Saturday, 23 December 2023 11:11

የሞት ቅኔ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ሚስቱን ማመን ካቆመ ቆየ ይህ ደግሞ የሆነው ስራ ተቀጥራ መስራት ከጀመረች ጀምሮ ነው ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ የምታደርገው ነገር በሙሉ እየተከታተለ ጥልቀቱን ሊረዳው የማይችለው ቅናት ውስጥ ገባ፡፡ ቅናቱ ስር እየሰደደ ሄዶ ወደ ንዴትና ጥላቻ አደገ፡፡ ይህም የንዴት ስሜት ህይወት መስርቶ በጭንቅላቱ ውስጥ ታዛውን ከቀለሰ ቆየ፡፡ አሁን ላይ ከቁጥጥሩ ውጭ ሆኖበታል፡፡ አይኖቿ ያበግኑታል፣ ስትራመድ ማየት አይፈልግም፣ እየሳቀች ከሰማት ከዛ አካባቢ መራቅ ነው የሚፈልገው፣ እሱን መውደድ እንዳቆመች ነው የተረዳው፣ እንደ ወንድ የምታየው አይመስለውም፣ ምክንያት ፈልጋ ቤቱን ጥላለት መኮብለል እንደምትፈልግ ነው የሚገምተው፣ ቤተክርስቲያን ልሂድ ብላ ሰንበት ላይ ስትወጣ የገዛ ፈጣሪው ላይ መቅናት ይጀምራል፡፡ ሁሉም ነገር ከጤነኝነት ያፈነገጠ እና እያደገም ሲሄድ ወደ እብደት ሊከተው እንደሚችል ነው እየተረዳ ያለው፡፡
ቢንያም ይህን እያሰበ ቦሌ ካልዲስ ካፌ ውስጥ በትካዜ ውስጥ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ድንገት ግን አንድ ቻይናዊ እሱ ከተቀመጠበት ወንበር ጋር መጥቶ ቆመ፡፡ ዮሴፍ ቀና ብሎ ተመለከተው፡፡ ቻይናዊው ጥርት ባለ አማረኛ ያናግረው ጀመር፡፡
“ይቅርታ የኔ ወንድም አንድ ጊዜ እንዳናግርህ ፍቃደኛ ነህ?”
ቢንያም በደመነፍስ ውስጥ ሆኖ እንዲቀመጥ በአይኑ ምልክት አሳየው፡፡ ምንም ነገር ማውራት ባይፈልግም አሁን ካለበት ሀሳቡ የሚያላቅቀውን ማንኛውንም ነገር ከመሞከር ወደ ኃላ እንደማይል ስለገባው ለቻይናው እንግዳ ፈቀደለት፡፡
ቻይናዊውም አጠገቡ ከተቀመጠ በኃላ ወዲያው ወደ ጉዳዩ ገባ፡፡
“ዛሬ ላማክርህ ይዤልህ የመጣሁት ሀሳብ እጅግ ድንቅ ነገር ነው፡፡ በናዝሬት ከተማ ውስጥ አንድ የሜዲቴሽን ማዕከል አለን፡፡ የማዕከላችን ዋና አላማም የሰው ልጆችን ወደ ከፍተኛው ንቃታቸው እና የማንነት ጥጋቸው ድረስ ሄደው ራሳቸውን እንዲያገኙት ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ላይ ብዛት ያላቸው ሰዎች በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡ በማዕከሉ ውስጥ ከሚሰጡ መንፈሳዊ እውቀቶች መካከል ነፍስን አውጥቶ መጓዝ (Astral projection) እና ነፍሰ ብርሀንን የመመልከት ጥበብ (Aura Reading) ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ቢንያም ካቀረቀረበት ቀና ብሎ ተመለከተው፡፡ ጠበቅ ባለ ንግግርም ጠየቀው …”ነፍስን አውጥቶ መጓዝ ነው ያልከው?”
“በትክክል::” አለ ቻይናዊው፡፡ “ከጥንታዊቷ ቲቤት ውስጥ በተላለፉ አስደናቂ ጥበቦች ላይ መሰረት አድርገን ነው ትምህርቱን የምንሰጠው፡፡”
“ነፍስን አውጥቶ መጓዝ ስትል…ማለቴ ትንሽ ስለነገሩ አስረዳኝ?”
“አስትራል ፕሮጀክሽን ማለት አሁን ያለህበትን ስጋዊ ንቃትህን እንደያዝክ በነፍስህ ያሻህ ቦታ መጓዝን ያካትታል፡፡ አንድ ጊዜ ነፍስህን አውጥተህ መጓዝ ከቻልክ በአካልህ ልትደርስባቸው የማትችላቸው ቦታዎች በሀሳብ ፍጥነትህ ልክ በቦታው መገኘት ትችላለህ፡፡ ህይወትንም አሁን ከምታይበት እይታ ውጭ ሆነህ በአዲስ አይን መመልከት ትጀምራለህ፡፡ የማሰብ አቅምህም የት ድረስ መለጠጥ እንደሚችል በገዛ ጭንቅላትህ ብቻ ተጠቅመህ ትደርስበታለህ፡፡”  
“በሀሳብ ፍጥነት የፈለከው ቦታ መሄድ ትችላለህ ነው የምትለኝ? እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? ይህ እኮ ሊሆን የማይችል ሀሳብ ነው እያነሳህ ያለህው፡፡ ስለ ተሸከምኩት አካሌ ጥልቅ እውቀት የሌለኝ ሰው ነፍሴ የቱ ጋር ትሁን የት ሳላውቅ በእንዴት አይነት መልኩ ላዛት እችላለሁ?”
ቻይናዊው በእርግጠኝነት መንፈስ ፈገግ ብሎ ቢንያምን ካየው በኃላ ይህን ተናገረው…”ጥያቄህ በሙሉ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ከመፈጠራችን በፊት እና ከሞትን በኃላ ያለውን ነገር ላይ ምንም እውቀት የሌለን ሰዎች ነበርን ሆኖም ባደግንበት ቦታ የሚነገሩንን መንፈሳዊ ሚስጥራቶች አድምጠን ያላየናቸውን አለማት አምነን ተቀምጠንም እናውቃለን፡፡ ይህም እውቀት እንደዛው ነው፡፡ ያልተመለከትከውን ሰው ሲጠይቅህ አላውቀውም እንደምትለው ሁሉ በውስጥህ ያለውንም ድንቅ ጥበብ በተመሳሳይ የእወቀት ቅርፅ ውስጥ ሆነህ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፡፡”
ቻይናዊው ከተቀመጠበት እየተነሳ… “ጊዜ ኖሮኝ ስለያንዳንዱ ነገር ባስረዳህ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ሆኖም በማዕከላችን መጥተህ በራስህ መንገድ እና ኢማጅኔሽ እውቀቱን ካላገኘህ በስተቀር እኔ ያልኩህን እያሰብክ ብቻ ነው የምትጓዘው፡፡ በዚህም ውሳኔህን እፈልገዋለሁና ይህች ቢዝነስ ካርዴን ይዘህ ልክ ስትወስን ደውልልኝ፡፡”
…ቢዝነስ ካርዱን ለቢንያም አቀብሎት አካባቢውን ለቆ ሄደ፡፡
ቢንያም የዛን ቀን እንቅልፍ ሳይተኛ አደረ፡፡ በየማህሉ ሚስቱ አቅሊስያን እየዞረ እያያት መናደዱን ግን አላቆመም፡፡ እንዲሁ ጠዋት ላይ ተነስታ ጥላው የምትጠፋ እየመሰለው ነው፡፡ ምን አድርጓት እንደሆነ ግን ሊገባው አልቻለም፡፡ በእርግጥም ነፍሱን አውጥቶ ያሻው ቦታ መብረር የሚችል ከሆነ አቅሊስያ የምትረግጠውን ምድር በሙላ እየተከተለ የምታደርገውን መመልከት ይችላል፡፡ ይህን ደግሞ ከሞት በላይ እረፍት እንደሆነ ተረዳ፡፡
አንድ ጊዜ ዞሮ ተመለከታት፡፡ በህልም ውስጥ ሆና የምትማግጥበት መሰለው፡፡ ሊቀሰቀቅሳት ፈለገ፡፡ ቀስቅሶ አንቺ ጨካኝ ሊላት፤ ምን አድርጌሽ ነው ብቻዬን ልትጥዪኝ ያሰብሺው ብሎ ሊጠይቃት በንዴት ውስጥ ሆኖ ቋመጠ፡፡ ሆኖም እስካሁን አንድም ነገር ያላገኘባትን ሴት ምን ብሎ ዘሙተሸበኛል ይበላት፡፡ ምንም ነገር አይቶባት ባያውቅም እንዲሁ ግን ውስጡ እየደጋገመ ልታመልጥህ ነው ነው የሚለው፡፡ በጣም ይወዳታልና እርግጠኛ መሆን አለበት፤ ለአስራ ሶስት አመታት አብረው ህይወትን እንደመፅሀፍ እያነበቡ ኖረዋልና በድንገተኛ ስሜት ብቻ አመታቶቹን መናድ አልፈለገም፡፡
ሲነጋ ጠዋት ላይ አቅሊስያን ቀስቅሶ ለስራ ወደ ናዝሬት እንደተላከና የሶስት ወር ፕሮጀክት እንዳለበት ነገራት፡፡ ወዲያው አምናው ተስማማችለት፡፡ በፊት ግን ትታገለው ነበር፡፡ አብሬህ ካልሄድኩ ትለው ነበር፡፡ እንዴት ቀድመህ አትነግለኝም ብላው ታኮርፈው ነበር፡፡ ታለቅስ ነበር፡፡ የዛን ቀን ግን ባለው ነገር ያለማንገራገር ተስማማችለት፡፡ ይህም ደግሞ አናደደው፡፡ ምን ስለሆነች ነው ካጠገቧ ስለይ ምንም የማይመስላት ብሎ በውስጡ በገነ፡፡ ምን ያረጋጋት ነገር እንዳለ በፍጥነት ማወቅ አለበት፡፡ የዛን ጠዋት ላይ በቅጡ ሳይሰናበታት ቤቱን ጥሎ ሄደ፡፡
ናዝሬት ከደረሰ በኃላ የቻይናዊው ስልክ ላይ ደውሎ የሜዲቴሽን ማዕከሉ ጋር ከብዙ ፍለጋ በኃላ ለመድረስ ቻለ፡፡
ማዕከሉ ግዙፍ ግቢ ውስጥ የተበጀ ሲሆን በውስጡም ከቅጠሎች መገጫጨት ውጭ የሚሰማ አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡ የሚተነፍሰው አየር ወደደው፡፡ የሚጠበቅበትን ምዝገባ ጨራርሶ አንድ ክፍል ለብቻው ተሰጠውና የመጀመሪያውን ምሽት አቅሊስያ ምን እያደረገች እንደሆነ እያሰበ አደረ፡፡
ነጋ፡፡
ብዙ ንጋቶችን ብቻውን መምህሮቹ የሚነግሩትን የአሰርምሞ ጥበብን እየተከተለ ሰነበተ፡፡
ቢንያም እጅግ የተረጋጋ መንፈስን ብቻ መተንፈስ ከሚችሉት የቡድሂስት አስተማሪ ስር ሆኖ ስለ ነፍስ አሰራር አጠና፡፡ ነፍስን ከቧት ስላለው ብርሀን (ነፍሰ ብርሀን) ምንነት ጥልቅ እውቀት ያዘ፡፡ በነፍስና በስጋችን መካከል ስላለው ድብቅ የንዝረት ህግ ጠንቅቆ ተረዳ፡፡ እንቅልፍ ሲወስደን ነፍሳችንን ይዞ ስለሚተመው ከሰውነታችን ጋር እንደ እትብት ተጣብቆ ስላለው ብርማው ገመድ ላይ እውቀቱ ተመነጠቀች፡፡ እሱና መላው አለም አንድ እንደሆኑና የእሱ እስትንፋስ አለም ላይ ህይወት እንደሚዘራ ተገለጠለት፡፡ በዚህ መሃል ግን ዋና አላማውን አልዘነጋም፡፡ በፍጥነት ይሄን ጥበብ አግኝቶ የሚስቱን መዳረሻ ነው ማወቅ የፈለገው፡፡
ለምን ሲናደድባት እንደምትረጋጋ፣ ለምን ተናዳለች ብሎ ሲያስብ እሷ ግን በተመረጡ አማርኞች ልታረጋጋው ትሞክር እንደነበር፣ የት ነህ…የት ነበርክ እያለች አስሬ የምትጠይቀው ሴት ለምን ድንገት መጠየቋን አቋርጣ በሚላት ነገሮች በሙላ መስማማት እንደጀመረች ማወቅ አለበት፡፡ አስራ ሶስት የትዳር አመታትን እንደቀልድ ማየት አልፈለገም፡፡ ብዙ ትግል ውስጡ አለበት፡፡ አቅሊስያን ነፍሱ ድረስ ወስዶ ተነቅሷታል፡፡ ራሱን ካላጠፋ በስተቀር ሊረሳት የማይችላት ሴት ናት፡፡  
ከብዙ ሙከራዎች በኃላ የመጨረሻው ቀን መጣና ይህ ተከሰተ፡፡
የቡድሂስቱ ጉሩ የማዕከሉን ሰልጣኞች ሰብስቦ ማናገር ጀመረ፡፡
“አሁን ሁላችሁም በዚህ ክፍል ውስጥ ያላችሁ ሰዎች ነፍሳችሁን አውጥታችሁ ለመጓዝ በቂ እውቀት አላችሁ፡፡ ዛሬ ላይም ስትናፍቁት የነበረው የነፍስ በረራ እና የአለማትን ጉብኝት የምትጀምሩበት ቀን ነው፡፡ ሆኖም ለጥንቃቄ ተብሎ የተነገራችሁን በሙሉ መተግበር አትዘንጉ፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን ከዚህ አለም ውጭ ሆናችሁ የምታዩት እይታ አማሏችሁ በዛው እንድትቀሩ ሊያደርጋችሁ ይችላልና ወደ ስጋችሁ መመለሳችሁን አትዘንጉ፡፡  ሁላችሁም የተማራችሁትን ተግባር ላይ ለማድረግ በክፍላችሁ ውስጥ መግባት ይጠበቅባችኃል፡፡ በእያንዳንዳችሁ ክፍል ውስጥ ባለውም ድምፅ ማጉያ ለዚሁ ምትሀታዊ ተግባር ተብሎ የተዘጋጀላችሁን የፍሪኩዌንሲ ሞገድ ይለቀቅላችኃል፡፡ መልካም እድል ለሁላችሁም እየተመኘሁ አሁን ሁላችሁም ወደ ክፍላችሁ እንድትሄዱ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ቢንያም የሚያደርገው ነገር የእብደቱን ልክ ገና መገንዘብ ሳይጀምር ነፍሱን አውጥቶ እንዲበር እየጠየቁት ነው፡፡ ሆኖም የሰው ልጅ ጥልቅ ፍላጎት መፍጠር የማይችለው ነገር እንደሌለ አድርጎ የሚያስብ የሰው አይነት ነበርና የአቅሊስያን ሁኔታዎች በሙላ ለመረዳት እና የሀሳቧ ጥጋት ስር ለመድረስ የሚራመደውን ያህል ለመራመድ ወስኗል፡፡
በክፍሉ ውስጥ ገብቶ  እንደተባለው በጀርባው ተኛ፡፡ ነፍስን እየጎተተ አለማትን በሚያስጎበኘው የሞገድ ድምፅ የሰመመን ስሜት ውስጥ ገባ፡፡ እንደተባለው አተነፋፈሱን እየቆጠረ በሰውነቱ ላይ ያውን ሀይል በሙሉ እኩል ለማድረግ ሞከረ፡፡ ሰውነቱ እንደ እፉዬ ገላ እየቀለለው መጣ፡፡ ሰውነቱ የከተመበት የስሜት ዳገት እንደ ህልም የሚመስለው ነው፡፡ ነገር ግን ህልም አይደለም፡፡ በሰውነቱ ላይ ከባድ የሆነ የኤሌክትሪክ ንዝረት ተሰማው፡፡ ልክ ይህ እንደተሰማው በፍጥነት ነፍሱ ስጋውን ለቃ ወጣች፡፡
የምትንሳፈፈው ነፍሱ ብቻ ናት እያሰበች ያለችው፡፡ ከስጋው ጋር ተዳብሎ የነበረው እውቀት አሁን ላይ የለም፡፡ በነፍስ አካሉ ውስጥ ሆኖ ዞሮ የገዛ አካሉን በአልጋው ላይ ተኝቶ ተመለከተው፡፡ ድንጋጤ ውስጥ ገባ፡፡ የሚያየውን ማመን አቃተው፡፡ የምር ሞትን ሳይሞት ሞትን እየሰለጠነው መሰለው፡፡ በህይወትም በሞትም ውስጥ ሆኖ እንዴት ራሱን ማግኘት እንደቻለ ለወራት ሰልጥኗልና እዚህ ሀሳብ ላይ በመፈላሰፍ ጊዜውን መፍጀት እንደሌለበት አውቋል፡፡ አሁን ላይ ከአዲሱ አካሉ ጋር ለጥቂት ጊዜም ቢሆን መላመድ ነው ያለበት፡፡ በክፍሉ ውስጥ ሆኖ እንደ እንግዳ ሰው በአልጋው ላይ ተኝቶ ያለው ራሱን ተመለከተው፡፡ አስቀያሚ ሰው ነኝ ብሎ ማሰብ ጀመረ፡፡ እስከዛሬ ሲያፈጥበት የነበረው መስታወት ሲዋሸው እንደከረመ ደረሰበት፡፡ ለካ እስካሁን መልኩ ምን አይነት እንደሚመስል ራሱ በራሱ አይን ነው ማየት የነበረበት፡፡
ጊዜውን ማባከን የለበትም፡፡ በፍጥነት የነፍሱ የህይወት ትንፋሽ ወደሆነችው ባለቤቱ አቅሊስያ በሮ እየሆነ ያለውን ነገር ማወቅ አለበት፡፡
በነፍሱ ውስጥ ያለውን ንቃት ተጠቅሞ አቅሊስያ ያለችበት ቦታ እንዲሰደው የገዛ እውቀቱን በሀሳብ ቃላቶች ጠየቀው፡፡ በሀሳብ ፍጥነት በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ራሱን አገኘው፡፡ የተከሰተው ክስተት ስለፈጠረበት ድንጋጤ እኔ ደራሲውም ብሆን ለማስረዳት ይቸግረኛል፡፡ ሆኖም ቢንያም አሁን ሆስፒታል ውስጥ ባለ አንድ ክፍል ውስጥ ነው ያለው፡፡ ከፊት ለፊቱ አንድ ዶክተርና ከሱም በተቃራኒ አቅሊስያ ተቀምጣ እያያቸው ነው፡፡ የፈራው ነገር እንዳይከሰት በነፍሱ ንቃት ውስጥ ሆኖ ለፈጠሪው ቅፅበታዊ ፀሎት አደረሰ፡፡
ዶክተሩ በሀዘኔታ አቅሊስያን ሲያናግራት ተመለከተና ፀሎቱን አቋርጦ ትኩረቱን ወሬያቸው ላይ አደረገው፡፡
“አቅሊስያ አሁን በሀዘን ህይወትሽን መግፋት የለብሽም፡፡ ያለሽን ጊዜ ከምትወጂያቸው ሰዎች ጋር በደስታ ማሳለፍ ነው ያለብሽ፡፡ ብዙ የሚወዱሽና የሚያከብሩሽ ሰዎች አሉ….
አቅሊስያ አቋርጣው መናገር ጀመረች፡፡
“ባለቤቴ ቢንያምን ምን ልለው እችላለሁ? እንዴት አድርጎ ያምነኛል? ምን ያህልስ ሊያዝን ይችላል?” ቢንያም ይህንን ሲያደምጥ ከዛ አካባቢ ጥፋ ጥፋ የሚል ስሜት ውስጥ መግባት ጀመረ፡፡ ሆኖም እሱ ራሱ ያልተረዳው ሀይል ባለበት ቆሞ የባለቤቱን ንግግር እንዲያደምጥ ያዘው ጀመር፡፡ እሱም እንደዛው አደረገ፡፡
አቅሊስያ ከተከዘችበት ቀና ብላ ዶክተሩን መጠየቅ ጀመረች፡፡  “አንተ እኔን ብትሆን ምን ብለህ ነው ለቢንያም የምትነግረው?”
ዶክተሩ በሀዘኔታ እያያት መለሰላት “ መሞታችን በተፈጥሮ የተሰጠን ግዴታችን ነው፡፡ መች እንደምንሞት ማወቃችን ምናልባት በምድር ላይ ቀሩብን የምንላቸውን ነገሮች እንድናደርግ ይረዱን ይሆናል… ሆኖም አንቺ ብቻ አይደለም የምትሞቺው…ሁላችንም መንገዳችን ወደዛው ነው፡፡ ቢንያምም ቢሆን፡፡”
“ካንሰር እንዳለብኝ እኮ እስካሁን አያውቅም፡፡ ለመሞት ሁለት ወራቶች እንደቀሩኝ እስካሁን አያውቅም፡፡ እሱ የሚያውቀው ከልጅነቱ በምኞቱ ፀንሶት ያለውን ዮሴፍ ብሎ በቅድሚያ ስም ያወጣለትን ወንድ ልጁን እንደምወልድለት ነው፡፡ እሱ የሚናፍቀው አሁን ካለንበት ቤት ወጥተን የተሻለ ኑሮ መኖራችንን ነው፡፡ እሱ እየለፋ ያለው እኔ ምንም ሳልለፋ እንደልዕል እንድኖርለት በማሰብ ነው፡፡ የትኛው ድፍረቴ ነው ከሱ ፊት አቁሞኝ የዛሬ ሁለት ወር እሞታለሁ እንድለው እድል የሚሰጠኝ? የትኞቹ አይኖቼ ናቸው አይኖቹን እያዩ እስካሁን የለፋህው ልፋትህን ሞት የተባለው እርግማን ተረጋግቶ ሊያወድምብህ ነው ብዬ በድፍረት ውድቀቱን እንድተርክለት የሚሰብኩኝ፡፡ ፈራሁ እኮ ዶክተር…ገና ሳልሞት የሞትና የፍቅር ሀይል በቁሜ አሰቃየኝ፡፡ ባህሪዬን ቀይሬበትም በፀጥታው ውስጥ ያወራኝ፡፡ መውደዱን መናፈቁን ይነግረኛል፡፡ በምድር ላይ ብቻችንን ነን፡፡ ለኔም ለሱም ያለነው አንደኛችን ለአንደኛችን እየተሳሰብን ነው፡፡ አሁን ለስራ ወደ ፊልድ ሄዷል፤ ከስራ ሲመጣ ከሚለፋላት ሚስቱ ጋር ሳይሆን ጨክና ከሞት ጋር ካመለጠችው ጨካኟ ባለቤቱ ጋር ነው የሚገናኘው፡፡ ሳልነግረው ስሞትበት ምን ይለኛል፡፡ ለምን ሀዘኑን ከማይ ብዬ እውነቱን ልደብቅበት፡፡ ለምን ጨከንኩበት፡፡ አሁን እየከበደኝ ነው፡፡”
ዶክተሩ ተስፋ በመቁረጥ ባለበት ሆኖ አቀረቀረ፡፡ አቅሊስያ በቀጣይ ለማውራት ሞክራ የገዛ የእንባዋ ሳግ ስለተናነቃት ክፍሉን ለቃ ወጣች፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ማልቀስ በማይችለው ነፍሱ፣ መጮህ በማይችለው አንደበቱ፣ መሮጥ በማይችለው እግሩ ከክፍሉ ሰማይ ላይ ተንሳፎ የሚያየው ቢንያም የሚያደርገው ጠፍቶት እየጠፋች ያለችውን አቅሊስያ በአይኑ ብቻ ሸኛት፡፡
እስካሁን ሚስጥር የሆነበትን ነገር ምላሹ ነፍስን በሚሸረካክት መንገድ ደረሰበት፡፡ አቅሊስያ ልትሞት ሁለት ወር ነው የቀራት፡፡ አቅሊስያ ካንሰር ይዟታል፡፡ አቅሊስያ እየዘሞተች አልነበረም፡፡ አቅሊስያ ቢንያምን ትወደዋለች፡፡ አቅሊስያ ልትሞት ነው….እነዚህ አረፍተነገሮች እንደ ፈረስ እየጋለቡ ነፍስያውን ይዞሩት ጀመር፡፡ በነፍሳዊ ንቃት ውስጥ ሆኖ መሞትን ተመኘ፡፡ ሆኖም የማይሞተውን ማንነቱን ይዞ ነው ከዚህ እውቀት ጋር የተዋወቀው፡፡ ሁሉም ነገር አስፈራው፡፡ ሆኖም ድንገት አንድ ሀሳብ ብልጭ አለለት፡፡ ወደ አካሉ ካልተመለሰ በዛው መቅረት ይችላል፡፡ ይህንንም የቡድሂስቱ ጉሩ አስተምረውታል፡፡ አዎ…ወደ ስጋው መመለስ አይፈልግም፡፡ ምን ቀረኝ ብሎ፡፡ የምትሞተው ሚስቱን ሞቶ ይጠብቃታል፡፡ የምትሞተው ሚስቱ ጋር አብረው ሞተው ልትበትናቸው ያለችውን ህይወት ድል ይነሷታል፡፡
ከዛን ቀን አንስቶ ቢንያም በነፍሱ እየበረረ በየቤተክርስቲያ ደጃፍ እየዞረ ከአቅሊስያ ጋር አብሮ አለቀሰ፡፡ ሙሾን አወረደ፡፡ ጥሎት የሄደውን የገዛ ስጋውን ረስቶት የሚናፍቃትን ነፍስ ከነፍስ እቅፉ ውስጥ እስክትመጣለት ድረስ አብሯት ሰነበተ፡፡ የምትሞትበት ቀናት ድረስ ሞቶ ተከተላት፡፡ የጠረጠራት ድረስ አስታውሶ እየደጋገመ ወደዳት፡፡ ህይወት በግሳንግስ ትርምሶቿ የቀማቻቸው እምነት እና ፍቅራቸውን በሞት ቅኔ ውስጥ አስመለሱት፡፡

Read 657 times