Sunday, 03 March 2024 19:57

በሥልጣኔ ቅርስነታቸው ወይም በምርታማነታቸው ሳይሆን ስማቸው በጦርነት ሲነሳ ያሳዝናል

Written by  ዩሃስ ሰ.
Rate this item
(2 votes)

ይሓ እና አክሱም፣ ላሊበላ እና ጎንደር፣ ዓምና ካቻምና ስማቸው ሲነሣ የነበረው በሥልጣኔ ታሪክና በቅርስ ሳይሆን በጦርነት ነው።
በእርሻ ምርታማነትና በእህል ንግድ ስማቸው መነሣት የነበረባቸው የምዕራብ ጎጃምና የወለጋ፣ የደብረማርቆስና የነቀምት አካባቢዎችስ?


የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ታሪክ፣ “እንደ አዲስ እያደር ይደምቃል” ተብሎ ቢገለጽ እውነት ነው። “ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ። “ሊሆን አይችልም” እላለሁ የግዴን።
ራሳችንን ካላሞኘን በቀር፣ ሁላችንም እናውቃለን። የጥንት ታሪክ፣ ያው የጥንት ታሪክ ነው። ወደ ኋላ ተመልሰን ልንሻሽለው ወይም ልናበላሸው አንችልም። ትክክል ነው። አንቀንስበት፣ አንጨምርለት! በዚህ እንስማማለን።
ግን ደግሞ በተደጋጋሚ እንደታየው፣ የአገራችን የሥልጣኔ ታሪክ ከምንጠብቀውና ከምንገምተው በላይ ሲሆንብን ምን እንበል? እያደር ይደምቃል አያሠኝም?
“የ500 ዓመት ዕድሜ ሳይኖረው አይቀርም” ተብሎ የተገመተና የተደነቀ ታሪካዊ ቅርስ፣ “የ1500 ዓመታት የዕድሜ ባለጸጋ” እንደሆነ በላብራቶሪ ምርመራ መረጋገጡን ስንሰማ ምን እንበል? “ከአውሮፓ የተኮረጀ ሳይሆን አይቀርም” ተብሎ የተገመተ የኢትዮጵያ ቅርስ፣ “ለካ፣ በዓለም ዙሪያ በታሪካዊነቱ ቀዳሚ ነው” ብለው ሲመሰክሩለትስ? በአባ ገሪማ ገዳም ውስጥ የተገኙ ጥንታዊ የሃይማኖት መጻሕፍት ዓለማቀፍ የክብር ቦታቸውን የያዙት በዚህ መንገድ ነው። እያደር ነው የታሪክ ማዕርጋቸው እየታወቀ፣ ዝናቸው ዓለምን ያዳረሰው።
እጅግ ጥንታዊ ቅርስ እንደሆነ የሚነገርለት የይሓ ቤተ መቅደስም ቢሆን፣ ምንም እንኳ ከመነሻው የሥልጣኔ ቅርስነቱ ቢታመንለትም፣ ውሎ ሲያድር ግን ከተገመተውም በላይ ባለ ግርማ ሞገስ እንደሆነ እየተገለጠ መጥቷል። በዚህ ተገርመን ሳንጨርስ፣ ከይሓ ቤተ መቅደስ አቅራቢያ፣ እዚያው ከአጠገቡ ሌላ አስደናቂ የሥልጣኔ ታሪክ ተሠርቶ እንደነበር ተመራማሪዎች ሲነግሩንስ ምን እንበል?
በዕድሜና በግዝፈት እጅግ የላቀ እንደሆነ የተነገረለት ጥንታዊ ሕንጻ፣ ከ2800 ዓመት በፊት የተገነባ ነበር አሉን። ባለ አምስት ፎቅ ግዙፍ ሕንጻ እንደሆነም ነገሩን። ይህን ማን ገመተ? አሁን ደግሞ፣ “ኧረ ከዚያም ሳይበልጥ አይቀርም” የሚሉ የምርምር ውጤቶች መጥተዋል።
ምናለፋችሁ!
የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ታሪክ፣ ከብዙ አድናቂዎች ግምት በላይ “እያደር ያብባል” ብንል ቅንጣት አልተሳሳትንም። እውነት ነው።
አሳዛኙ ነገር፣ ታሪከኛዋ አገር ከምኞታችን በታች የወረዱና ከስጋታችንም የባሱ የጥፋትና የውድቀት ታሪኮችንም አስተናግዳለች። ለሥልጣኔ ታሪኳ የማይመጥኑ የረሀብና የጦርነት መከራዎች በጣም አብዝተው ተደጋግመውባታል። አብዝተን እየደጋገምንባት ነው ብንል ይሻላል።
እንዲያም ሆኖ፣ ድንቅ ታሪኮቿ አልደበዘዙም። ካለፈው ሳምንት እስከ ዛሬ ሳምንት ብላችሁ በማሰብ ብቻ ማረጋገጥ ትችላላችሁ።
በዓለም ዙርያ እጅግ የተከበረና የመላው አፍሪካ ፋና እንደሆነ የሚታመንበት የዐድዋ የድል ታሪክ አለ። በዓለም ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ የቻለ ትልቅ ታሪካዊ ድል ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንድትሆን ተመርጣ፣ የአህጉሪቱን የመንግሥታት ጉባኤ ስታስተናግድ መሰንበቷ ምን ይገርማል? ይገባታል። ሲያንሳት ነው። የዐድዋ ድል መታሰቢያ ሕንጻ ተገንብቶና ተመርቆ፣ ለክብረ በዓል መድረሱስ ምን ይጠየቃል?
(በነገራችን ላይ፣ ለሕንጻው የሚመጥኑ የኪነ ቅርጽ ፈጠራዎች ሊኖሩት ይገባ ነበር ብለን አስተያየት ብንሰጥ፣ የታሪኩን ትልቅነት በማሰብ አይደለም ወይ? ጥቃቅን አስተያየቶችም ጭምር ዋጋ የሚኖራቸው ከዐድዋ ድል ታሪካዊ ትርጉም ጋር ከተያየዙ “ጸጉር ስንጠቃ” ወይም “አቃቂር የማውጣት ሙከራ” ከመሆን ይድናሉ። እንዲያው ስታስቡት፣ “ፕላዛ” የሚል ከጣሊያንኛ ወይም ከስፓንሽ ቋንቋ የተወረሰ ቃልስ ከዐድዋ መታሰቢያ ሕንጻ ይመጥናል? ሌላ አገርኛ ቃል ጠፍቶ ነው?)
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ለወቀሳ የሚሰነዘሩ ትችቶችና ጥቃቅን አስተያየቶች ሳይቀሩ ኢትዮጵያ የትልልቅ ታሪኮች አገር መሆኗን ሊመሰክሩ ይችላሉ። የታሪካዊ ቅርሶች ምስክርነትማ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ እንደሚመጣ አይተናል።
ምን ያደርጋል! ኢትዮጵያ፣ ስለ ጦርነትና ስለ እልቂት “እንደ ሪፕሌይ” እየደጋገሙ የሚያወሩባት አገር ናት።
የምግብ እጦትና ረሀብ ያነሰ ይመስል፣ “የእህል እርዳታ ተዘረፈ፤ ረሀብ ተደበቀ” እየተባለ በዓለም ዙሪያ የኢትዮጵያ ስም ሲነሳ ብዙ ጊዜ ሰምተናል።
ይሄም ያነሰ ይመስል፣ “መንግሥትን ለማሳጣት” ከመጓጓታቸው የተነሣ ኢትዮጵያ ላይ ብዙ መከራ ቢደርስ የሚመኙና ችግሮችን አጋንነው የሚያወሩ አላዋቂ ቀሽም ሰዎች ይኖራሉ። የዚህ ግልባጮም አሉ።
በረሀብና በጦርነት የሚደርሰው ስቃይና እልቂት ሊያስጨንቃቸው ሲገባ፣ ስለ ረሀብና ስለ ጦርነት መወራቱ የሚያሳስባቸው ባለሥልጣናት መኖራቸው ያሳዝናል።
የረሀብ አደጋን ማጋነን ምን ያደርጋል? ማጋነን የማያስፈልገው ከባድ ውድቀትና አደጋ ነው - ረሀብ ማለት።
ረሀብን መደበቅስ ምን ያደርጋል? ረሀብን ያባብሳል እንጂ ሌላ ትርፍ የለውም። ደግሞስ፣ ከደበቅንም የየራሳችንን ረሀብ እንጂ የሌሎች ሰዎችን ረሀብ መደበቅ ምን የሚሉት ጭካኔ ነው?  
ብቻ… እንዲሁ ስታስቡበት፣ የኢትዮጵያ ነገር ያሳዝናል። በጣም አሳዛኝ የሚሆነው ደግሞ፣ በአርአያነት የሚጠቀስ የሥልጣኔ ባለ ታሪክ ባለ ቅርስ አገር መሆኗ ነው። ለዚያውም እያደር የሚደምቅ የሥልጣኔ ታሪክና ቅርስ!
የኢትዮጵያ ቅርሶች በአሜሪካ ለእይታ የቀረቡበት የሙዚዬም ትይዕንት እንደተዘጋጀ ሰምታችሁ ይሆናል። ትዕይንቱ እስከዛሬ ያልታየ ትልቅ የታሪክ “ድግስ” ነው የሚል አድናቆት አግኝቷል። (የዋሽንግተን ፖስት አባባል ነው - “The exhibit is a sensory feast” በማለት ትዕይንቱንና አዘጋጆቹን አሞግሷል)።
በተመሳሳይ ጊዜ፣ በታዋቂው የአሜሪካ ጋዜጣ በዎል ስትሪት ጆርናል ታትመው የወጡ ሁለት ጽሑፎችን ደግሞ ተመልከቱ።
በገጽ 11 ላይ የወጣው ሰፊ ዘገባ፣ ኢትዮጵያ የታሪክ ባለጸጋ መሆኗን ይጠቅሳል። ኢትዮጵያውያን በየዘመናቸው አኩሪ ታሪክ እንደሰሩ ይገልጻል። የረዥም ዘመን ታሪኳን ሲጠቅስም፣ የአይሁድ፣ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት በቀዳሚነት ከተስፋፋባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች ይጠቁማል።
ለክርስትና ሕጋዊ ዕውቅና የሰጡ ሁለት የዓለማችን ቀዳሚ አገራት አርሜኒያና ኢትዮጵያ ናቸው ይላል - ዘገባው። በአክሱም ዘመን የዛሬ 1700 ዓመት ገደማ ማለቱ ነው።
In the second quarter of the fourth century, the original Ethiopian kingdom—the Aksumite Empire—became the second nation to adopt Christianity (after Armenia); its church, we learn, adapted some practices from ancient Judaism, which had a strong foothold there, with lore tracing it back to the Queen of Sheba and her liaison with the Israelite King Solomon. Islamic conquests also play a strong role….
እዚያው ሕትመት ገጽ 6 ላይ ደግሞ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በጦርነት ላይ የምግብ እጦት ተደርቦ እንደመጣና በርካታ ሰዎች በረሀብ መሞታቸውን ያስነብበናል።
ዎል ስትሪት ጆርናል በሁለት ገጾች ያተማቸው ሁለት ዘገባዎች፣ የአገራችንን አሳዛኝ መንታ ገጽታዎች የሚያሳዩ ናቸው።   
በአንድ ወገን ስለ ጦርነትና ስለ ረሀብ ያወራል።
ባለፉት ዓመታት በጦርነት ሲመሳቀሉ የቆዩ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ አሁን የምግብ እጦት እንደተደረበባቸው ይነግረናል። 400 ገደማ ሰዎች በረሀብ መሞታቸውን የኢትዮጵያ የዕንባ ጠባቂ ተቋም እንደገለጸም ጋዜጣው ያስነብበናል። አሳዛኙን የኢትዮጵያ ገጽታ ያሳየናል።
አክሱም እና ላሊበላ፣ ይሓ እና ጎንደር፣ ዓምና ወይም ካቻምና ስማቸው ሲነሣ የነበረው፣ በሥልጣኔ ታሪክና በቅርስ ሳይሆን በጦርነት ነው። በእርሻ ምርታማነትና በእህል ንግድ ስማቸው መነሣት የነበረባቸው የምዕራብ ጎጃምና የወለጋ፣ የደብረማርቆስና የነቀምት አካባቢዎችም እንዲሁ በጦርነትና በግጭት ስናወራላቸው ከርመናል።
በሌላኛ ገጽ ዘገባው ደግሞ፣ አስደናቂውን የኢትዮጵያ ገጽታ ያሳየናል። ኢትዮጵያ ትልቅ ባለ ታሪክ አገር እንደሆነች ጋዜጣው በሰፊው ይዘረዝራል።
የዘገባው ትኩረት፣ በአሜሪካ የተዘጋጀውና በሦስት ሙዚዬሞች ለእይታ እንዲቀር ታስቦ የተሰናዳው የቅርሶች ትዕይንት ነው። “ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ” በሚል ስያሜ የቀረበው የቤተ መዘክር ትዕይንት (የሙዚዬም ኤግዚቪሽን)፣ የምዕተ ዓመታት ታሪኮችንን ይዳስሳል። ለዚህም ከ220 በላይ ቅርሶችና የታሪክ መዛግብት ተሰባስበው የተመልካቾችን ዐይንና ቀልብ ለመማረክ እንደተሰናዱ የትዕይንቱ አዘጋጆች ገልጸዋል።
በእርግጥ ቅርሶችንና መዛግብትን ከማሰባሰብ ያለፈ ትልቅ ሥራ እንዳከናወኑም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ታሪክ በደንብ እንዲታወቅ ነው የፈለጉት፡፡ የቅርሶቹ ምንነት ለማብራራትና የኢትዮጵያ ታሪክን በሰፊው ለማስረዳት፣ በምሁራን የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎች በወጉ ተፈትሸውና ታርመው ለሕትመት እንዲበቁ ብዙ ደክመዋል።የጥናታዊው ሰነድ አቀናባሪና አርታኢ ክርስቲን ሻካ፣ የትዕይንቱ ዋና መሪ እንደሆኑ ዘገባው ይጠቅሳል። ምን ያህል እንደተሳካላቸውም እንዲህ ይመሰክርላቸዋል።
The show’s curator Christine Sciacca… has created an elaborate survey of a remarkable national heritage, not only in its religious distinctiveness but in Ethiopia’s proud autonomy as the only African nation never colonized.
የኢትዮጵያ አገራዊ የታሪክ ጸጋዎች አስደናቂ የመሆናቸው ያህል፣ ይህን የረዥም ዘመን ታሪክ የሚዳስስ ድል ያለ የቅኝት ድግስ አሰናድተዋል ሲል የትዕይንቱን ዋና አዘጋጅ ክርስቲን ሻካን አወድሷል።
ትዕይንቱ የኢትዮጵያን ሃይማኖታዊ ታሪኮችና ባህሎች ያስቃኛል - ልዩ አገራዊ አሻራቸውን በሚያሳይ መንገድ፡፡
ከዚያም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ የአፍሪካ አገር እንደመሆኗ መጠን ኩሩ የነጻነት ታሪኳንም ያስቃኛል በማለት ዘገባው በድርብ አመስግኗል።
ከዎል ስትሪት ጆርናል ሕትመት፣ እንዲህ ዐይነት የአድናቆት ምስክርነት በቀላሉ አይገኝም።
የቤተ መዘክር ትዕይንቱ በደንብ ታስቦበት በረዥም ዘመን ስም በተከሉ ተቋማትና በስመ ጥር ባለሙያዎች  የተዘጋጀ ትዕይንት እንደሆነ ከዘገባው መረዳት ይቻላል።
እርግጥ ነው፤ የውጭ አገር ምሁራን እስኪነግሩን፣ የውጭ አገር ተቋማት እስኪያሳዩን ድረስ ሳንጠብቅ፣ የአገራችንን ታሪክ በጥልቀት መመርመርና በስፋት መማር ብንችል መልካም ነበር። ካልሆነም ግን፣ ዕውቀት ከየትም ቢመጣ ያው ዕውቀት ነውና፣ የውጭ አገር አዋቂዎች የጨበጡትን መረጃ ማየትና መማር በጎ ነው።

Read 294 times