Saturday, 16 December 2023 20:44

እኛማ እንቆጥራለን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እኛማ እንቆጥራለን
ዛሬም ሙሉ ሳቅክን
ያልተሸራረፈ ሙሉ ፈገግታህን
እንዳቀፍን አለን በየምላዳችን የነገ ሰብልህን..
አሴ ኩራ ኩራ፣ ባለህበት ኩራ፣
ብርሃን ያዘምራል፣ ያሳብህ ተራራ..
ዓመቱማ ያልፋል ወደ ፊት ገፍትሮን
ዘመኑ ቢሸብት፣
አይረሴ ራዕይ፣ ነጭ ፀጉር የለው
ከቶ መች ይረሳል
ህልምህ የወይን ጠጅ፣ ሲነጋ ይበስላል
የነበረህና የነበረን ሀሳብ፣ እያደር ይጠራል፡፡
ስምህ ማዘርዘሩ፣ መንፈስህ መብቀሉ
እምነት ፍልስፍና ውልና ፈትሉ
ዕውቀትና ትጋት ብርሃን ፊደሉ
ሩቅ እንዳሰብነው ሩቅ ነው ገድሉ
ዛሬም አለ ቃሉ፣
ያውም በርቶ ፈክቶ፣ እስከ ማዕዜኑ፡፡
አውቃለሁ ታውቃለህ
የመከረኛ አገር መከሯ እስኪገባ
መከራ መብዛቱ
እውን ቢሆን እንኳ
ራዕይህ አለ ምስክር ይቆማል፤ ቀኑ ለመንጋቱ
አይቆምም ጉዟችን ባይቆምም ስጋቱ....
አይደለም ራእይ ብሳና- ዛፍ ግንድ
ሽበት አይወርሰውም የዕድሜ ዘመን ግርድ
አይረሴ ራዕይ የቸገንክበትን
የፍል ዕውቀት እርሻ የዓለም አሂዶህን
ታያለህ ማሳውን፡፡
አሴ ኩራ ኩራ
ብርሃን ያዘምራል ያሳብህ ተራራ....
የራዕይ ተራራ....
ነቢይ መኮንን

Read 1441 times