Sunday, 03 March 2024 20:27

ኪነት ያቆየልን አገር!

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(3 votes)

‹‹ዋ!...
አድዋ ሩቅዋ፤
የዓለት ምሰሶ - ጥግዋ፤
ሰማይ ጠቀስ፣ ጭጋግ ዳስዋ፤
አድዋ…
ባንቺ ህልውና፤
በትዝታሽ ብጽዕና፤
በመሥዋዕት ክንድሽ ዜና፤
አበው ታደሙ እንደገና፤
ዋ!....››    
(‹‹አድዋ›› - የዓለም ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን።)
መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት አገር ሰጥተውናል፤ ድንበር ቆርሰውልናል፤ ለሕልውናችን ሲሉ ተዋድቀዋል፤ በሰላሙ ቀን አንኮላ፣ በጦርነቱ ቀን አጥንታቸውን ከስክሰው ዎረታ ውለዋል፤ አገር ማቅናታቸውን ማስተባበል የበሉበትን ወጬት እንደማንኮታኮት ነው፤ አብዛኛውን ጊዜ እነሱ አምጥተው ራሳቸው ያሮጣሉና፣ ሲያሻቸው ደግሞ መልሰው አገር ነጥቀውናል፤ ሕዝቡም አገሩን ቢነጥቁት ግጥም ውስጥ፣ በሙዚቃ፣ በድርሰት፣ በሥዕል፣ በፎቶግራፍና በሌላው አገሩን ፈልጓል፤ አግኝቷልም፤ እየፈለገም ይገኛል፤ ኪነ-ጥበብ መሸሸጊያውና መጽናኛው ሆኖ ቆይቷል።
በግጥም፣ በዘፈን፣ በድርሰት…ወዘተ. ውስጥ የምትሳል ኢትዮጵያ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ‹‹Fairytale›› (የቢኾን ዓለም/የምናብ) ዓይነት እንድምታ አላት፤ ይኼ መልካም ነው፤ ቸርዋን፣ ሰው ወዳድዋን፣ ማዓዛዋ የሚጠራዋን፣ ማጀቷ ያልተጓደለባትን፣ ለዛዋ ያልተጨመቀባትን አገር እንድናጣጥም ይረዳናል። በአገር ተስፋ መቁረጥ የሽንፈት ሁሉ ሽንፈት ነውና፣ በአገራችን ተስፋ ከማጣት ይከላከላል።  
የአሁን ዘመን ሰው ወድዶ አይደለም የባሕል አልባሳት ላይ ሙጥኝ የሚለው፤ አገር፣ አገር የሚሸትቱ እና ኢትዮጵያ የሚል ሥም ያለበት ዘፈን ለማድመጥ ጆሮውን ስሎ ታየዋለህ፤ አልባሳቱ ወስጥ አገሩን የሚያገኛት ይመስለዋል፤ በእየሙዚቃው እናት አገሩን ያገኛታል፤ በእየግጥሙ ኢትዮጵያን በይበልጥ እየቀረባት ይመጣል፤ በእየቲያትሩ የትውልድ ቀዬውን ፍለጋ ይደላደላል፤ በእየድርሰቱ እሸትዋን ቅሞ፣ ወለላዋን ያጣጥማል፤ በእየተውኔቱ ማጀቷ ያፈራውን ተቋድሶ፣ የማድጋዋን ጉሽ እንትፍእንትፍ እያለ ፉት ይላል።
ኪነት ፈር ጠቋሚ ነው፤ በፖለቲካ ለውጦች፣ በግጭቶች፣ በኑሮ ውድነት፣ በባሕል መባረዝ፣ በማሕበራዊ አኗኗር መዛነቅ፣ በተለያዩ ትርምሶች ምክንያት የተሰወረችብንን ኢትዮጵያ ገላልጦ የሚያስጎበኘን ኪነት ነው።
የሰው ልጆችን አድማስ ከሚያሰፉ ነገሮች አንዱ ትምህርት ነው፤ ግና የትምህርት ሥርዐታችን ሰልሏል፤ አገሩን ክዶ አገሪቱ ባልዋለችበት ውሏል፤ በሌላት ጉዳይ ላይ መቃዠት ከያዘ ሦስት አሥርት ዓመታት በከንቱ መክነዋል፤ ታሪካችንን፣ ጀግኖቻችንን፣ አርአያዎቻችንን፣ ሀብታችንን፣ መታደላችንን፣ ማሕበራዊ ውቅራችንንና ያለንን አስገንዝቦን ሲያበቃ፤ የተጓደለውን ለማሟላት መታተር ነበረበት፤ እንዳለመታደል ሆነና አልሆነም፤ ትምህርት ችግር እየፈታ አይደልም፤ እኛን አለማማከሉ ነው ትልቁ ክፍተት፤ ግብረ-ገብና ማሕበራዊ እሳቦታችን ተውሸልሽሏል፤ ማሕበራዊ እሴቱና ግብረ-ገቡ የተናደ ሕብረተሰብ አንድ እንጨት እንደሚያስር ሰው ለድካም የተፈጠረ መሆኑ አያጠራጥርም። ለፍቶ መና ነው።
የውስጥ ጉዳያችን፣ ፖለቲካችን፣ በመንግሥት ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች፣ ውትድርናው፣ መሪዎቻችንና ሌሎችም አገር የማኖርና ቁምነገር የመጣፍ ጉዳይ ላይ የሚረባ ውለታ እየዋሉ አይደለም፤ ዛሬ እንጂ ነገን መተለም ውግዝ ነው የተባለ ይመስል ለቃሉ የሚያድር እየተመናመነ መጥቷል፤ ጉዳዩ አገር የሚያስቀጥል እያልመሰለ ነው።
በአሁን ወቅት የተለያዩ መስኮችን የቤት ሥራ በአብዛኛው እየተወጣ ያለው ኪነት ነው፤ ኢትዮጵያን በይበልጥ ያወቅናትና የቀረብናት ቀለም ልንቀስም በተገኘንበት ትምህርት ቤት ሳይሆን፣ በሙዚቃ ውስጥ ነው፤ ተዟዙረን መላውን አገራችንን እንዳንጎበኝ ብዙ ጉድባዎች ዕንቅፋት ይሆኑናል፤ ግና ሙዚቃ ያለንበት ድረስ አንክብክቦ ያመጣልናል፤ ድርሰት የጎጃምን መልክዐ-ምድር፣ የሐረርጌን ኮረብታዎች፣ የካፋን ጥቅጥቅ ደን፣ የጋሞን የተንጣለለ ኃይቅ ቅልብጭ አድርጎ ይስልልናል።
የዓጼ ቴዎድሮስን ገድል ተማሪ ቤት የሚገኝ ክታብ ከነገረን በላይ የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን ቲያትር ወገግ አድርጎ እንዳብራራልን ማስተባበል ከባድ ይሆናል። የጌታቸው ካሳ ‹‹አገሬን አትንኳት›› የሚል ዘፈን ለአገር የተዋደቁ ባለውለታዎችን በማወደስ ረገድ የሚገዳደረው የለም። ብሎም የቴዎድሮስ ታደሠ ‹‹በቸር ይደር›› ዘፈን በድንቅ ግጥምና ዜማ ተውቦ ትላንትናችንንና የአገራችንን ውለታ መርሳት እንደሌለብን አስገንዝቦን ያልፋል።
ትላንትናችንን፣ ጣፋጭና መራራውን፣ መውደቅና መነሳትን፣ ስኬትና ስብራትን፣ ታሪክና ትውፊትን እንዲሁም ተረኮቻችንን በአምሥት ደቂቃ ሙዚቃ ውስጥ በወጉ ሰግስገው አስደምጠውናል ሙዚቀኞቻችን፤ ሠዓሊ ታሪካዊ ገድልን ከሸራው ዕኩል በልቡናችን አኑሯል፤ የቲያትር ባለሙያዎች በስሜት እየተናጥን ጀግኖቻችንን እንድንመኝና ገድላቸውን እንድንደግም አነሳስተውናል፤ ደራሲዎቻችን አገር የማስተዋወቅ ድርሻን ተወጥተዋል፤ ምስጋና ሲያንሳቸው ነው ሁሉም!
በእርግጥ የረጅም ጊዜ ውጥንቅጡ የወጣ ታሪካችን፣ መሪዎች እና ሕዝቡ በጋራ የወለዱት መሆኑ አያሻማም፤ መሪዎችን ብቻ ለይቶ ማብጠልጠል ለሚዛን ይቀላል፤ ሕዝቡም መሪውን መቅረጽና መጥረብ ነበረበት፤ መሪዎችም የሕዝቡን ደካማነት እንደ ድል በመቁጠር መዘባነን አልነበረባቸውም፤ የሌላው ዓለም ፖለቲካዊ ተጽእኖ እና ጦርነቶችም በተለያዩ ጊዜያት ደቅተዋት ከርመዋል፤ ደቅታቸዋለችም፤ እንደ መቀርቀሪያ ከወዲህ ወዲያ አሹረዋታል፤ እንደ ጃንጥላ ዘውረዋታል፤ ሆኖም ሳንካዎችን ተሻግራ ዘልቃለች፤ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም እጅጋዬሁ ሺባባው (ጂጂ) ‹‹ኢትዮጵያ›› በሚል ዘፈኗ፡-
‹‹ያገቡሻል ይፈቱሻል፤
ያጩሻል - አሁንም ድንግል ነሽ፤›› የተሰኘቺው።
የሆነው ሆኖ፣ ኪነት ጥላ ሆኖ ሕዝቡን ከንዳድ ታድጓል፤ ሕዝቡ የአገር ፍቅሩን እንዲያዳብር፣ ለአገሩ ያለውን ክብር እንዲገልጽና እንዲወጣ ጉልህ ሚናን ተጫውቷል፤ መቼም የኤፍሬም ታምሩን ‹‹እንዴት ነሽ አገሬ›› አድምጦ አገሩን ለማወቅ ያልጓጓ አለ ብሎ መገመት በመጠኑም ቢሆን ያዳግታል፤ እዚያ ውስጥ በሩቅ የምናውቃቸው ሥፍራዎች አሉ፤ አገራችን በእነዚያ ሥፍራዎች ትገለጻለች፤ መልካም ገጽታዎቿ ናቸው፤ ማወቅ እንዳለብን እንብሰለሰላለን። በበረኃና ሽው ባለ ሜዳ ከሚገማሸረው የባሮ ወንዝ በእልፍኝ ጠልቀን መጎንጨት፣ ወላ ጣፋጭ ትዝታን ይዘን ለመቅረት በመወጠን ጣፋጩን ዓሳ አጥምደን ማጣጣም እንከጅላለን።  
የኪነት ትልቁ ቁምነገር ማሳተፍ መቻሉ ነው፤ አድማጭ ተመልካችን ማነኹለል ሳይሆን፣ በገዛ አገሩ ፍቅር እንዲወተወት ማድረግ መቻሉ ነው፤ ፍቅርን መከተል ይበጅስ የለም ወይ! ኪነት ማሳመጽ ይችላል፤ ኪነት ፍቅርን በመላ አካላችን ነዝቶ በቅጡ ያልተረዳናትን ኢትዮጵያ በወጉ እንድንረዳ ያደርገናል፤ ስለአገራችን ታሪክና ሀብት፣ ከፍታና ውድቀት፣ ልምላሜና የተንጣለለ መስክ፣ እርሻና ማዕድን የታሪክ መዛግብት ሊያወጉን ይችላሉ።
ነገር ግን ይኼ ሁሉ በኪነት ሲገለጽ በወቅቱና በቦታው የነበረውን ክንውን እየተወኑ፣ እየገለጹና እያብራሩ በመሆኑ ሥሜት ለመፍጠር፣ ለመጨበጥና ለመገንዘብ እጅግ እጅጉን ቅርብ ነው፤ የአላፊ ጊዜ ክንውኖችን የአሁን ጊዜ በማስመሰል ማከናወን ለኪነት ቀላል ነው፤ መዛግብት ብታገላብጥ ተርኮልህ ሊያገባድድ ይችላል፤ ኪነት ግን ከመተረክ ጎን ለጎን ይከውናል፤ ሲከወን ስታይ ተንትነህ የመመዝገብ ዕድሉ ሰፊ ነው።
የምትሰማው ሙዚቃ ግጥሙ አንከብክቦ ባሮ/አኮቦ ወይ ጊቤ ሊከትህ ይችላል፤ ወላ እዚያ ካለ የማንጎ ማሳ ውስጥ ድንቅ መዓዛ እየማግክ፣ አመሻሽ ላይ ወርቅ የፈሰሰበት የሚመስለውን የባሮን ወንዝ ትቃኛለህ፤ ጣፋጭ ትዝታ እንዲኖርህ ካሻህ ደግሞ ጣፋጩን ዓሳ አጥምደህ ታነክታለህ፤ አገር እንዲህ ነው፤ ማጣጣም መቻል፤ መኖር መቻል ነው ቁምነገር፤ ካለው ነገር ጋር መኖር ትልቅ ስኬት ነው። ታዲያ፣ ኪነት አገራችን ካላት ተፈጥሮና ተሰጥኦ ጋር አብረን እንድንኖር ያደርጋል።
ለዛሬ የሂሩት በቀለን ‹‹የኔው ተስፋ›› የሚል ዘፈን በአጭሩ እንመልከትማ፤ የዘፈኑ መልዕክት የመዝሙር ለዛን የተላበሰ ነው፤ አገር በመልካም ምኞት ታፍራና ተከብራ እንድትኖር የመማጸን ዓይነት ጠባይ ያለው ቆንጆ ዘፈን ሰጥታናለች ሂሩት፤ መዓዛዋ እንዳይነጥፍ፣ ሰላሟ እንዳይናጋ ትለማመናለች፤ የግጥሙ ደራሲ ይልማ ገ/አብ ነው፤ የዜማው ደራሲ ደግሞ ሞገስ ተካ ነው፤ ከ‹‹ደህና ሁን›› አልበም››፣ 1980 ዓ.ም. ለሰሚ ጆሮ የበቃበት ወቅት ነበር፤ ለሞገስ ተካ የመጀመሪያ ድርሰቱ እንደሆነ ይታወቃል፤ ለሂሩት በቀለ ደግሞ የመጨረሻ አልበሟ ነው፤ አጃቢው ሮሃ ባንድ ነው፤ ሂሩት በእንስፍስፍ ስልት፡-
‹‹የተጠበክሺልኝ - አንቺ ነሽ የኔው ተስፋ፤
አገሬ በምድርሽ ላይ፣ ፍቅርሽ ሰላምሽ ይስፈን፤
የተጠበክሺልኝ - አንቺ ነሽ የኔው ተስፋ፤    ጽገሬዳሽ ይበርክት፣ ቃናው በዙሪያሽ ይስፋ፤›› ብላ ትጀምራለች።
ተስፋ የምንጥልበት ነገር ወይም ጉዳይ መኖሩ በጣም መልካም ነው፤ ተስፋ የሌለው ነገር ፍጻሜው አያምር ይሆናል፤ ታዲያ፣ ከላይ በተዘረዘሩ ስንኞች ገላ ውስጥ ውለታ የወለደው መልካም ምኞት አለ፤ ተስፋዋ አገርዋ ናት ለባለድምጽዋ (በዘፈን ውስጥ ሆኖ የሚተርክ ባለድምጽ ነው የሚባለው)፤ ታፍራና ተከብራ የኖረች፤ የተጠበቀች አገር እንዳለቻት ትናዘዛለች፤ አባቶቿ ያወረሷት ትልቅ ሀብት እንደሆነች እርግጥ ነው፤ እርሻዋ እንዲቀናና እሸቷ እንዲቃም ትማልዳለች፤ አገርዋ ውሎ አዳሯ በሰላም የተሞላ እንዲሆንና መዓዛዋ አውዶ ዙሪያዋን መልካም ሽቱ እንዲናኝ ትመኛለች።
በቀጣዮቹ ስንኞች ደግሞ፡-
‹‹በዘምባቦችሽ ተክል፣ በአበቦችሽ ጥሪኝ፤
የፍቅርሽ ቀማሽ ልሁን፣ የችግርሽ ቀን ጥሪኝ፤›› ትሰኛለች።
ከላይ ባሉ ስንኞች ውስጥ ሆደ ቡቡነት አለ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ልምላሜዋን ትመኛለች፤ አበቦችዋ እንዲበራከቱ ትካድማለች፤ ዛፏ እንዲዘናፈልና እንዲዘናጠፍ ትለማመናለች፤ ውበቷ ስለአለመንጠፉ ትባባለች፤ ከንቱ መባባት ብቻ አይደለም፤ ከአባቶቿ የተረከበቻት አገር በቸገራት ጊዜ ደጀኗ ለመሆን መልዕክት ትሰዳለች፤ የችግሯን ቀን ባትመኝም፣ የቸገራት እንደሆን አለኝታዋን እንደማትነፍግ ቃል ታኖራለች፤ ጣፋጭዋን አጣጥማለችና፣ የጣዕሯ ቀን ቢደርስ ዘብ መቆም እንዳለበት ትናዘዛለች። አለኝታ አያሳጣን! አለው የምንለው ጉዳይም አያሳጣን፤ ለዓላማ የሚኖር ሰው የሚቆምለት ነገር ይኖረዋል፤ ትልቁ ቁምነገር ደግሞ ለዓላማ መቆም ወይም አለኝታ መሆን መቻል ነው።
ባለድምጿ ምኞትዋን በተክልና በሰብል ብቻ አጥራ አታበቃም፤ ዘለስ ትልና፡-  
‹‹ጎርፉ አይብዛብሽ፣ አይጉዳሽ ውሃ፤
ለጭንቅ አይጣልሽ፣ ሰፍቶ በረሃ፤›› ስትል ትወርዳለች።
ተፈጥሮን ስለ አገሯ ደኅንነት ትለማመናለች፤ አገርዋ ከመጥፎ አጋጣሚዎች የተጠበቀች መሆንዋ ይገዳታል፤ ከምድሯ ጭንቅ እንዲወገድ ትሻለች፤ ደግሞ በዜማ ሲሆን ልብ ይመዘምዛል። ሂሩትም ሂሩት ናት፤ ማንሰፍሰፍ ትችልበታለች። ተንሰፍስፋ ታንሰፈስፋለች፤ አንተም ለአገርህ ሆድህ ይተራመሳል፤ መልካሙን ሁሉ አግተልትለህ ትመኝላታለህ፤ ለመልካም ተግባር በኪነት አጋዥነት ተሳተፍክ ማለት ይኼኔ ነው! ዘፈኑ ዙሪያ ገባውን ይዳስሳል፤ አለፍ ይልና፡-  
‹‹ንፋስሽ ይርጋ፣ ሞገድሽ ይቅር፣
ለመርከብ ጉዞ፣ ለዋናው ፍቅር፤
ይስከን ባሕርሽ፣ ማዕበል ሳይሻ፤
ይጥቀም ለንግድሽ - መመላለሻ፤
በኬላሽ ዙሪያ፣ በምድርሽ ወለል፣
ፍቅር ይርከፍከፍ፣ ሰላምሽ ይትረፍ፤›› ትለናለች ሂሩትዬ።
የወንዙ ሙላት ሰላምና ምጣኔ ሀብቱን እንዳያደፈርስ ትባባለች፤ ለዛዋ የድንጉጥ እናት ነው፤ አንድ እንደወለደች፣ ኮሽ ባለ ቁጥር እንደምትንሰፈሰፍ እናት ዓይነት ባለድምጽ በዚህ ዘፈን ውስጥ አለች፤ አገራችን ንፋስዋ ይስከን፤ ማዕበሏ ይርገብ። ኪነ-ጥበብ እንዲህ ነው እንግዲህ፤ የአገር ፍቅርን በልባችን የማስረጽ ጉልበት አለው፤ የአገር ፍቅርን ያላበሰን ኪነ-ጥበብ ነውና፣ ታላቅ ጸጋነቱ አይካድም!
ለመደምደሚያችን፣ ከቴዎድሮስ ታደሠ ‹‹በቸር ይደር›› ከተሰኘ ዘፈን ጥቂት ስንኞችን ልጋብዛችሁና ላብቃ፤ የግጥም ደራሲ ይልማ ገ/አብ፤ የዜማ ደራሲ አበበ መለሠ።
‹‹ይመስክር አካሌ፣ ጉያሽ ያደረጀው፤
የእናትነት ጣዕምሽ፣ ውለታሽ ያበጀው፤
በማጀትሽ ወተት፣ በጤፍሽ እንጀራ፤
በማር በወለላሽ፣ በጓሮሽ ሸንኮራ፤
ብድር አለብኝ፣ ልክፈልና ልኩራ፤
ክብርሽ ከፍ ይበል፣ ከሰላምሽ ጋራ፤››
***
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛ እና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፤ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።

Read 366 times