Sunday, 04 February 2024 00:00

ሦስት መዓዘን

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ምዕራፍ 1
-ኪሩቤል ሳሙኤል -
የሚተነፍሰው ትንፋሽ ከዛፎቹ ቅጠሎች ጋር እየተጋጨ ደግሞ ደጋግሞ ይሰማዋል፡፡ ትንፋሹ ከአፍንጫው ሲወጣ ጥሎት ላይመለስ እየኮበለለ ነው የሚመስለው፡፡ በጣም ደክሞታል፡፡ ወደ የት እየሄደ እንደሆነ የሚያውቀው ታሪክ የለም፡፡ በዚህ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ የሚተነፍስና የሰው ፍጥረት የሆነው እሱ ብቻ ነው፡፡ እህል ባልጎበኘው ሆዱ ለግማሽ ቀን ያህል ነው በነዚህ ዛፎች መካከል መልስ ፍለጋ ሲኳትን የከረመው፡፡ ሆኖም ሁሉም ነገሮች ምንምን ብቻ ነው እያስረዱት ያሉት፡፡
ድንገት…
ካለበት አካባቢ በቅርብ ርቀት ድንገት አንድ ድምፅ ሰማ፡፡ የተቻለው ድረስ ድምፁን ወደ ሰማበት ቦታ በሀይል እየተራመደ ተመለከተ፤ ምንም ነገር የለም፡፡ አሁንም ሳያቋርጥ መራመዱን ቀጠለበት፡፡
በመንገዱም ላይ እያለ ያለምንም ተስፋ የፈጠረውን ፈጣሪውን በህሊናው ውስጥ ቅርፅ አበጅቶለት፣ ሊፀልይለትና አንዳች ተዓምር እንዲሰራለት ሊለምነው ተመኘ፤ ሆኖም ምኞቱ ሙሉ አልነበረም፡፡ ምኞቱ ውስጥ እውቀት የለበትም፣ ሀሳብ የለበትም፤ ስሜት የለበትም፡፡ ድካምን ለመካድ ከሚደረግ የአዕምሮ ውስጥ ጨዋታ ውጭ ይህ ሰው አላማ ብሎ ሊያስቀምጠው የሚችለው የህይወት ስርዓት አብሮት የለም፡፡ ብቻውን ነው፡፡
ሆኖም ይህ የተዘበራረቀ ስሜት ብዙም ሳይቆይ ሰብሳቢ የህይወት ገጠመኝ ይዞለት መጣ፡፡ ከርቀት አንዲት ደሳሳ ቤት ከወደ ፊቷ አጎንብሳ በዛፎች መካከል ተሰፍታ ተመለከተ፡፡ ማመን አቃተው፡፡ እንደምንም እየተንደረደረ ሄዶ የቤቱ በር ጋር ቆመ፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገባው፡፡ ዝም ብሎ እንዳይገባ እሱ ራሱ ያልተረዳው ህግ መጥቶ ድፍረቱ ላይ ተከመረበት፡፡ እዛው በሩ ላይ ተገትሮ አንድ እሱን የመሰለ ፍጥረት ከቤቱ ውስጥ እስኪወጣ ድረስ ቆሞ እንዳይጠብቅ፣ በምንም አይነት ታሪክ ትዕግስት መስጠት የማይችለው ረሀብ በሆዱ ውስጥ የአመፃ ድምፁን እያስተጋባበት ነበር፡፡ ህይወት በሁለት የተስፋ ገመዶች ተወጥራ ይህን ሰው የተምታታ ምስሎችን ብቻ በጭንቅላቱ እንዲፈለፍል እያስገደዱት ነው፡፡
አልቻለም፡፡ ረሀቡን አልቻለውም፡፡ ወደቤቱ ተጠግቶ የጨለማ ጥቀርሻ የተቀባውን የቆርቆሮ በር ዘመም አድርጎ ከፈተው፡፡ ቅጥሩ የተጣሰበት ይመስል በቤቱ ውስጥ ተደብቆ ተቀምጦ የነበረው የጨለማ ፀዳል ሲረበሽ ታወቀው፡፡ ካጠገቡ የመብራት ማብሪያና ማጥፊያ አግኝቶ መብራቱን ተጫነው፡፡ ክፍሉ ላይ ብርሀን ሰለጠነበት፡፡ የብርሀኑ ሰበብ የሆነው አምፖል ግን የት ጋ እንዳለ ለማየት አልቻለም፡፡
ክፍሉ ባዶ አይደለም፡፡ በውስጡ አንድ በላዩ ላይ በሸረሪት ድር ተጀቡኖ የመጻሕፍት ክምር ያለበት ጠረጴዛ፣  የእንጨት ወንበር፣ በግድግዳው ላይ የተለያዩ የተለጣጠፉ ፎቶዎች፣ በፎቶዎቹ ላይ የአቧራ ቂጣ ተለጥፎባቸው፣ ከቤቱ ሰጎጥ ስር ደግሞ አንድ ተለቅ ያለ በእንጨት የተበጀ ሳጥን ይዟል፡፡
ይህ ሰው በቅድሚያ ትኩረቱን የት ላይ ማድረግ እንዳለበት በቆመበት ትንሽ ካሰላሰለ በኋላ በቅድሚያ በግድግዳው ላይ ወዳለው የፎቶግራፎች ሰልፍ ጋር ሄዶ ቆመ፡፡ በላያቸው ላይ ያለውን ቆሻሻ በእጁ ካፀዳ በኋላ በተቻለው ጥረት አጥርቶ ለመመልከት ቀረብ ብሎ መመልከት ጀመረ፡፡ በመጀመሪያ የተገናኘው ከራሱ ፎቶ ጋር ነው፡፡ ግራ ገባው፡፡ እንዴት ሆኖ የእሱ ፎቶ እዚህ ለምድር የተሰወረ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ሊገኝ እንደቻለ ማመን አቃተው፡፡ በፍጥነት ሌሎች ፎቶዎችን እያፀዳ መመልከት ውስጥ ገባ…የራሱ ብዙ ፎቶዎች፣ ከአንዲት ሴት ጋርና አብሯቸው ደግሞ አንድ ወንድ ህፃን ልጅ ይዘው፣ በሌላ ቦታም የራሱ ፎቶ የወታደር ልብስ ለብሶ ከሌላ ሴት ጋር የተነሳው፣ በሌላ ቦታ መጀመሪያ ያየው ህፃን ልጅ አደግ ብሎ ብቻቸውን የተነሱት ፎቶና በከፊልም ቢሆን ከዚህ ቀደም ያለው ህይወቱን የሚናገርበት የፎቶ ክምር ተመልክቶ ነፍሱ ደርቃ ቀረች፡፡
ብዙ ነገር ተረጋግቶ ማሰብ ይችል ነበር፡፡ ሆኖም አሁንም ሊመለከታቸው የሚገቡ የቤት እቃዎች ባሉበት ሆነው እየጠበቁት እንደሆነ ሲረዳ፣ፊቱን አዙሮ መጻሕፍቶቹ ላይ ትኩረቱን አደረገ፡፡ በመጻሕፍቱ ላይ ያለውን የሸሪት ድር አንስቶ መመልከት ውስጥ ገባ፡፡ አብዛኞቹ በእጅ ፅሁፍ የተፃፉ ድርሳናት ይታያሉ፡፡ ከዛም ባለፈ የብራና ጥቅሎችም አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡
ድርሳናቱንና ጥቅሎቹን ለማንበብ ጊዜ አልሰጠም፡፡ ዞሮ ወደ እንጨት ሳጥኑ ቀርቦ ለመክፈት ሙከራ አደረገ፡፡ ሳጥኑ ተለቅ ባለ ቁልፍ የተከረቸመ ነው፡፡ አሁኑኑ ሳጥኑን ከፍቶ ማየት እንዳለበት ተገነዘበ፡፡ ጎጆውን ለቆ ወጥቶ ጋኑን የሚሰብርበትን ድንጋይ ማፈላለግ ጀመረ፡፡ ፍለጋ ላይም እያለ ጥቃቅን በትውስታ ውስጥ የሚንፀባረቁ ምስሎች ያለ እሱ ፈቃድ ድንገት እየመጡ ብልጭ ድርግም ይሉበታል፡፡
ከግድግዳው ላይ ተለጥፎ ያየው ህፃን ልጅ መልክ ድንገት ብልጭ ብሎ ይታየዋል…አብሮት ሲስቅ…አብሮት ሲሮጥ…አብሮት ከሶፋ ላይ ተጋድመው መፅሐፍ ሲያነብለት….እነዚህ ሶስት ምስሎች ልክ እንደ ልብስ መስፊያ የሲንጀር ባህሪይ እየተመላለሱ ጭንቅላቱን ይተከትኩት ጀመር፡፡ ሆኖም ምንም ሊያደርገው የሚችለው ትዝታ አይደለም፡፡ የራሱ ልጅ ይሁን የሌላ የሚያውቀው እውቀት ባዶ ነው፡፡ ሆኖም ከጭንቅላቱ ስውር ስፍራ ውስጥ አስቀምጦት እንደነበር ግን መጠርጠር ውስጥ ገብቷል፡፡
ተለቅ ያለ ድንጋይ አጋጠመው፡፡
በፍጥነት ወደ ሳጥኑ ጎጆው አመራ፡፡ በጎጆው ውስጥ ሰርጎ በጋኑ ላይ ድንጋዩን ያመላልስበት ጀመር፡፡ በሳጥኑ ውስጥ ምግብ ቢያገኝ በወደደ ነበር፡፡ የራበው ሰው የሚያደምጠው በጆሮው ነው እንዲል ካልሂል ጅብራን፣ ይህም ሰው ቀስ እያለ እያጨለመው ያለውን ድካሙን የሚያሸንፍበትን መሳሪያ ብቻ ነው የሚፈልገው፡፡ ምግብ፡፡
ከብዙ ድብደባ በኋላ ጋኑ እጅ ሰጥቶ ተከፈተ፡፡ ቀስ ብሎ ከፈተው፡፡ ባየው ነገር በጣም ደንግጦ በፍጥነት ወደ ኋላው አፈገፈገ፡፡ ክፍሉ እጅግ ነፍስን በሚያጎመዝዝ ሽታ ታወደ፡፡ ደንግጦ ለጥቂት ደቂቃዎች ከወደቀበት ሆኖ በሳጥኑ ላይ ሲያፈጥበት ከቆየ በኋላ፣ያየው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ በቀስታ መልሶ ተጠጋው፡፡ ደግሞም ሲመለከተው ነገርየው ራሱ ነው፡፡
ነገርየው… በሳጥኑ ውስጥ እየተመለከተው ያለው  ራሱን ነው፤ ራቁቱን እጥፍጥፍ ብሎ ተኝቶ በመበስበስ ላይ ያለውን የራሱን አስክሬን ነው ያየው….
      

"ኤልዛቤል?"
ጥያቄው ከእንቅልፏ አባነናት፡፡
"አቤት…"
"የምጠይቅሽን ጥያቄ በጥንቃቄ ለመመለስ ሞክሪ? አለበለዚያ ለሚደርስብሽ ስቃይ ተጠያቂ ማንንም እንዳታደርጊ፡፡ ሁሉም ውሳኔ ያንቺ ነው፡፡ ተግባባን?"
"አዎ…" አለች ኤልዛቤል፤ በጨርቅ የተሸፈኑት አይኖቿ ላይ የእንባ ድፍድፍ እያመረተች፡፡
"ስንት ሆናችሁ ነው ወደዚህ ቦታ የመጣችሁት?"
"አልገባኝም…እኛ እነማን ነን? "
ይህን እንደተናገረች ድንገት አንዳች የኤሌክትሪክ ንዝረት ሰውነቷን አነዘረው፡፡ በሀይል ጮኸች፡፡ አለቀሰች፡፡ ጠያቂው በተረጋጋ መንፈስ ጥያቄውን ቀጠለ፡፡
"ስንት ሆናችሁ ነው የመጣችሁት?"
ኤልዛቤል ትንፋሽ ሰብስባ ለማሰብ ሞከረች፡፡ እነዚህ ሰዎች ያለምንም ርህራሄ እያሰቃዩዋት እንደሚሰነብቱ እንዲሁ ገባት፡፡ እያሰቃያት ያለው ሰው ስለ ማን እና ስለ ምን እየጠየቃት እንደሆነ ልታውቅ አልቻለችም፡፡ አሁን ላይ ሆና ተረጋግታ አስባ ልትደርስበት የሚቻላት ታሪክ ከኋላዋ ሊታያት አይችልም፡፡ ማምለጥ ብቻ እንዳለባት ነው ህሊናዋ እየደጋገመ እየነገራት ያለው፡፡ ይህን እያሰበች ያለችበት ወቅት ላይ ድንገት የኤሌክትሪኩ ንዝረት መጥቶ አንድ ጊዜ በሀይል አስጮሀት፡፡
"እሺ ታገሰኝ…" አለችው ንዴትና እልህ በተቀላቀለበት አንደበት፡፡
"ስንት ሆናችሁ ነው የመጣችሁት?" ጠያቂው ድምፅ ላይ መጠነኛ የድል አድራጊነት ስሜት ይደመጥበት ጀምሯል፡፡
"አራት ነን…" መለሰች ኤልዛቤል፡፡
"ለምንድን ነው የመጣችሁት? አላማችሁ ምን ነበር?"
"መረጃ ይዞ ለመውጣት ብቻ ነው የመጣነው፡፡" ኤልዛቤል በጥንቃቄ ጥያቄዎቹን ማድመጥ እንዳለባት እየገባት ነው፡፡ ጥያቄው እስካለ ድረስ መልስ ስፍራዋን ፈልጋ መክተሟ ግድ ነው፡፡
"ምን አይነት መረጃ ነው መሰብሰብ የፈለጋችሁት?"
"የማህበራችሁን አጠቃላይ አላማ…ከተቻለ ሙሉ ማኒፌስቶዋችሁን ይዘን ለመውጣት ነው የተላክነው፡፡"
ድንገት ፀጥታ ሰፈነ፡፡ በድን ዝምታ ውስጥ ሆና ኤልዛቤል የጠያቂዋን ትንፋሽ ለማድመጥ ሞከረች፡፡ ጠያቂው በፍጥነት በመተንፈስ ላይ ነው፡፡ ትልቅ ሀላፊነት ይዞ ወደ እሷ እንደመጣ ገባት፡፡ የሚፈልገውን መረጃ ካላገኘ አለቃው በሰላም እንደማይቀበለው አውቃለች፡፡ ስለዚህ ከራሷ ውጭ የዚህንም ሰው ህይወት መታደግ እንዳለባት ነው እየገባት ያለው፡፡ ፍርሀቱን መጠቀም እንዳለባት ገባት፣ ስጋቱ ድረስ ሄዳ የልቡን አድምጣለት ከአለቃው ይልቅ እሷ ደህነቱ ሆና የመገኘት ሀላፊነት አለባት፡፡ በዛ ውስጥ ነው መዳን የምትችለው፡፡ በንቃት ውስጥ ሆና የጠያቂውን ቃላት መጠበቅ ጀመረች፡፡
"እንዴት እንደተያዥስ ታስታውሻለሽ?"
"ምንም አይነት ትውስታ የለኝም፡፡ ሰውነቴ በጣም ደክሟል፡፡ በትክክል ላስብ አልችልም፡፡ በዚህ ስቃይ ውስጥ ማንስ ትላንቱን ማስታወስ ይችላል፡፡ እንደምታየኝ ነኝ፡፡ አቅም የለኝም፡፡ እንደፈለክ ብታደርገኝ ራሴን የምከላከልበት መንገድ የለም…እንደፈለክ ልታደርገኝ ትችላለህ…እሱን ደግሞ ጠንቅቀህ ታውቀዋለህ፡፡ እንደፈለክ…."
ይህን ተናግራ ፀጥ አለች፡፡ የልብ ትርታው ጋር የነፍሷን ጆሮዎች ላከቻቸው፡፡ በሀይል እየደለቁ ናቸው፡፡ ምራቁን ሲውጥ እያንዳንዱን የጉሮሮውን ክርክር በማድመጥ ደረሰችበት፡፡ "እንደፈለክ ማድረግ ትችላለህ…" እያለች ደጋግማ ቃላቶቹን የተጠቀመችው የወሲብ ከፍታውን ለማናር ብቻ ነበር፡፡ ለዚህ ሰው ጉልበትና ወንድነቱን ሰጥታዋለች፡፡ ከዚህች ደቂቃ አንስቶ እስረኛው ሳትሆን የወሲብ መገልገያ ቁሱ እንደሆነች አድርጎ ማሰብ እንደሚጀምር ታውቃለች፡፡ አውቃ ነው ይህን ያደረገችው፡፡ ጠያቂው ጉሮሮውን ጠራርጎ ጠየቃት…
"እስካሁን ለምን እንዳልተገደልሽ ታውቂያለሽ?"
"አዎ…በምሰራበት የስለላ ድርጅት ውስጥ ቁልፍ ሰው ከሚባሉት ሰዎች ውስጥ ስለሆንኩ፣ የእውቀት ስፋቴ ከየትኛውም የድርጅታችን ሰራተኞች በላይ ከፍ ስለሚያደርገኝ እና ተፈላጊ ስላደረገኝ፣ ቆንጆ ስለሆንኩ፣ ያየኝ በሙሉ ስለሚመኘኝ….ለዛ ይመስለኛል ሞት ወዳጆቼን መቀማት ችሎ የኔ ደጅ ጋር መድረስ ያቃተው፣ የሚወዱኝም የሚጠሉኝም በእኩል አይን ነው የሚያዩኝ…ሁሉም የሚወዱኝ የሚያከብሩኝ ሰው ነኝ፡፡ ያልሞትኩት ኤልዛቤል ስለሆንኩ ነው፡፡"
 ያ ፀጥታ ተመልሶ መጣ፡፡ የጠያቂው ነፍስ ጋር ቀረብ ብላ ልታደምጥ ሞከረች፡፡ ትንፋሹ በሀይል ጨምሯል፡፡ መረቧ ውስጥ እያስገባችው እንደሆነ እየተረዳች ነው፡፡ ጊዜ ማባከን አልፈለገችም፡፡
"ይቅርታ…እኔን ከመግደልህ በፊት አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅህ?"
ጠያቂው ጥቂት ካንገራገረ በኋላ ፈቀደላት፡፡
"ትኩር ብለህ ስታየኝ አምራለሁ? ሌሎች ሰዎች ታምሪያለሽ እያሉ ያቆዩኝ ዘመኔን ከመርገሜ በፊት ይሄን ብቻ መልስልኝ….አምራለሁ…?"
ጠያቂው በቀስታ ሲጠጋት ተሰማት፡፡ ወደ ፊቷ እየተጠጋ መሆኑን ከርቀት እየጋለ በሚመጣው እስትንፋሹ ገባት፡፡ አንገቷ ስር ገብቶ ሲተነፍስ ተሰማት፡፡ ጊዜ ማባከን አልፈለገችም፤ አንገቷን በሀይል ወደ ጎን ስባ በሀይል መንጋጋው ስር በጭንቅላቷ አጎነችው፡፡ እዛው ታፋዋ ስር ወደቀላት፡፡
ኤልዛቤል…
ለመኖር ያላት እድል በደቂቃዎች ውስጥ እንደሚወሰን ደርሳበታለች፡፡
ነፃነቷ ታፋዋ ላይ ተጋድሞ እየጠበቃት ነው፡፡
                                     
የዘካሪያስ አይኖች ተገለጡ፡፡ አለመሞቱን ያወቀው ያኔ ነው፡፡ ተበሳጨ፡፡ እንዴት አድርጎ እንደዳነ ለማስታወስ ጊዜ አላገኘም፡፡ የአንዲት ሴት ድምፅ ሊሰደድ ያለው ሀሳቡን ስባ አሁኑ ላይ መለሰበት፡፡
"ወንድም ዘካሪያስ ….እንኳን ወደ ሰው ልጆች መንደር በሰላም ተመለስክ?"
የልጅቷን መልክ ለማየት ሲዞር አንገቱ ላይ የተሰማው ህመም አላዞር አለው፡፡ ልጅቱ ይህን ተመልክታ አጠገቡ መጥታ ቆመች፡፡ ዘካሪያስ አተኩሮ ተመለከታት፡፡ ያውቃታል፡፡ አዘውትሮ ቡናውን የሚጠጣበት ካፌ ውስጥ አስተናጋጅ ሆና ያውቃታል፡፡
"አስታወስከኝ?" አለችው ስስ ፈገግታ ለአይኑ እየሰጠችው፡፡
"አውቅሻለሁ…የት ነኝ ያለሁት?"
"ለጊዜው ምንም አይነት እውቀት ባልሰጥህ ደስ ይለኛል፡፡"
"ለምን አዳንሺኝ…ማነሽ አንቺ?"
"ራስህን ነው ያዳንከው ወንድም ዘካሪያስ፡፡ እኔ ምንም ያደረኩልህ ነገር የለም፡፡ ለማንኛውም አሁን ላይ በጣም የምትፈለግ ሰው ነህ፡፡ በኔም ሆነ በብዙዎች፡፡ በጣም የሚያስቅህ ነገር ምን ልሁን ብዬ እንደሆነ እንጃ በሁለት የተለያዩ ግለሰቦች ነው ተቀጥሬ ስከታተልህ የከረምኩት፡፡ አሁን ግን ግራ የገባኝ ለየትኛቸው አሳልፌ ልስጥህ የሚለው ሀሳብ ነው፡፡ እ….ምን ይሻላል ትላለህ?"
ዘካሪያስ በፍርሀት ነው እያያት ያለው፡፡ በመሰረታዊነት ለአመታት እያፈላለገው ያለ ሰው እንዳለ ያውቃል፡፡ ሆኖም ስለ ሁለተኛው ሰው ደግሞ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡
"ስለ ምን እያወራሽ እንደሆነ ላውቅ አልቻልኩም፡፡ እኔ ሰላማዊ ሰው ነኝ፡፡ በማንም ላይ ጉዳት አድርሼ አላውቅም፡፡ እስከዛሬም ባለው ህይወቴ አንድም ጠላት ተነስቶብኝ አያውቅም…."
የለበጣ ሳቅ እየሳቀች አጠገቡ ተጠግታው ተቀመጠች፡፡
"እርግጠኛ ነህ ዘኪ? የምሬን ነው… ስለምታወራው ነገር በጣም እርግጠኛ መሆን አለብህ፡፡ ይሄን ያልኩህ ዋነኛው ምክንያት፣ አንተን አስሼ እንዳገኝህ የሚፈልጉ ሰዎች ከለመድኩት ወጣ ባለ ከፍተኛ ገንዘብ ነው የተደራደሩኝ፡፡ እና ሳሰላስለው ይሄ ሰው ማን ቢሆን ነው በዚህን ያህል ደረጃ እየተፈለገ ያለው ብዬ ነገሮችን እንድመረምር ሆንኩኝ፡፡
ከዛም ስላንተ ማጥናት ጀመርኩኝ፡፡ በጥንታዊ የአስማት ጥበቦች ላይ እውቀት ያለህ ሰው እንደሆንክ፣ ሚስትህ እንደሞተችብህ፣ አሁን ላይ የት እንዳለች የማታውቃት አንዲት ሴት ልጅ እንዳለችህ፣ የልቤ የምትላቸውጓደኞች እንደሌሉህ፣ ያላሳተምከው ሚስጥረ ራዛኤል የሚል መፅሐፍ እንደፃፍክ፣ ከዛም ባለፈ ማንም እጅ ላይ የሌለ… የመላው ሁለንታን ሚስጥር የሚያትት…ከምድር ሆድ እቃ ውስጥ ያሉትን ማዕድናት አስሶ የሚጠቁም የብራና ጥቅል ለብቻህ ደብቀህ እንደምትኖር እና አሁን ላይ የማልገልፅልህን የህይወትህን ክፍል በደንብ አድርጌ ደረስኩበት፡፡ "
"እና ምን ውሳኔ ላይ ደረሽ?" ዘካሪያስ ረጋ ብሎ ጠየቃት፡፡
"ማን እያሳደደህ እንደሆነ እንደምታውቅ አውቃለሁ፡፡ ማወቅ የምፈልገው ግን ለምን የምትለዋን ነው፡፡ ለምንድን ነው የሚፈልጉህ…? በዚህ ሀሳብ ላይ ያንተን እውቀት ሳትዋሽ ከነገርከኝ ነፃነትህን ምናልባት ልሰጥህ እችላለሁ፡፡"
የዚያን ሰዓት ላይ ነው ዘካርያስ ከተኛበት አልጋ ጋር የጥፍንግ እንደታሰረ የተረዳው፡፡
"የምፈለገው ለእውቀቴ ነው፡፡ በሰው ልጅ አይን ታይቶ የማይተረጎም እውቀትን ከነፍሴ ከትቤ በሚስጥራዊው እውቀት ውስጥ የምመላለስ ሰው ነኝ፡፡ ህይወቴ ሚስጥር ነው፡፡ እውቀቴ ሚስጥር ነው፡፡ እምነቴ ሚስጥር ነው፡፡ እዚህ እሳቤ ድረስ እንዳስብ ያደረገኝም ሀሳብ በራሱ ሚስጥር ነው፡፡ ምንም ልነግርሽ የምችለው እውነት የለም፡፡ ለማንም አሳልፈሽ ብትሰጪኝ መልሴ ተመሳሳይ ነው፡፡ የልቤን ተረድቶ መልስ ወደሚያሻኝ ስፍራ የሚሰደኝ ሞት ነበር …እሱንም አንቺ ቀድመሽ ቀማሺኝ፡፡  ከቻልሽ መልሰሽ ግደይኝ? አሁን በጭንቅላቴ ውስጥ የከመርኩት እውቀት እያሰቃየ እንደበረዶ አሟሙቶ በስቃይ ሳይጨርሰኝ በፊት አንቺው ግደይኝ?
”ራሱን ሊገድል ከሚሻ ልብ ውስጥ ምንም አይነት ተስፋ አትፈልጊ፡፡ የምታስፈራሪኝ እየመሰለሽ ከሆነ ደግመሽ ማሰብ ይጠበቅብሻል፡፡ ብለምንሽ …ውለታ ብጠይቅሽ፣ የምጠይቅሽ አንድ ነገርን ብቻ ነው፡፡ ግደይኝ እና እኔንም ሆነ ይህችን ምስኪን ሀገር ታደጊያት፡፡ "
ልጅቷ አሁንም ፈገግ ብላ ስታየው ከቆየች በኋላ ከተቀመጠችበት አልጋ ላይ ተነስታ በጠረጴዛ ላይ ያስቀመጠችውን ስልክ አንስታ የዘካርያስን አይኖች በጥናት እያየች ደወለች፡፡ ስልኩ ተነሳ፡፡
"መምጣት ትችላላችሁ--" ይህን ተናግራ ከዘካሪያስ አይኖች ተሰወረች፡፡

Read 389 times