Monday, 22 January 2024 08:47

ሠላሳዎቹ” - በወጣት ጸሃፍቱ አንደበት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሊድያ ተስፋዬ እባላለሁ። ትውልድና እድገቴ አዲስ አበባ ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ በኢኮኖሚክስ ቀጥሎም በእንግሊዝኛ ሥነ ጽሑፍ ተመርቄአለሁ። በሕትመት ሚድያው ላይ ከጀማሪ ዘጋቢነት ጀምሮ በተለያዩ ድርሻዎች ሠርቻለሁ፣ አሁንም እየሠራሁ ነው። ድርሰቴ በመጽሐፍ ላይ ሲታተም የአሁኑ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በመደበኛነት እሠራ በነበረበት “አዲስ ዘመን“ ጋዜጣ እንዲሁም በኋላ ላይ “አዲስ ማለዳ“ ጋዜጣ ላይ የተለያዩ ጽሑፎችን ለአንባቢያን የማድረስ እድልን አግኝቻለሁ። “ሠላሳዎቹ“ በተሰኘው መድበል ውስጥ ‘’ስለምን ታለቅሺያለሽ?’’ የሚለው ድርሰቴ ተካትቶልኛል፡፡
ድርሰትሽ በ“ሠላሳዎቹ“ የአጫጭር ልብወለዶች መድብል ውስጥ በመካተቱ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብሽ? ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ዕድል ገጥሞሽ ያውቃል? የራስሽን መጽሐፍስ አሳትመሻል?
በቅድሚያ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ይህን እድል ስለሰጠን በጣም አመሰግናለሁ። ከዚህ ቀደም የራሴን መጽሐፍ አላሳተምኩም። በተለያዩ ደራሲዎች በኀብረት ተዘጋጅተው የታተሙ የአጫጭር ልብወለድ እንዲሁም የግጥም ስብስብ ሥራዎች መኖራቸውን አውቃለሁ እንጂ እንዲህ ያለ እድል ገጥሞኝ አያውቅም። ደራሲ የመሆን ምኞት  አለኝ፡፡ ድርሰቴ በዚህ “ሠላሳዎቹ“ የተሰኘ መድበል ውስጥ መግባቱን ሳውቅ በጣም ነበር ደስ ያለኝ። በአንድ በኩል መመረጡ ራሱ ለወደፊት በተስፋ እንድበረታ የሚያግዘኝ ነው። አንድ ብሎ መጀመር ከባድ ነው፣ አንዳንዴ እንዲህ ያለ እድልን ይፈልጋል። በሌላ በኩል፤ ለሕትመት ወጪ እንድንጨነቅ አልተደረግንም። ከዚያም ባልተናነሰ በሥነ ጽሑፉ ዘርፍ  የተመሰገኑ፣ የተደነቁ ሰዎች ናቸው አርትዖቱን የሠሩት። ድርብርብ እድል ማለት ነው። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የተነሳ እድሉን ማግኘቴም፣ ቀድሞ ነገር እድሉ ራሱ መፈጠሩ ደስ አሰኝቶኛል። በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ምክንያት የሆነውን የጀርመን ባሕል ማዕከል ወይም ጎተ’ን፣ እንዲሁም በዋናነት ሐሳቡን ከመጸነስ ጀምሮ ልብወለዶቹ እንዲህ መጽሐፍ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ፣ ባየነውም ባላየነውም ሂደት ውስጥ ሲደክም የነበረውን ዮናስ ታረቀኝን  በጣም አመሰግናለሁ።
የአጫጭር ልብወለዶች ስብስቡን እንዴት አገኘሽው?
በጣም ወድጄዋለሁ። የተለያዩና ጥልቅ ሐሳቦችን፣ ዕይታዎችን፣ ስሜቶችን የተሸከሙ ሥራዎች ናቸው። በወጣቶች ዐይን ሀገር፣ ዓለም፣ ማኅበረሰብና ራሱ ሕይወት የተሳሉበትን መንገድ አሳይቶኛል። ወደፊት በአዳዲስ ሥራዎች  ላያቸው የምናፍቃቸው ደራሲዎችን አስተዋውቆኛል።  
የወጣት ጸሐፍት ሥራዎች እንዲህ ተሰባስበው በጋራ መታተማቸው ምን ፋይዳ አለው ብለሽ ታስቢያለሽ?
ይህን ከኹለት አንጻር ነው የማየው፣ ከደራሲዎችና ከተደራሲዎች አንጻር። ከደራሲዎች አንጻር መተባበርን፣ አንድነትን፣ መተዋወቅን የሚፈጥርና እንደ ሃምሳው ሎሚ የቤት ሥራን አከፋፍሎ ድካምን የሚቀንስ ነው። ይህን የእኛን ሥራ እንኳ ብንመለከት፣ ሠላሳዎቻችንም በመጽሐፉ ላይ በተካተተ አንድ ሥራችን ብቻ የተነሳ አፋችንን ሞልተን መጽሐፉን ‘የእኔ መጽሐፍ’ እንላለን። ልክ እንደዛ ሁሉ፣ አብሮ መሥራቱ አንድነትን ይፈጥራል፣ ያበረታል፣ ያተጋል። ከተደራሲዎች አንጻር ደግሞ የተለያየ ጣዕምን ይሰጣል። አንባቢዎች የአንድ ደራሲን ወይም የአንዲት ደራሲትን ሥራ አይደለም የሚያነብቡት፣ የተለያዩ ደራሲዎችን ሥራ በአንድ ላይ ነው የሚያገኙት። ማኅበራዊ ሚድያው ተወዳጅ ያደረገው አንድ ጠባዩ ይህ ይመስለኛል፣ የተለያዩ ሰዎች ዕይታዎችና ሐሳቦች በአንድ አውድ የሚቀርብበት መሆኑ። በዚያ ልክ ባይሆንም እንኳ፣ መጽሐፍም በራሱ ሜዳ በተለያዩ ጸሐፍት በጋራ የተዘጋጁ ሥራዎችን ሲይዝ፣ ለአንባቢ ምርጫን ያሰፋል ብዬ አምናለሁ። ከዚያ ባሻገር ለሥነ ጽሑፍ አጥኚዎችም  የጥናት ግብዓትና መነሻ ሊሆን ይችላል።
በጀርመን የባህል ማዕከል ድጋፍ ከተሰጣችሁ አጭር ሥልጠና ምን አዲስ ትምህርት ቀሰምሽ?
ድርሰቶቻችን ከተመረጡ በኋላና ለሕትመት ከመዘጋጀታቸው በፊት የሁለት ቀናት ሥልጠና ወስደን ነበር። በዚህ አጋጣሚ እርስ በእርስ ከመተዋወቃችን ጎን ለጎን፣ ስለሥራዎቻችን ጥንካሬና ደካማ ጎን ተነግሮናል። በበኩሌም አስቀድሞ በአስተውሎት የማላያቸው የነበሩ ጉዳዮችን በትኩረት እንዳይ አንቅቶኛል። በዚያው ሥልጠና መሠረታዊ የሚባሉ ከሥነ ጽሑፍ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችንም በተመለከተ ሐሳቦችን አግኝተናል። በሥልጠናው የሰማናቸው ልምዶችም ጽሑፎቻችንን ብቻ ሳይሆን እንደ ጸሐፊ ራሳችንም ላይ እንድንሠራ የሚጋብዝ ሆኖ ነው የተሰማኝ።
ከአገራችን ወይም ከውጭ አገራት የአጭር ልብወለድ ጸሐፍት ማንን ታደንቂያለሽ?
ጥቂት ከሚባሉ ሴት ደራሲያት መካከል ሕይወት እምሻውን ብጠቅስ እወዳለሁ። በብዛት በግጥም፣ በጥቂቱ ደግሞ በረጅም ልብወለድ ሥራዎች የሚጠቀሱ ደራሲያት አሉ። በአጫጭር ልብወለድ ግን ጎልተው የሚጠቀሱ ሴት ደራሲያት መኖራቸውን እርግጠኛ አይደለሁም። ከእኔ የንባብ እጥረት ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ካሉትና ከማውቃቸው ግን ሕይወት እምሻውን አደንቃለሁ።

Read 456 times