Wednesday, 28 February 2024 20:49

የገጣሚ ሥነ-ልቡናዊ ጣጣዎች

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹አራት መስመር ግጥም፣
ለጆሮ የምትጥም፤
እንደ ዶሮ ቅልጥም፤…››
(ሰሎሞን ደሬሳ)



ግጥም ስለ ግጥም/Poetry for poetry! ብለን እንዝለቅ…
…ሥነ-ግጥምን መበየን ንፋስን እንደ መግራት ያለ መባከን ውስጥ እንዲዘፍቅ ዕሙን ነው፤ ሣይንስ እግዚሔር ውለታውን ይክፈለው! ቁመት በሜትር የሚለካበትን፣ ክብደት በግራም/በኪሎ ግራም የሚመዘንበትን፣ የሙቀት መጠን በቴርሞ-ሜትር የሚረጋገጥበትን፣ ውሃ በሊትር የሚሰፈርበትን፣ ብሎም ተያያዥ ቁርጥ ያሉ መለኪያዎችን አበጅቷል፤ ሰው በዚያ እየተመራ ካልደረሰበት ይደርሳል፤ ያረጋግጣል፤ ሥነ-ሕይውት ደግሞ ምላስን ወደ አራትና አምሥት ቦታ ሸንሽኖ ሲያበቃ፣ ይኼኛው ክፍል ጣፋጭን ለማጣጣም፣ ማንትሲዬ ደግሞ መራራን ለማረጋገጥ ይበጃል ሲል የምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል።
ከዚህ በተቃራኒ፣ ሥነ-ግጥም ቁርጥ ያለ መበየኛ ያለው ሆኖ አይታየኝም፤ መለኪያና ተመን ሥነ-ግጥምን ለመግለጽ አይቻላቸውም፤ ሕግጋት አይቀይዱትም፣ የተበጀለት ኬላ ያለ አይመስለኝም፤ ሥነ-ግጥም በአላባዊያኑ ምህዋር ላይ ብቻ ታክኮ መጥመልመል አይጠበቅበትም፤ ቋንቋ፣ ጭብጥ፣ ዘይቤ፣ ሥነ-ውበት፣ ፍካሬ፣ ሙዚቃዊነት፣ ሥዕላዊነት፣ ምት፣ ምጣኔ እና ሌሎች መስፈሪያዎች በቂ መገለጫው አይደሉም፤ ለዚህም ነው ሥነ-ግጥም ለገጣሚም ሆነ ለአንባቢ እያደር እንግዳ፣ ለፈጠራ ምቹ፣ ለምናባዊነት ዝግጁ፣ እንዲሁም ለመመራመር ሰፊ ዕድልን የሚሰጠው…
…ወደ አሁኔ ልስከንተር…
ጣጣ 1፡-
በሥነ-ግጥም ገላ፣ ቋንቋ ሀሳብን መሸከም መቻል አለበት፤ ‹‹ከቃል መርጠው ለኪነት›› ነው ዕውነታው፤ ገጣሚ በቋንቋ ተራዳኢነት ሀሳብ ይመረምራል፤ ሀሳብ አይዘግብም/አይናገርም። ፍካሬ፣ ወይም መፈከር ማለት ሕይወትን መተርጎም ማለት ነው፤ ገጣሚ ሀሳቡን አይዘግብም፤ የዓለምን መልከ-ብዙ ዕውነታ አዟዙሮ ይፈክራል/ይተረጉማል እንጂ፤ ለአብነት ያህል፣ ፈሊጣዊ-ንግግርን፣ ሥነ-ቃልን፣ አፈ-ታሪክን፣ ተረት-ተረትን፣ ድርሳነ-ደብተራን እና ሌሎች አጎራባች ዲስፒሊኖችን እንደ ግብዐት ተጠቅሞ ወደ ተነሱበት ሀሳብ መሰግሰግ ነው መፈከር ማለት፤ የዚህ ፋይዳ ሕይወትን በሥነ-ውበት ማመላከት ማለት ነው።
ሥነ-ግጥምና ሥነ-ውበት የተቆራኙ እንደመሆናቸው መጠን ፍካሬያዊ አሰነኛኘት የግጥም ጭብጥን ያጎላል፤ እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ነገር አንድ ገጣሚ ሕይወትን ለመፈከር ሲተልም፣ ተልሞም ግብዐት ሲያፈላልግ ከተነሳበት ሀሳብ ጋር የሚጋጭ አለመሆኑን ልብ ማለት አለበት፤ ይኼ ጣጣ ምናልባት ‹ግጥም እየገጠምኩ ነው› ብሎ የሚነሳ ሰው ሊያጋጥመው ይችላል ብዬ እሰጋለሁ፤ እውነታው ‹ግጥም እገጥማለሁ› በማለት ብዕር የሚጨብጥ ግለሰብ ከተነሳበት ዐውድ፣ ሀሳብ/ጭብጥ ጋር የማይጣጣም ትርጉም ያለው ፍካሬያዊ ቃል፣ ሐረግና ስንኝ ሊያካትት ስለሚችል ነው።
ሥነ-ግጥም፣ የወለሎና የመሆን ተብሎ በሁለት ይበየናል፤ በመጀመሪያው ጎራ ቃላት፣ ሐረጋትና ስንኞችን በመሰደር ሀሳብ ማስተላለፍ ሊይዝ ይችላል ገጣሚ፤ በሁለተኛው በኩል ደግሞ አሁናዊ ሁናቴውን ሊያንጸባርቅ ይችላል፤ ካለ መነሸጥና፣ ካለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ እገጥማለሁ ብሎ መቀመጫው ላይ የተደላደለ ገጣሚ የቤት መምቻ ቃላትን በማፈላለግ ሂደት ውስጥ የሆኼያት መመሳሰልን ብቻ ከግምት በማስገባት፣ ወይም ቤት ይምታልኝ በሚል ቀብድ የማይገናኝ ትርጉም ያላቸውን ቃላት አገልግሎት ላይ ሊያውል ይችላል።
የቤት ሥራ፡-
ገጣሚ፣ ቃላት፣ ገላጭ-ሐረጋት፣ ምሳሌያዊ አነጋገር፣ ፈሊጥና ዘይቤ ላይ እራቀቃለሁ በሚል ሰበብ የግጥምን ደም ደመ-ከልብ ሊያደርግ ይችላል፤ በመሆኑም፣ ስሜቱና ዕውነቱ ተጋጭተው፣ የተያያዘውን የግጥም ትርጉም መና ሊያስቀር ይችላል። ይኼንን ችግር ለመቅረፍ፣ ለቃላት አገባባዊ ፍቺ፣ ለምሰላው አሃድ ተስማሚነት፣ ለፍካሬው ተገቢነትና ለዘይቤአዊነቱ አንድምታ ትኩረት መስጠት ይገባዋል።   
ጣጣ 2፡-
ገጣሚ ማሕበረሰባዊ የሆነውን ኩነት መጠንቀቅ እንዳለበት፣ ብሎም በግጥሞቹ ገላ ማንጸባረቅ እንደሚገባው ዕሙን ነው፤ ሥነ-ግጥም ማሕበራዊ ፋይዳው ጉልህ ነውና። ውስጣዊ ጣመንና እርካታ በስንኝ ተደርድረው ሲቀመጡ የማራድ ኃይልን ይጎናጸፋሉ። ወይም ግጥም ሲቆጣ፣ ሲለብቅና ሲፋጅ ጥሩ ይመጣል። መነሾው ዘማማዎችን ለማቅናት ቢሆንም፣ በሌጣ ዘገባና ምክር አንባቢን የማያሰለች ግጥም ሲሆን ነው ታዲያ። ከአጥቁ ያላፈነገጠ፤ ፈር ስቶ መረን ያልነካ፤ ምናልባትም ዕድሜው አልፎ ያልባዘነ የስንኝ ስብስብ፤ ከሃፎቱ ውጭ አድሮ ልጬጫነትን ያልሸረካከተ ግጥም ሲሆን ደግሞ ወደ ልከኛነት (perfection) ይጠጋል።
በአጎራባች መስኮች ዙሪያ ነንና፣ ጥቂት እናነጻጽር፤ ስፓኛዊው የሥዕል ጉምቱ ሰው ፐብሎ ፒካሶ ውስጣዊ ጣመኑን በተዐምረኛ ብሩሹ ገሃድ ያውለዋል። የአሳሳል ይትባሃሉ ደግሞ የእራስ ንድፍ (Self portrayal) ይሉት ፈርጅ እንደሆነ ዕውቆች እማኝ ናቸው፤ ታዲያ ይኼ ድኅረ-ዘመናዊ ሠዓሊ ሥነ-ጥበብ ውስጣዊ መጨበጥን ሲበጣ የገዘፈ ትርጉም እንደሚኖረው በሥራዎቹ መስክሯል፤ ለዚህም ምስክር እንዲሆነኝ ‹‹Guernica›› ይሉት ዕውቅ ሥዕሉን መጥቀስ አለብኝ፤ የሥዕሉ መነሾም ሆነ ይዘት በስፓኝ የነበረውን የእርስ-በርስ ጦርነት ማዕከል ያደረገ ነው፤ የፒካሶ ነፍሱ ሠርክ ስትሰቃይና ስታታጥር በሥዕሉ ገላ ውስጥ መመልከት እንችላለን።
ወዲህ ደግሞ፣ አንዲት ሥሟን የማላስታውሳት ደቡብ አፍሪካዊ ደራሲ ነበረች፤ በአፓርታይድ ወቅት ልምዷን የሻቱ ወጣት ደራሲያን እግሯ ስር ተኮልኩለው፣ ‹‹እሜይቴ፣ ስለ ምን እንጻፍ? ውሉ ጠፋብን እኮ!›› ይሏታል አሉ እየተቁለጨለጩ። ታዲያ ይህቺ ብልህ ሴት በመልስ ምት ‹‹ስለኒያ አንገፍጋፊ ጊዜያት ጻፉ!›› ማለቷን መዝግቤአለሁ። እንግሊዛዊው ሪዛሙ ሁሉ ገብ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ዊሊያም ሼክስፔር፣ ጫፍ የነኩ ሥራዎቹን እንካችሁ ያለን ከልጁ ሞት አስከትሎ እንደሆነ መዝግቡልኝ፤ ስልቪ ፓሌትንም ማንሳት ተገቢ ነው፤ በሥራዎቿ የተብሰለሰለች እንደሆነች ተንትኖ መረዳት አያዳግትም።
ሥነ-ግጥም ማሕበረሰብ ነክ ርዕሰ-ጉዳዮች ማዕከሉ ቢሆኑም፣ የቸከ መሆን የለበትም፤ የምናውቀውን መልሶ መንገር የለበትም፤ ከገባንበት ማሕበራዊ፣ ሥነ-ልቡናዊና ፖለቲካዊ ቀውስ የምንላቀቅበትን መንገድ መጠቆም መቻል አለበት። ገጣሚ የከፋ ዛሬው ገንትሮት ማላዘን፣ እንዲሁም አሳካው ብሎ መኮፈስ የለበትም፤ በግጥም ገላ ውስጥ መጓዝና መሻገር ሊንጸባረቁ ይገባል፤ በገጣሚ ዓይን፣ ጣፋጭ እንዴት እንደሚመር፣ ወይም መራራ እንዴት እንደሚጣፍጥ ማጣጣም አለብን። የምናውቀውን ከነገረን ተረተ እንጂ ገጠመ አይባልም።
ግጥም እንደ ዜና ተነብቦ የሚታለፍ ሳይሆን ዘለዓለማዊነቱ ዕሙን መሆን ያለበት የኪነ-ጥበብ ሁሉ አውራ ነው፤ ቦይ ይምሳል፤ አንድ እርምጃ ቀድሞ ፈር ያበጃል፤ ዳና ያሳርፋል፤ የመጣውን አብዮት ታክኮ አያላዝንም፤ ዜናነትን ወግድ ብሎ ከዕውን ያልራቀ ምናባዊ ሀሳቦችን ያንጸባርቃል።
የቤት ሥራ፡-
ገጣሚ ስለ ዛሬ ብቻ ሊደሰኩር አይገባም፤ ነገን በራሱ ልክ ከርክሞ ሊያሰርጽብን የቤት ሥራ አለበት፤ ተዐምር ይሥራ እያልኩ አይደለም፤ ለሚያላዝን አንባቢ ሌላ የማላዘኛ ምክንያት ከመጨመር ይቆጠብ፤ ለአንባቢ ብቻ መግጠምን ገትቶ ለግጥምም መግጠም መቻል አለበት፤ ሀሳቡና ትልሙ ጥላ ይሆኑናል ስንል፣ ለንዳድ አስረክቦን መሄድ የለበትም፤ ስለዚህ፣ ለምናቡ ለከት አበጅቶ ሲያበቃ፣ ትልሙን ሊያስጎበኘን ቢችል መልካም ነው።
ጣጣ 3፡-
ትልቁ የገጣሚ ሥነ-ልቡናዊ ጣጣ ከሚያደንቀው፣ ከሚወደው፣ ወይም አርአያ አድርጎ ከሚወስደው ገጣሚ አንዳንድ ነገሮችን መኮረጅ ነው፤ በየትኛውም መስክ አርአያ ተደርገው የሚወሰዱ ግለሰቦች አሉ፤ ነገር ግን መልካም ተሞክሮዎቻቸውን እንደ ግብዐት እንጂ እንደ መነሻነት መገልገል ያዘወተረ ራሱን ችሎ ለመቆም ሊቸገር ይችላል።
ከአርአያ ገጣሚያን ዘይቤአዊነትን፣ የቃላት አመራረጥን፣ ሀሳብ ማዋቀርን፣ ዜማን እና ሌሎችን ኮርጆ የራስ አድርጎ ማቅረብ እየተለመደ መጥቷል፤ ይኼ ድክመት የሚመነጨው፣ አንደኛ አርአያ አድርገው የሳሉትን ገጣሚ እያስታወሱ፣ ወይም ስለ ግጥሞቹ አንዳንድ ፍተሻዎችን እያከናወኑ፣ ወይም ካከናወኑ በኋላ በሚገጥሙ ገጣሚዎች ላይ ሲስተዋል፤ ይኼ የሚሆነው፣ ለመማሪያው ወይም ለአርአያው ገጣሚ ሥራዎች ካላቸው ክብርና አድናቆት የመነጨ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም፣ ባለማወቅ ጉዳዩ ወደ መመሳሰል ሊያዘነብል ይችላል።
ሁለተኛው ደግሞ፣ አርአያ ተደርጎ የተወሰደውን ገጣሚ፣ ወይም ሥራዎቹን ለመምሰል የሚደረግ አጉራ ዘለልነት ነው፤ በመሆኑም፣ ተወዳጅ ሥራዎቹን የመሻማትና የመንጠቅ ያህል ተመሳስሎ ውስጥ ሊዘፈቁ ይችላሉ። ታዲያ፣ ሁለቱም ክፍተቶች ራስን ችሎ ከመቆም ያቅባሉ፤ ከዚህ አልፎ ቃራሚ ያስብላሉ፤ ወንጀልም ነው።
የቤት ሥራ፡-
የተሻለ ከሚሠሩ፣ ወይም ይሠራሉ ተብለው ከሚታሰቡ ሰዎች ልምድ መውሰድ ልማድ ነው፤ ነገር ግን አንድ ገጣሚ አርአያዬ ብሎ ከሰየመው ገጣሚ ላይ ግብዐት የሚሆን ነገር እንጂ መነሻው ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ የለበትም። ጉዳዩ ከዚህ ከከፋ ትርፉ ውስልትና ነው።      
ጣጣ 4፡-
ሥነ-ግጥም ለፌዝ፣ ለፈገግታና ለለገጣ ብቻ የታለመ መሆን የለበትም፤ በእርግጥ ገጣሚ መኳሸት፣ ማዛነቅና ቅርጽ ቀያይሮ መሰናኘት ይችላል፤ ነገር ግን ዋንኛ ዓላማው ሳቅ ለመፍጠር ብቻ መሆን የለበትም፤ ሳቅና ደስታን መፍጠር አስፈላጊ ቢሆንም፣ አንባቢ ጊዜና ገንዘቡን ሰውቶ እንደሚያነብ ሊገነዘብ ይገባል፤ ግጥም ብሉይ ነው፤ በሌሎች ዘውጎች ቀልድና ፌዝ የበዛበት ሃቲት ማቅረብ አያዳግትም፤ አብዛኛውን ጊዜ ባክኖ አንባቢን ሊያባክን አይገባም፤ ፈር ስቶ ማላገጥ የለበትም ባይ ነኝ፤ ይኼም የሚፈጠረው ምናልባት የግጥም ሀሳብ ለሚዛን ሲቀል በሳቅ ለውሶ ለማለፍ ዓይነት አጉል ሽወዳ ሊሆን ይችላል፤ ከገጣሚ የሥነ-ልቡና ጣጣዎች አንዱ ነው።
ከሥነ-ግጥም ጠባዮች አንዱ ቁጥብነት ነው። በቃላት አመራረጡ፣ በገላጭ ሐረጋትና ስንኝ አጠቃቀሙ ገጣሚ ፌዘኛና ላንቲከኛ መሆን የለበትም። ማብራራትን ገትቶ ማስጨበጥ አለበት፤ ይኼ ካልሆነ ከቅኔያዊነት ተናጥቦ ዜና ይሆናል።    
የቤት ሥራ፡-
ግጥም ብሉይ ነው፤ ለጊዜያዊ ፌዝና ፈገግታን ለማጫር ብቻ የታለመ መሆን የለበትም፤ ነገነቱ የተረጋገጠ መሆን አለበት፤ ማስተማር፣ ተስፋንና ፍቅርን ማስፈን፣ ማነሳሳት፣ ማሳተፍ እና ሌሎችም የሥነ-ግጥም ጠባያት እንደሆኑ ገጣሚ መገንዘብ ይኖርበታል።
ከዚህ በዘለለ፣ ሥነ-ግጥም በንባብ ወቅት አታካች እንዳይሆን፣ የሀሳብ ተያያዥነትን ዕውን ለማድረግ፣ ፍሰትን ለመጠበቅ…ወዘተ. አያያዥ ቃላትን ይሻል፤ ሆኖም እነዚህ አያያዥ ቃላቶች (በአብዛኛው የዚህ ጊዜ ገጣሚያን ሥራ ላይ የሚስተዋሉ፤ ለምሳሌ፡- እና፣ ስለዚህ፣ ዳሩ ግን፣ ውዴ፣ እቴ፣ ሆኖም እና ሌሎችም) የግጥምን ዜማ ይሸራርፋሉ፤ ደንቃራነታቸው ዕሙን ነው፤ ያታክታሉ፤ አንባቢ ስንኞቹን በሚገባ ወላ በምጣኔ እንዳይዘፍናቸው ይከላሉ፤ ያልተመጠነ ግጥም ዜማ አልባ ሊሆን ይችላል፤ ሥነ-ግጥምና ገጣሚ የዚህ ሰለባ ሆነዋል፤ እባካችሁ ባለሙያዎች ምክክር አድርጉበት።
በአጠቃላይ፣ የገጣሚ የሥነ-ልቡና ጣጣዎች ግጥምን ያለምሻሉ፤ በዚህ ዘመን በመርቀቅ ሰበብ ቃላት ላይ በመራቀቅ ፍጆታ የስሜትንና የዕውነታን ልዩነት የማያገናዝቡ ገጣሚያን ብዙ ናቸው፤ ቃላትን ካለ ጎራቸው እየዶሉ ትርጉም የሚያዛቡ ማለቴ ነው፤ ሌላኛው ጣጣ በአርአያ ገጣሚያን ጥላ ሥር ሆነው የኩረጃ ያህል የተጠጋ ግጥምን ለንባብ ማቅረብ ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ የሥነ-ግጥምንና የሥነ-ውበትን ተራክቦ በአግባቡ ባለመለየት ዕውነታንና የዓለምን ስብጥርጥር ገጽታ በአግባቡ መፈከር ያለመቻል ጣጣ ነው፤ እነዚህ ነጥቦች ከግምት ቢገቡ መልካም ይሆናል።
**
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።













Read 303 times