Saturday, 16 December 2023 20:15

መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ነው ልታፈራ ወይ ልትፈነዳ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

አገራችንን ስለወደድን ብቻ፣ ከንቱ ውዳሴ፣የውሸት አድናቆት፣ ወይም ከእውነት የራቀ ተስፋ መደርደር የለብንም። ሌሎችን ለማታለልና ደስ ለማሰኘት ወይም ለማስቀናትና ለማበሳጨት ስንሞክር፣ ብዙም ሳንቆይ በራሳችን ውሸት ራሳችንን ማታለል እንደምንጀምር አትጠራጠሩ። ከእውነትና ከዕውቀት መጣላት ደግሞ፣ ለማንም አይበጅብም። ደግሞም፣ የማወደስና የማድነቅ መልካም ቀና መንፈስ ይኑረን እንጂ፣ ኢትዮጵያ የድንቅ ነገሮች ምድር፣ ባለታሪክ ግርማዊ አገር ናት።
አዎ፣ ብዙ የሚቆጩ ስህተቶችንና አሳዛኝ ውድቀቶችን ያየች ያስተናገደች አገር መሆኗም እውነት ነው። የውድቀት ታሪክ ሳይነካካት፣ እንደ ጥንቱ
ሥልጣኔ እንደ አጀማመሯ በስኬት ብትቀጥል ኖሮማ፣ በድህነትና በጦርነት የኢትዮጵያ ሥም ባልተሰማ ነበር። እንደ አክሱም እንደ የሐ ሥልጣኔ
ቢሆን ኖሮማ፣… ይሄ ባይሳካላትን እንኳ፣ ከሐረርና ከጎንደር ጅምሮች ተምራ መልካም መልካሙን ይዛ መጓዝ ብትችል ኖሮማ… ዛሬ ስለ ረሃብና ስለ እርዳታ እህል ባላወራን ነበር።
የኢኮኖሚ ቀውስና የብድር ዕዳ መውጫ መግቢያ ባላሳጣን ነበር።ክፋቱ ግን የሥልጣኔ ጉዞዎች እንደ አጀማመራቸው አልቀጠሉም።
ተቋርጠው ቀርተዋል። እስከመረሳትም ደርሰዋል። አስደናቂ የሥልጣኔ ግሥጋሤዎችና ጅምሮች በየጊዜው እየተደናቀፉና እየተፍረከረኩ፣…
እየፈረሱና በጦርነት እየተቃጠሉ ጭምር፣ ከአፈርና ከአመድ ስር ተቀብረዋል፡፡
በጊዜ ርቀት ተሸፍነው፣ ታሪካቸው “ከእውነት መዝገብ” የተሰረዘ ያህል እንደ ተረት የሚቆጠሩ ሆነዋል። ታሪክ መሆናቸው ጠፍቶን አይደለም፡፡ ዘመናትን ያስቆጠሩ አስገራሚ የሥልጣኔ ቅርሶችን ማየታችን አልቀረም፡፡ ነገር ግን ትርጉማቸውና ምሥጢራቸው ውስጣችን ድረስ ዘልቆ አይሰማንም።
እውነት እውነት አይመስሉንም። ጥንታዊዎቹ ግንባታዎችና ሐውልቶች ወፍ ዘራሽ ክስተቶች ግን ጥሩ አጋጣሚዎች ሆነው
ይታዩናል፡፡ ግን አይደሉም፡፡ የስልጣኑ አካል የነበሩ ቅርሶች ናቸው፡፡ ዛሬ የሥጠሳኔ ቅሪት ሆነው የሚታዩን፡፡
የሥነ-ምግባርና የጨዋነት ባሕልን የፈጠረ አገር፣….
የተወሰነ ያህል ሕግና ሥርዓትን ያደላደለ ፖለቲካ፣ ደህና የኢኮኖሚና የኑሮ ዓቅም፣…
በአጠቃላይ ወደ ሥልጣኔ የሚጓዝ አገር ነው። እነዚያን ድንቅ ሥራዎች የሚገነባው። ዛሬ ግን ቅርሶቹ ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡
እናም እውነት እውነት አይመስሉንም። አስደናቂ ሕንፃዎችና ሐውልቶች በአንዳች ተዓምረኛ አጋጣሚ የተፈጠሩ ሆነው ይታዩናል፡፡አዎ፣ ታሪክ ናቸው፡፡
ነገር ግን እንደ ተረት ይሆኑብናል። “ከእለታት አንድ ቀን” ብለን የምናወራው ዓይነት። ከየሐ ግንባታዎች እስከ አክሱም ሐውልቶች፣ ከአብርሐ ወ አጽብሐ ጽሑፎችና የመገበያያ የወርቅ ሣንቲሞች እስከ ንጉሥ ካሌብ መርከቦች ድረስ፣…
ብዙ ድንቅ ታሪኮች ታይተዋል፡፡ ምዕተ ዓመታትን መሻገር የቻሉ የሥልጣኔ ጉዞዎች ናቸው። እና የት ገቡ? የት ደረሱ? በምን ምክንያት ተዳክመው እንዴት ፈረሱ?
በእርግጥ ምዕተ ዓመታትን የዘለቀ የሥልጣኔ ታሪክ ሲባል፣ እንቅፋት ሳይገጥመው፣ ያለ ስህተትና ያለ አንዳች ጥፋት በስኬት ተጉዟል ማለት አይደለም። ራሳቸውን የሚያሰናክሉና የሚወድቁ አይጠፉም። ተነስተው ሲራመዱም ከየአቅጣጫው የሚመጡ አደናቃፊዎች ይኖራሉ።
የኢኮኖሚ ችግር ያጋጥማል። አላስፈላጊ ግጭትና ጦርነትም ይፈጠራል።
አሁን እያየን እንዲህ ዓይነት ከንቱ እልቂትና ውድመት አገርን ያዳክማል፡፡ ለተጨማሪ ጥፋትም ያጋልጣል፡፡ የውድቀት ምክንያቶችና ሰበቦች ብዙ ናቸው፡፡ የውስጥ ችግሮችና የራስ ጥፋቶች… እንዲሁም ከሩቅና የቅርብ የሚመጡ የውጭ ፈተናዎችና ጥቃቶች በየጊዜው ይፈጠራሉ፤
ይከሰታሉ፡፡ ጥንታዊዎቹ የአገራችን የሥልጣኔ ጉዞዎችም ከውጣ-ውረድ አላመለጡም። እየወደቁ እየተነሱ ነው የተጓዙት - ለምዕተ ዓመታት።
ከንጉሥ ካሌብ በኋላ ግን፣… የዛሬ 1300 ዓመት ገደማና ከዚያ ወዲህ ግን፣ ከውድቀት የመነሳትና እንደገና የማንሰራራት የኢትዮጵያ ዓቅም
እንደተዳከመ ታሪክ አጥኚዎች ይናገራሉ። ለምን? በራሱ ጥፋት የሚደናቀፍና በሌሎች ጥቃት የሚያሰናክል ጠፍቶ አያውቅም ብለናል።
መውደቅና መነሳትም በየዘመኑ ነበር ብለናል። እና ምን አዲስ መዓት መጣ? ጥሎ የሚጥልና እዚያው የሚያስቀር ምን እርግማን ደረሰባት?
እንደገና የመነሳት ዓቅምን የሚያሳጣ ውድቀት የተፈጠረው፣…
አንድም በአገሪቱ ሃይማኖቶች ውስጥ ዓለማዊ ኑሮን የሚያጥላላ አስተሳሰብ በመስፋፋቱ፣ሁለትም… ኢትዮጵያ ከዓለማቀፍ ንግድ በመቆራረጧ እንደሆነ ታሪክ ጸሐፊዎች ይገልጻሉ። ሃይማኖቶች የተወሰነ ያህል፣ ሁሉን ዓቀፍ የሥነ-
ምግባር መርሆችን ልሕቀትንና ቅድስናን የማክበር መንፈስም ይሰጣሉ፡፡ ያስተምራሉ። በጎ ገፅታቸው እዚሁ ላይ ነው።
ነገር ግን ዓለማዊ ኑሮን ለሚያንቋሽሽ አስተሳሰብ እየተጋለጡና እያጋለጡ የበርካታ አገራት ሥልጣኔዎችን ለውድቀት ዳርገዋል።
ሁሉን አቀፍ የሥነ-ምግባር መርህ በማስተማር የዘረኝነት ክፉ ስሜቶችን ለመግራት የሚያግዙ ሃይማኖቶች፣ በጭፍን እምነት ሳቢያ ለክፉ ግጭት
መንስኤና ማባባሻ ይሆናሉ፡፡ በዚህም በርካታ አገራት ተረብሸው፣ ተሸብረው፣ ተበላሽተው በዘመናት ነደው ጨልመዋል።
እነዚህ ሁሉ የበርካታ አገራት ገጠመኞች ናቸው። ኢትዮጵያም እነዚህ እድሎችንና እርግማኖች አይታለች፡፡ ጥንታዊ ኢትዮጵያ ግን ተጨማሪ ፈተና
ነበረባት። ትልቁ ፈተናዋም፣ የባሕር በሮችንና መተላለፊያዎችን የሚዘጋባት ዓለማቀፍ የፖለቲካ ለውጥ የዛሬ 1400 ዓመት ገደማ በመፈጠሩ እንደሆነ ታሪክ ጸሐፊዎች ይገልጻሉ። ለብዙ ዘመናትም ኢትዮጵያ ከዓለም ተገልላ ለከልላ ቆየች ይላሉ፡፡ ዛሬስ? እንዲህ፣ ለክፉም ለደጉም ዘመኑ የኢትዮጵያ ይሆናል ብለናል፡፡ ለበጎ ካደረግነው፣መጪው ዘመን የኛው ነው - ካወቅንበትና በጥበብ ከተጋንበት። አኩሪ ታሪኮችን እየደጋገሙ የሚሠሩ ድንቅ ሰዎች በአገራችን ሊበረክቱ ይችላሉ። የሕዝብ ብዛቷን፣ ታሪካዊ ቅርሶቿንና ወቅታዊ ሁኔታዋን አይቶ የተገነዘበ ሰው፣ ኢትዮጵያ እጅግ
ጥልቅና ዕምቅ ኃይል በውስጧ ያቀፈች አገር መሆኗን አይጠራጠርም። ዕምቅ ኃይል፣ እንደ ሥያሜው በጥልቀትና በርቀት የሚገኝ እንጂ ከአቅራቢያ የሚጨበጥ ኃይል አይደለም። ዕምቅ ኃይል እንደ ስሙ ብርቱ ኃይል ቢሆንም፣ገና ያልተለኮሰ ታምቆ የተያዘ ኃይል ነው።የሕይወት ነዳጅ የኑሮ ጉልበት ሊሆንልን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አደገኛ ፈንጂ ሊሆንብን ይችላል። ዕምቅ ኃይል፣ ለክፉም ለደጉም፣ ለተቃራኒ መንታ መንገዶች፣ መምዘግዘጊያ ጉልበት ነው። የኢትዮጵያ የወደፊት ታሪክም እንዲሁ፣ ለመንታ መንገዶች ተቀባብሎ የተዘጋጀ ነው ማለት ይቻላል። በእርግጥ፣ ይሄ ለአገራችን አዲስ ነገር አይደለም። ድሮም የተስፋ ምድር ናት። ግን የስጋት አገርም ሆናለች። ዕምቅ ኃይል እንደዚህ ነው። በቀላሉ የማይገኝ ዕድል፣ የግሥጋሤ ጉልበት፣ የበረከት ጸጋ ነው። ግን አደገኛም ነው። ውስጣዊው ጸጋ ፈንቅሎ ይወጣል።አገሪቱም በልምላሜ አብባ ታፈራለች (እንደ አፋችሁ ድርገው)። ወይም ደግሞ…
ውስጣዊው ኃይል በግላጭ ሳይወጣ ሥር ለሥር ሊሰራጭ፣ አልያም እንደታመቀ ቆይቶ ድንገት ሊፈነዳ ይችላል። አገሪቱም ውስጥ ለውስጥ ተመርዛ
ወይም ድንገት ፈንድታ አካባቢውን ታምሳለች (አያድርገው፤ ሰይጣን አይስማ)። በሌላ አነጋገር፣ ለክፉም ለደጉም፣ መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ነው። ይሄ ቀላል ጉዳይ አይደለም። የሚያጓጓም የሚያስፈራም ነው። ትናንሽ ድሃ አገራት ሲመጥቁም ሲወድቁም፣ ሲለመልሙም ሲጠወልጉም፣ ነገር ሲሰምርላቸውና ሲያምርላቸው ወይም ሲበላሽባቸውና ሲያተራምሳቸው፣… አገር ምድሩን፣ አካባቢውንና አህጉሩን ሁሉ የሚያደምቅ በረከት አይወጣቸወም፡
፡ ወይም ከዳር እስከ ዳር የሚያጨልም እርግማን አይሆኑም። የቅርብና የሩቁን ተመልከቱ፡፡ ሶማሊያ ስለተተራመሰች፣ ጎረቤቶቿ ተረብሸዋል። ነገር ግን
ከቁጥጥራቸው ውጭ አልሆነችባቸውም። ሶማሊያ ትልቅ አገር አይደለችም። የኤርትራ ኢኮኖሚ በዕጥፍ ቢወርድ ወይም በዕጥፍ ቢያድግ፣ በጎረቤቶች ላይ ብዙም ተጽእኖ የለውም። በኢኮኖሚም በህዝብ ብዛትም ትንሽ አገር ናት። የኢኮኖሚ ዓቅምና የሕዝብ ብዛት፣ ትልቅ ትርጉም አላቸው።
ከኢትዮጵያ ጋር አይደለም ከኬንያና ከሱዳን ጋር ሲነጻጸሩም፣ ሶማሊያና ኤርትራ ትንንሽ አገራት ናቸው። የኢኮኖሚና የህዝብ ብዛት ብቻ አይደለም
ጉዳዩ። የባህል እና የታሪክ ቅርሶችም፣ ዕምቅ ዓቅም ናቸው ። በእነዚህ የተስፋና የአደጋ መመዘኛዎች ዓለምንና አህጉራቱን ስንመለከት፣ የኢትዮጵያ ስም ደብዝዞ ሳይሆን ደምቆ ይታየናል። እንዲህ ሲባል ግን በእልልታ ያስጨፍራል ማለት አይደለም። ለክፉም ለደጉም ነው። ሊፈነዳም ሊያፈራም ነው መድመቁ። ኢትዮጵያ ባለ ታሪክ ትልቅ አገር ናት። የባህር በር ግን የላትም፡፡ የባህር በር የሌላት ትልቅ አገር! በእርግጥ፣ የባህር በር የነበራት ጊዜ፣ በተለይ በደርግ ዘመን፣ ሁሉም ነገር ሰምሮላት ከዳር እስከዳር ሰላም ሰፍኖባት ነበር ማለት አይደለም፡፡ የባህር በር፣ በራሱ ጊዜ ሥልጣኔና ብልጽግና አይሆንም፡፡ ሶማሊያና የመን የሰላም አምባዎች አይደሉም፡፡ በዚያ ላይ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ባህር አልባ አገር
አይደለችም፡፡ የባሕር በር የሌላቸው አገራት በርካታ ናቸው።ቢሆንም ግን የኢትዮጵያ ይለያል፡፡ እንግዲህ የህዝብ ብዛት፣ በረከትም እርግማንም
ሊሆን እንደሚችል ተነጋግረናል፡፡“ዝም ያለ ነገር” አይደለም፡፡ እምቅ ኃይል ነው ለተስፋም ለአደጋም ፡፡ የኢትዮጵያ ደግሞ ከሌሎች
ሁሉ ይለያል ባህር አልባ ትልቅ አገር!
የኢትዮጵያ ግን ይለያል። ምድር የተቆለፈባቸው አገራት ውስጥ ከሚኖረው የሕዝብ ብዛት ውስጥ ሩብ ያህሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።
ምድር የተቆለፈባት ትልቅ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት።
ከትልልቆቹ ደርዘን የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ናት። በአፍሪካ ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት። ከአፍሪካ ሕዝብ ውስጥ 9 በመቶው
ኢትዮጵያዊ ነው ማለት ይቻላል። ወደ 10 በመቶ እየተጠጋ ይሄዳል። ከ30 ዓመታት በፊት ከአንድ ሺ አፍሪካዊያን መካከል 76ቱ
ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ዛሬ 86 ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ከአንድ ሺ የዓለም ሕዝብ መካከል፣ 10ሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ይሄ የኢትዮጵያውያን ድርሻ በሠላሳ ዓመታት ምን ያህል እንደተለወጠ ይታያችሁ።ከአንድ ሺ የዓለማችን ሕዝብ 15ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። በአጭሩ፣ ከትልልቆቹ ደርዘን የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ናት -
ኢትዮጵያ። ይሄን እውነታ ከኢኮኖሚ ጋር አያይዘን እንመልከተው፡፡ የሕዝብ ብዛት ባለሁለት ስለት እንደሆነ አስታውሱ፡፡ ለእድገትም ለቀውስም
የተመቻቸ ነው፡፡ የእህል ምርት ባይቀንስ እንኳ ካላደረገ 30 ሚሊዮን ሰዎች ለረሀብ ይጋጣሉ፡፡ እግዚኦ ያስብላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ትልቅ አገር ለፈጣን እድገት ይመቻል- እንደ ቻይና፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ይፈረጥማል፡፡ ያለ ባሕር በር ግን አይዘልቅም፡፡ እንግዲህ አስቡት፡፡
በ20 ዓመታት ውስጥ፣ ከውጭ ተገዝቶ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የምርት ብዛት ወደ 4 ዕጥፍ ጨምሯል። 25 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ነበር።
አሁን ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በዓመት ከውጭ ይገባል። በቀጥታ የሚመጣ የዕርዳታ እህል ሳይጨመርበት ማለት ነው።
የነዳጅ ፍጆታም፣ በሃያ ዓመታት ውስጥ 4ዕጥፍ ሆኗል።
1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ይመጣ ነበር። ዛሬ 4 ሚሊዮን ሆኗል። በሊትር እንግለጸው ከተባለ…
ከሃያ ዓመት በፊት፣1.3 ቢሊዮን ሊትር ነዳጅ ይመጣ ነበር። ዛሬ 5 ቢሊዮን ሊትር ገደማ ነው። ማዳበሪያ ደግሞ በአስር ጨምሯል፡፡ ዛሬ ወደ ሃያ ሚሊዮን ኩንታል ተጠግቷል፡፡ የመንግስት ዕቅድ ሲታይ ደግሞ፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ ከ30 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ይደርሳል ተብሎ
ይጠበቃል፡፡ ማዳበሪያ ለመግዛት ብቻ ሳይሆን ለማጓጓዝ ስንት ጣጣ እንደተፈጠረ አምናና ካቻምና አይታችኋል፡፡ ወደፊትስ?
ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት የታየው የኢኮኖሚ ለውጥ ቀላል ለውጥ አይደለም። ነገር ግን፣ እነዚህ የቁጥር ለውጦች ሁሉ የድህነት ቁጥሮች ነው። ኑሯችን እንዲሻሻል፣ አገራችን እንድትበለጽግ የምንመኝ ከሆነ፣ ገና ምኑንም አልነካነውም ማለት ይቻላል። የእስከዛሬው እድገት፣ እንደ መነሻ ይረዳ እንደሆነ እንጂ፣ ከቁጥር አይገባም። አገር ሊያድግ ከሆነ፣ የውጭ ንግድ እጅግ በፍጥነት ማደግና መስፋት አለበት። ወደ አገር
የሚገባ ምርት ብቻ አይደለም። ወደ ውጭ አገራት ወደ አለም ገበያ የሚሄድ ምርት፣ በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ውስጥ፣ ቢያንስ ቢያንስ አስር ዕጥፍ ማደግ አለበት። በትንሹ ማለቴ ነው። በጣም ለመበልጸግ አይደለም። ወደነ ኬንያ ለመጠጋት ያህል ነው። እንዲያውም፣ መንግሥት “የዓሥር ዓመት ዕቅድ” ብሎ ያወጣውን ሰነድ ማየት ትችላላችሁ። በ10 ዓመት ውስጥ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከዕጥፍ በላይ ለማሻገር፣ በየዓመቱ በአማካይ በ10 በመቶ ማደግ፣ የውጭ ንግድ ደግሞ በ20 በመቶ መጨመር እንዳለበት ይገልጻል (ገጽ 27)።
ለዓሥር ዓመት ከታቀዱት ግቦች መካከል አንዱ፣ በወደ ውጭ የሚሄዱ ምርቶችን ማሳደግ፣ዓመታዊው ሽያጭም ከ3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 18.3
ቢሊዮን ዶላር ማድረስ እንደሆነ ተጠቅሷል።
“to increase merchandise export revenues from USD 3.0 billion to USD 18.3 billion” (ገጽ 46)። በሌላ አነጋገር፣ የአገሪቱ “ኤክስፖት”…. በዓሥር
ዓመት ውስጥ ወደ 6 ዕጥፍ፣ በ15 ዓመት ውስጥ ወደ 15 ዕጥፍ ይደርሳል ማለት ነው፤ የመንግስት እቅድ
ከተሳካ። ሊሆን አይችልም አይባልም። ነገር ግን፣ “የኤክስፖት ምርቶችን” በ15 ዓመት በትንሹ ወደ 10 ዕጥፍ ማሳደግ ያስፈልጋል። የውጭ
ንግድ ካላደገ፣ የአገር ኢኮኖሚንና የዜጎችን ኑሮ በወጉ የማሻሻል ዕድል ይመናመናል። ግን፣ ቢሳካ እንኳ፣ ያ ሁሉ ምርት እንዴት ነው
ወደ ውጭ አገራት በጊዜ መጓጓዝ የሚችለው?“የመሬት መንቀጥቀጥ” እና “የእሳተ ጎመራ”ክስተት የሚያሰጋው የጂቡቲ መንገድ አንዳች
ነገር ቢገጥመው፣ ወይም ጅቡቲ ውስጥ አንዳች የፖለቲካ ትርምስ ቢከሰት፣ ኢትዮጵያ መፈናፈኛ አይኖራትም።
አሁን ከየመን የተላኩ “ድሮኖች” እና የተተኮሱ ሚሳዬሎች እየሰማን ነው እና በቀይ ባሕር ላይ የሚተላለፉ መርከቦች አደጋ ላይ ቢወድቁ፣
መተላለፊያ ቢያጡ፣ ለማን አቤት ይባላል?

Read 740 times