Saturday, 24 February 2024 20:22

ክፋትህና ውሸትህ ሲጠፋብህ፤ ጠላትህን አስታውሰኝ በለው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አንድ ንጉሥ አንድ ብልህ አጫዋች ነበራቸው። በየጊዜው ከሚመክራቸው ምክር መካከል ሰሞኑን የነገራቸውን ለመቀበል ከብዷቸዋል። ሰሞኑን የመከራቸው “ከወዳጆችዎ ይልቅ፣ ስለርስዎ ድክመት ዕውነቱን የሚነግሩዎ ጠላቶችዎ ናቸውና አዳምጧቸው” የሚል ነበር። ንጉሡ አላመኑበትም። ስለዚህ ለማረጋገጥ መዘዋወር ጀመሩ።
ንጉሡ በጣም የሚፈሩና አይበገሬ ነኝ የሚሉ ናቸው። በሄዱበት ቦታ ሁሉ የሚያገኟቸውን መኳንንቶች “እስቲ ስለ እኔ ጉድለት ንገሩኝ?” ይሉና ይጠይቃሉ።
“ንጉሥ ሆይ! እርስዎ ላይ እንዴት አይነት ሰው ነው ጉድለት ሊያገኝ የሚችለው። ደግሞ እርስዎ ምን ይወጣልዎታል!” ይሏቸዋል።
ቀጥለው ወደ ሠራዊታቸው ይሄዱና፤
“ምን እንከን አለብኝ? እስቲ ስለራሴ ንገሩኝ?” ይላሉ።
ከሠራዊታቸው ታማኙ ባለሟል ብድግ ብሎ፣
“ንጉሥ ሆይ! እርስዎ ከቁመናዎ ጀምሮ፣ ለጀግንነትዎ፣ ለዕውቀትዎ፣ ለዓለም ተደማጭነትዎ ምን የሚቀነስ የሚወጣልዎ ነገር አለብዎ!” ይላቸዋል። እንዲህ ከርመው አንድ ቀን በአጋጣሚ ከጠላቶቻቸው ጋር በሚሲዮን ይቀመጣሉ። አጠገባቸው የተቀመጠው ቀንደኛው ባላንጣቸው ቀስ ብሎ፤
“ስሙ ንጉሥ፤ ሲናገሩ አፍዎት መጥፎ ጠረን ያመጣል” ይላቸዋል።
ንጉሱ ይናደዳሉ። “እንዴት እስከዛሬ አንድ ወዳጄ ይሄን አልነገረኝም? እንዲህ በአደባባይ እንድጋለጥ ያደረጉኝ ወዳጆቼ ናቸው! ቆይ ግድ የለም! ባልሰራላቸው!” ይላሉ በሆዳቸው። ስብሰባውን እንደጨረሱ ሲገሰግሱ ወደ ቤተ-መንግስታቸው ይሄዱና ንግስቲቱን አስጠርተው፤
“አፌ ጠረን እንዳለው እስከዛሬ ያልነገርሽኝ ለምንድን ነው?” ሲሉ በቁጣ ጠየቁ። ንግስቲቱም፤ በንፁህ ልቦናና በቀናነት፤
“ንጉሥ ሆይ! የሁሉም ንጉስ አፍ እንደ እርስዎ አፍ አይነት ሽታ ያለው መስሎኝ ነው” ሲሉ መለሱ።
ንጉሡም እጅግ የቅርባቸው የሆነችው የገዛ ባለቤታቸው ጉድለታቸውን ሳትነግራቸው፤ ሩቅ የሚኖሩት ጠላቶቻቸው ማወቃቸውን ልብ ሲሉ፤ ያ አስተዋይ አጫዋቻቸው የነገራቸው ቁም ነገር እውነት መሆኑን ተገነዘቡ።
***
ማንኛውም መሪ፣ በማንኛውም ደረጃ ያለ ቢሆን፤ አንድ ሀቅ ልብ ማለት አለበት። ራሱን ብቻ የሚያዳምጥ መሪ፤ ከወዳጆቹ የሚጠብቀው ምንጊዜም ምስጋናን ስለሆነ ጉድለቶቹን የማየትም የመስማትም እድል አያገኝም። ወገኖቹም አይደፍሩትም። እሱም ራሱን አይደፍርም። ይህ ሁሉ የሚሆነው ሁሌ በሰላም ጊዜ በሆነ ባልከፋ። ሁኔታዎች በውጥረትና በችግር በሚሞሉበት ሰዓት ሲመጣ ነው አደጋው። ምክንያቱም የሁኔታዎች መወሳሰብን ተከትለው ሰዎችም ይለወጣሉና ነው። ችግሩ ግን በዚህ ብቻ አያቆምም። መሪውን መስለውና አክለው ማደግ ሲመኙ የቆዩ ባለሟሎቹና ተከታዮቹ አለማዳመጥ ሰናይ ስነምግባር እየመሰላቸው እነሱም እኩዮቻቸው የሚሉትን አልሰማ ይላሉ። በዚህ ምክንያት ካለመደማመጥ አልፎ፣ የሚፈጠረውን ጩኸት ለመገደብ ካለመቻል ደረጃ ይደረሳል። በየመንበራቸው እንደተቀመጡ በየራሳቸው ደሴት ውስጥ ይዋጣሉ። ውለው አድረውም የታችኞቹ በላይኞቹ ላይ ቅያሜን ያጠነክራሉ። ቀስ በቀስ በተለይ የመረረ የመከፋት ስሜት ውስጥ በገቡ ጊዜ፤ እንደ ሮማው ካሽየስ፣ ባለቃው ላይ ማሴርን፣ ራስን እንደማዳን ሲቆጥሩ፤ ከላይ ወደ ታች ይወርዱ የነበሩ ትእዛዛት ወደ ጎንም፣ ወደ ይም እንዲያመሩ ሲፈለግ፣ ለወትሮው የአለቃውን ድክመት ሁሉ የእኔ ነው እያለ አሜን ይል የነበረው ሁሉ፣ ድርሻ ድርሻችንን እንውሰድ በሚል፤ ሌላውን ማነሳሳትና ብሶቱን ሌላው ላይ ማጋበቱን ይያያዘዋል። ይሄኔ እንደ ሮማው ብሩተስ ያለው በትዕግስት የሚያገኘውን ስልጣን ቄሳርን በማስወገድ ሊፈጽመው እንዲሻ ሲተነኮስ፣ ወይም ሲወነባበድ፣ ነገር የተገላቢጦሽ ይሆናል። ቄሳር በመሞቻው “አንተም ብሩተስ?” ያለበት ሰዓት የሚመጣ እንግዲህ ያኔ ነው።በተለይ ስልጣንን በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመጋራት ልምድ በሌለበት እንደ እኛ ባለው አገር ብርቱ ጥንቃቄ የሚጠይቀው፣ በወንበሩ ዙሪያ አስፈላጊ ትዕግስትና መቻቻል አለመኖር ነው። መተማመን እንዲኖር ሀሳብን መግለጽ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ነጻነቱ አስፈላጊ ነው። ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት በሀቅና ከልብ ካልታመነበት፤ “ለብ ለብ ዲሞክራሲ” “ገባ ያለው ዲሞክራሲ” እና “ስፔሻል ዲሞክራሲ” እያልን እንድንከፋፍል ልንገደድ ነው። “አካሄዱ ፍጻሜውን ያሳያል” እንዳንል፤ አባይን ጭብጦዬን ከቀማኝ ወዲህ አላምነውም፤ የሚሉ ወገኖች ይሟገቱናል። የለም “ግቡ አካሄድን ያሳያል” - የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው ነው ነገሩ- ለሚሉት ደግሞ ካልታዘልኩ አላምንም፣ ስንቱ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ አይደል ወይ መላው የጠፋው የሚሉ ይኖራሉ። ሁኔታዎችን አጣጥመን መጓዝ የሚያስፈልገን ለዚህ ነው። የሚያግባባንን መንገድ ከንፍቀ-ክበባችን ውጭም ቢሆን ማዳመጥ፣ ከባላንጣዎቻችንም ቢሆን መማር፣ ሁሌ ከመተላለፍ አንዳንዴ “ምን ይሆን?” ብሎ ለሌሎች ሀሳብ ትንሽ እድሜ መለገስ፤ ቀስ በቀስ ግትርነታችንን ሊያረግበው ይችላል።
አለንልህ ያልነውንና በእርሱም ትከሻ ለስልጣን የበቃንለትን፣ ከቀን በኋላ ከእርሱ እጅ የማንወጣውን ህዝብ ማዳመጥ እንደሚኖርብን እንድናስብም ፋታ ይኖረናል።
ስለሌላው ውሸት እንጂ እውነት በተናገርን ቁጥር፣ ስለሌላው ድክመት እንጂ አንድ አንኳር ጥንካሬ እንኳን ባነሳን ቁጥር፣ እኛ ብቻ ሀቀኛ፣ እኛ ብቻ ጠንካራ እያልን እንገበዛለን። ይህ ደግሞ ስለራሳችን እውነተኛ ገጽታ እናዳናውቅ ያደርገናል። የእኛኑ ቅኝት የሚያዳምጡ ወገኖቻችንና ደጋፊዎቻችን እውነተኛ ይዘትና ቅርጻችንን አይነግሩንም።
ስለዚህ ከእኛ ውጭ የማዳመጥ ባህል ማዳበር ደግ ነገር ነው- ከ”ጥላትም” ሰፈር ቢሆን። አበው “ክፋትህና ውሸትህ ሲጠፋብህ፤ ጠላትህን አስታውሰኝ በለው” የሚሉት ይሄንኑ ሊያስገነዝቡን ነው፡፡

Read 1471 times