Saturday, 06 January 2024 21:16

ገና እና አከባበሩ እዚህ እና እዚያ

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekle@gmail.com)
Rate this item
(1 Vote)

 “ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ እነሆ ሰብአሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡ ” ይላል የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 2.
የጌታችን የመድሃኒታች የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲከበር ከዚህ ደርሷል፡፡ ክርስትያኖችም ኢየሱስን በየራሳቸው መንገድ የመስበካቸውን ያህል ስያሜአቸውም ተለያይቷል፡፡ ስያሜ ብቻ ሳይሆን የክርስቶስ ልደት (ገና)ን የሚያከብሩበት ቀንም በዓሉን የሚያከብሩበት መንገድም የተለያየ ነው፡፡
ብዙ የተከተለው ትክክል ነው ትንሽ የተከተለው ትክክል አይደለም የሚል አንድምታ ባይኖርም አብዛኛው የምዕራቡ ዓለም ካቶሊካውያን እና የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስትያናት ልደትን የሚያከብሩት በቀን አቆጣጠራቸው መሠረት በዓመቱ መጨረሻ ዲሴምበር 25 (በኢትዮጵያ ታኅሣስ 15/16 ነው፡፡ብዙዎቹ የምሥራቅ አብያተ ክርስትያናት ኦርቶዶክሶች ደግሞ በዓሉን በኢትዮጵያ የቀን ቀመር አዲሱ ዓመት በገባ በዐራተኛው ወር መጨረሻ  ታኅሣስ 29 ቀን ወይንም በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣስ 28 ቀን ነው የሚያከብሩት፡፡
ዲሴምበር 25 ከሚያከብሩ ሀገራት መካከል ስሎቫኪያ፣ ቼክ፣ እንግሊዝ፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ብራዚል፣ ቺሊ፣ አውትራሊያ፣ ናይጄርያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ቶጎ ካሜሩን ሲገኙበት በታኅሣስ 28/29 ከሚያከብሩ ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሕንድ፣ አርሜንያ፣  ሶርያ፣ ሰርቢያ፣ ሩስያ፣ ይገኙበታል፡፡ ኪርኪዚስታንን የመሰሉ ሀገራት ደግሞ በዓሉን ታኅሣስ 29/30 (ጃኑዋሪ8) ያከብራሉ፡፡
የክርስቶስ ልደት ከሚከበርባቸው ነገር ግን የኅዝብ በዓል ካልሆኑባቸው ሀገራት መካከል ደግሞ ሞንጎሊያ፣ የተባበረው አረብ ኢምሬቶች፣ ሞሮኮ፣ ቻይና፣ እስራኤል ይገኙባቸዋል፡፡  ገና የኅዝብ በዓል ባይሆንም በእስራኤል ከኢትዮጵያ፣ ከግሪክ፣ ከሩስያ እና ከሌሎች ሀገራት የተውጣጡ ክርስትያኖች እና ጎብኚዎች ገና በድምቀት በሀገረ እስራኤል እንደሚያከብሩ ይታወቃል፡፡
አከባበር
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስትያን በዓሉን የሚያከብሩት ከኅዳር 15 ጀምሮ በመፆም ነው፡፡ በአብያተ ክርስትያናቱ ካሉ ሰባት በሕግ የተደነገጉ አጽዋማት አንዱ ይኸው ለገና እለት የሚፈታው ፆመ ነቢያት ተብሎ የሚጾመው ፆም ነው፡፡ በፆሙ ፍጻሜ  ቅዳሴው በእኩለ ሌሊት ከተከናወነ በኋላ እንደየዐቅሙ በግ፣ በሬ በማረድ፣ ድፎ ዳቦ በመጋገር፣ ጠላ እና ጠጅ በመጥመቅ ወዘተ ይከበራል፡፡ በብዙ ቦታዎች የገና ጫወታ (ሩር በዱላ የምትለጋበት የቡድን ጫወታ) ይኖራል፡፡ አሁን አሁን ይህንኑ የመገባበዝ ባሕል በማዳበር ሰንበት ተማሪዎች እና ሌሎች ወጣቶች ገንዘብ በማዋጣት እና እርድ በማከናወን ያጡ የነጡ እና የኔብጤዎችን በማብላት ያከብሩታል፡፡
እንደ ኢትዮጵያው ሁሉ ከሚኖረው የቅዳሴ እና ሌላ መንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ በሶርያ ገና ሲከበር ሶርያውያን ስጦታ ይሠጣጣሉ፡፡ ልጆች በበዓሉ ዋዜማ ጫማቸውን ደጅ ይተዋሉ፡፡ በአጠገቡም ለሰብአሰገል (ለጥበብ ሰዎች) ይመስላል ድርቆሽ እና ውሃ ያስቀምጣሉ፡፡ ጫማቸውም በስጦታ እቃ ይሞላላቸዋል፡፡ የሶርያ ጎረቤት በሆነችው ኢራቅ በዓሉን በአብዛኛው የሚሳልፉት እርስበርስ በመጠያየቅ ነው፡፡ በግሪክ በዓሉ የሚከበረው የአሳማ ሥጋ በመመገብ ነው፡፡ በማር የተነከረ ሜሎማካሮና የተባለ ምግብ እና ኩርቢዲ የተባለ በቅቤ የተለወሰ ኩኪስም ይበላል በግሪክ፡፡በሩስያ ደግሞ በበዓሉ ዋዜማ መፃኢ ዕድል ከወትሮ በተለየ ይተነበይበታል፡፡ ይህ ምንአልባት ከሰብዓሰገል በከከብ ተመርተው ኢየሱስን ካገኙበት ጋር ሊዛመድ ይችላል፡፡ ሩስያኖች በበዓሉ ዋዜማ ከእህል፣ ከደረቀ ፍራፍሬ እና ከማር የተሠራ ምግብ ይበላሉ፡፡ ሌሎች በርካታ የሀገሬው ምግቦች ይበላሉ፡፡ ምግቡ የፆም ወሩ መጠናቀቁንም አመላካች ነው፡፡ ሩስያውያንም በዓሉን ለቤተሰብ መሰብሰቢያነት ከማዋላቸውም በላይ ይቅርታ የሚደራረጉበትም ቀን ነው፡፡
ሩስያ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው በዓሉን እንደኛው በታኅሣስ 28/29 ታከብራለች፡፡ ጎረቤቷ ዩክሬንም በዚሁ ቀን ስታከብር ቆይታለች፡፡ እንደ ምስራቃውያን ስታከብር የቆየችው ሀገር እንደ ምዕራባውያን ለማክበር ቀኑንም ወደ ዲሴምበር ለመለወጥ እያሰበች እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሆኖም በዩክሬን እና አንዳንድ ሀገራት በዓሉ ዲሴምበር 25 ተጀምሮ ጃኑዋሪ 6 ወይም 7 በጥምቀት በዓል እስኪጠቃለል ለቀናት የማክበር ልምድም አለ፡፡
ገና ሃይማኖታዊ ይዘቱን እያጣ መጥቷል ከሚባልባቸው ሀገራት አንዷ በሆነችው ካናዳ በበዓሉ ከሚጎሉ ነገሮች አንዱ ቤትን በገና ዛፍ ማጌጥ ነው፡፡ ዋነኛው የገና ምግብ በሀገሪቱ የተኪና ዶሮ ጥብስ ቢሆንም የሀገሪቱ ነዋሪዎች እንደየመጡበት ሀገር በሌሎች በርካታ የምግብ አይነቶች በዓሉን ያከብራሉ፡፡
የተባረከ ዐውደዓመት ይሁንላችሁ፡፡


Read 730 times