Saturday, 30 December 2023 19:58

የሰው ሆዱ ...

Written by  የአብፀጋ ተመስገን /maddbn/
Rate this item
(2 votes)

ዐይን ለምን አየህ አይባልምና ፣ ካለሁበት ሆኜ ዙሪያ ገባውን ስማትር ድንገት ከዓይኔ ገባች። መሰጠችው መሰል አንገቴ እስኪታክተው ጅማቶቼ እስኪዝሉ ወደ’ሷ እያዞረኝ ተስለመለመ። ውበቷን በብሌኖቹ መዝኖ ወደዳት። የት አባታቸው እንደሚያውቋት እንጃ፣ ነገረኛው ዓይኔን ተከትለው  ቀልብና ልቦናዬ በአንድ ድምፅ በልጅቷ ተማርከው አረፉት። የነገሩ አፈጣጠን ስላልጣመኝ ግራ ተጋባሁ።  መቼም ሰው ውስጡ ሲቀዣበር ነውና የሚደናገረው  ውስጤን ታዘብኩት። እውነትም ከቆዳዬ ስር ነውጥ ተነስቷል፤ ዓይኔ ባመጣው ጣጣ ልቤና አንጎሌ ዱላ ቀረሽ አተካራ መግጠም ይዘዋል። ህሊናዬ ወይንም  አቶ አዕምሮ አንድ እጁን እንደ ነገረኛ ወገቡ ላይ አኑሮ በሌላኛው ግንባሬን ተደግፎ እንዲህ ሲል ሰማሁት፤
  ”እኔ በጭራሽ በዚህ ጉዳይ አልስማማም። እንዴ !? የትም የማናውቃትን፣ ለአንድ አፍታ እንኳ ቀረብ ብለን ያላጤንናትን ልጅ እንዲሁ ዝም ብሎ በዘፈቀደ መውደድ ለእኔ እብደት ነው!”    ልቤ ሳቀ፡፡ ከትከት ብሎ እየተንፈቀፈቀ ከልቡ ሳቀ ልቤ። ሌሎች አካላቶቼም አብረውት ሳቁ። ማሽቃበጣቸው ነው። ያው ለሁሉም ደም የሚያከፋፍላቸው እሱ ነዋ! ልብ መሣቁን አቁሞ እንዲህ አለ፤
  ”እኔ ሁለ ነገሯን ወድጄዋለሁ፤ አንተ የራስህ ጉዳይ ነው፤ አይ የምትል ከሆነ ደግሞ ትቀምሳታለህ! መቼም ታውቃታለህ አይደል የኔን ዱላ! ኧ?”  አለና እየተጀነነ ዙሪያውን የከበቡትን አሸርጋጅ አካላት ገርመም አድርጎ  ”አይደለም እንዴ ?“  ብሎ ጠየቀ ።
     “አዎ ልክ ነው!”
     “እውነቱን ነው!”
 “ትክክል እኮ ነው የተናገረው ምን አለበት እሺ ብትል?”  ሁሉም ቀጣይ ለሚፈጠረው ቀድመው ስለሰጉ  ለልብ ወገኑ። ህሊናዬ ግን አሻፈረኝ አለ።
  “ምን እንዳይመጣ ቲሽ! እኔ ለህሊናዬ ነው የማድረው፤ ገና ለገና እንዲህ ሆናለሁ ብዬ የሚመጣብኝን በመፍራት ራሴን አልሸነግልም፤ ህልም ተፈርቶ ሣይተኛ አይታደርም !” በቁጣ ተናገረ።
 “ካልክ ምን ይደረጋል እንግዲህ” አለና ልቤ በቀጥታ ወደ አንጎሌ የሚደርሰውን የደም ስርጭት እንዲቋረጥ አደረገ።
  ኩራተኛው አቶ ህሊና፤ “የመጨረሻውን ቃል ለጀግናው ተውለት” እንዲሉ ቀደምት ፀሀፌ ተውኔቶች፤ እንደምንም እያቃሰተ፤
  “ድሮም ዓለም የጉልበተኞች ናት ፣ አሳቢያን እውነት ይዘው ጥጋቸው ላይ ከማጉረምረም አልፈው አያውቁም !” ብሎ ራሱን ሳተ። እኔም ተከትዬው በሙሉ ቁመቴ መሬት ላይ ተዘረጋሁ። ውስጥ የነበረው ነውጥ ጋብ ብሎ ሠከን ወዳለ ስብሰባ ተለወጠ።
   ከአንገት በላይ በጭንቅላት ዙሪያ የሚገኙ ሁሉ የራስ ቅል ላይ ሠፍረው ተመካከሩ። እነ ሰርን ፣ እርግብግቢት ፣ ጆሮና ጉሮሮ እንኳ ሣይቀሩ ለጥቂት ደቂቃዎች ከተወያዩ በኋላ በአንድ ሀሳብ ተስማሙ፤ ጉሮሮን ወደ ልብ ዘንድ አማላጅነት በመላክ። ለአንገት ማሳሰቢያ ተሰጠው፤ የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግለት ጥሩ የምትለውን ሠፋ ያለ ቱቦ ለመንገድነት እንዲጠቀም ፍቀድለት ተባለ። ከትንሽ አድካሚ ጉዞ በኋላ አማላጅ ጉሮሮ ወደ ተማላጅ ልብ ዘንድ ደረሰና እጅ ነሣ፣ ልብ ከተኮፈሰበት ቀና ብሎ ለጉሮሮ ሰላምታ ምላሽ ሰጠና ፤  ”ምን እግር ጣለህ “  ብሎ ጠየቀ  እንዳላወቀ ሆኖ። ጉሮሮ ለመናገር ተዘጋጀ፤ ጉሮሮውን ስሎ በሚያምር ለጆሮ በሚጥም የአማላጅ ድምፅ ንግግሩን ጀመረ፤
   ”ያው መቼም ጠብ ያለ ነው። ሁሉም ነገር አብሮ እስከኖረ ድረስ መጋጨቱ አይቀርም፤ እግርና እግር እንኳን ይጋጫል..... ፤ አቶ ህሊና ሳያውቅ በስህተት እንዳስቀየምዎት ሁላችንም የምናውቀው ነው። እርስዎ መቼም ብዙ  ሀላፊነት አለብዎ ፣ የማንም አላዋቂ ባስነሳው አምባጓሮ ጫማ በመለካካት ጊዜ የሚያጠፉ አይደሉም።  ለድፍረቱ ቅጣቱ ይበቃዋል፤ እኛም እንዳይደግመው እንመክረዋለን። እንዲያው ለኛ ብለው ይቅር ይበሉት“  ብሎ እግሩ ስር ተደፋ።
   ልብ ትንሽ ካቅራራና ከተገበዘ በኋላ ወደ አንጎሌ ደም ማሰራጨቱን ቀጠለ። አቅሌ አይኑን ገለጠ፤ እኔም ከተዘረርኩበት ተነስቼ ልብሴን የነካውን አቧራ መጠራረግ ያዝኩ።  የዓይኔ ልጅቷ ላይ መንቀዋለል አሁንም እንደቀጠለ ነው። እብሪተኛው ልቤም የልብ ልብ ተሰምቶት ልጅቷን በመውደዱ እንደፀና ነው። ጭራሽ መላውን አካላት ስብሰባ ጠርቶ መመሪያ መስጠት ጀመረ፤
  ”አንተ ሸፋፋ እየሰማኸኝ ነው? ቀጥ ብለህ ወደ ልጅቷ ትሄዳለህ፤ መወለካከፍ ምናምን የለም፤ ኮራ ጀነን ብለህ እሺ!“ ለእግሬ ትዕዛዝ ሰጥቶ ፊቱን ወደ እጅ አዞረ፤
       ”በቀኝ መዳፍህ ትጨብጣታለህ!“  እጄ፤ ” እሺ” ብሎ እጅ ነሳ።
 ተረኛው ምላስ ነበር ፤ “ ከህሊና ጥሩ ጥሩ ቃላቶችን ተውሰህ የልጅቷን ልብ እንድታቀልጥ፤ አብራው እንድትቆይ የተቻለህን ጥረት አድርግ !”  “ አብራው “ ያለው እኔን መሆኑ ነው።
“እሺ እታዘዛለሁ፤ እንዳሉኝ አደርጋለሁ፤ አይጨነቁ እናሳካዋለን፤ ልጅቷ ገር ቢጤ ናት” አለ ምላሴ። ከባድ ተናጋሪ ነው፤ ምላሱ ጤፍ ይቆላል።
 በመጨረሻም የኔ ተራ ደረሰ፤  “ ሁሉንም ነገር ሰምተሀል ፤ በአንተ ቁጥጥር ስር ናቸው፤ ቡድኑን በብቃት እንድትመራ ! በል ቀጥል ወደ ስራ ዳይይይ!”  ተባልኩ።
   ወደ ልጅቱ ሄድኩና ለሠላምታ እጄን  ዘረጋሁላት። “ አትደፈር”  ብላ ጨበጠችኝ። “አትደፈር” ስሟ መሆኑ ነው። << አቶ ልብ >> የሚል ቃል ለጥቂት  ከአፌ ሊያመልጥ ነበር። “እንደ ልቡ” ብዬ የራሴን ስም አስተዋወኩና እያግባባኋት መጨዋወት ያዝን። በደንብ ተናበን የልብ የልባችንን እያወጋን ስንዋሃድ፣ ያልታዘዝኩትን ደፈር ብዬ ክንዴን ትከሻዋ ላይ ጣል በማድረግ አቀፍኳት።   ልቤ በደስታ ብዛት ጮቤ መርገጥ ጀመረ፡፡  “ጎበዝ በደንብ እቀፋት! እንዲህ ነው እንጂ ጎበዝ! በሉ አጨብጭቡለት! ” አለ ከውስጥ።  ህዋሳቴ ተነቃቁ፤ ሁሉም እየተጋገዙ አበረቱኝ። እነ ሣንባ ፣ ኩላሊት፣ ጉበት፣ ትልቁም ትንሹም አንጀት፤ “በርታ አይዞህ ከጎንህ ነን”  አሉኝ። ጨጓራዬ ብቻ እንደለገመ ቀርቷል፤ ይሄ ጠቋራ ሁሌ እንዲህ ነው። “ናርሲሲስት” ቢጤ ሣይሆን አይቀርም። ከመጥቆሩ መገገሙ ብሽቅ!
  “የመጨረሻው መጀመሪያ” እንዲል የድሮ ደራሲ ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ሳለ ከእኔ የማይጠበቅ የሞኝ ድርጊት ፈፀምኩ። ልቤን ይበልጥ አስደስተዋለሁ ብዬ ልጅቷን ሳምኳት። ወዲያው ሁሉም ነገር ተለዋወጠ፤ ጎኔ የነበረችው ልጅ ከመቅፅበት ፊቴ ተገተረች።  ስትሰነዝረው ያላየሁት ጥፊ እንደ አውሎ ንፋስ ፀጉሬን ወዝውዞ በጆሮዬ በኩል ዥውው ብሎ አልፎ ጉንጬ ላይ አረፈ። ከንፈሬን ጉንጬ ተቀየመ፤ ልጅቷ ጥላኝ ሄደች፤ እኔ በቀኝ እጄ የተመታሁበትን እንደያዝኩ ፈዝዤ ቀረሁ።
   የተልዕኮውን መክሸፍ የተረዳው አቶ ህሊና፤ የራስ ቅሌ እስኪናጋ በሳቅ ተንፈቀፈቀ። ሣቁን ሲያበቃ ወደ ግጥም ተሻገረ።
“በጠራ ጨረቃ ፤ በእኩለ ሌሊት
 ዓይኖቿ እያበሩ ፤ እንደ ክዋክብት
 ሣማት ሣማት አለው ፤ እቀፍ እቀፋት
 አላወላወለም ፤ ወጣቱ ታዘዘ
ወገቧን አንገቷን ፤ በእጅና በእጁ ያዘ
ምንም እንኳ ጡቷ ፤ እንደሾህ ቢዋጋ
ጧት በመሆኑ ፤ የጉማሬ አለንጋ
ጆሮ ግንዱን ሰማው ፤ በጥፊ ሲናጋ”
 በማለት “በጠራ ጨረቃ” የተሠኘውን  የአብዬ መንግስቱ ለማን ግጥም አንበለበለና በሾርኔ ጠቅ አደረገን። ይሄኔ ልቤ ጨሰ፣ ንዴቱ ጣራ ነካ፣ ደሙ ፈላ፤ ብስጭቱን መቆጣጠር አቅቶት ስራውን አቆመ። እኔም እንደፈረደብኝ ተከትዬው ተዘረርኩ።


Read 386 times