Saturday, 30 December 2023 19:47

ቶሞካ ቡና በደንበል ሲቲ ሴንተር ላይ የ48.2 ሚ. ብር ክስ መሰረተ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ቶሞካ ቡና ኃ.የተ.የግል.ማህበር በንኮማድ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር (ደንበል ሲቲ ሴንተር) ላይ የ48.2 ሚሊዮን ብር ክስ መመስረቱ ታወቀ፡፡
ከሳሽ ቶሞካ ቡና ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ስፋቱ 137 ካሬ ሜትር የሆነውንና በደንበል ሲቲ ሴንተር ህንፃ ላይ የሚገኘውን ቦታ እስከ ጥር 6 ቀን 2021 ዓ.ም ለአስር ዓመት ለቡና መሸጫ ካፊቴሪያነት አገልግሎት ለማዋል ከንኮማድ ኮንስትራክሽን ጋር የኪራይ ውል መዋዋሉን የክስ ጭብጡ ያስረዳል፡፡ ከሳሽ በዚሁ ውል መሰረት በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም በተፈፀመ የግንባታ ውል ቦታው ለቡና መሸጫነት ምቹና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን 1 ሚሊዮን 491 ሺህ 403 ብር ወጪ በማድረግ አድሶና አሳምሮ ስራውን መቀጠሉን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ ችሎት፣ የውል ጉዳዮች ችሎት የቀረበው የክስ መዝገብ ያመለክታል፡፡
ይሁን እንጂ ተከሳሽ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የኪራይ ውሉ መቋረጡን በመግለፅ  ካፌው የሚጠቀምበትን የኤሌክትሪክ የመብራት መስመር በማቋረጥና አገልግሎት እንዳይሰጥ በማድረግ በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱን ከሳሽ ለፍ/ቤቱ ባቀረበው ክስ አመልክቷል፡፡
ተከሳሽ     ውሉን ያቋረጠባቸው ምክንያቶች ከህግና ከስነስርዓት ውጪ በመሆናቸውና ለኪሳራ ስለዳረገኝ ፍርድ ቤቱ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ተከሳሽ 48 ሚሊዮን 272 ሺህ 360 ብር እንዲከፍለኝ እንዲወስንልኝ ሲል መጠየቁን የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን በስልክ የጠየቅናቸው የንኮማድ ኮንስትራሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ መንገሻ “በስልክ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጥም” በማለታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡

Read 2118 times