Saturday, 23 December 2023 10:57

የዓባይና የቀይ ባህር ጉዳይ በሰላም ይሆናል?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)


       ኢትዮጵያን በስጋት ሊያዩ የሚችሉ አገራት፣ ብትፈርስ ከመመኘት አልፈው ሲዝቱም አይተናል። ምኞታቸውን አያውቁትምና ይቅር ይበላቸው።
ኢትዮጵያ ብትበታተን እንደግልግል ሊቆጥሩት ቢልጉም እንኳ፣ ለአካባቢው አገሮች ሁሉ መከራ ያመጣል እንጂ ሰላም አይሰጣቸውም። የሱዳንና የሶማሊያ ትርምስ የአካባቢውን አገራት እንዴት እንደሚረብሽ ታይቶ የለ! በብዙ ዕጥፍ የምትበልጥ አገር ከተተራመሰችማ፣ ለአካባቢው ገሀነም ትሆናለች።
በዚያ ላይ፣ ኢትዮጵያ በሰላም ብትበለጽግ ነው፣ ለሌሎችም ተጨማሪ እንጀራ የምትፈጥርላቸው። የአንድ አገር ብልጽግና፣ ለጎረቤቶችም ይተርፋል። የአንድ አገር መከራ እንዲሁ ለሌሎቹም ይተርፋል።
እና ምን ይሻላል? በአንድ በኩል፣ ኢትዮጵያ ባትበጠበጥና ባትፍረከረክ ነው የሚበጃቸው። ሰላምና ጤና ሊመኙላት፣ ሕመሟና ችግሯ ሊያሳስባቸው ይገባል።
ነገሮች ከተበላሹ በኋላ፣ ከግራና ከቀኝ ተረባርቦ ማረጋጋትና ሰላም ማውረድ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ፣ በራሳችን ታሪክ እያየነው ነው። በሶማሊያ አይተነዋል። ሱዳንንም መመልከት ትችላላችሁ። አገር ከተናወጠ በኋላ ለያዥ-ለገራዥ ያስቸግራል። አንዴ ከተቀጣጠለ በኋላ ማጣፊያው ያጥራል። በጊዜ ነው መተሳሰብ።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ካልተበጠበጠችና በኢኮኖሚ ማደግ ካለባት፣… አስተማማኝና አማራጭ የባሕር በር ያስፈልጋታል።
ይሄ ያሳስባቸዋል።
ትልቅ አገር፣ በትንሽ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው ጡንቻው የሚፈረጥመው።
የሆነ ጊዜ፣ የሆነ ፖለቲከኛ፣ በአቋራጭ ተወዳጅነት ለማግኘት ሲል የሕዝቡን ስሜት ለማነሳሳትና ቁጣ ለመቆስቆስ ቢሞክር፣ ኢትዮጵያውያንን ለግጭትና ለጦርነት ቢያነሳሳ፣ “ምን ዋስትና ይኖረናል?” ብለው ቢጨነቁ አይገርምም።
ጥያቄው አስቸጋሪ ነው።
የኢትዮጵያ ከተቃወሰች፣ ከተዳከመችና ከተተራመሰች  የሚያሳስባቸው ከሆነ፣ በሰላም ማደጓና መጠንከሯም የሚያሰጋቸው ከሆነ፣ ምን ይሻላል?
ስጋታቸውና ጭንቀታቸው፣ እኛንም ሊያሳስብ ይገባል የሚል ነው መልሱ።
የአባይ ውኃ፣ የሕዳሴ ግድብና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ያስፈልገናል። የግድ ነው። የኑሮ ጉዳይ ነው። በዚያ ላይ “የክብር ወይም የውርደት ጉዳይ” ሆኖ መታየቱም አይቀሬ ነው።
ከአባይ ወንዝ ውኃ 80 በመቶ እና ከዚያም በላይ የምታመነጭ አገር፣ “አንዲት ጠብታ እንዳትነኪ” ተብላ ከተከለከለች፣ በውኃ የመጠቀምና ግድብ የመገንባት አቅም እንዳይኖራት የሚያዳክም የሴራና የተንኮል በደል ከበዛባት፣ ውሎ አድሮ የኑሮና የመንፈስ ቁስል መባባሱ ምን ይጠረጠራል?
ይሄ በጎ አይደለም - ለሱዳንም ለግብፅም።
ከባሕር በር ጉዳይ በኢኮኖሚ የመበልፀግና የመደኽየት ጉዳይ የመሆኑን ያህል የአባይ ውኃና የኤሌክትሪክ ኃይልም ለኢትዮጵያ የእህል የእንጀራ ጉዳይ ነው።
እና የኤሌክትክ ኃይልና፣ የባሕር በር የአገር የልብ ትታና የደም ስር ናቸው። አገር ሲዳከም የባሕር በር ያጣል። የባሕር በር ሲያጣም መከራው ይከብዳል። ኤሌክትሪክም እንደዚያው ነው። ድኽነት  ኤሌትሪክን ያሳጣል። ኤሌክትሪክ ማጣት ደግሞ የኢንቨስትመንት እና የዕድገት ዕድሎችን ያመነምናል። በዚህ ዓይን ኢትዮጵያን እንይ።
አገራችን በዓለምና በአፍሪካ ውስጥ ምን ያህል ቦታና ድርሻ እንዳላት እንመልከት። ቦታ የላትም ማለት ይቻላል። ከኬንያ፣ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር እንገዳደራለን።
የዓለም የኤልክትሪክ ኃይል አገልግሎት በ25 ዓመት ውስጥ ከ3 ሚሊዮን ሜጋዋት ወደ 8 ሚሊዮን ሜጋዋት ከዕጥፍ በላይ ጨምሯል። የኢትዮጵያ ግን ከዐሥር እጥፍ በላይ አድጓል።
የዓለም የኤሌክትሪክ ማመንጫ ዓቅም
1981    2 ሚ    ሜጋዋት
1995    3 ሚ    ሜጋዋት
2001    3.6 ሚ    ሜጋዋት
2005    4 ሚ    ሜጋዋት
2021    8 ሚ    ሜጋዋት

የሜጋ ዋት ጨዋታው በሚሊዮኖች ነው።
ከ25 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎች ጠቅላላ አቅም 420 ሜጋዋት ነበር። ዛሬ 4900 ሜጋዋት ነው። ትልቅ ለውጥ ነው። ቢሆንም ግን፣ መነሻችን ከቁጥር የሚገባ አልነበረም። እናም ገና ብዙ ይቀረናል።
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ዓቅም
1981    240    ሜጋዋት
1995    420    ሜጋዋት
2001    700    ሜጋዋት
2005    900    ሜጋዋት
2021    4900    ሜጋዋት

ከሕዝብ ብዛት ጋር ስናነጻጽረው፣ የኢትዮጵያ የኤክትሪክ ኃይል፣ ኢምንት ነው። እንደ ሕዝብ ብዛቷ ቢሆን፣ የኢትዮጵያ ድርሻ፣ ከ120 ሺ ሜጋዋት መሆን ነበረበት። አሁን ግን ገና 5 ሺ አልሞላም።
በእርግጥ ተስፋ እንቁረጥ ማለት አይደለም። በጭራሽ! በቁጭት ለመነሳት እንጂ።
አሁንም የ25 ዓመታት ለውጥ እንመልከት። የማመንጫ ጣቢያዎች ዓቅም አይተናል። በተግባር ምን ያህል እንደሚያመነጩና ለአገልግሎት እንደሚቀርቡ እናነጻጽር። ሁለት ቁምነገሮችን ልብ እንላለን። ኢትዮጵያ አስደናቂ ዕምቅ አቅሟን ተጠቅማ ወደ ከፍታ መገሥገሥ ትችላለች። በሌላ በኩል ደግ እጅግ ከባድና ትልቅ ችግር ውስጥ መሆኗን እናያለን።
በዓለም ዙሪያ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል፣ በዕጥፍ ጨምሯል። ከ13 ሚሊዮን ወደ 27 ሚሊዮን ጊጋዋትዓወር ደርሷል።
የዓለም ዓመታዊ የኤሌክትሪክ ኃይል
1981    8 ሚ    ጊጋዋትዓወር
1995    12.5 ሚ    ጊጋዋትዓወር
2001    15 ሚ    ጊጋዋትዓወር
2005    17 ሚ    ጊጋዋትዓወር
2021    27 ሚ    ጊጋዋትዓወር

የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ግን፣ ከዐሥር ዕጥፍ በላይ ሆኗል (ከ1450 ወደ 14500 ጊጋዋትአወር ማለት ነው)።
የኢትዮጵያ ዓመታዊ የኤሌክትሪክ ኃይል
1981    680    ጊጋዋትዓወር
1995    1,450    ጊጋዋትዓወር
2001    2,000    ጊጋዋትዓወር
2005    2,900    ጊጋዋትዓወር
2021    14,500    ጊጋዋትዓወር

ከ1990ዎቹ ወዲህ ተስፋ ሰጪ ትልቅ ለውጥ እንደተፈጠረ ማየት ትችላላችሁ። ነገር ግን ከሕዝብ ብዛት አንጻር ሲታይ፣ ከቁጥር ይገባል ለማለት ያስቸግራል።
በግለሰብ ብናሰላው ስንት ስንት ይደርሳቸዋል?
በዓለም ደረጃ፣ በሃያ አምስት ዓመታት ልዩነት፣ የአንድ ሰው አማካይ የኤሌክትሪክ ኃይል ድርሻ፣ ከ2200 ኪሎዋትአወር ወደ 3450 ኪሎዋትአወር አድጓል።
ከዓለም አማካይ የኤልክትሪክ አገልግሎት ጋር ሲነጻጸር፣ ኢትዮጵያ ገና በአካባቢው የለችበትም። ከወለል በታች ናት ማለት ይቻላል።
ሌላውን ትተን ድሃዋ የአፍሪካ አህጉር ውስጥም፣ የኢትዮጵያ ቦታ፣ ከወለል ስር ነው። የአፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በሩብ ምዕተዓመት ውስጥ፣ በዕጥፍ ብቻ ነው የተለወጠው።
በአማካይ የአንድ ሰው ድርሻ፣ 300 ወደ 600 ኪሎዋት አወር አድጓል።
አዎ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጣን ለውጥ ታይቷል።
የአንድ ሰው አማካይ ድርሻ፣ ከ25 ኪሎዋት አወር ተነስቶ 120 ኪሎዋትአወር ደርሷል። የሕዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምር ደግሞ፣ የአገሪቱን ኤሌክትሪክ በዕጥፍ ያሳድገዋል።
እንዲያም ሆኖ የዓለም አማካይ ላይ ለመድረስ አይደለም፣ አፍሪካ ውስጥ ወደ መካከለኛ ደረጃ ለማደግ፣ ተጨማሪ ሁለት የሕዳሴ ግድቦች ያስፈልጋሉ። ምን ማለት እንደሆነ ይገባችኋል! እጅግ በጣም ወደ ኋላ ቀርተናል።      
ሁለት የህዳሴ ግድብ መጨመር? አንድ ግድብ በመገንባት እንዴት ከባድ እንደሆነ አይተነዋል፡፡ ከድሃ የአፍሪካ አገራት ጋር ለመሰተካከል እጥፍ ድርብ መገንባት አለብን፡፡ ከባድ ነው፡፡ ግን ደግሞ እየቀለለ ይሄዳ፡፡
የህዳሴ ግድብ በትክክል ከሰራ ረሰሱን ችሎ፣ በራሱ ገቢ ሌላ የህዳሴ ግድብ ቁጥር ሁለትን መገንባት ይችላል፡፡ ያንበትን የመከራ ጥልቀትና የከፍታ ብሩህ ተስፋችንን ነው በየቦታው የምናየው፡፡
ተስፋ ሰናይ በሌላ ጎኑ የሚያስቆጭ ውድቀት እናያለን፡፡  
እንዴት ከአፍሪካ በታች እጅግ ዝቅተኛ ወለል ላይ እንሆናለን?
ከጎረቤቶቻችን ከኬንያና ከሱዳን ጋር ለመስተካከል እንኳ፣ ከባድ ፈተና ሆኖብናል።
የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ከኢትዮጵያ በዕጥፍ ይበልጣል። የሱዳን ደግሞ ከሦስት ዕጥፍ በላይ ነው።
የግብፅ? ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር፣ 15 ዕጥፍ ያህል ነው።
 የዛሬ 25 ዓመትማ፣ የግብፅ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከኢትዮጵያ በ30 ዕጥፍ ይበልጥ ነበር።
አማካይ የአንድ ሰው ዓመታዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ድርሻ
ዓለም    3,450    ኪሎዋትዓወር
አሜሪካ    12,500    ኪሎዋትዓወር
ጀርመን    6,700    ኪሎዋትዓወር
ጃፓን    7,600    ኪሎዋትዓወር
ቻይና    5,700    ኪሎዋትዓወር
አፍሪካ    600    ኪሎዋትዓወር
ግብፅ    1,850    ኪሎዋትዓወር
ሱዳን    360    ኪሎዋትዓወር
ኬንያ    220    ኪሎዋትዓወር
ኢትዮጵያ    120    ኪሎዋትዓወር

እንግዲህ እውነታው ይሄው ነው።
አዎ፣ ኢትዮጵያ ለተወሰነ ጊዜ የሰላም እፎይታ ካገኘት በዕድገት የመገስገስ ዓቅም እንዳላት ድሮም ዛሬም ይታወቃል።
ግን ደግሞ፣ በየጊዜው እንደምታዩት ነው፡፡ ሰላም አድራ በማግስቱ ጦነት ይገጥማታል፡፡ ትንሽ እየተነሳች ተመልሳ ትወድቃለች፡፡
በየጊዜ ትራምዳለች፡፡ ታሪክ ይመሰክራል፡፡
በየጊዜው እየተደናቀፈችና ሰላሟ እየደፈረሰ፣ ከዚያም አልፎ እየተበጠበጠ፣ እጅግ ወደኋላ ቀርታለች። የዘመናት መረጃዎችም ይህን ይመሰክራሉ።
በአንድ በኩል፣ በፍጥነት የመሻሻል ዕድሏ ጠፍቶ እንደማይጠፋ በተደጋጋሚ ታይቷል። በመረጃም ይረጋገጣል። ተስፋም ይሰጣል።
በሌላ በኩል ግን፣ ከዓለም ጋር የተራራቅነው እንደ ተራራና እንደ ሸለቆ ነው። ተቀራራቢ የሕዝብ ብዛት ካላት ከግብፅ ጋር የዚያን ያህል መራራቅ ነበረባት ወይ? እንደገና ተመልከቱት
በግብፅ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በአማካል ለአንድ ሰው 1800 ኪሎዋት አወር ነው።
የኢትዮጵያ 120 ኪሎዋት አወር።
ይሄን ሁሉ ልዩነት የሚያዩ ሰዎች፣ ኢትዮጵያ እስከ ወዲያኛው ከወለል በታች ጨለማ ውስጥ ተቀብራ ታስራ መቀጠል አለባት ብለው ለመፍረድ ይጨክናሉ?
ትርጉሙ ብዙ ነዋ። የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ጠቅላላ የኢኮኖሚና የኑሮ “ቴርሞሜትር” ነዋ። ራሱን የቻለ አገልግሎት ቢሆንም፣ የብልጽግናና የድኽነት መለኪያም ነው።
የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ዓቅምና አቅርቦትን በመመልከት፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ድክመት፣ የወደፊት የዕድገት ተስፋዋንና የሚጠብቃትን መከራ መገመት ይቻላል።
ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የታየው የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጥ፣ የኢትዮጵያን ተስፋ የሚጠቁም፣ በዚያው ልክ ደግሞ የድኽነት ሸክሟንም አጉልቶ የሚያሳይ ነው።
ትንሽ ሻል ያለ የሰላም ፋታ ባገኘችባቸው ዓመታት ውስጥ ኢኮኖሚዋን የማሳደግ ዕድል ስለተፈጠረ፣ ሙዚቀኛው “ጋሽ አበራ ሞላ” እንዳዜመው፣…
የኢትዮጵያ ልጆች የጣና በለስ፣ የተከዜና የግልገል ጊዜ ግድቦችን ተሰርተዋል። ከዚያም ወደ ሕዳሴ ግድብ ተሸጋግረዋል።
የሰላም ፋታው ለኢትዮጵያ ቢሰነብትላትስ?በሰላም ተደላድላ በዕድገት መገስገስ ከጀመረች፣ ብዙ ነገር በፍጥነት እየተገነባና ወደ በጎ እየተለወጠ እንደሚሄድ ምን ይጠረጠራል?
ኢትዮጵያ እየሰመረላትና እያደገች ከተጓዘች፣… “የውኃ ጉዳይ ትልቅ ፈተና ይሆንብናል” ብለው ቢሰጉስ ይገርማል?
አይገርምም። በሌላ አነጋገር፣ የኢትዮጵያ ውድቀት ሊያስጭንቃቸው ይገባል የምንለው ያህል፣ ኢትዮጵያ ስኬት እንደሚያሰጋቸው አያከራክርም።
እና ምን ይሻላል? ኢትዮጵያ ውኃ ልትዘጋብን ነው እያሉ ጭፍን የጥላቻ ስሜትን ማራገብና የጦርነት እሳት መለኮስ ያዋጣል? በጭራሽ። ለሁሉም ኪሳራ ነውና። ማሸነፍም እንኳ በኪሳራ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር እፈልጋለሁ ብላ ትወረናለች እያሉ የጸብ ስሜት ማጋጋልስ ይጠቅማል? በፍጹም አይጠቅምም። እንኳን በጸብ በሰላምም፣ ኑሮ የከበዳቸው አገራት እንዴት ጸብን ይመርጣሉ?
ስለዚህ የሚበጃቸውን አስበውና አውቀው አርፈው ይቀመጡ? የራሳቸው ጉዳይ ነው ብለን እንዳሻን አንሁን? በጭራሽ!
ይልቅስ፣ የአባይን ውኃ መጠቀምና ግድብ መገንባት፣ መስኖ መዘርጋትና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ፈለግን እንጂ፣ ከተሳካም ለጎረቤቶች የሚተርፍ መልካም ፍሬ እንድናገኝበት ተመኘን እንጂ፣ ጎረቤቶችን የመጉዳት መጥፎ ሐሳብም ሆነ ክፉ ስሜት እንደሌለን በመግለጽ የራሳችንን ሐላፊነት መወጣት ይኖርብናል።
 የግብጽና የሱዳን ግድቦችን በማጉደል ቅንጣት ጥቅም አናገኝም። ቢሞላላቸው ምኞታችን ነው።
ለብልጣብልጥነት የውሸት እየተናገርን እንሸንግላቸው፤ እንሸውዳቸው ማለት አይደለም። በትክክለኛ ሐሳብና ከቅን ልቦና እንጂ።  የባሕር በር መፈለግም፣ የመንጠቅ ፍላጎት ማለት አይደለም። በመብለጥ ወይም በማሳጣት የሚገኝ ጥቅም የለም። ብዙ የባሕር በር ቢኖራቸው እሰዬው ነው። ልክ እንደዚያው ኢትዮጵያም ያስፈልጋታል። የጥላቻ ወይም የእልህ ስሜት የማይነካካው ቀና ፍላጎት መሆኑን ሁሌም መግለጽና ማስረዳት፣ የጦርነትና የጸብ ቁስቆሳን ለመከላከል ያግዛል።
ግን በዚህ መንገድ ብቻ ጦርነትን በሩቁ ማስቀረትና በሰላም ኢኮኖሚን ማሳደግ ኑሮን ማሻሻል፣ ስልጣኔ ታሪክን መስራት ይቻላል፡፡ ወይ? ምክንያታዊ አስተሳሰብ እና ፍላጎት ያስልጋል፡፡ ለሁነኛ መፍትሔ አስማማኝ መሰረቶች ናቸው፡፡
ወደ መፍትሔ ዘዴ ተጠግተናል፡፡ ሁለመናውን አብጠርጥን ለማየት ደግሞ መነሻ ፍንጮች አናጣም፡፡ ግብፅና ከሱዳን ጋር ጦርነት እዳይፈጠር መከላከል ተችሎ የለ? እስከዛሬ ተቿል፡፡ ከዚህ የአባይ ወንዝ የሕዳሴ ግድብና ታሪክ በመነሳ፣ የሰላ መፍትሔ ዘዴዎችና ቀመሮችን እናያለን፡፡



Read 229 times