Saturday, 23 December 2023 11:04

በኢትዮጵያ ለ3ኛ ጊዜ የተካሄደው ዓለም አቀፍ የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ማክሰኞ ህዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም  በጀርመን፣ ጎተ የባህል ማዕከል በተከናወነ  እጅግ አስደሳችና አስገራሚ በሆነ ዝግጅት ተጠናቋል። ፊልሞቹን ካዩ በኋላ በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙት ብዛት ያላቸው ትምህርት ቤቶች መካከል የስምንት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ በሀገራችንም ሆነ በአለማችን  ችግር ፈጣሪ  የሆኑ ፕላስቲኮችን ጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ የሰሯቸውን አስገራሚ ስራዎችና ስለ አፈር መሸርሸርና አካባቢ ጥበቃ ለአንድ ወር ያህል ያደረጉትን ምርምር ውጤቶች ይዘው ቀርበዋል።
በዚህ አስገራሚ የመዝጊያ ፕሮግራም ላይ፣ የመሀል ግንፍሌ፣ እየሩሳሌም፣ ዳግማዊ ሚኒሊክ፣ ፎፋን/ሰላም፣ ጃካራንዳ፣ ጀርመን ቸርች ፣ ብሔረ ኢትዮጵያ እና ዋን ላቭ  አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተሳተፉ፤ ሲሆን ከወዳደቁ ፕላሲኮች፣ ከቤት ማጌጫ እቃዎች ጀምሮ፣ የቤት ውስጥ ችግር መፍቻ ማሽኖች፣ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ የሚያስችሉ የኮንስትራክሽን አጋዥ እቃዎችን አክሎ፣ በራሪ ሂሊኮፕተር የመስራት ጥረቶች ታይተውባቸዋል።  ተማሪዎቹ ያቀረቧቸው ስራዎች ብዙዎቹ በአለም አቀፉ የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ተመርጠው ከመጡት ስራዎች እጅግ የተሻሉና ፍፁም የአዕምሮ ፈጠራ ውጤቶች ነበሩ። እነዚህን ስራዎች ተማሪዎቹ እንዲሰሩ ከፍተኛ እገዛ ላደረጉ መምህራንና ርዕሰ መምህራን ከፍ ያለ ልባዊ አድናቆታችንን እናቀርባለን።
የስምንቱም ትምህርት ቤት ተማሪዎች ያቀረቧቸው ስራዎችና ስለስራዎቻቸው ያቀረቡባቸው መንገዶች፣ ለሳይንስ ያላቸው ፍቅርና ለፈጠራ ያላቸው ጉጉት እጅግ አስገራሚ ነበር። በአብዛኛው ስራዎቻቸው የአካባቢያቸውን ችግር ለመፍታት ያላቸውን ልባዊ ፍላጎት በተግባር አሳይተውበታል። የህብረተሰቡን ችግሮች፣ ድክመቶች፣ ፍላጎቶች በዚህ እድሜያቸው ያስተዋሉና የተረዱ እንዲሁም ያንንም ለመቅረፍ አቅም እንዳላቸው የሚያሳዩ ነበሩ። በእርግጠኝነት ትንሽ ድጋፍ ካገኘ ሀገሩን ከፍ የሚያደርግ የተሻለ ትውልድ እየመጣ እንደሆነ የታየበት ፕሮግራም ነበር።
የአለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫሉን የጀርመን የባህል ማዕከል፣ ጎተ ኢንስቲቲዩት ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር በየአመቱ የሚያቀርብ ሲሆን፤ ዝግጅቱን ለኢትዮጵያ ህፃናት ለማዳረስ የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን መስፈርት የማይገኝለት ከፍተኛ ትብብር አድርጓል።
የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል በደቡብ ምስራቅ እስያ፣ በደቡብ እስያ ፣ በአፍሪካ ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በላቲን አሜሪካ የሚካሄድ የሳይንስ ግንዛቤ ልምድ ልውውጥ በዓል ነው። የሳይንስ እውቀትን ያስተዋውቃል እና የወቅቱን ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂና የአካባቢ ጉዳዮች ግንዛቤን ለመፍጠር መንገዶችን ያመቻቻል። የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል ሳይንሳዊ ጉዳዮችን ተደራሽና አዝናኝ በሆነ መልኩ ለብዙ ታዳሚዎች ያቀርባል፤ እናም ሳይንስ አስደሳችና አዝናኝ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል።  ዝግጅቱ በ2005 ተጀምሮ ዛሬ በአለም ትልቁ የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል ለመሆን በቅቷል። በ2023፣ 2015፣ የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል በአለም አቀፍ ደረጃ ከመስከረም 20 እስከ ህዳር 20 የተካሄደ ሲሆን፤ ፌስቲቫሉ በኢትዮጵያ ሲካሄድ ይህ ለሶስተኛ ጊዜው ነው። የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል በዚህ ዓመት በሥነ ምህዳር መልሶ ማቋቋም ላይ የተባበሩት መንግስታትን የአስር ዓመት ዘመቻን የሚደግፍና በአጋርነት መቆሙን ያሳየበት ነው።  የዘንድሮ የሳይንስ ፌስቲቫል ጭብጡ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ ሥነ ምህዳሮችን ከአደጋ ለመጠበቅና  እንደገና ለማደስ የተደረገ ጥሪ ነው። የፌስቲቫሉም ዋና መልዕክቶች
ዳግም ማሰላሰል
እንደገና መጀመር
እንደነበረ መመለስ
የሚሉ ነበሩ።
የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል በዚህ ዓመት ከ 102 አገራት ከ1700 በላይ ፊልሞችን ተቀብሎ ከ35 አገራት የተላኩ 150 ፊልሞች  መርጧል።
 ከእነዚህ ውስጥ ለሀገራችን በተለይ ለወጣቶችና ህፃናት ተስማሚ የሆኑ 26 ፊልሞች ላለፉት ሁለት ወራት ሲታዩ ቆይተዋል። የአለም የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫል ከእነዚህ ከተመረጡት ፊልሞች ውስጥ አሸናፊ ለሚሆኑ ስድስት ፊልሞች ሽልማቶችንም ይሰጣል። በዘንድሮው የሳይንስ ፊልም መዝጊያ ላይ እንደታዘብነው፣ ልጆቻችን ያቀረቧቸው ስራዎች ምናልባት በሚቻለው መንገድ ታግዘው ለፊልም ፌስቲቫሉ ተልከው ቢሆን ኖሮ በእርግጠኝነት ቢያንስ ከስድስቱ ሽልማቶች አንዱን የማሸነፍ ብቃት እንደነበራቸው ነው።
በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይም የጀርመን የባህል ማዕከል የፕሮግራሞች ኃላፊ አቶ አማኑኤል ፈለቀ፤ በሚቀጥሉት የአለም አቀፍ የሳይንስ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ የኢትዮጵያ የሳይንስ ፊልሞች እንደሚካተቱ ተስፋ እንዳላቸው ገልፀው፤ በተለይ በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ ስራቸውን ያቀረቡ ትምህርት ቤቶች እጅግ እንዳስገረሟቸውና ትምህርት ቤቶቹ ለቀጣዩ አመት እንደ ዘንድሮው ድንቅ ስራ ለማቅረብ ቢጥሩ፣ጎተ ኢንስቲቲዩት ከጎናቸው እንደሚቆም አረጋግጠዋል።


Read 945 times