Saturday, 10 February 2024 10:00

ከሩጫ ባሻገር ለዝላይና ውርወራ ስፖርቶች ትኩረት ያስፈልጋል

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(2 votes)

ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ለማፍራት ቢቻልም ብዙ አልተሰራበትም

ግሩም ሰይፉ


በ53ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ1100 በላይ አትሌቶች ተሳትፈዋል። በሁለቱም ፆታዎች በተመዘገበ አጠቃላይ ውጤት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 360 ነጥብ በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን

መቻል  በ253 ነጥብ እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ216 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ላይ በረጅም ርቀት ሩጫ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ አገራት አንዷ ናት። በአጭር ርቀት ሩጫዎች፤ የሜዳ ተግባራት በሆኑት የዝላይና ውርወራ ውድድሮች ግን በጣም ወደኋላ

ቀርታለች። በአህጉራዊና ዓለምአቀፍ መድረኮች ውጤታማ ለመሆን ይቅርና በቂ ተሳትፎ ለማግኘትም አስቸጋሪ የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ባለፈው ሰሞን በተካሄደው 53ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ

ለመታዘብ የተቻለዉም ይህን የሚያስቆጭ ሁኔታ ነው። በሻምፒዮናው የሚሳተፉ ክልሎች፤ ክለቦችና የማሰልጠኛ ተቋማት  ለዝላይና ለውርወራ ስፖርቶች በቂ ትኩረት አለማድረጋቸው ይስተዋላል። በውድድሮቹ ላይ

ብቁ አትሌት መልምለውና ዝግጅት አድርገው የሚሳተፉ አይመስልም። በተወዳዳሪዎቹ መካከል የሚታየው ቀዝቃዛ ፉክክር ሲሆን ተወዳዳሪዎችም  በአሰለጣጠን፣ በልምምድና ቴክኒክ ስራዎች ላይ ገና ብዙ መስራት

እንደሚኖርባቸው መገንዘብ ይቻላል ። በስፖርት አካዳሚው ለሜዳ ተግባራቱ የተተከሉት መወዳደርያዎችም እያረጁ መጥተዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብ አሎሎ ወርዋሪ ነነዌ ጊንዳባ በ53ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አስደናቂ ውጤት ካስመዘገቡ አትሌቶች መካከል ይገኝበታል፡፡ በሻምፒዮናው ላይ በአሎሎ ውርወራ ከ40 ዓመታት

በላይ የቆየን የኢትዮጵያን ሪከርድ ለማሻሻል በቅቷል፡፡ ነነዌ ወደ አሎሎ ውርወራ ስፖርት  በቅርብ አመት መግባቱን ይናገራል። ባለፈው ሰሞን ካስመዘገበው ውጤት በኋላ ዋና ዓለማው በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ

ውድድሮች አገሩን መወከል እንደሆነ አስታውቋል፡፡ በአሎሎ ውርወራ ከ40 ዓመታት በፊት የተመዘገበው ሪከርድ 15.98 ሜትር ነበር። ነነዌ በበ16 ሴሜትሮች በማሻሻል በአሎሎ ውረወራ አዲሱ የኢትዮጵያን

ሪከርድ በ16.94 ሜትር ሆኗል ለመያዝ በቅቷል።
ነነዌ ለስፖርት አድማስ እንደተናገረው በሻምፒዮናው ላይ መቻልን ወክሎ የተሳተፈው እንደወታደራዊ ግዳጅ   ነው። ያስመዘገበው ውጤትም ለሰራዊቱ ሞራል የሚሰጥ ይሆናልም ብሏል።  መቻል ስፖርት ክለብ  

በሁሉም አይነት የስፖርት ውድድሮች ሻምፒዮናውን በመሳተፍ ተምሳሌት እንደሚሆንም አስረድቷል። በኢትዮጵያ ስፖርት ከአጭር ርቀት ሩጫ ጀምሮ በውርወራና ዝላይ ስፖርቶች ላይ በበቂ ደረጃ አለመሠራቱን

የገለፀው ነነዌ፤ ክልለሎች፤ ክለቦችና የማሰልጠኛ ተቋማት ከሩጫ ውጭ ላሉት ስፖርቶች ትኩረት አለመስጠታቸውን እንደ ክፍተት ቆጥሮታል፡፡ ለዝላይና ውርወራ ስፖርት ስልጠናና ዝግጅት የሚያስፈልጉ ጂሞችና እና

የስፖርት ቁሶች ክለቡ መቻል ማሟላቱን በምስጋና ያነሳው አሎሎ ወርዋሪው፤ በቀጣይ ጠንክሮ በመስራት በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ባንዲራውን ወክሎ ለመሰለፍ ማቀዱን ይናገራል፡፡ በአትሌቲክስ ፌደሬሽን

በኩል ለስፖርቶቹ በቂ ትኩረት እንዲሰጥ ግን አሳስቧል። ስፖርተኞች በርትተው እንዲሰሩ ፌዴሬሽኑ በጥናትና ምርምር  መንቀሳቀስ አለበት ብሏል፡፡ በሻምፒዮናው ላይ በዝላይና ውርወራ ውድድሮች የሚደረገው

ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበትም ተናግሯል። ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ዓመታዊ ውድድር መኖሩ ስፖርተኞችን ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያደርግና ውጤታቸውንም በማሻሻል ከአገር ውጭ የሚደረጉ ውድድሮችን

ለመሳተፍ የሚያበቃቸው ይሆናል ብሏል፡፡ በስፖርቱ ላይ የሚሰሩ አትሌቶችና አሰልጣኞችን ብቃት ለማሳደግ ውጤታማ ወደ ሆኑ አገራት በመጓዝ ተመክሮ መውሰድን እንደአማራጭ ማየት እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ ነነዌ

ጊንዳባ ከ40 ዓመታት በላይ የቆየውን ብሄራዊ ክብረወሰን ካሻሻለ በኋላ ዋና ትኩረቱ ወደ አፍሪካና የዓለም ሪከርድ የሚወስደውን ስልጠና እና ልምምድ መስራት እንደሆነ ለስፖርት አድማስ ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ወጣቶች የስፖርት አካዳሚ አሰልጣኝ የሆነው ተስፋዬ ለማም የዝላይና ውርወራ ስፖርቶች እንደሩጫ ስፖርት የሚገባቸውን በቂ ትኩረት አለማግኘታቸውን ይናገራል።   በዝላይና ውርወራ ስፖርቶች ላይ

የስፖርት መሰረተ ልማቶችና መወዳደርያ ቁሶች ተሟልተው አይገኙም። ዘመናዊና ወቅቱን የጠበቀ እውቀት ያላቸው አሰልጣኞች በብዛት አለመኖራቸውም ሌላው ሁኔታ ሲሆን የብቃት መለኪያ ውድድሮች በበቂ ሁኔታ

አለመደረጋቸው ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችን የማግኘቱን እድል አሳጥቷል በማለት አሰልጣኝ ተስፋዬ ለስፖርት አድማስ አብራርቷል፡፡ ወጣቶች  በሜዳ ላይ ስፖርቶች ከመስራት ይልቅ በቶሎ ተጠቃሚ በሚያደርጓቸው

የሩጫ ውድድሮች ላይ ማተኮራቸውን በመጥቀስም በዝላይና ውርወራ በየጊዜው አዳዲስ አትሌቶች የሚወጡበትን ሂደት እንዳጓተተው አመልክቷል። በሜዳ ላይ ስፖርቶች ብቁ አሰልጣኞችን በየክልሉ እና በየክለቡ

በብዛት ማሰራት ፈጣን ለውጥ ሊያመጣ ይችላ ብሎ የመፍትሄ ሐሳብ አቅርቧል። በስልጠናው ላይ አተኩሮ በመሥራት በአጭር ጊዜ ውስጥ በውርወራም በዝላይም ምርጥ ስፖርተኞችን ለማግኘት የሚቸግር

አይደለም ነው የሚለው - አሰልጣኝ ተስፋዬ ለማ፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በስፖርት አካዳሚው  በምርኩዝ ዝላይ ሴት ስፖርተኞችን ማሰልጠን ተጀምሮ ከ10 በላይ ምርኩዝ ዘላዮችን ለውድድር ለማብቃት ተችሏል፡፡ በወንዶች በኩልም በምርኩዝ ዝላይ ከ20

ዓመታት በላይ ልምድ መኖሩን የገለጸው አሰልጣኝ ተስፋዬ፤ ከ15 በላይ ምርኩዝ ዘላዮችን መኖራቸውንም ጠቁሟል፡፡ የስፖርት አካዳሚውን በመወከል በሻምፒዮናው ላይ የተሳተፉት በሴቶች ምድብ የበላይነት

ተቆጣጥረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት 2.45 በመዝለል ሻምፒዮን የሆነችው አትሌት ጫልቱ ኢታፋ ዘንድሮ ደግሞ 2.75 ሜትር በመዝለል ሻምፒዮናነቷን አስጠብቃለች፡፡ ጫልቱ ለስፖርት አድማስ በሰጠችው አስተያየት

የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ የምርኩዝ ዝላይ ስፖርተኞችን በማየት ወደ ስፖርቱ መሳቧን ገልፃ፤ ለስፖርቱ ያላትን ፍቅር በቲቪ ክትትል ማሳደጓንና አሁን በአካዳሚው ባገኘችው አሰልጣኝ ጥሩ ውጤት ማምጣት መጀመሯን

ተናግራለች፡፡እንደ አሰልጣኝ ተስፋዬ ለማ አመለካከት ኢትዮጵያ ውስጥ ከረጅም ርቀት ባሻገር በአጭር ርቀት የሩጫ ውድድሮችና በምርኩዝ ዝላይ አገራቸውን የሚያስተዋውቁ አትሌቶች ማፍራት ይቻላል፡፡ ይህን

ለማሳካት ግን ስፖርተኞች ልምምድ የሚሰሩባቸውን ዘመናዊ ጂሞች መገንባት፤ ከልጆቹ አቅም ጋር የሚሄዱ የስፖርት ቁሶችን ማሟላት ያስፈልጋል። በሩጫ ብቻ ሳይሆን በሜዳ ስፖርቶች ፕሮፌሽናል አትሌቶችን

ለማፍራት ክለቦች፤ ክልሎችና ማሰልጠኛ ተቋማት መሰራታቸውም ወሳኝ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በዝላይና የውርወራ ስፖርቶች ኢትዮጵያ ያለችበትን ርቀት ለመገንዘብ በየስፖርቱ የተመዘገቡ የአፍሪካና የዓለም ሪከርዶችን ከኢትዮጵያ ሪከርዶች ጋር ማነፃፀር ይቻላል። በከፍታ ዝላይ  በወንዶች እስከ 50 ሴሜ

በሴቶች እስከ 1ሜትር ፤ በረጅም  ዝላይ በሁለቱም ፆታዎች እስከ 1.50 ሜ ፤ በምርኩዝ ዝላይ እስከ 1.60 ሜ  በወንዶችእስከ 2 ሜትር በሴቶች እንዲሁም  በስሉዝ ዝላይ በሁለቱም ፆታዎች ያለው

ልኬት ከ3-5 ሜትር ዝቅ  ያሉ ክብረወሰኖችኢትዮጵያ ላይ ተመዝግበዋል። በውርወራ ስፖርቶችም ያለው የሪከርድ ልዮነት በጣም ሰፊ ርቀት መኖሩን ያመለክታል።
 በአሎሎ ውርወራ ከ5-7 ሜትር፤ በዲስከስ ከ20-30 ሜትር፤ በጦር ውርወራ ከ30-35 ሜትር እንዲሁም በመዶሻ ውርወራ እስከ 35 ሜትር ኢትዮጵያውያን ከአፍሪካና ከዓለም ሪከርዶች ርቀው ይገኛሉ።
አትሌቶች ፤ አሰልጣኞችና ሌሎች የአትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት ከሚሰጡት አስተያየት መረዳት የሚቻለው
ኢትዮጵያ በየውድድር አይነቶቹ  ከሌሎች አገሮች ጋር ለመፎካከር የሚያስችል አቅም ላይ አልደረሰችም።
 በዘርፉ ትኩረት በማድረግና በረጅም ጊዜ እቅድ በመሥራት ብቁ አትሌቶችን የማፍራት እድል ቢኖርም በአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኦሎምፒክ ኮሚቴ እስከአሁን ለውድድሮቹ በቂ ትኩረት አልተሰጣቸውም። ለስልጠናና

ለውድድር የሚያስፈልጉ የስፖርት ቁሳቁሶች በበቂ ሁኔታ ተሟልተው አይገኙም። በዓመት ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች በቂ አይደሉም።
  የአሰልጣኝና የተወዳዳሪዎችን ሞራል የሚገነቡ በስፖርቱ ዙርያ ያላቸውን እውቀትና አቅም የሚያሳድጉ ተከታታይ ስልጠናዎች ተደርገውም አያውቁም።
በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት  የሜዳ ተግባራት ላይ እምቅ ችሎታ ያላቸውን ስፖርተኞችን ለማገዝ የተሰሩ ነገሮች አሉ።
ስፖርተኞችን ጥናትና ምርምር አድርጎ በአገር አቀፍ ደረጃ በመልመል  ብቃታቸውን ለማጎልበትና ልምዳቸውን ለማጠናከር በሜዳ ስፖርቶች ውጤታማ ወደሆኑ አገራት በመላክ ለማሰልጠን ሞክረዋል። በስፖርት አይነቶቹ

ብቁ ከሆኑ አገራት አሰልጣኞችና ባለሙያዎችን ቀጥሮ በማስመጣትም ተንቀሳቅሰዋል።
ታዋቂ የስፖርት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በዝላይና ውርወራ ስፖርቶች በተክለ ሰውነትና በጉልበት ጥሩ አቅም ያላቸው አትሌቶች እንዳሉ ይገልፃሉ።
ስፖርተኞቹን በተገቢው መልምሎ የሚጎላቸውን የቴክኒክ ችግር ሳይንሳዊ በሆነ ስልጠና በመሙላት መስራት ግን  ብዙ  እንደሚቀረው ጠቅሰዋል።በየውድድር አይነቶቹ ውጤታማ ለመሆን በአሰለጣጠን፣ በልምምድና

ቴክኒክ ስራዎች በመለወጥ ጊዜው ከደረሰበት ሁኔታ አኳያ ለመስራት ማቀድም ያስፈልጋል።  ስፖርቱን በሚመሩ ተቋማት፤ ክልሎች ፤ ክለቦችና የማሰልጠኛ ተቋማት ከሩጫ ውጭ ባሉ ስፖርቶች ብቁና ፕሮፌሽናል

አትሌቶችን በማውጣት መሥራት እንደሚቻል ተገንዝበው መነሳት አለባቸው። በአሰለጣጠን በኩል ያለውን ክፈትት ለመሙላት በጋና፣ ኩባና ደቡብ አፍሪካና በሌሎች አገሮች ከሚገኙ አሰልጣኞች ጋር በመነጋገር

በኢትዮጵያ መጥተው እንዲያሰለጥኑ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች አቅማቸውን ማጎልበት የሚችሉበት ተከታታይ ስልጠና ለመስጠትም መታሰብ አለበት። የውድድር አማራጮችን ማስፋት፣

የስፖርቱን ቁሳቁሶች ማሟላትና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ማዘጋጀት ደግሞ የፌዴሬሽኑ እና የኦሎምፒክ ኮሚቴው ግንባር ቀደም ሃላፊነት ነው።


Read 465 times