Saturday, 13 January 2024 00:00

አርቲስት አምለሰት የከፍታ አፓርትመንቶች አምባሳደር ሆና ተመረጠች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሮክስቶን በ1ቢ.ብር የመኖርያ አፓርትመንቶች እየገነባ ነው


         የጀርመኑ ሪልእስቴት ሮክስቶን ኢትዮጵያ፤ ታዋቂዋን ተዋናይት፣ የሚዲያ ባለሞያና ግንባር ቀደም የአረንጓዴ ልማት ተሟጋች አርቲስት አምለሰት ሙጬን፣ የከፍታ አፓርትመንቶች ብራንድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙን ሰሞኑን  አስታውቋል፡፡
የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በሪልእስቴት ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው ሮክስቶን ኢትዮጵያ፤ በመዲናዋ  ሲግናል አካባቢ በ1 ቢሊዮን ብር  በጀት ከፍታ በአዲስ አበባ የተሰኘ የመኖሪያ አፓርትመንቶች እያስገነባ ሲሆን አፓርትመንቶቹ ከ30 ሚሊዮን ብር እስከ 150 ሚሊዮን ብር ያወጣሉ  ተብሏል፡፡
አርቲስት አምለሰት ሙጬ የከፍታ አፓርትመንቶች አምባሳደር ሆና መመረጧን አስመልክቶ ባለፈው ረቡዕ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል የሮክስቶን ኢትዮጵያ ከፍተኛ አመራሮችና አርቲስቷ በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ የስምምነት ፊርማም ተፈራርመዋል፡፡  
 አርቲስት አምለሰት ሙጬ በብራንድ አምባሳደርነት የተመረጠችበት ዋነኛው ምክንያት አረንጓዴ ዓለምን ለመፍጠር በሚደረጉ ሁለንተናዊ ተሳትፎዎች ላይ እውቅናዋን ተጠቅማ የተለያዩ ንቅናቄዎችን ማሳካት በመቻሏ ነው ያለው ሮክስቶን ሪልእስቴት፤ ከዚህ በተጨማሪም አርቲስቷ ያላት ሰብዕና፣ ቁርጠኝነትና ትልልቅ ራዕዮቿ በሙሉ ድምፅ እንድትመረጥ አድርገዋታል ብሏል።
 አርቲስት አምለሰት አምባሳደርነቷን አስመልክቶ በሰጠችው ማብራሪያ፤ “ዘላቂነት ካለው የሪልእስቴት ልማት ኩባንያ ጋር አብሬ በመስራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከፍታ፤ አዲስ አበባን የሚያምር ገፅታ በማላበስ፣ አረንጓዴነቷን በማስቀጠል የተፈጥሮ ሀብትን ለትውልድ እያስቀጠለ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው። በተጨማሪም እኔ እራሴ በከፍታ አፓርትመንት የቤት ባለቤት በመሆኔ  ኩራት ይሰማኛል፡፡” ብላለች፡፡
 ለብራንድ አምባሳደርነቷ ምን ያህል እንደተከፈላት ከጋዜጠኞች የተጠየቀችው አምለሰት፣ የክፍያውን መጠን ለመናገር ፈቃደኛ ሳትሆን የቀረች ሲሆን ይልቁንም፤ ”አንድ ቤት የሚሰጡኝ ይመስለኛል፤ፔንትሃውስ ቢሆን ደስ ይለኛል፡፡” ስትል በቀልድ ተናግራለች፡፡
ከኩባንያው ጋር ለመሥራት የተስማማሁት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑና በህንጻዎቹ ዲዛይን ላይ የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ በማንጸባረቁ ነው ብላለች - አርቲስት አምለሰት፡፡
የሮክስቶን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሚስተር ዲትሪክ ኢ. ሮጄ ስለ አምለሰት በብራንድ አምባሳደርነት መመረጥ ሲናገሩ፤ “አርቲስት አምለስት ባላት የግል ማንነት ከፍታ የያዘውን የዘመናዊነትና የአካባቢ ጥበቃ ተነሳሽነት ለብዙ ደንበኞቻችን ለማሳየት ወሳኝና ተመራጭ እንስት ናት። በአስገራሚ ሰብዕናዋና ከማህበረሰቡ ጋር ባላት ጠንካራ ትስስር፣ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅሟ ከፍተኛ ስለሆነ ከፍታ አፓርትመንቶችን በማስተዋወቅ እንዲሁም አዲስ ነገሮችን በጋራ የመፍጠር ራዕያችንን ታሳካለች ብለን እናምናለን፡፡” ብለዋል፡፡
 የሮክስቶን ኢትዮጵያ  ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አድያምሰገድ ኢያሱ በበኩላቸው፤ “አርቲስት አምለሰት ሙጬ ብራንድ አምባሳደራችን በመሆኗ በጣም ደስተኞች ነን። አምለሰት የእኛን የልህቀት፣ የጥራትና የማህበራዊ ሀላፊነት እሴቶች የምትጋራ መልካም ሰብዕና ያላት ድንቅ አርቲስት ናት። ለድርጅታችን ትልቅ ሀብት እንደምትሆንና ወደምንፈልጋቸው ደንበኞቻችን እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እንድንደርስ ትረዳናለች ብለን እናምናለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
  ሮክስቶን ሪልእስቴት በጀርመን የተመሰረተ በግንባታው ዘርፍ ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥ የሪልእስቴት ገንቢና የኢንቨስትመንት ድርጅት ሲሆን፤ በጀርመን ስፔንና ፖርቹጋል በየተለያዩ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡   


Read 344 times