፣ በየሞያ ዘርፉ ብዙ የደከማችሁና የድካማችሁን ያህል ያልተመሰገናችሁ ብትኖሩ ሥራችሁና ታሪካችሁ ያመሰግናችኋልና በርቱ! ሌሎቻችሁ ደግሞ ሥራችሁ ሀገር  ሞልቶ፣የብዙ ሰዎችን ቀለም ቀይሮና መንገድ አሳምሮ ምሥጋና እንኳ የተሰሰተባችሁና እኛን የሠራችሁ እንደ ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ ያላችሁ ውዶችና ምርጦች ደግሞ እኛ ሽልማቶቻችሁ ነንና በርቱልን።...የኛ ልብ ያጥንላችኋልና በርቱ! እንደ ጸሐፌ ተውኔቱ  ውድነህ ክፍሌ ባለቤት፣(እንደባለቤቷ አጠራር “ፍሬ”) ቤታችሁንና ትዳራችሁን ሠርታችሁ፣ ለእኛ የሚሆን ፍሬ እንዲገኝ ያደረጋችሁ ምርጥ ሚስቶች፣ ሽልማቱ የእናንተ ነውና በርቱ፤ ጽኑ!

Read 534 times