Saturday, 24 February 2024 20:18

ሃይማኖት፣ ፍልስፍና፣ ሳይንስና ኪነጥበብ የየራሳቸው ንጉሦች ወይስ ተቀናቃኞች?

Written by  ዩሃስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

ገና ከመነሻችን፣ የማያከራክሩ እውነታዎች ላይ አተካራና ሙግት ለመፍጠር ተብለው የሚመጡ ክርክሮችን በማስወገድ እንጀምር።
አካልና አእምሮ የሰው ተፈጥሯዊ ገጽታዎች የመሆናቸው ያህል፣ መንፈሳዊ ባሕርያትም በሰው ተፈጥሮ ላይ የሚታዩ ገጽታዎች ናቸው። ከሦስቱ ተፈጥሯዊ ገጽታዎች መካከል በአንዱ ገጽታ ላይ ማተኮርና ማጥናት፣ መማርና ማወቅ ይቻላል። ተገቢም ነው። በአንዴ ሁሉንም ነገር ማወቅ አይቻልምና።
ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባይሎጂ… እያልን የምንማረውም በሌላ ምክንያት አይደለም። የተፈጥሮ ገጽታዎች ናቸው። ሁሉንም በአንድ ጊዜ ጠቅልሎ ማጥናትና ማወቅ ደግሞ አይቻልም። አንዱን ገጽታ እየመዘዝን በትኩረት በማጥናት ነው፣ ዕውቀትን የምናገኘው። የሰው አካላዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ ገጽታዎችንም እንዲሁ።
ታዲያ፣ ሌሎቹን የሕይወት ገጽታዎች በመዘንጋት ወይም በመሠረዝ አይደለም። ሁሉንም ገጽታዎች እንደ መሠረት ይዘን እንደ መደብ እንደ ማዕቀፍ ልንጠቀምባቸው ይገባል። ነጥለን ወይም ገንጥለን በማውጣት ሳይሆን፣ እዚያው መደብ ላይ አንዱን ገጽታ በማጉላት ነው ማጥናት የሚኖርብን። ምክንያቱም፣ አካል፣ አእምሮ፣ መንፈስ… የአንድ ተፈጥሮ ሦስት ገጽታዎች እንጂ የተነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም።
አካላዊ ገጽታዎች ላይ አተኩረን ስንማር “ዐይን፣ አንጎል፣ የነርቭና የኒዩሮን አውታሮች” እንላለን።
አእምሯዊ ገጽታዎችን አጉልተን ስናጠናም “አየች፣ ተመለከተ፣ አስተዋለች፣ አገናዘዘ፣ ተማረች፣ ዕውቀትን ገነባ” ብለን እንናገራለን።
መንፈሳዊ ገጽታዎች ላይ ስናነጣጥር ደግሞ፣ “የተካነችበት የአስተዋይነት ብቃቷ፣ ሙያ መውደዱ፣ የማወቅ ጉጉቷ፣ ለእውነታ የመታመን ጽናቱ፣ የዕውቀት ተቆርቋሪነቷና አክብሮቷ” የሚሉ ሐሳቦችን እናገኛለን።
እርስበርስ የተሳሰሩ ገጽታዎች ስለሆኑ ሳንነጣጥላቸው፣ አንዱን በትኩረት አጉልተን ማጥናትና መነጋገር እንችላለን።
ገነጣጥለን ስንነጣጥላቸው ነው ችግሩ።
“ለሳይንሳዊ ዘዴዎችና መርሆች ተቆርቋሪ ነኝ” ብሎ፣ የሰው መንፈሳዊ ገጽታዎችን ለማራከስ የሚተጋና የሚሰብክ “የሳይንስ ቲፎዞ” ይኖራል። በእውን ለሚታየው ተፈጥሮ፣ ለተጨባጩ ዓለም ታማኝ እንሁን ብሎ ሲሰብክ ግን፣ “የታማኝነትን” ፋይዳ የሚያንኳስስ ከሆነ ምን ትርጉም አለው? መቼም፣ “ታማኝነት” በእውን የሚታይ የተጨባጩ ዓለም ቁስ አይደለም። ከሰው ተፈጥሮ የሚጠበቅ መንፈሳዊ ባሕርይ ነው። ተቆርቋሪና ታማኝ የመሆን ኀላፊነትን ተሸከሙ የሚለን፣ ለእውነታና ለመርሆች ምን ዕዳ አለብን? ከመነሻውስ፣ “ታማኝና ተቆርቋሪ መሆን” ምን አመጣው? ብንሆን ባንሆን ምን ጨነቀን? ምናችን ሆነና ነው? ለነገሩ እሱስ ምን ዕዳ ኖሮበት ይሆን?
የሳይንስ ተቆርቋሪ፣ መንፈሳዊነትን ሲያጣጥል እዚያው በዚያው አንዳች ጥቅም አገኝበታለሁ በሚል ስሌት ሳይሆን፣ “በመንፈሳዊ ግለት” ነው። በመንፈሳዊ ጡዘት ወይም በአስመሳይ መንፈሳዊነትም ሊሆን ይችላል። አለበለዚያ፣ “ተቆርቋሪነቱ” ትርጉም ያጣል።
“የሰው አካል ከንቱ ነው፤ ቅዠት ነው” ብሎ የሚያስብ “መንፈሳዊ መምህርም” ይኖራል። ግን ምን ላይ ቆሞ በምኑ ይናገር? እጁን እያወራጨ ጉሮሮው ደርቆ ምላሱ እስኪተሳሰር ድረስ የመስበክ ትጋት ባይጎድለው እንኳ፣ በምናችን እንስማው? በጆሯችን? በዚህ ካልተሳካለት፣ በብርቱ ክንድ እየደበደበ ሊሳምነን ነው? ሰነፍ ከሆነ፣ “የሰው አካል የእውን ነው” ብለው የሚያስቡ አላዋቂዎች ላይ ለማላገጥ ምላሱን ቢያወጣባቸው ደግሞ አስቡት።
“አስተማማኝ ዕውቀት የለም” ብሎ ከሚሰብክ ሰው ጋር ይመሳሰላሉ። ዕውቀት አስተማማኝ አይደለም ብሎ በማብራሪያና በትንታኔ የዐቅሙን ያህል ይደክማል። ለምን? ሊያሳውቀን! ሊያሳምነን!
ለእንዲህ ዐይነት ሙግቶች እልባት መስጠት አያስቸግርም። እርስበርሳቸው እየተላተሙ የሚወድቁ ናቸውና።
“ሃይማኖት ሁሉም ነገር ነው” የሚል ክርክርም፣ ከሁሉም የሰው የሕይወት ቅርንጫፎች ጋር የተሳሰረ ነው ለማለት ከሆነ እውነት ነው። ሳይንስም ከሁሉም የሕይወት ቅርንጫፎች ጋር የተሳሰረ ነው።
ነገር ግን፣ የሃይማኖት ትምህርት የእርሻ ዕውቀት ወይም የብረታብረት ሙያ ይሆናል ማለት አይደለም። ስለ እርሻ ወይም ስለ ብረት ሥራ በጥቅሉ የሚነግረን ጉዳይ ይኖረዋል። የማዳበሪያ ዕውቀትና የብየዳ ስልጣና ባናገኝበትም ግን፣ የሃይማኖትን ክብር አያጎድልበትም። የሃይማኖት ግዛት ሌላ ነውና።
“ፍልስፍና የማይነካው የሰው ጉዳይ፣ የማይዳስሰው የዕውቀት ዘርፍ የለም” ይባላል። እውነት ነው። ነገር ግን በቤት ግንባታና በምግብ አሠራር ላይ ፍልስፍና ልዩ ሥልጣን የለውም። እንዲህ ስንል፣ የፍልስፍናን ግዛት ለማጥበብ ወይም ክብሩን ለማሳነስ አይደለም። ግዛቱና ክብሩ እንደተጠበቀ ይቀጥላል። ከፍልስፍና መጻሕፍት ውስጥ የንግድ ዘዴዎችንና የልብስ አዘገጃጀት ጥበብን መማር ባንችል፣ የፍልስፍና ድክመት አይደለም። የፍልስፍና ግዛት በባሕርይው ከእነዚህ ይለያልና።
ልክ እንደዚያውም፣ ሃይማኖትም ሁሉንም የሕይወት ቅርንጫፎች የሚያጠቃልል ቢሆንም፣ በሒሳብ ወይም በፖለቲካ ዕውቀት ላይ ልዩ ሥልጣን የለውም። የፊዚክስ ወይም የአስትሮኖሚ፣ የኬሚስትሪ ወይም የባይሎጂ ትምህርት አይሆንልንም። እንዲሆንልን ብንጠብቅ የኛ ስህተት ነው። አለበለዚያማ፣ እነ ፊዚክስ እነ ባይሎጂ ለምን አስፈለጉ?
የከርሰ ምድርና የጠፈር ምርምር አይደለም - ሃይማኖት። ከነ ሉሲ የቅሪተ አካል ጥናት ጋር ተቀናቃኝ፣ አማራጭ ወይም ተፎካካሪ አይደለም። የጀነቲክስ ምርምር ወይም የኢቮሊሽን ንድፈሐሳብ ሲመጣ፣ የሃይማኖትን ዕድሜ የሚያራዝም ዐጋዥ ወይም ሃይማኖትን የሚያጠፋ ገዝጋዥ መጣ ማለት አይደለም። ፊዚክስና ባይሎጂ፣… የሳይንስና የዕውቀት ፈርጆች በሙሉ፣ እውኑን ዓለምና ሕይወትን ያጠናሉ እንጂ፣ የእውኑን ዓለም ወይም የሕይወትን ተፈጥሯዊ ባሕርይ ሊቀይሩ አይችሉም።
የአንዲት ነጠላ ወረቀት ውስብስብ የአቶም ቅንብሮችን አብጠርጥሮ የሚያውቅ የፊዚክስ ሊቅ ከአጠገባችሁ ቢኖር፣ ወረቀትነቱን አይለወጠውም። በወረቀቱ ተፈጥሮ ላይ የሚጨምርለትና የሚቀንስበት ነገር የለም። የሳይንስ ምርምሮች፣ የሰውን ተፈጥሮ ሲያጠኑ፣ የሰውን ተፈጥሮ ባሻቸው መንገድ እንዲጠፋ ወይም እንዲከሰት የሚወስኑ አዛዦች አይሆኑም። የሰው አካላዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ ገጽታዎች በምርምር ብዛት፣ ወይም በምርምር እጦት የሚፈጠሩ የሚጠፉ ገጽታዎች አይደሉም። ተፈጥሯዊ እውነታዎች ናቸው።
ግን ደግሞ፣ ነገርዬው “የማስታረቅና የማቃረን ጉዳይ” ብቻ ባይሆንስ? ድራማና ዜና፣ ግጥምና ንግግር፣ ጤንነትና ውበት፣ ፍቅርና ሚዛን… በሆነ ነገራቸው ተቃራኒ ናቸው ብለን መከራከር እንችላለን።
“ሲኳሉ ሲያጌጡ ይመላለጡ” ይለናል አንዱ። ጤንነትና ውበት እንደሚቃረኑ ይነግረናል። “የሚያስፈልጋችሁ ሌላ፣ የምትፈልጉት ሌላ” ትለናለች አንዷ። “ትለብሰው የላት፣ ትከናነበው አማራት” በማለትም፣ ስሌትና ስሜት እንደሚጋጩ ትነግረናለች።
“ፍቅር ሌላ፣ ትዳር ሌላ” ይሉ ነበር የጥንት ወላጆች።
“ፍቅር እውር ነው፤ መመዘኛና መስፈርት ለሥራ ቅጥር፣ ምናልባትም ለትዳር ይጠቅም ይሆናል። ፍቅርና እርካታ ግን በቀመርና በስሌት አይሆንም” ይላሉ ዘመነኞች።
የሷና የሱ መረጃዎች ተመዝግበው፣ ጠንካራና ደካማ ጎኖች በሰንጠረዥ ተሰናድተው፣ በማጣሪያ ተወዳድረው፣ ተለክተውና ተመዝነው ውጤታቸው እስኪታወቅ ድረስ አይጠብቅም - የፍቅር መንፈስ፣ የእርካታ ስሜት።
እንዲያውም “ለምን ወደድኳት?” ብሎ ቢጠይቅ አሳማኝ መልስ ለማግኘት ብዙ ደካም ይጠብቀዋል (እንደወደዳት ካወቀ በኋላ)።
“ለምን አፈቀርኩት?” ብላ ዘጠና ምክንያቶችን ለመደርደር፣ የጎደለ ነገር እንዳይኖርም በምናብ እየፈጠረችና ልትጨምርለት እንቅልፍ አጥታ የምታድረው ካፈቀረችው በኋላ ነው።
ማልቀስና መሳቅ፣ እንባና ፈገግታ የኛን ውሳኔ አይጠብቁም ብንልም ያስኬዳል። ሐሳብና ስሜት በጣም ይራራቃሉ፤ በየፊናቸው ተለያይተው የሚኖሩ ራስ-ገዝ ዓለማት ይመስላሉ።
ግራ ቀኙን አመዛዝነን፣ “ይሄኛው ታሪክ አሳዛኝ እንደሆነ ተመስክሮለታል። ያስለቅሳል ስለተባለም የእንባ በሮች እንዲከፈቱ ትእዛዝ ተላልፏል” አንልም። በሃዘን ስሜት ከተንገበገብን በኋላ፣ “በጣም ያሳዘነኝኮ…” ብለን እንናገራለን።
“ይሄኛው ንግግር አሪፍ ቀልድ እንደሆነ ተረጋግጧል፤ የሳቅ ድምፆች እንዲለቀቁ ተፈቅዷል” አንልም። እንስቃለን። ለትንታኔና ለማረጋገጫ ጊዜ አይኖረንም። ስቀን ስንጨርስ የማሰቢያ ጊዜ ስናገኝ፣ አስቂኙን ቀልድ እየተነተንን እያፍታታን፣ እየሰበሰብን እየገጣጠምን ብንጨዋወትበት ብንመራመርበት ከልካይ የለንም። የበለጠ ሊያዝናናን ይችላል።
አንዳንዴ ግን የቀልዱን አሪፍነት እናብራራለን ብለን ስንሞክር የቀልዱን ለዛ እናደበዝዘዋል። ባሰብንበት ቁጥር አስቂኝነቱ ይሳሳብናል፤ የቀልድ ስሜቱ ይጠፋብናል። ሐሳብና ስሜት ተቃራኒ ፍጡራን ቢሆኑ ነው ያስብላል። ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ፣ ሐሳብና ስሜት የማይስማሙበት ጊዜ ቢኖር ነው እንላለን።
የልብ ጓደኞች ገና ሲተያዩ ልባቸው ወከክ ይላል፤ መንፈሳቸው ክንፍ ያወጣል። ለምን? ሚዛን የሚደፉና የሚያሳምኑ ምክንያቶችን በቁጥር አይዘረዝሩም። “ዐይኖች በደስታ እንደከዋክብት እንዲደምቁ፣ ፊቶች በፈገግታ እንዲፈኩ ተወስኗል” አይሉም። ሳይታወቃቸው ሁለመናቸው ወዳጅነታቸውን ይናገራል። ውስጣዊ መንፈሳቸው በሜጋዋት ብርሃን ፊታቸው ላይ ፏ ብሎ ይታያል። ሜጋዋት “አንድ ሺ ሻማ” እንደማለት ነው።
እንግዲህ፣ እንዲህ እንዲህ እየጠቃቀሱ የስሌትና የስሜት ተቃራኒነትን፣ የውበትና የጤንነት ግጭትን ይተነትናሉ። ፍቅርና ምክንያት፣ ጥላቻና ማስረጃ ለየቅል ናቸው ብለው ይዘረዝራሉ። ለዚያ ለዚያማ ሐሳብና ሐሳብም ይጣረሳል። በዚህና በዚያ አጋጣሚ አንዱ ገጽታ ከሌላኛው ገጽታ ቢጋጭ፣ በተፈጥሮ ለግጭት የተፈጠሩ ናቸው ማለት አይደለም። ይልቅስ፣ ሐሳቦች እርስ በርስ እንዳይጣረሱ በአስተዋይነት መጠንቀቅና መመርመስ አስፈላጊ የመሆኑ ያህል፣ ሐሳብና ስሜት፣ ውበትና ጤንነት፣ አካልና መንፈስ በአንዳች ሰበብ እንዳይቃረኑም ጥረት ያስፈልጋል።
በሌላ አነጋገር፣ የሰው ተፈጥሯዊ ገጽታዎች፣ እርስ በርስ ተስማምተውና ተደጋግፈው ማደግ ያለባቸው ተጣማሪ ገጽታዎች ናቸው ብንል ስህተት አይሆንም። ዕውቀትና መንፈስ፣ ሐሳብና ስሜት፣ የምንፈልገውና የሚያስፈልገን፣ ፍቅርና ሚዛን፣… እንዴት እንደሚለያዩ፣ አንዳንዴም እንደማይስማሙና እንደሚቃረኑ ብናይም፣ ግንኙነታቸውንም አለማየት አንችልም። ሳቃችንን ወይም ፍርሃታችንን፣ ደስታችንን ወይም ሃዘናችንን የመቆጣጠር ቅንጣት ዐቅም የለንም ማለት አይደለም። የተወሰነ ያህል እንችላለን። ግንኙነት አላቸው።
በዚያ ላይ፣ ቀስ ብለን ስናስብባቸው ይበልጥ ስሜታችንን የሚነኩ ጉዳዮች መኖራቸውስ ምን ይጠየቃል?
በሆነ ሰበብ የጠላነው ሰው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያወቅነው ስንሄድ ወዳጃችን ሊሆን ይችላል። ያደነቅነውና የወደድነው ሰው፣ አንዳንድ ነገሮቹን በቅርበት መመልከት ስንጀምር፣ የወዳኝነት መንፈሳችንን የሚበርዙ ነገሮች እንታዘባለን።
በዕድሜ፣ በዕውቀትና በልምድ ባደግን ቁጥር፣ የሚማርኩንና የሚያስጠሉን፣ አስቂኝና አናዳጅ የምንላቸው ነገሮች እዚያው በነበሩበት ቦታ ቆመው አይቀሩም። ዕውቀትና መንፈስ፣ ሐሳብና ስሜት የየራሳቸው የተለያየ ባሕርይ ቢኖራቸውም፣ እርስ በርስ የሚያስተሳስር ግንኙነት እንዳላቸውም አያጠራጥርም።
በእርግጥ፣ ዝምድናቸውን ለማሳየት ብለን፣ ልዩነታቸውን መዘንጋት ወይም ማድበስበስ አለብን ማለት አይደለም። ለምን ብለን? ለማጣመር ብለን፣ ያልሆኑትን እንዲሆኑ፣ አንዱ የሌላው ጊዜያዊ ተቀጥላ፣ ወይም አንዱ የሌላኛው የዘላለም እስረኛ ብናደርጋቸው፣ ራሳችንን ከማታለል ውጭ ምን ትርፍ አለው? ልዩነትን ማጋነንና ተመሳሳይነትን መካድ ከእውነታ ጋር ያራርቃል። ልክ እንደዚያው፣ ልዩነቶችን እያድበሰበስን ተመሳሳይነትን እያጋነንን ሁሉንም ነገር ለማቀራረብና ለማስታረቅ መሟሟትም፣ ከእውነት መንገድ ያስወጣል።
ከግጥም ውስጥ መረጃንና ዕውቀትን ጠምቀን ለመቅመስ፣ ከዜና ውስጥም ጥበብንና መዝናኛን አጥለለን ለማውጣት መሞከር እንችላል። በዚህም መረጃንና ውበትን፣ ዕውቀትንና ጥበብን፣ የግጥም ስንኞችንና ሰበር ዜናዎችን አቀራርበን አስታረቅናቸው ማለት ነው? ብዙም ቁምነገር የምናገኝበት አይመስልም። የየራሳቸው ግዛት ቢኖራቸው ነው።
ግን ደግሞ ዝምድናቸውን አለማየት አንችልም። ሰው እንደሆነ ሰው ነው። በሁለት በሦስት ግዛቶች ድንበር የተበጀለት የቁርጥራጮች ስፌት አይደለም።
እናም፣ ልዩነታቸውን የመገንዘባችን ያህል፤ ዓለማዊና መንፈሳዊ፣ ሃይማኖትና ኑሮ፣ እምነትና ዕውቀት፣… ከሰው ሕይወት ገጽታዎች ጋር አያይዘን ዝምድናቸውን ብናይ፣ ብዙ ቁምነገር የምንጨብጥ ይመስለኛል።

Read 699 times