Saturday, 30 December 2023 20:27

የልጅ መዘክር…ለአባት መታወሻ

Written by  አብዲ መሐመድ -
Rate this item
(0 votes)

አባትነት አያሌ መገለጫዎች አሉት፡፡ በብዙ መልኩም መተርጎም ይቻላል፡፡ ወንድ ልጅ ከልጅነት እስከ እውቀት ያለው ሰብዕና ለአባትነት የተዘጋጀ ነው፡፡ ተፈጥሮም ራሷ ሰብዕናችንን የምትቀርጸው ለአባትነት ብቁና ምቹ እንድንሆን አድርጋ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ ያጠኑ ጠቢባን ሁሉ የሚስማሙበት ሀቅ ነው፡፡ መንፈሳዊ መሪው ማይለስ ሙንሮ “The Fatherhood Principle” በተሰኘ ተወዳጅ መጽሐፉ አባትነትን እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡፡…“አባት መሠረትና መስራች ብቻ አይደለም፡፡ ለሁሉም ነገር ምክንያትም ጭምር ነው፡፡ አስተማሪ ነው፣ መመሪያ ይሰጣል፡፡ መስራች ነው፣ ሀገር ይገነባል፡፡ ፈጣሪ ወንድን ሲፈጥር አባት እንዲሆን ከፈጣሪ የተወሰነ ነው፡፡ በመሰረቱ በየትኛውም ትንሽ ወንድ ልጅ ውስጥ አባት የመሆን እምቅ ማንነት አለ፡፡ ይህ በራሱ ፈጣሪ ማንኛውንም ወንድ ልጅ ወደ አባትነት እንዲያድግ ማቀዱን አመላካች ነው፡፡ ምክንያቱም እግዜር የፍጡራን ሁሉ አባት ነው፡፡ በወንድ ልጅ ውስጥ አባትነት እስካልተገለጠ ድረስ በምንም አይረካም፡፡ አባትነት የወንድ ሁሉ ስሪትና ፍፃሜ ወይም ስኬት ነው”…ይላል፡፡
አባትና አባትነት የተለያዩ ትርጓሜዎች አሉት፡፡ ጥልቅ ነው ፍቺው፣ እልፍ ነው መገለጫው፡፡ “የሚሰማ ጆሮ ቢኖር ኖሮ” በሚል ርዕስ የተሰናዳ የግለ ህይወት ማዕድ ነው፡፡ የብላቴን ጌታ ወልደ ማርያም አየለ ታሪክ፡፡ እኚህ በደረታቸው ላይ ኒሻን የደረደሩ አባት ምን ተናግረው ይሆን፤ ጆሮዋችንን እንድናውሳቸው የሚማፀኑት? ብዬ በክልስ ልጃቸው የተቀነበበ ድርሳናቸውን ለንባብ ካገላበጥኩት ሰንበትበት ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ መጽሐፉን በምልዓት ለመገንዘብና ለማጤን ሌላ አንድ ተጨማሪ ስራ ማግኘት ነበረብኝ፡፡ -በመኩሪያ መካሻ የተሰናኘ የብላታ ወልደማርያም መዘክር፡፡ ፓስካል ይህን የአባታቸውን የትዝታ ማህደር የከተቡት በአፍላነት ዘመናቸው ጭላንጭል ትዝታ ላይ ተመርኩዘውና በምልሰት ወደ ኋላ ተመልሰው መሆኑን በቀዳሚ ቃላቸው ጠቁመዋል፡፡…“አባቴ ገና ከጅምሩ ሁሉንም በፅሁፍ የማስቀረት ልምድ ነበራቸው፡፡ ዘራችን ከየት እንደመጣ፣ የዘር ግንዳችንና ቅርንጫፉን ሁሉ ዘርዝረው ዳጎስ ያለመዝገብ አዘጋጅተው ቄስ፣ ወታደር፣ ገበሬ…የሆነውን ሁሉ በሙያ-በሙያው ከፋፍለው አስፍረው ቢሰንዱ  ለልጆቻቸው ሳይደርስ የገባበት ጠፍቷል፡፡ ከሀገሬ ወጥቼ፣ አስራ አምስት አመታት በትምህርት፣ ሃያ አራት አመታት በስራ በድምሩ ሰላሳ ዘጠኝ አመታት ቆይቼ ስመለስ ታሪክ የሚያውቅ ሰው የማግኘት እድሉ ጠፍቶ ቆየኝ፡፡ የቤተሰቤን ታሪክ የሚያውቁ አዛውንቶች በሙሉ አልቀዋል፡፡ (ገጽ.19)
እንግዲህ ፓስካል የወልደማሪያም አየለን ታሪክ ለመጻፍ ምንም ፍንጭና መነሻ ባይኖራቸውም የልጅነት ደብዛዛ ትውስታ ግን አላጡም፡፡ ያ -ፍንጣቂ በራሱ በቂ አልነበረም፡፡ መሪ መሆንም፣ ሊሆንም አልቻለም፡፡ ብላቴን ጌታን በፊደላት ኩለው የተሟላ ስዕል መስጠት፣ በጉልህ ማሳየት ግን አልተሳናቸውም፡፡ ፓስካል ኩርማን ታሪክ ላይ ተንጠላጥሎ፣ የተቀረውን በምዕናብ ሞልቶ ከማተት ይልቅ፤ ሰውዬውን በዝርዝር እንድናውቃቸው፣ ትውልድም እንዲማርባቸው የተቻላቸውን ያላሰለሰ ሙከራ በማድረግ ተግተዋልና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ወልደ ማርያም በማዕረጋቸው ብላቴን ጌታ ናቸው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያው ዘመነ መንግስት የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር፣ የማዕድን መምሪያ ዋና ዳይሬክተርና በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኋላ በ1936 በጦርነቱ ምክንያት ፊታውራሪ ተክለሀዋሪያት ተክለማርያም ከፓሪስ እንደተመለሱ በወልደ ማርያም መተካታቸውን መዘክራቸው ያስረዳል፡፡ በርግጥ ስለወልደ ማርያም የተፃፉ ሌሎች ነባርህትመቶችም አሉ፡፡  በአመዛኙ በወቀሳ መልክ ይሁን እንጂ ‹‹የአክሊሉ ማስታወሻ›› ውስጥ ብላቴንን የተመለከቱ ሌሎች መረጃዎችና ማስረጃዎች እናገኛለን፡፡ በወረራው ወቅት ከፋሽስት ጋር ስለነበራቸው ግንኙነትና ስለሚያራምዱት ግላዊ አቋም፣ የፕሬስ አታሼ ሆነው በኤምባሲ ስለመስራታቸው፣ ጃንሆይ ወደ ፓሪስ ሲመጡና ወደ ጄኔቭ ሲሄዱ ዋነኛ ተቀባያቸው፣ አስተናጋጃቸው እሳቸው እንደነበሩ ወዘተ፡፡… ፓስካል በዚህ መጽሐፋቸው ከልጅነታቸው ይጀምሩና ብላቴንን በውስን ገፆች በማውሳት አስቃኝተውን ሲያበቁ፤ በቀጣይ ምዕራፎች አባታቸው ለሀገር ስላከናወኗቸው ተግባራት፣ ከንጉሱ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት፣ በወልደ ማርያም እና በፀሀፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ መሀል ስለተፈጠረ አለመግባባትና ግጭት እንዲሁም ወደ ጎልማሳነታቸው ዘመን እየተመላለሱ ይተርካሉ፡፡ በሚያነሷቸው አንኳር ትዝታዎቻቸው ሁሉ አብዝተው የሚመሰጡ ይመስላሉ፡፡ ምንም እንኳን ትዝታቸው በአመዛኙ ምናባዊ እሳቤና ሁኔታ ቢታከልባቸውም  ሀቲታቸውን ቆፍረው እሚዘግኑት ከትናንታቸውና ከትዝታቸው ነው፡፡ የህይወት ታሪኩ በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ የተዋጣለት ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሰናኙ ደራሲና ሀያሲ አለማየሁ ገላጋይ ነው፡፡ እርስቱን ሽጦ ለዚህ ማስታወሻ ለመጠበብ ሲል በምስለኔነት ያደረ ታማኝ ሎሌ ሆኖለታል፡፡ አርቅቆታል፣ አጥልቆታል፣ አበልጽጎታልም፡፡ ሁለንተናዊ ድርሻው ሰፊ ነው፡፡ በዚህ በኩል በስነጽሑፋዊ ገለፃና ቴክኒክ ዳብሯልና ተነባቢነቱ ጥያቄ የለውም፡፡ በዚያ በኩል ደግሞ የትውስታውን ቅርጽ የሀያሲው ተፅዕኖ አርፎበት፤ ቁመናውን ወደ ልቦለድነት ሲያዘነብልና የፓስካልን ብዕር እንዳናይ ሲጋርደን በንባባችን ሂደት እናስተውላለን፡፡
ደካማ ጎን
በአምስት አመቱ የፋሺስት አገዛዝ ወቅት በከፍተኛ ስልጣን ላይ የነበሩ አያሌ ጉምቱ ልሂቃን፣ እውቅ ሹማምንት ለኢጣሊያን ስለማደራቸው እግረመንገድ ሲጠቀሱ፣  በዘመነኞቻቸው ሲጋለጡም ያጋጥማል፡፡ ይሄ እንግዳ ጉዳይ አይደለም፡፡ ፓስካል አባቴ ከእውነት በራቀ በሀሰተኝነት በአክሊሉ ሀብተ ወልድ ያልሆነ ስም ተሰጥቷቸዋል ባይ ናቸው፡፡ ይኼን የታሪክ ክስለ መከላከል ሲሉ በርካታ ገፆች አላስፈላጊ ፍጆታ ላይ ውለዋል፡፡ ይሄ ለተደራሲ ግርታን ይፈጥራል፡፡ ትውስታው ላይም አሉታዊ የቂም በቀል ምስል እንዲያጠላ በማስገደድ ያሻማል፡፡ ከሰባ አመት በፊት የነበረ የስራ ላይ አለመግባባት፣ መጠላለፍና ሽኩቻ በመጻሕፍት እንደ ሀውልት ተቀርፆ፣ ታንጾና ተሰንዶ ለትውልድ መሻገር የለበትምና በይቅርታ መሻር ይኖርበታል፡፡ ወልደ ማርያም እንደሰው ተበድለውም ሆነ ፍትህ ተጓድሎባቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የፍትህ መጓደል ገንፎ ውስጥ እንዳለ የእንጨት ስንጥርጣሪ ጉሮሮን እየወጋጋ ነፍስን ጤና ይነሳ ይሆናል፡፡ ፓስካል እሱን ለማጥራት የሄዱበት እርቀት ተገቢ ነበር ብዬ አላምንም፡፡ የሞተን ቁርሾ በይቅርታ ረስቶ ማዳፈን እንጂ እየቆሰቆሱ ማባባስ ለዚህ ትውልድ ያለው ፋይዳ ግልጽ አይደለም፡፡ እንዲህ ያሉ የታሪክ ጉዳዮች በባለሞያ ተጣርተው ለበደሎች እውቅና ተሰጥቶ፣ በምህረትና በይቅርታ መታለፍ ካልተቻለ በተጨባጭ እንደሚታየው ለልዩነት መዳረጋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ ይመስላል ዶ/ር ሙሉጌታ ኢተፋ የተባሉ ምሁር “ትዝታና ዝምታ” በተሰኘ ዜና መዋዕላቸው ውስጥ እንዲህ ያለ የፍትህ መጓደል  ተያያዥ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ምክረ ሀሳባቸውን እንዲህ በማለት የሚያካፍሉት፤ “…አያሌ ብሂሎቻችን ፍትህ አለመኖሩን ያሳያሉ፡፡ ፍትህ ለጉልበተኛ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም እንደሚገባ ማስተማር አለብን፡፡ ፍትህ ለጉልበተኛ ብቻ የሚሆነው ለጫካ አውሬዎች ብቻ ነው፡፡ “The rule of jungle” የተባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የህግ የበላይነትን ማወቅና ማሳወቅ ከጫካ ህግ ያድናል ብቻ ሳይሆን ከዲሞክራሲና ከስልጣኔ ምልክቶች አንዱ ነው፡፡ ፍትህ ሊኖር የሚችለው ሁሉም ሰው ከህግ በታች ሲሆን ነው፡፡ ይኸን ለማድረግ በብዙ አገሮች ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ አሁንም እየተከፈለ ነው፡፡” (ገጽ.139)
 ይህ በትውስታ ላይ ተመስርቶ በልጃቸው የተፃፈልን የብላቴን ጌታ ወልደ ማርያም መታወሻ የሆነው መዘክር፤ ህይወታቸው ላይ ከማጠንጠን ባሻገር በታሪክ መዝገብ ሊሰፍር የሚችል ጠቃሚ የሆኑ የቀድሞ ታሪካችንን የሚያቀርብና የሚዳስስ ነው፡፡ መጽሐፉ እንዲፀነስና ለህዝብ እንዲደርስ በርካታ ውዝግቦች፣ አሻሚ ጉዳዮች፣ ገፊ ምክንያቶች ሆነው መንገድ ጠርገዋል፣ በር ከፍተዋል፡፡ እርሱን የማጥራት ጉዳይ ለታሪክ ተመራማሪያን ትተን ከሰውዬው የምንቀስማቸው ፍሬ ነገሮች፣ ቁም ነገሮች ግን አያሌ መሆናቸውን አስረግጠን መግለፅ ይገባናል፡፡ አስተማሪና አመራማሪ ሌሎች የታሪክ ሰበዞችን መምዘዝ፣ የተዋቀረባቸው ኩነቶችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለ ማዕድን፣ ስለ ፀጥታ፣ ስለ አውሮፕላን ግዢ፣ ስለ ጋምቤላ ወሰናችን፣ ስለ ጣና ባህር ልኬትና ግደባ…የመሳሰሉ ዝርዝር ማስታወሻዎችም ቀርበውበታል፡፡ ይሄ ትውልድ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያውቅበታል፣ እያመሳከረ በጥንቃቄ ቢያነበው በቂውን ያህል ይማርበታልም፡፡

Read 329 times