Saturday, 23 December 2023 10:58

መሀል ላይ መቁለጭለጭ

Written by 
Rate this item
(3 votes)


          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው… መቼም ጨዋታ አይደል፣ ግራ ግብት ያለን ነገር አለ። ‘ስልጣኔ’ ማለት… አንዳንዴ ትርጉሙ ግራ አይገባችሁም! አለመሰልጠናችንን የሚነካን በዛብና። አለ አይደል… የእኛ የእኛ የሆነውን ሁሉ የ‘ፋራነት’ … የነሱ የሆነው ሁሉ የ”ስልጣኔ” እየሆነ ተቸግረናል።
ስሙኝማ… አንዳንዶቻችሁ “በአውሮፕላን የምትመጡም…” ሰዎች! ሰላም ስጡና… ‘ዋትስ አፕ’ ‘አውችን’ ይዛችሁ መጥታችሁ… ገና ከዋሻ የወጣን አታስመስሉና! ምን መሰላችሁ… የአንዳንዶቻችን ሩጫ!... አለ አይደል… ከራስ ለማምለጥ የሚደረግ ሩጫ ሆኗል። ክፋቱ ደግሞ… ስንሮጣት እንከርማታለን እንጂ መድረሻ የለንም።
‘ፈረንጅ’… ‘አይደንቲቲ ክራይስስ’ ነው… ምናምን የሚላት ነገር አለች አይደል… አንዳንዶቻችን አውላላ ሜዳ ላይ ከተንላችኋል። አለ አይደል… ከራሳችንም ሸሽተን… ‘እነሱም’ በመጤነት እንኳን አልቀበል ብለውን… አያሳዝንም! እንዴ… ኮሚክ ነገር እኮ ነው። እንትና የ‘ቺካጎ ቡልስ’ ቲሸርት ስላደረገ… እኔ በሌጣ ከኔተራ ስለሄድኩ… እሱ ስልጡን… እኔ ‘ፋራ’ እንሁን!
ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… አለ አይደል ይሄ ስልጣኔና ‘ፍርንጅናን’ የማያያዝ ነገር አለ። እንግዲህ… እነሱ ‘ሲግቱን እኛ ስንጋት አይደል የተከራምነው! አንዳንዶቻችንማ… አለ አይደል… የፈረንጅ’ ‘ሞሮን’ ያለም አይመስለን። በእነሱ ባይብስ! እዚህ አዲስ አበባ ሞልቶ የለ። ምን ይደረግ… በቃ ‘ቆዳ’ ስልጣኔ ሆነላችሁና… ስንት የሀበሻ ባለሙያ ቆሎ ሲቆረጥም… የፈረንጅ ‘ማሞ ቂሎ…’ “ከፍ በል ዝቅ በል” ይለናል።
(እንትናየ… ያ ‘ፈረንጁ’… እንዴት ሆናችሁ? አይ…‘ልትፈነገይ’ ነበር ሲሉ ሰምቼ… ቂ…ቂ…ቂ… እስቲ ምናለ… እኛ ቤንች የተቀመጥነው ሞልተን… ምንድነው ፈረንጅ ላይ የሚያሻማችሁ! አሃ… አሁን እኛ  የእነሱን ያህል “አቅቶን” ነው!... “ቂ…ቂ…ቂ…!)
እናላችሁ… የእኛ የ‘አገር ቤት’ ሰው ስድስት ወር ሀምበርገር ሲገምጥ ከርሞ ይመጣና “በቃ አበሻም አልሰለጥን አለ…” ሲላችሁ… አለ አይደል ታዝናላችሁ። ኧረ ‘ባካችሁ… ሰልፍ ኮንፊደንስ’… ‘ከተደበቀበት’ ፈልጉልን! (በነገራችን ላይ… ይሄ ከኒዮርክ ምናምን የ‘ፈረንጅ’ መኪና እየተደገፉ… ፎቶ መላክ… እሱ ነገር ቀነሰሳ! አሃ… ተነቃቃና!... አሁን አሁንማ… ከዚያ ወደዚህ የሚመጣው ዶላር ቀንሶ… ከዚህ የሚሄደው ድርቆሽ እየበዛ ነውሳ! እንትና መቼም አንተም እንደ እኔ… ‘ኮምፕሌይን’ ማድረግ ትወዳለህ… “ከሀገሩ የወጣ እስኪመለስ…” ለሚለው አዝማሪ መሸለም እችላለሁ። እኔ የምለው… ከሀገሩ የወጣ ሰው በቅሎ ይሁን የሜዳ አህያ… መቼ ሄደህ ነው ያወቅከው … ወይስ በታሳቢነት ነው። እስከዚያው አለ አይደል… እኔ አንድ ትሪፕ ቢሾፍቱ እስፖንሰር አደርግሃለሁ) እኔ የምለው … አንዴ!... በቃ ሹካ አያያዝ ካልቻልን… አልሰለጠንንም ያለው ማነው! እኔ‘ኮ ስለቴክኖሎጂ ምናምን እሺ ያውሩ… መቼም በሱ በኩል ‘ይቅደሟችሁ… ይከተሉ’ የተባልን ነው የሚመስለን። ግን… ፖስታን መጠቅለል መቻልና አለመቻል የስልጣኔ መለኪያ ያደረገው ማነው? ‘ፈረንጅ’ ፓስታውን በዳቦ ስለበላ… እንጀራ በወጥ የበላውን ቅንጣት ታክል ዝቅ የሚያደርገን ነገር የለም። እናላችሁ… በቴክኖሎጂ ኋላ መቅረታችን ልክ ነው። ይሄ ነገር ሰውነታችንን የሚያሳንስ አይደለም… አለ አይደል… እዚሁ እንኳን ነገሬ ብላችሁ ስታዩ… የሚያበሽቃችሁ መአት ነገር አለ። ለጨዋታው ያህል ዛሬ ማርቲን ሉተርኪንግ… ምናን አይነት ሆንኩባችሁ አይደል! የምር ግን… አንዳንዴ ይሄ ራስ በራስ የሚደረግ ጭቆና ያበሳጫል።
አሃ ገና ለገና ቢላው ሹካው እንዴት እንደሚያዝ “አላውቅም…” የሚል የ‘ፈረንጅ’ ምግብ ንክች የማያደርግ ሞልቶላችኋል። እንዴ… ልክ አይደለም ወይ! አያያዙን ማወቅ የ‘እነሱን አበላል ማወቅ’ እንጂ… መሰልጠን ማለት አይደለም።
ሙዚቃ… ለምሳሌ… የ‘ዓለም ቋንቋ ነው’… አይደል! ግን አሬታ ፍራንክሊንን መስማት… ስልጣኔ… ሽሽግ ቸኮልን መስማት  ‘ፋራነት’ ያደረገው ማነው! የምር… ይገርማችኋል። የኬኒ ሮጀርስ ጊታር… የስልጣኔ  ‘ግሪን ካርድ’… የይርጋ ዱባለ ማሲንቆ… የፋራነት ‘ላይሰንስ’ ሲሆን… አለ አይደል… የሆነ ነገር አይሰማችሁም!
እናላችሁ… የ‘ስልጡንነትና’ የ‘ፋራነት’ መለኪያዎች… ራሳችንን ከመሬት በታች እነሱ ከመሬት በላይ!... ነገርየውማ ያው የምንሰማው የምናየውም… የምናነበውም… እነሱን አይደል… በጽሑፉም በአልበሙም በምኑም እንደማንረባ ነው የሚነግሩን! ክፋቱ ምን መሰላችሁ… ሳይታወቀን ተቀብለነዋል።
ይኸው… በፖለቲካውም በምኑም ‘ስንጣላ’ እንኳን  ሮጠን እነሱ ጋር አይደለንም! አሃ ‘ስልጣኔ’ መሆኑ ነዋ! እዚሁ… በአገር ባህል እኛ “አንተም ተው… አንተም ተው…” ወይም  “የበደለም ይቅርታ ይጠይቅ… የተበደለም ለእግዚአብሔር ብሎ ይቅር ይበል…” ማለት እያለ ‘ለ ፈረንጅ’ እየሄዱ “ልብ አድርጉልኝ… ብቻ! “ማለት ሆኗል። ምን መሰላችሁ በአገር ባህልኛ መስማማት ‘ፋራነት’ ነዋ!
እናላችሁ… ይሄ የ”ስልጡንነትና” የ “ፋራነት” መለኪያ አለ አይደል… ለ‘እኛ ሳይሆን ለእነሱ ሆኖ የተቀደደ ነው የሚመስለው። ስለ ላሊበላ ህንጻ ሲነግሩን ከእቁብ የማንከተው ሰዎች ስለ ‘ኢምፓየር እስቴት ቢልዲንግ’ ግን “አጀብ የሰው ስራ!” እንላለን። ይህ ደግሞ… እንዲያው አጉል “አገሬ ናፈቅሽኝ” ምናምን ሳይሆን… ይህ ‘የእኛ የሆነው ነገር ሁሉ’ ‘ያለመሰልጠን’ ምልክት መሆኑ ስለማይታየኝ ነው።
ብቻ… ከራስ መሸሽ የመሰለ እርግማን የለም። የምር… በአንድ በኩል እኛነታችንን በ‘ቪም’ ለማጠብ ስንሞክር… በሌላ በኩል  እነሱ… “ደግሞ አንተ ከእኔ ጋር ምን ያመሳስልህና!” ሲሉን በቃ መሃል ላይ መቁለጭለጭ ነው። እስቲ ልቦናውን ይስጠን።
ደህና ሰንብቱልኝማ!
    

Read 2093 times