Wednesday, 13 December 2023 10:33

ኢትዮ ቴሌኮም ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮ ቴሌኮም ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር አሰራርን ለማዘመን፣ የቴክኖሎጂ ሶሉሽኖችን ለማቅረብና ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን አስታወቀ፡፡

 
 ኢትዮ ቴሌኮም፤ ከዚህ ቀደም የሚኒስቴር መ/ቤቱን አሰራር ለማዘመን የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂና ዲጂታል ሶሉሽኖችን ለማቅረብ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቁሞ፤ በቀጣይም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሶሉሽኖችን በስፋት ለማቅረብና የስራ ፈጠራን ለማበረታታት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ፣ የዜጎችን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የፊርማ ሥነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት መከናወኑን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ አመራሮች መካከል ከዚህ ቀደም ስትራቴጂካዊ አጋርነትን የበለጠ ለማሳደግና ውስጣዊ አቅሞችን ለአገራዊ ተልዕኮ አቀናጅቶ ለመጠቀም የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ፣ ኩባንያው  ወደ ውጭ ሃገራት ዜጎችን የሚልኩ ህጋዊ ኤጀንሲዎች ፍቃድ ለማውጣትና ተዛማጅ ክፍያዎችን በቴሌብር አማካኝነት ለመፈጸም የሚያስችላቸው አሰራር  ተግባራዊ ማድረጉን አስታውሷል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም አክሎም፤ ወደ ውጭ ሃገራት ለሥራ የሚሄዱ ዜጎች በተዘጋጀላቸው የሮሚንግ አገልግሎት አማካኝነት በያዙት የሃገር ቤት ሲም ካርድ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም በቴሌብር ሃዋላ አማካይነት ገንዘብ ወደ ሃገር ቤት ለሚልኩ የማበረታቻ ልዩ ጥቅሎች ዝግጅት ማጠናቀቁን ጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያው፣ የሚኒስቴር መ/ቤቱን አሰራር ለማዘመን የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂና ዲጂታል ሶሉሽኖችን ለማቅረብ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን የጠቆመ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የሚኒስቴር መ/ቤቱን የዳታ ሴንተር ማዕከላት የማዘመን፣ ቅርንጫፎችን ከማዕከልና እርስበርስ በፈጣን ኢንተርኔት የማስተሳሰር፣ እንዲሁም የጥሪ- የግንኙነት ማዕከል አገልግሎት ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡

Read 967 times