Saturday, 23 December 2023 11:15

አንድ እግር

Written by  ራሄል ይትባረክ
Rate this item
(3 votes)

 ሁሉም ይጮህ ነበር። ስሜቱን በጩኸትና ዋይታ መግለጽ ለማልችል ለእኔ፣ ምን ያህል ከባድ ጊዜ እንደነበር ማስረዳት ያዳግታል። በጣም ነበር የምወደው። መውደድ እሱ ለእኔነቴ የሆነልኝን ከአከለ፣ አዎ በጣም  እወደዋለሁ።
አባት ከሆነበት ቀን ጀምሮ እኔን ስትወልድ ያጣት አካሉን፣ ሕመምና ቁስል በእኔ ፈገግታ እያከመ የኖረ ሰው ነበር። ቤት አጽድቶ፣ ምግብ አብስሎ፣ ልብስ አጥቦ፣ እንጀራ ጋግሮ… ብቻ ቤት ውስጥ  ሁሉን ነገር ሞልቶ ነው ያሳደገኝ። ፀጉሬን አጥቦ፣ ሹርባ ሳይቀር ይሠራኝ ነበር።
የእናትና አባት ፍቅር የማያውቀው አባቴ፣ ለእኔ እናትም አባትም እንዴት መሆን እንደቻለ ሳስብ እደነቃለሁ። ምናልባት በአካል  የማላውቃት፣ ከአባዬ አፍ ግን ጠፍታ የማታውቀው እናቴ፣ ምን አይነት ፍቅር ሰጥታው ይሆን ስል አስባለሁ። አባዬ ሁሌ የሚለኝ ነገር ነበር!
“እኔ እናቴም አባቴም እህቴም ወንድሜም እግዚአብሔር  ነው።” ምን ማለት እንደሆነ የገባኝ አባቴ ከሞተ ከአርባ ቀን በኋላ፤ አንድም ሰው አጠገቤ ሳጣ ነበር። “ዋይ! ዋይ!” ብሎ ቤቱን ሲያተራምስ የነበረ ሰው ሁሉ ያኔ ጠፋ። ቤታችን ኦና ሆነ። ዝም፤ ጭጭ።… ብቻዬን ቀረሁ። እንደ እሱ የሚሆንልኝ ቀርቶ፣ እንደው ነበር እንኳ ለማለት የሚሆን ሰው አጠገቤ አላገኘሁም።
ያኔ አባቴን ብቻ አይደለም፣ የማላውቃት እናቴንም ጭምር  ናፈቅሁ። ከእኛ ጋር አለመኖሯ አንድም ቀን ተሰምቶኝ የማላወቀው፣ እናቴ ብትኖር ብዬ ተመኘሁ። አባዬንማ የማላስብበት፣ እሱን የማያስታውሰኝ ነገር አልነበረም። ከራሴ ጋር ብዙ ታገልሁ። ግን ልረሳው አልቻልሁም። ታሪኬን  ልጽፍ የወሰንሁትም አባዬን ለመርሳት ያደረግሁት ጥረት ባለመሳካቱ፣ በጊዜ ሂደት ስለእሱ እያሰብኩ መታመምንም ቢሆን መውደድ ስለጀመርኩ ነው።
በእኔ ውስጥ አባዬ በብዙ አለ። ከልጅነቴ አንሥቶ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እስክጨርስ ከሥሩ አልጠፋሁም። በሁሉም የሕይወቴ አጋጣሚዎች አብሮኝ ነበር። ስደሰትም፣ ስከፋም፣ ስጨነቅም፣  ሁሉን ሳልነግረው ያውቅ ነበር። የሆነ ነገር ሲያስፈልገኝ እንኳ እስክጠይቀው አይጠብቅም። እንዴት እንደሆነ እንጃ ብቻ ሁሉን ነገር ያውቅልኝ፣ ያውቅብኝ ነበር።
ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቅሁ በኋላ አባዬ ብዙም ሳይቆይ ስለተለየኝ ብቸኛ ሆኜ ነበር። ልማድ ምን ያህል ሊጎዳ እንደሚችል ለማየት ጊዜ አልፈጀብኝም። ጠዋት ስነቃ ሮጬ ሄጄ ልስመው ያነሳሁትን እግሬን አጥፋለሁ፤ ቁርስ አብስዬ ስጨርስ፣ ”አባ ቁርስ ደርሷል!” ብዬ ልጠራ የከፈትሁት አፌን መልሼ እዘጋለሁ፤ የቤታችንን የውጭ በር ዘግቼ ስወጣ፣ እጁን ልይዘው የዘረጋሁት እጄን እሰበስባለሁ፡፡ ምሳ ሰዓት የሚደውል እየመሰለኝ ስልኬ በጮኸ ቁጥር ልቤ ድንግጥ ይልብኛል። ማታ እንደለመድነው ከቤታችን አቅራቢያ ካለችው ኪዳነ-ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በር ላይ የሚጠብቀኝ እየመሰለኝ ዐይኔ ይንከራተታል። ጸሎታችንንም አድርሰን ስንጨርስ እናደርገው እንደነበረው፣ እዚያው መንገዳችን ላይ ካለች ሻይ ቡና ከምንልባት ካፌ ልገባ እልና አባ እንደሌለ፣ ቀድሞ ሣቅና ጨዋታ  እንደሌለ ሳስብ ትቼው አልፋለሁ። ሁሉ ቦታና አጋጣሚ ትዝታ ይጭራል።
እናቴ እኔን ስትወልድ በማለፏ፣ ቤታችን ውስጥ  የኖርሁበት ትዳር አልነበረም። ግን ስለ ትዳር፣ ስለ እናትና አባት ድርሻ ሁለቱንም ሆኖ አስተምሮኛል። አሁን ላለኝ ሕይወት፤ ከእኔ ተርፎ ለባሌና ለልጆቼ የምሰጠው ፍቅር፤ ከአባቴ የሸመትሁት እንደሆነ አስባለሁ።
በእኔ ያለ መልካም ነገር ሁሉ የአባዬ ነው። እኔን ሲወድ፣ በዙሪያው ላሉት ሰዎች ስሜት ሊጠነቀቅ፣ አንድም ነገር እንዳይጎድልብኝ  ከዕድሜውና ከአቅሙ በላይ ሲሠራ፣ ሰው ሲረዳና እንዲህ ነው ብዬ መግለጽ የማልችለው ዓይነት ፍቅር ሲያሳየኝ ነው ያደግሁት። አባዬ ካለፈ እንደ ዋዛ ዐሥራ አምስት ዓመት ሆኖታል። ፈገግታው፣ ሣቁ፣ ጨዋታው፣ እንደ ቀልድ አድርጎ የነገረኝ ቁም ነገሩ፣ ኋላም የሕይወቴ መርህ ያደረግኋቸው ነገሮቹ ሁሉ ትላንት የሆኑ ያህል በግልጽ ይታዩኛል። እሱ ከነገረኝ ነገር ጠብ ያለ አልነበረም። እንዴት ካላችሁኝ፤ ሕይወቴ ባጭሩ አባዬ ያለኝን ሰምቼ ያለፍኩትና፣ ያለኝን ችላ ብዬ የወደቅኋቸው ፈተናዎች ድምር ነው።
አባቴ በምድር የማውቀው እግዚአብሔር ነው። ይህን ሆኖ ደግሞ የሰማዩ አባቴን አሳይቶኛል። በደግነቱ፣ በእንክብካቤው፣ በጥበቃው የሰማዩን አምላክ ፍቅር በልቤ ስሎልኛል። አጠፋሁም አለማሁም እሱ ለእኔ ያው ነው።
ሳጠፋ የጥፋት መንገዴ እንደማይመቸኝ ስለሚያውቅ እስክመለስ ይጠብቀኛል። በቤቱ የለመድሁትን ደስታ ሽቼ እንደምመለስ አይጠራጠርም ነበር። ነጋም ጠባም ደስታና ሰላም የማይጎድላት ጎጆው በር ላይ ሆኖ ይጠብቀኛል። ስመጣ ከሩቅ ያውቀኛል። አይቆጣም። ክፉ ቃልም ከአፉ አይወጣም። ይልቁንም አቅፎ ስሞ ይቀበለኛል። ከሌላው ቀን አብልጦ ፍቅር እንክብካቤንም ይሰጠኛል።
ይህን ለምን እንደሚያደርግ ለረጅም ጊዜ ጥያቄ ፈጥሮብኝ ነበር። ቆይቼ የተረዳሁት ግን ከእኔ በላይ ጉዳቴ ስለሚሰማው እንደሆነ ነበር። ከምክሩ ወጥቼ ባልታረመ መንገዴ ላይ  መኳተኔ፣ ከእኔ በላይ ስለሚያመውና ስለሚደያክመው እንደነበር ገብቶኛል።
ሲያመኝ፣ ከሕመሜ በላይ ፊቱ  ላይ ሊደብቀው የሚታገለው ጭንቀቱ ይሰማኝ ነበር። ትዝ ይለኛል፣ አንድ ቀን ትምህርት ቤት ታምሜ ተደውሎለት፣ ሲከንፍ መጥቶ አቅፎኝ ያለቀሰውን አልረሳውም። ለየትኛውም ፈተና እጅ የማይሰጠው ቆራጡ አባቴ፣ የሆነ ነገር ስሆንበት (የእናት አንጀትም ስላለው ነው መሰለኝ) እንባውን መግታት አይችልም።
አባ ልዩ ሰው ነው። አድልቼለት አይደለም፤ ምክንያቱም ለራስ ማድላትን አላሳየኝም። ነፍስ ከአወቅሁ ጀምሮ ለእኔ ሲል ሰምቼው አላውቅም፤ ያገኘውን ነገር ሁሉ ለእኔ ይተው ነበር። ለራሱ የሚቀይረው ጫማ ሳይኖረው፣ ለእኔ ሁለት ሦስት፤ ከዚያም በላይ ይገዛል። ለአንተስ ስለው፣ “አንቺ እኮ እኔ ነኝ!” ይለኝ ነበር። ለእኔ በማድረግ ውስጥ ፍጹም ይደሰታል። አባ እኔን ከአገኘ በኋላ ለራሴ ያለው ሕይወት አልነበረውም።
ይልቁንም፣ እኔም ምሳሌውን ተከትዬ “ለእኔ ብቻ” እንዳልል በቃልም በግብርም ያበረታኝ ነበር። ለምሳሌ ወደ ትምህርት ቤት እየሸኘኝ፣ ትምህርት ቤት በር ጋር ልንደርስ ስንል የያዘልኝን ቦርሳና ምሳ ዕቃዬን እየሰጠኝ፣
“እማ ከከተትሁልሽ ምሳ ስትበይ ትንሽ ማስተረፍ አትርሺ እሺ!?” ብሎ ግንባሬን ይስመኛል።
“እንዴ አባዬ፣ ካልጠገብኩስ!?” እለዋለሁ።
“እናቴ ብዙውን እኮ አንቺ ትበያለሽ፣ ትንሿን ደግሞ በጣም የራበው ሰው  ስለሚኖር ለእሱ ትሰጫለሽ!”
ብዙ ባላምንበትም፣ ወይም ባይገባኝም፣ አባዬ ስላለኝ እሺ ብዬ፤ አጎንብሶልኝም ወደሚርቀኝ ፊቱ ተንጠራርቼ ስሜው እገባለሁ። ሰዓት ደርሶ ከትምህርት ቤት ይዞኝ ሲመለስ፣ መንገዳችን ላይ ላሉ የኔ ቢጤ እሱ ያስተረፈውን ምሳ ሲሰጣቸው፣ እኔም ምሳ ዕቃዬን አውጥቼ እሰጣለሁ። ታዲያ እንዴት በደስታ ይቀበሉንና ይመርቁን እንደነበር ትዝ ይለኛል። ይህንንም አባዬ ሲያደርግ እኔም የማደርገው የእሱ የህይወት መርህ እንጂ ምጽዋት ነው ብዬ አስቤው አላውቅም።
አሁን ከአደግሁ በኋላ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ላይ የሚሰጡን የምግባር ትምህርቶች፣ እኔ በልጅነቴ የአባዬ ሕይወት መርሕ ናቸው ብዬ የተቀበልኳቸው ነገሮች መሆናቸውን ሳይ፣ አባቴ ምን ያህል ለእግዚአብሔር ቅርብ እንደነበር አስባለሁ።
ማታ ማታ ከመተኛታችን በፊት እግሩ ላይ አስተኝቶ ጸጉሬን እያባበሰ ቀኔን እንዴት እንደነበር ይጠይቀኛል። እኔም፣ “እንዲህ ሆኖ፣ በዚህ ገብቶ፣ በዚያ ወጥቶ… “ እያልሁ የባጡንም የቆጡንም ሳወራ በትዕግስት ይሰማኛል። በዚያው አውቄውም ይሁን ሳላውቅ ያጠፋሁትን ሁሉ እነግረዋለሁ። ከጓደኞቼ የሰረቅሁትን እርሳስ፣ ሳልናገር ወስጄ የላስሁትን ስኳር…. ብቻ ሁሉም አይቀርም፤ እናገራለሁ። አንድም ቀን ግን ለምን እንዲህ ሆነ ብሎ ፊቱን አያጠቁርም። የሠራሁት ስራ ልክ እንዳልሆነና የሰረቅሁትንም እርሳስ እንድመልስ ይነግረኛል። ሌሎች ጥፋቶቼንም በዚህ መልኩ ነበር የሚያርመኝ።
በተለይ ከፍ ካልሁ በኋላ ዱላ ይገባኝ ነበር በምልባቸው ስሕተቶቼ እንኳን በትዕግስት መክሮ ሲያልፈኝ እንባዬን መቆጣጠር ያቅተኝ ነበር። ከአሰብሁት በታች ሲቀጣኝ፣ ልቤ የባሰውኑ በጥፋቴ ይጸጸት ነበር። ንስሐ ማለት ይሄ ነው ብሎ ግን ነግሮኝ አያውቅም።
በርግጥ፣ ስለጸሎት ምንነት ሳይነግረኝ፣ ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት እንደሚወራ ያስተማረኝም አባዬ ነው። በልጅ አንደበቴ ጠዋት ከመኝታዬ ስነሳ እግዚአብሔርን “እንዴት አደረህ?” ብዬው፤ ማታ ስተኛ ደግሞ “ደህና እደር እግዚአብሔር” ብዬ እተኛ ነበር። ያ ንግግር ግን ጸሎት እንደሆነ ያወቅሁት ከአደግሁ በኋላ ነው። ብቻ  ብዙ ነገር። ብዙ መልካም ነገር አስተምሮኛል። ለዚያ ነው በምድር የማውቀው እግዚአብሔር እሱ ነው የምለው። ከእሱ የምደብቀው፣ እሱ ያላየብኝ የሕይወት ገጠመኝ የለኝም። ምን ያህል እንደሚተማመንብኝ ሳስብ፣ እንዴት ይህን ያህል እምነት እኔ ላይ ሊኖረው ቻለ እያልሁ እገረማለሁ። ለነገሩ፣ እኔም፣ ራሴን ከማምነው በላይ እሱን አምነው ነበር። የነገረኝንም ነገር ሁሉ እንደ መጽሐፍ ቃል አምንና አከብር ነበር።
“አናየውም እንጂ እግዚአብሔር እኮ እኛ ቤት ነው!” ብሎ ከነገረኝ በኋላ፣ አምላክን ቤታችን ውስጥ እንዳለ ሦስተኛ ሰው እቆጥረው ነበር። ስለዚህም ገበታ ስንሠራ አንድ ተጨማሪ ሳህን ለእሱ አስቀምጣለሁ። ስንተኛም አባቴን “ጠጋ በልለት” እለው ነበር። ለረጅም ጊዜ በእምነቴ እየተደነቀ ከእኔ ጋር አብሮ እንደ ልጅ ይሆን ነበር።
አባዬ ካስተማረኝ ከዚህ ሁሉ ነገር፣ ያልተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ እግዚአብሔርን በእሱ ልክ ማሳነሴ ነበር። ለአባቴ ካለኝ ፍቅር የተነሳ፣ በአባቴ በኩል በጥበብና በሞገስ ሲያሳድገኝ የነበረውን አምላክ ዘነጋሁት። አባቴ ያደረገልኝ ነገር ሁሉ ከእሱ ብቻ እንደሆነ አስቤ ህይወቱን ሙሉ ያስተማረኝ ትምህርቱን አሳነስሁበት።
“እግዚአብሔር ውለታ አያስቆጥርም” ይለኝ ነበር። እውነቱን ነው። አንድም ቀን ከአባቴ በፊት አመስግኜው አላውቅም። ይህ እንዳይሆን አባ ብዙ ጊዜ ቢነግረኝም፣ እኔ ግን ከረፈደ ተረዳሁት።
ለዚያም ነው ልክ አባን ከአጠገቤ ሳጣው ሰማይ ምድሩ የተደበላለቀብኝ። ተስፋ ቆረጥሁ፤ ልቤን ሰንጥቆ እስኪሰማኝ አዘንሁ፤ ታመምሁ፤ ያለ እሱ ምንም ማድረግ የማልችል እንደሆንሁ ተሰማኝ። እግዚአብሔርንም ወቀስሁት። ከአባዬ አልጋ አጠገብ ካለው የጌታችን የስቅለቱ ስዕለ አድኅኖ ስር ቁጭ ብዬ አማረርሁት። ከዚያ ቆይቼ ሳስበው ነው ልወቅስበት ከስሩ የተቀመጥሁት ሥዕለ አድህኖ ፍቅሩን ለማድነቅ እንጂ፣ ለወቀሳ እንደማይመች ያስተዋልሁት።
ጌታችን በር የሚያንኳኳበት እንኳ ቢሆን፣ “የአባዬ አርባ ካለፈ በኋላ የተዘጋ ደጄን ለምን አታንኳኳም? ምናለ ሰው የሰለቸው በሬን ብትመታ? ሳዝን የሚያጽናናኝ አባቴን ከወሰድህ፣ እኔን ማጽናናት ያንተ ድርሻ ነውና  አይዞሽ በለኝ! አባቴ እንደሚያደርገው ጸጉሬን  እያሻሸህ-አባብለኝ---” ሌላም ብዙ ብዙ ልለው እችል ነበር። ነገር ግን የእሾህ አክሊል የደፋ፣ የተቸነከረ፣ በመስቀል የተወጠረ እንኳን የአንድ ሰው ሀዘን እስከዛሬ የሰው ልጅ የተሰማው ህመም ቢደመር የእሱ ሕማም ጋር ሊደርስ የማይችል፣ ረሀብ፣ ጥም፣ ግርፋት ያደከመውን ጌታ ምን ይሁን ብዬ እንደወቀስሁት ሳስብ አዝናለሁ። ፊቱ እንዲያ ደም ለብሶ እያየሁ ምን አድርግ እንዳልሁት አላውቅም።
ከአባዬ ቀብር በኋላ፣ የእሱን ቁርባን ለመክፈል ካልሆነ በስተቀር ለረጅም ጊዜ ቤተ ክርስቲያን አልሄድም። ኩርፊያ መሆኑ ነበር። መንገዴ ላይ ያለችውን ኪዳነ ምሕረት እንኳን ሳልሳለም ነበር የማልፈው። ጭንቅ አማላጇን አጽናኟን አልፌ ማን እንዲያጽናናኝ፣ ማን ከህመሜ እንዲያድነኝ ፈልጌ እንደነበር እስካሁን ሳስበው ግራ ይገባኛል።
በአንድ እግሬ ነበርሁ። እንኳን ወደፊት መሄድ ያለሁበት ቦታ ላይ መቆም ከብዶኝ ነበር። “ጎዶሎ ነኝ!” የሚለውን አስተሳሰቤን ማከም ደግሞ ከዚያ በላይ። የእኔ አንድ እግር አባ ነበር። አንድ እግር ሲጎድል ሌላ ድጋፍ ካልመጣ በስተቀር መሄድ ይቅርና መቆም ይከብዳል።ብዙ ህልም ነበረኝ። ብዙ ወደፊት ያልኋቸው፣ ነገ ይደርሳል ብዬ ዛሬ ያልተራመድኋቸው ብዙ የሕይወት ጉዞዎች ነበሩኝ። ነገር ግን ጊዜ ቀደመኝ። አባዬን ወስዶ፣ በአንድ እግሬ አስቀረኝ። ለእሱ ሳልኖርለት ሄደ። ይህን ህመም ጨርሶ ከውስጤ ላወጣው አልቻልሁም ነበር። ጸጸት እንደ እሳት ሲፈጀኝ ይሰማኛል። በሰዓቱ ምንም ላደርገው የምችለው ነገር ባይኖረኝም፣ እንዲህ ቢሆን ኖሮ በሚል ከንቱ ምኞት ራሴን ቀጣሁ። አባን መጦር፣ የልጅ ልጁን ማሳየት።… በቃ ሁሉም ሕልም ሆኖ ቀረ። አባ ላይመለስ፣ በአንድ እግሬ ጥሎኝ ሄደ።
ሕይወትም ክፉ ገጿን አሳየችኝ። የምደገፈው፣ የምጠጋው አንዳች ነገር እንደሌለኝ አይታ እንዴ ወዲህ፣ አንዴ ወዲያ አንገላታችኝ። አባቷን ያጣች፣ ጠባቂ የሌላትን ልጅ ማን ይንከባከባታል? ማንስ የኔ ብሎ ይመለከታታል?  በአባዬ ትከሻ ላይ ምቾትን የለመደ ሰውነቴ ከሳ፤ ጎሰቆለ።
ዓለም የት ወስዳ እንደጣለችኝ በማላውቅበት በዚያ ሰዓት አባዬ በነገረኝ የጠፋው በግ ታሪክ ውስጥ ያለው መልካም እረኛ፣ ቢመጣ ብዬ ተመኘሁ። እስኪያገኘኝ እንዲፈልገኝ፣  ሲያገኘኝም እንዲያቅፈኝ ፈለግሁ። እንደ አባዬ እቅፍ የሚያሳርፍ፣ የሚያሞቅ ዕቅፍ ውስጥ  እንዲያስገባኝ።  አይዞሽ የሚል፣ የሚያባብል እቅፍ። በአንድ እግሩ ለቀረ ለእንደኔ ዓይነት ሰው ምርኩዝ የሚሆን ዕቅፍ።
ከዚያ… ቃላትን ማሸከም ከሚያዳግተኝ፣ ከብዙ ሕመም በኋላ  የአባዬን ኅልፈት ለማመን መሞከር ጀመርሁ። እሱ የሌለበትን ቀዝቃዛ ቤት መልመድ እንዳለብኝ ለራሴ ነገርኩት። ስለ እሱ እያሰበ ልቤ እንዲሰቃይ  ፈቀድሁለት። መቃብር ስፍራው እየሄድሁ ብዙ አለቀስሁ። ጽኑ ያልሁት አባቴ ከአፈር  በታች እንደቀረ፣ አይረታም ያልሁት ክንዱ እንደተሸነፈ፣ ከሁሉ አብልጬ የምወደው ጠረኑ እንደተቀየረ ውስጤ እስኪቀበለው መቃብር ስፍራው እየተመላለስሁ ተመለከትሁት። አባ የለም።… ሞቷል።
ለካ ሁሉም የለም አልሁ። ማንም እንደሌለኝ እናትም፣ አባትም፣ እህትም፣ ወንድምም።አባ እንደሚለው እግዚአብሔር መሆኑን ሕይወት በራሷ ምስክር ሆነችኝ። ለመራመድ ድጋፍ እንደሚያስፈልገኝ፣ በአንድ እግሬ መቅረቴን ተቀበልሁ። ከዚያ ሕመም በኋላ ግን ዳግም ላጣው የምችለውን ነገር መደገፍ አልመረጥሁም።

Read 375 times