Saturday, 17 February 2024 21:15

ዝክረ ወንድዬ አሊ (1950 - 2016)

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“--ወንድዬ ዓሊ በ1950 ዓ.ም  በቀድሞው የወሎ ጠቅላይ ግዛት፣ ወረኢሉ አውራጃ ካቤ በምትባል መንደር ታክል ከተማ ተወለደ፡፡ ለወላጆቹ አምስተኛ ልጅ የሆነው ወንድዬ፤  በእናቱ ፍቅር ተምበሽብሾ፣ ወደ ጫና በሚያደላው በአባቱ ጥብቅ ሥነ- ምግባር ተኮትኩቶ አደገ፡፡ ግጥም መግጠም የጀመረው፣ ገና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ ነበር፡፡

‹‹የእናትና አባቴ ትዳር ከፈረሰ በኋላ አባቴ ሌላ ሚስት አገባ፡፡ የእንጀራ እናቴ - በራሷ “ክፉ ቀን! ክፉ ሰው!” ሆነችብኝ፡፡ ፊቷ በገረፈኝ ቁጥር ቁጭቴን የምወጣው ወረቀት ላይ ነበር፡፡ አምስተኛ ክፍል ስደርስ እንጉርጉሮዎቼ አንድ ደብተር ሞሉ፡፡ ጥራዟን “ሲከፉ” የሚል ርእስ አወጣሁላት›› ይላል ወንድዬ፤ አጀማመሩን ሲያስታውስ፡፡

ግጥሞቹ ግን ከባድማ ልቡ ብቻ የወጡ አልነበሩም፤ ከማንበብና መጻፍ በስተቀር ምንም ዘመናዊ ትምህርት ያልቀሰሙት አባቱ፤ ለሕክምናም ሆነ ለፍርድ ቤት ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ባሉ ቁጥር ብርቅዬ ጫማና አልባሳት ሳይሆን መጻሕፍት ገዝተውለት ነበር የሚመጡት፡፡ ጦቢያ (የመጀመሪያው ልቦለድ በአፍሪቃ)፣ ወዳጄ ልቤ፣ አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም፣ ፀሐይ መስፍን፣ እንቅልፍ ለምኔ ወዘተዎቹን. . . ያነበበው ካቤ መንደሩ ሳለ በኩራዝ ነው፡፡ የንባብ ፍቅር በዚያው ተጠናውቶት ቀረ፡፡

በጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ በሚገኘው በታዋቂው የወይዘሮ ስኅን ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ደሴ ከተማ በ1965 ዓ.ም  ሲሄድ እንጀራ እናቱ ከሚያደርሱበት ሃበሳ ተገላገለ፡፡ እንጉርጉሮ - ጎርጉሮ የመክተቡም ነገር አብሮ ቀጥ አለ፡፡

ኪነ-ጥበባዊው ደመ-ነፍሳዊ አደራ ግን እንደ ጪስ (ጢስ) መውጪያ ስንጥቅ አታጣምና  መንፈሳዊ ግጥሞችን መጫጫር ጀመረ፡፡ በደብረ ዘይት የእንስሳት ሕክምና ኮሌጅ በ1971 ዓ.ም  ገበቶ የደብረ ዘይት መካነ ኢየሱስ ኳየር ሲቀላቀል አምሮቱን ተወጣ፤ 200 ግድም ዜማ-ግጥሞችን (Lyrics) ዘመረ፤ አዘመረ፡፡ ስለ ዜማ-ግጥም ሥራዎቹ ሲናገር እንዲህ ይላል፡- ‹‹እነሱ እኮ! … ግጥሞቼ ሳይሆኑ፣ የዐውደ ዕለት ማስታወሻዎቼ (Diary) ናቸው፤ ግጥሞቼ ደግሞ - ታሪኮቼ››፡፡  ከነፍሱ ጥሪ በተቃራኒ እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የገባው በጊዜው ከነበረው ቀይ ሽብር አደጋ ለመሰወር ያህል ብቻ እንደ ነበረ - ያስታውሷል፡፡

ከኮሌጅ ሲመረቅ በሐምሌ 1972  አርሲ ተመደበ፡፡ በእንስሳት ሐኪምነትና በእንስሳት እርባታ ማኔጀርነት ዘጠኝ ዓመት ተኩል በሠራባቸው ዓመታት እውነተኛ ገጣሚነቱ ተፍለቀለቀ፡፡ በ1984 ዓ.ም  በታተመቺው የመጀመሪያ መድበሉ “ወፌ ቆመች” ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች አብዛኛዎቹ የተጻፉት በአርሲ ቆይታው ነበር፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ኮተቤ ኮሌጅን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት “በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ” ክፍል ለማስተማሪያነት በካሪኩለም ውስጥ ለመካተት የበቃቺው “ወፌ ቆመች” እንግዲህ የእንስሳት ሐኪሙ - የቅኔ ዛር ምጥ ናት ማለት ነው፡፡

የወፌ ቆመች መታተም እና ዝና ኋላ ላይ ፍቅሩም፣ እንጀራውም ወደ ሆነው የሥነ ጽሑፍ ሙያ ይቀላቀል ዘንድ መንገድ ጠረገለት፡፡ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት የሥነ ጽሑፍ ድርጅት ባልደረባ ይሆን ዘንድ ጋበዘው፡፡ (በዚህ ረገድ የአቶ ጌታቸው በለጠ ድርሻ ትልቅ ነበር፡፡ ግብርና ሚኒስቴርን ለቆ (ሞፈሩን ሰቅሎ፣ ቀምበሩን ሰብሮ) በትንሽ ደመወዝ በረዳት መጽሔት አዘጋጅነት ተቀጠረ፡፡

‹‹መጽሔት፡- እንደ ‹ቡፌ› ገበታ የተለያዩ መልእክቶች፣ በተለያዩ አቀራረቦች፣ በተለያዩ የአቀራረብ ቀለሞች፣ የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች መከሸን ይገባዋል፤›› ብሎ  የሚያምነው ወንድዬ፤ የቃለ ሕይወትን መጽሔት እንደ ልቡ ናኘባት፡፡ እያንዳንዷን ቅጽ፡- የመጣጥፍ፣ የታዋቂ ሰዎች ፕሮፋይል፣ የቃለ ምልልስ፣ የግጥሞች . . . ገበታ አደረጋት፡፡ (እንዳሰኘው ይጽፍ ዘንድ ሙሉ ነፃነት ያጎናጸፉትን የቅርብ አለቆቹን ያመሰግናል)፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ከሥነ ግጥም በተጨማሪ በሌሎችም የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች ለመጻፍ ተሰጥዖ እንዳለው ራሱን ያሳመነው፡፡ በተለይም በታሪክ እና የሕይወት ታሪኮች አተራረክ ረገድ ብዙ እርምጃ ተራመደ፡፡ ለዚህም ነበር፣ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንን ከፊል ታሪክ የሚሸፍነውን (1920-1966 ዓ.ም) ለመጻፍ የቻለው፡፡

በሁለት ቅጽ የተዘጋጁት መጻሕፍት “በመከራ ያበበች” እና “የእኩለ ሌሊት ወገግታ” ይሰኛሉ፡፡ እንደ ቅደም ተከተላቸው በ1990 ዓ.ም እና 1992 ዓ.ም የታተሙ ናቸው፡፡ መጻሕፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የፕሮቴስታንት (ወንጌላውያን) ቤተ እምነት ታሪክ በመሆናቸው በርካታ የሥነ መለኮት ኮሌጆች ሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) ውስጥ ተካተቱለት፡፡ በዚህ ደስ የተሰኙት አለቆቹ Tear fund England ከሚባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር፣ ኬኒያ - ናይሮቢ በሚገኘው Daystar ዩኒቨርስቲ የትምህርት ዕድል አመቻቹለት፡፡ በ40 ዓመቱ ተመልሶ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በአራት ዓመት ቆይታ ለመጀመሪያ ድግሪ መርሐ ግብር የተላከው ወንድዬ፣ በሦስት ዓመት ቆይታ የማስተርስ ዲግሪውን ይዞ ተመለሰ፡፡ ይህ ለብዙዎች ታምር ያህል እውነት ነው፡፡ ጥያቄም ነው፡፡

‹‹ሰው እንዴት ከveterinary ዲፕሎማ ተነስቶ በሦስት ዓመት፣ ለዚያውም ለMature Students የሚሰጠውን መሸጋገሪያ ኮርስ (Bridging Course) ሳይወስድ፣ ሁለተኛ ዲግሪውን ለዚያውም በሦስት ዓመት ብቻ ሊያጠናቅቅ ይችላል?›› ይህን  ለመዘርዘር ውጥኔ አይፈቅድልኝም፡፡ የወንድዬን የአዕምሮ ጉልበትና ሥራዎቹን በደንብ የተረዱ ሰዎች ‹‹ይህን ሰው ለመጀመሪያ ድግሪ ማስተማር “ማባከን ነው” በማለት ከዩኒቨርስቲው ጋር የተሟገቱ እንደ ነበሩ ወንድዬ ያስታውሳል፡፡ የአቶ ወርቁ ኃይለ ማርያምን ግትገታ (ውትወታ) ግን ከሁሉ የበለጠ ነበርና ወንድዬ ሁሌም ያስታውሰዋል፡፡

ወርቁን እና ወዳጆቹን አላሳፈራቸውም፡፡ የመመረቂያ ወረቀቱን፡, “THE CONTRIBUTION OF ORAL LITERATURE IN COMMUNICATING THE GOSPEL TO THE OMOTIC PEOPLE OF SOUTHERN ETHIOPIA: A CASE STUDY OF THE WOLIATE PIONEER EVANGELISTS” በሚል ርእስ ሠርቶ፣ በ2003 (እኤአ) በማስተርስ ድግሪ ተመረቀ፡፡

ከናይሮቢ እንደ ተመለሰም የቃለ ሕይወት ሥነ ጽሑፍ ክፍል ኃላፊ ሆኖ ተመደበ፡፡ ግና ምን ያደርጋል? ሹመቱን ሰጥተው የቀድሞውን ነፃነቱን ነፈጉት፡፡ ከሁለት ዓመት መፍገምገም በኋላ ሥራውን ለቆ Population Media Center (PMC) በኤክስፐርትነት ተቀጠረ፡፡ ጥቂት፣ ግን መልካም የፊደላት የምርት ዘመን አሳለፈ - 2 ዓመት ብቻ፡፡ በክብር ተሰናብቶ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ሆነ፡፡ ሁለተኛዋን የግጥም መድበል “ውበትና ሕይወት” (ወፌ ቆመች - ቅጽ -2) የታተመችው በ1998 ዓ.ም  ነበር፡፡ ይህም ማለት በ1ኛዋ እና በ2ኛዋ የግጥም መድበል መካከል የ15 ዓመት ግድም ክፍተት አለ ማለት ነው፡፡ በስሎ፣ ሰክኖ፣ ነትሮ ራሱን የገለጠባት መድብል ሆነች፡፡

ከሌላ 17 ዓመት ቆይታ በኋላ 3ኛ ቅጹን ለማሳተም ኮምተራይዝ እያደረገ ይገኛል፡፡ አልፎ አልፎ በፌስ ቡክ በሚለቃቸው ያልታተሙ ግጥሞቹ፣ የወፌ ቆመች 3ኛ ቅጽ አቀማመር ካለፉት ሁለቱ ለየት እንደሚል ያመላክታሉ፡፡ ለኅትመት ጉድ ጉድ ማለቱን የሰማ አንድ ወዳጁ ‹‹የማያርጠው ገጣሚ›› በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ሳያሳትማት ዘገየች፤  ‹‹እየታመምን እንጽፋለን፣ እየጻፍን እንታመማለን›› ይላል በራሱ ሲቀልድ፡፡ ከህመሙ በኋላ እንኳን አራት መጽሐፎች ታትመውለታል፡፡
 
ስለ ግጥሞቹ ውበትና  ለዛ፣ ይዘትና ቅርጽ አብዝተው ከጻፉት መካከል፡- አቶ ዘሪሁን አስፋው (በሥነ ጽሑፍ መሠረታውያን መጽሐፉ)፣ እንዲሁም ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገበየሁ (በሥነ ግጥም ማኑዋል መጽሐፉ)  ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ሁለቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ናቸው፤ (ብርሃኑ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ያስታውሷል)፡፡ በህትመትሚዲያው ደጋግመው ከጻፉት መካከል ደግሞ፡- ደረጀ በላይነህ፣ ተሻገር ሺፈራው (ዶ/ር) እንዲሁም ወጣቱ ገጣሚ መዘክር ግርማ ይገኙባቸዋል፡፡  ከሁሉም በላይ ሥራዎቹን ተመርኩዘው የመመረቂያ ጽሑፎቻቸውን የጻፉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች 15 ያህል እንደሆኑ አንድ ወዳጁ ለወንድዬ ነግሮታል፡፡

ታዲያ ምን ያደርጋል፤ ገጣሚውና ሐያሲው ደረጀ በላይነህ ‹‹ዓይናፋሩ ገጣሚ›› ሲል እንደ ገለጸው፣ በእርሱ ዙሪያ የተጻፉትን የትውልድ ቅርሶች ቢያንስ ለልጆቹ እንኳ ሲል ያሰባስባቸው ዘንድ ጥረት አላደረገም፡፡ ይህ ልክ ያለፈ ትህትናው (Humility)፣ ምናልባት ልክ ያለፈ ድካሙ  ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጋባዡ ብዙ ቢሆንም፣ በመድረክ፣ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ . . . ትዕይንታት አይሳተፍም፡፡ ከተሳተፈም በጥንቃቄ መርጦ ነው፡፡ ውካታና ሆያ-ሆዬ አይወድም፡፡---“
***

(ከላይ የቀረበው ታሪክ፣ ደራሲና ገጣሚ ወንድዬ አሊ በህይወት ሳለ፣ የዝነኞችንና የታዋቂ የጥበብ ሰዎችን የህይወት ታሪክ በመሰብሰብና በመሰነድ ከሚታወቀው “ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን” ድረገጽ  የተቀነጨበ ሲሆን፤ ደራሲና ገጣሚ ወንድዬ ዓሊ በተለይ በግጥሞቹ በኩል፣ የአዲስ አድማስ ቤተኛ እንደነበር ለማስታወስ እንሻለን፡፡ በርካታ ግጥሞቹ በጋዜጣው ላይ ታትሞለታል፡፡ ከደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ ጋር ያደረገው ቃለምልልስም፣ በሁለት ክፍል ለንባብ በቅቶለታል፡፡ የዝግጅት ክፍሉ ሰሞኑን በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት በተለየው አንጋፋው የጥበብ ሰው ወንድዬ ዓሊ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ፤በተለይ ለቤተሰቦቹ፣ ለቅርብ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡ ወንድዬ አሊን  በየጊዜው በጥበብ ሥራዎቹ እየዘከርነው እንቀጥላለን፡፡)
***
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጥሪ፡-
 ከደራሲና ገጣሚ ወንድዬ ዓሊ ጋር በተያያዘ ትዝታችሁን፣ የምታውቁትንና በስራዎቹ ላይ የተጻፉ አስተያየቶችን ለምትልኩልን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ቅድሚያ ሰጥተን እንደምናስተናግደው ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

 

 

Read 546 times