Saturday, 02 March 2024 21:01

ይድረስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወያኔ” የሚል ቃል የፓርቲ ስያሜ ማድረግ በህግ ሊከለከል ይገባል

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 እና ይህንን አዋጅ ተከትሎ በወጣው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በአድናቆት የሚታዩ እና ከበሬታ የሚገባቸው መሆኑን ሳልገልጽ ባልፍ ንፉግነት ይሆንብኛል፡፡
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በ1992 ዓ.ም እና በ1997 ዓ.ም በተካሄዱ አገር አቀፍ ምርጫዎች በመሳተፍ በተወዳደረበት ወረዳ አብላጫ ድምፅ በማግኘት አሸንፏል፡፡ በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆንም አገልግሏል፡፡ በእነዚህ ምርጫዎች በተሳተፍኩበት ወቅት የታዘብኩት ነገር ቢኖር፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫዎችን ለማስፈጸም ያዘጋጃቸው መመሪያዎች፣ ማንዋሎች፣ ፎርማቶች (ቅፆች) እና የምርጫ መርሐ-ግብር ከማውጣት ጀምሮ የሚከተላቸው የአሰራር ሂደቶችና የአፈጻጸም ስርዓቶች ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ለማስፈጸም ጠቃሚ መሆናቸውን ነው፡፡ መመሪያ፣ ማንዋል፣ ቅጽ፣ የአሰራር ሂደቶችም ሆነ የአፈጻጸም ስርዓት ፋይዳ ሊኖረው የሚችለው ግን በራስ የመተማመን መንፈስ ያላቸው፣ ገለልተኛ አስፈጻሚ ሰራተኞች ሲኖሩ መሆኑ ግን አብሮ መታየት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህንን ካልኩ በኋላ ወደዛሬው መጣጥፍ ፍሬ ነገር ላምራ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ “ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ” ለተሰኘ ፓርቲ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም የምዝገባና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሰጠ መሆኑን ከመገናኛ ብዙኃን ስሰማ ይህንን መጣጥፍ ለመጻፍ ብዕሬን አነሳሁ፡፡
ከላይ በርእሱ ላይ እንደተጠቀሰው የዚህ መጣጥፍ ዓላማ፣ ቦርዱ በስያሜው ላይ “ወያኔ” የሚል ቃል ለያዘ ፓርቲ (ለሳልሳይ ወያኔ ትግራይ) የሰጠው የምዝገባና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አዋጁን የሚጻረር መሆኑን በመግለጽ የቀረበ አቤቱታ ነው፡፡ ተቃውሞዬን ያቀረብኩበትን ምክንያት ከመዘርዘሬ በፊት፤ የክልል የፖለቲካ ፓርቲ ስለ መመስረት እና መመዝገብ የማይችል የፖለቲካ ፓርቲን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ላቅርብ፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎች
የክልል የፖለቲካ ፓርቲ መመስረትን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 65፣ ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ “አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በክልል የፖለቲካ ፓርቲነት የሚመሰረተው” ካለ በኋላ፤ ፊደል ተራ “ሀ” ላይ “፬ መቶ ሺ [400,000] መስራች አባላት ሲኖሩት” መሆኑን ይደነግጋል፡፡
መመዝገብ የማይችል የፖለቲካ ፓርቲን በተመለከተ የተደነገገው በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 69 ላይ ሲሆን፤ ዝርዝሩም በንዑስ አንቀጽ 1 ከፊደል ተራ “ሀ” እስከ “ረ” ድረስ ተሰፍሯል፡፡ ከእነዚህ ዝርዝሮች ውስጥ ሁለቱን (ሀ እና ሐ) ብቻ እጠቅሳለሁ፡፡
“ሀ) [ፓርቲው] የመረጠው ስም፣ አሕጽሮተ ስም፣ … ከአገሪቱ ባህልና የስነ ምግባር እሴቶች አኳያ ተቀባይነት የሌለው ከሆነ፤” ወይም
“ሐ) [ፓርቲው] የመረጠው ስም፣ አሕጽሮተ ስም፣ … በዘር፣ በኃይማኖት እና በመሳሰሉት ልዩነቶች ላይ የተመሰረተ ጥላቻና ጠላትነት በዜጎች፣ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና በሕዝቦች መካከል በማስፋፋት ጦርነትና ግጭት መፍጠርን ዓላማ ያደረገ … ከሆነ፤”
ፓርቲው በህጋዊነት እንደማይመዘገብ ተደንግጓል፡፡ የህግ ድንጋጌው ይህ ከሆነ “ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ” የሚለው ስያሜ ከመስፈርቶቹ አንጻር እንዴት ይታያል? የሚለውን ጥያቄ እናንሳ፡፡ በቅድሚያ “ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ” በሚለው ስያሜ ውስጥ “ወያኔ” የሚለው ቃል ያለውን ትርጉም እንመልከት፡፡
በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት በ1962 ዓ.ም የታተመው የደስታ ተክለወልድ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት “ወያን” የሚለውን ቃል፤ “ጦር ጠማሽ፣ ግዳይ ፈላጊ” ይለዋል፡፡ “ወያኔ” የሚለውን ቃል ደግሞ “የወያን ወገን፣ ብርቱ፣ ጨካኝ…” (ገጽ 431) በማለት ይተረጉመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል፣ በየካቲት 1993 ዓ.ም ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ፤ “ወያኔ” የሚለውን ቃል እንደሚከተለው ይተረጉመዋል፤ “ወያኔ ስ. 1) ሸፍቶ በረሃ የገባ አመፀኛ፤ ጦር ጠማሽ 2) ለግዳይ ሲል ጦርነት የሚገጥም ሰው” (ገጽ 414) ማለት ነው ይለናል፡፡
የደስታ ተክለወልድ፤ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፣ “ዋጅራት” የሚለውን ቃል፤ “በትግሬ ውስጥ ያለ … የሽፍታ፣ የቀማኛ፣ የወያኔ፣ የነፍሰ ገዳይ፣ ማህበር” (ገጽ 418) በማለት ይተረጉመዋል፡፡
ከላይ እንደተመለከተው “ወያኔ” የሚለው ቃል የመዝገበ ቃላት ትርጉም አሉታዊ ነው፡፡ ከታሪክ አኳያ ስንመለከተው ደግሞ “ወያኔ” የሚለውን ቃል ያነገቡ ኃይሎች፣ ከደቡብ ትግራይ በመነሳት ሰሜንና ሰሜናዊ ምስራቅ ወሎን እስከ ባቲ ድረስ በመውረር፣ ህዝቡን በአሰቃቂ ሁኔታ በመጨፍጨፍ፣ እርጉዝ ሴትን ሆዷን ቀደው ህፃኑንም እናትየውንም በመግደል፣ ወንድ ህፃናትንና ታዳጊዎችን ብልታቸውን በጭካኔ በመስለብ (በመቁረጥ)፣ የህዝቡን ሀብት፣ ንብረትና እንስሳትን በመዝረፍ፣ ወጣቶችን በባሪያነት በመፈንገል፣… አሰቃቂ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ይፈጽሙ እንደነበር በታሪክ የተመዘገበ ሲሆን፤ የዚሁ ሰለባ የነበሩ ግለሰቦች (ብልታቸውን የተሰለቡ ሰዎች) አሁንም በህይወት አሉ፡፡ ይህ “የወያኔ” የዘረፋና የጭፍጨፋ ድርጊት በየተወሰነ ዓመት በወረራ መልክ በአፋር (በዚያ ወቅት በአውሣ አውራጃ) በሚገኙ የአፋር ማህበረሰብ ላይ ይፈጸም እንደነበርም በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ “የዋጅራት” (ወያኔ) እንቅስቃሴ እንደሚባልም በታሪክ ሰነዶች ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ “ወያኔ” የሚለው ቃል እና “የዋጅራት” እንቅስቃሴ በአፋር፣ በየጁ፣ በራያ፣ በከፊል በአምባሰል፣ በባቲ፣ በከፊል በላስታ፣ በሰቆጣ፣ በወፍላ እና በመሳሰሉት አካባቢዎች (በተለይም በሙስሊም) ማህበረሰቦች ዘንድ በጭካኔ ተግባርነት የሚታወስ፣ በአረመኔ ድርጊትነቱ የሚዘከር፣ በፀያፍነት የሚኮነን ለህዝቦች ሰላምና አብሮነት የማይበጅ አሉታዊ ትርጉም ያለው ነው፡፡
ስለሆነም፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ “ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ” ለተሰኘ ፓርቲ፣ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1 ከፊደል ተራ “ሀ” እና “ሐ”ን በመተላለፍ የሰጠውን የምዝገባና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በማገድ ፓርቲው ስያሜውን እንዲያስተካክል የእርምት እርምጃ እንዲወስድ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከአዋጁ ድንጋጌ አንጻር “ወያኔ” የሚለው ቃል የፓርቲ ስያሜ መሆኑ ተገቢነት እንደሌለው እስከተረጋገጠ ድረስ “ወያኔ” የሚለውን ቃል ቀደም ሲል የስማቸው አካል ያደረጉ ፓርቲዎች ካሉ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ “ወያኔ” የሚለውን ቃል ከስያሜነት እንዲያወጡ ሊደረጉ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል፤ “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ - ሕወሓት” ይባል የነበረው ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ እንዲከስም መደረጉ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በፖለቲካ ውሳኔ ይሁን በሌላ መንገድ “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ - ሕወሓት” ይባል የነበረው ድርጅት እንደገና ህጋዊ ሰውነት የሚሰጠው ከሆነ “ወያኔ” የሚለውን ቃል የስያሜው አካል ሊያደርግ እንደማይገባው ቦርዱ ከወዲሁ ሊገነዘበው ይገባል፡፡
በመጨረሻ የማነሳው፤ “የክልል የፖለቲካ ፓርቲ” መመስረትን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 65፣ ንዑስ አንቀጽ 1፣ በፊደል ተራ “ሀ” ላይ፤ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በክልል የፖለቲካ ፓርቲነት የሚመሰረተው… “፬ መቶ ሺ [400,000] መስራች አባላት ሲኖሩት” ነው የሚለውን በተመለከተ ነው፡፡ ይህ የአዋጁ ድንጋጌ “4 ሺህ” ለማለት የተፈለገና በአጻጻፍ ስህተት (Typing Error) “400,000” ተብሎ የታተመ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ቁጥር ስህተትም ቢሆን አዋጅ ሆኖ በነጋሪት ጋዜጣ እስከታተመ ድረስ ቦርዱ “፬ መቶ ሺ (400,000) በሚለው ቁጥር መሰረት ሊፈጽም ይገባዋል፡፡ ስለሆነም ይህ በአጻጻፍ ስህተት (Typing Error) “፬ መቶ ሺ” ተብሎ የተጠቀሰው ቁጥር ካልታረመ አዋጁን ባወጣው አካል የእርምት ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚገባ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 483 times