Thursday, 14 March 2024 00:00

ጋዜጠኞች የሚደርስባቸውን ጥቃት የሚከታተል ድረገፅ ሥራ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ጋዜጠኞች የሚደርስባቸውን ጥቃት የሚከታተል ድረገፅ ሥራ ጀመረ

•  የሚዲያ ነጻነትን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (ኢአማ)፤ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚከታተልና የሚሰንድ ድረ-ገጽ፡- sojethiopia.org  ይፋ አደረገ፡፡

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (UNESCO) ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ተዘጋጅቶ ስራ ላይ የዋለው ይህ ድረ-ገጽ (ፖርታል)፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ በሦስት ቋንቋዎች፡- በአማርኛ ፣ ኦሮምኛና እንግሊዝኛ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡

ማኀበሩ ከትላንት በስቲያ በማዶ ሆቴል በሰጠው መግለጫ፤ ድረ-ገፁ በጋዜጠኞችና በብዙኃን መገናኛ ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ ወከባዎች፣ እስሮችና ግድያዎችን ለመመዝገብ፣ ለመሰነድና ሪፖርት ለማድረግ የሚያስችል ነው ብሏል፡፡ ድረገፁ በተጨማሪ፣ በማህበራዊ  ሚዲያና  በሌሎችም  መንገዶች  የሚደረጉ  ማንቋሸሽ ፣ ዘለፋ ፣ ስም  ማጥፋትና የመሳሰሉትን በመመዝገብ ፣ በማጣራትና ለቀጣይ ውትወታ ስራዎች ግብዐት በመሰብሰብ መገናኛ ብዙሃን ነፃነታቸው ተጠብቆ በኢትዮጵያ  የዴሞክራሲያዊ  ማህበረሰብ  ግንባታ ሂደት ላይ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ያስችላል ነው የተባለው፡፡   

sojethiopia.org የተሰኘው ድረ-ገፅ፤ ጋዜጠኞች ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት የሚደርስባቸውን ወከባና  የመሳሰሉ ክስተቶች  ከመከታተልና ከመመዝገብ በተጨማሪ በተለየ ሁኔታ፤ ሴት ጋዜጠኞች በስራ ቦታቸውም ሆነ በጋዜጠኝነት ጉዞአቸው ላይ የሚደርሱባቸውን ፆታዊ ጥቃቶች ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መንገድ የሚመዘግብና የመፍትሄ ሒደቶችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሚበጅበት  ማዕቀፍ ነው፡፡


በኢትዮጵያ የጋዜጠኞችን እስርና የመብት ጥሰቶች በተመለከተ መረጃዎችን የሚያወጡት የውጭ ተቋማት መሆናቸውን የገለጸው የአርታኢያን ማህበር፤ አዲሱ ድረ-ገጽ እኒህን መረጃዎች ከውጭ ሳይሆን ከራሳችን በቀጥተኛ መንገድ ለማግኘት ያስችላል ብሏል።

Read 594 times