Tuesday, 23 January 2024 06:25

ትንሽ በጥቂቱ ስለ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ ) የማውቀውን

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ይህ ሰው ሁሌም በመረጃ አሰባሰብ፣ በዝግጅት አቀራረቡና በሌሎች ነገሮቹ  ድንቅ ከሚሉኝ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው።
 ሁለገቡ ሰው ገነነ መኩሪያ( ሊብሮ)።
 ሊብሮ የምትለውን ስያሜ ያወጣለት በአብዛኛው የእግር ኳስ አፍቃሪ በአዝናኝነቱ፣ በእግር ኳስ ወዳድነቱ የሚታወቀው የኳስ ሜዳው ሰው ሀይሌ ካሴ ነው። በወቅቱ ጊዮርጊስ ከሜታ አቦ በተጫወቱበት ጊዜ አምስት ተጫዋቾችን አልፎ ግብ  ባስቆጠረበት ጊዜ ነበር የተቀፅላው መነሻ።
ሊብሮ የተወለደው ይርጋለም ከተማ ቢሆንም፣ እድገቱ ግን ሻሸመኔ ቀበሌ 09 ነው ።
በልጅነት ወቅትም እግርኳስ ይወድ የነበረው ገነነ፤ በጊዜው በየ15 ቀኑ አዲስ አበባ  የሚመጡት የሆቴላቸው  ሾፌር አብሮቸው ያቀና ነበር፤ በነበራቸው ቆይታም ካምቦሎጆ ገብተው እግር ኳስ ተመልክተው ይመጡ  ነበር፤ በዚያ  በአፍላነት ጊዜው መሆኑ ነው።
ሌላው የሚገርመው ገኔ ሻሸመኔ ውስጥ ላለ ቡድን  ለAም፣ ለBም፣ ለCም ይጫወት ነበር፤ በአንድ ቀን ውስጥ።
የቀበሌ 09 ቡድንም በወቅቱ የአቶ ሙኩሪያ ቀበሌ ቡድን ይባል ነበር። በጊዜው እሱን ጨምሮ ስድስት ወንድሞቹ እዛ ቡድኑ ውስጥ ይጫወቱ  ነበሩ። እንደዚህ እያለ ነው ወደ እግር ኳስ ተጫዋችነት ያመራው።  ወደ ክለብ ደረጃም መጀመሪያ የመጣው በ1975 ዓ.ም አካባቢ፣ የትምህርት ቤት ውደድሮች ላይ በመታየት ከእነ ታሪኩ መንጀታ፣ አስቻለው ጋር በመሆን ነበር፤ ወደ ሜታ ቢራ የተቀላቀለው።
እዚህ ጋ  በወቅቱ በአጨዋወትና በሌሎች ተዛማጅ ነገሮች  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከአሰልጣኞች ጋር ሙግት ይገጥም ነበር። በጊዜው ሜታን ያሰለጥን ከነበረው ስዩም ጋር ይጋጩ እንደነበር ይጠቀሳል። በእግር ኳስ ተጫዋችነቱ ወቅት እረፍት ሰአቱን በማንበብ ማሰለፍ ይወድ እንደነበር አብረውት የተጫወቱት ይመሰክራሉ።
የሊብሮ ጋዜጣው መነሻ
ከዛ በፊት በበጎ ፍቃደኝነት በተለያየ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ይሰራ ነበር። ከሰራባቸው የህትመት ሚዲያ ውስጥም መረሀ ስፖርት፣ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ውስጥ ይጠቀሳል።
በመቀጠል ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ማለትም አበበ ወልደ ፃዲቅ፣ ሁሴን አብድልቀኒ ጋር በመሆን ሻምፕዮን የምትባል የስፖርት ጋዜጣ መስርተው ሰርተዋል።
በማስከተልም የራሱ የሆነችውን ሊብሮ ጋዜጣ አቋቋመ።  የዚህች ጋዜጣ አመሰራረት የሚገርም ነው፤ በተለይ በወቅቱ የነበሩቱ የቦሌ ማተሚያ ስራ አስኪያጂ አሰፋ ከበደ ሊመሰገኑበት የሚገባ ድርጊት ነው። በጊዜው ገነነ የሚያሳትምበት ገንዘብ እጥረት ያጋጥመዋል፤ ሁሉን ነገር ጨርሶ ከሰራ በኋላ ግን እጁን አጣጥፎ ከሰማይ መና አልጠበቀም፤ ወደ ቦሌ ማተሚያ ቤት  ሄዶ ስራ አስኪያጁን ያለበትን ነገር ሁሉ አስረድቶ  በእሳቸው ቀና ትብብር አማካኝነት ጋዜጣዋ ለመጀመሪያ ጊዜ  ለህትመት በቃች። በጊዜውም በጣም ተወዳጅ ጋዜጣ እንደነበረች በጊዜው የነበሩ ሰዎች ያስታውሳሉ፡፡ አብዛኛውን ትኩረት የምታደርገው የሀገር ውስጥ ዜናዎች ላይ ነበር። ለነገሩ አብዛኛዎቹ የዚያን ዘመን ጋዜጦች ትኩረታቸው የሀገር ውስጥ እንደነበር መመልከት ይቻላል።
በህትመት ግን ለ13 አመታት ከብዙ ችግሮች ጋር እየተጋፈጠች ለህዝብ ተደራሽ መሆን ችላ ነበር ። አብዛኛውን ስራ እራሱ  ገነነ ነበር የሚሰራው። የጋዜጣ ስራ ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ  የሚያውቀው ያውቀዋል።
ነገር ግን ጋዜጣዋ ከተቋረጠች በኋላ ለአጭር ጊዜ በድረ ገፁ በኩል ጀምሮት ነበር። ቢሆንም ግን  ሊዘልቅ አልቻለም።  ሁሉን ነገር ገታ አድርጎ  በመተው  በመፅሐፍና ሌሎች ተዛማጅ መስኮች ላይ በመስራት በተከታታይ በእግር ኳስ ዙሪያና ፖለቲካ ላይ የሚያጠነጥኑ መፅሀፎችን አበረከተለን፡፡  ለመጥቀስ ያህል፡-
*የአሸናፊ ግርማ የህይወት ታሪክ፤ ከአሸዋ ሜዳ እስከ አርጀንቲና
*የእግር ኳስ ወጎች
*ኢህአፓና ስፖርት 1 እና 2 እዚህ ጋ በቅርብ ለእይታ የቀረበው የነገን አልወልድም የታሪኩ መነሻ ከ ኢህአፓና ስፖርት 1 የተወሰደ ነው)
እና ሌሎች በህትመት ደረጃ ያልወጡ በሙዚቃና በሌሎች ጉዳዮች ያተኮሩ መፅሐፍት ሲያሰናዳ ነበር፡፡
ሌላው በ90ዎቹ አጋማሽ ላይ በስፋት ይወራ ስለነበረው የኢትዮጵያዊ ስልጠና ሀሳብ አመንጪ ሰው ነው፡፡ በተለምዶ  Gk የሚባለውን  የስልጠና ፍልስፍና በኋላ በካሳዬ አራጌ  ዳብሮ ለአጭር ጊዜ የተሞከረው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ዙሪያ ላይ በ1994 ዓ.ም ኢትዮጵያ ስልጠና መፅሀፍ ማውጣቱ አይዘነጋም። እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ደብዳቤ ፅፏል በስልጠናው ዙሪያ ላይ።
*****
ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ ) ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ማረፉ ተሰምቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል፣ በታላቁ የስፖርት ሰው ገነነ መኩሪያ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ፤ ለቤተሰቦቹ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡ ፈጣሪ ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርለት፡፡

 

 

Read 817 times Last modified on Tuesday, 23 January 2024 06:34