Tuesday, 12 December 2023 20:15

የጉራጌ ብዝኃ የእሴት ስርዓት

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

       ቋንቋ ድምፅ ነው፡፡ ድምፅ ሁሉ ግን ቋንቋ አይደለም፡፡ ድምፅ በራሱ ትርጉም የሚሰጥ ካልሆነ ቋንቋ ሊባል አይችልም፡፡ ቃልም  ቢሆን ትርጉም ያለው መሆን ይኖርበታል እንጂ በማንም ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ቃል ሁሉ ቋንቋ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ምክንያት ድምፆች፣ቃላት፣ ሐረጎችና ዓረፍተ ነገሮች ተቀናብረው በቋንቋ ህግ መሰረት አንድን መልዕክት ማስተላለፍ አለባቸው፡፡ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ህብረተሰብ በልዩ-ልዩ ምክንያቶች ከአጎራባቹ ህዝብ ጋር ይገናኛል፡፡ የጉራጌ ህዝብ አምስት ቋንቋዎች ተናጋሪ ነው፡፡ እነዚህም፤… ኢሄ፣ ኢያ፣ አነ፣ ኸዲ፣ አኔቲ…በመባል ይጠራሉ፡፡ ሁሉም የተለያየ የአነጋገር ዘዬ አላቸው፡፡ እያንዳንዳቸው አጠቃላይ የሚባሉና በጠቅላላው የጉራጌ ህዝብ ዘንድ የሚነገሩ የቤተ-ጉራጌ ልሳን ናቸው፡፡ ከእነዚህ አምስት ቋንቋዎች መካከል የኢያን እሚናገሩ ደግሞ ኻዥ፣ ቸሀ፣ ጉመር፣ ጌቶ፣ እነሞር፣ ኤነር፣መስቃንና እንደጋኝ ናቸው፡፡ በቸሀ ወረዳ ሲስ ቀበሌ ተወልዶ እምድብር ያደገው ደራሲና ተርጓሚ ሳህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም ከጉራጊኛ ቀበልኛዎችአንዱ በሆነው አፍ በፈታበት፣ በሚናገርበት በቸሀ ቋንቋ ጽፎ ያቀረበው ብቸኛ ስራው ነው - የሺንጋ መንደር፡፡ ሳህለ ሥላሴ ተማሪ በነበረበት ወቅት የስነ-ልሣን ምሁር የነበሩት ፕሮፌሰር ሌስሎ፤ በጉራጊኛ አንድ ጽሁፍ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብላቸው ይጠይቁታል፡
፡ እርሱም የሺንጋ ቃያን ይጽፋል፡፡(ይህ መጽሐፍ Shineqa’s Vilage - በሚል ወደ እንግሊዝኛም ተተርጉሟል)፡፡ ይህም የመጀመሪያው የጉራጊኛ ልቦለድመሆኑ ነው፡፡ ሰባት ቤት ጉራጌ የሚለው ስያሜ፤ ሰባት የተለያዩ ጎሳዎች ተሰባስበው እሚጠሩበትና በጋራ የመሰረቱት ህብረት እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በአካባቢው እየተዘዋወሩ የብሔረሰቡን ታሪክና ትውፊት (ማን ነበር? የሰላምና የማህበራዊ ደህንነት ምሰሶው ትውፊት ነው ያለው!) በማስመልከት ጥናት ያደረጉ፣ መጽሐፍ የጻፉ…የዘርፉ ምሁራን ጥቂት አይደሉም፡፡ ምንም እንኳን የጉራጌ ህዝብ እንደ አፈርሳታ መሰል ጥንታዊ እና አኩሪ የሆነውን ነባር ታሪኩን በጽሁፍ አስፍሮት ባይገኝም፤ ነገር ግን በትውፊት
በተላለፉ የታሪክ መረጃዎችን ተንተርሶ በርካታ ታሪካዊ እውነቶችን መገንዘብ ግን አያዳግትም፡፡ ከዚህ ባሻገር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሰናሰሉ በመወራረስ የተላለፉ ጥንተ ጥንታዊነት ያላቸው የታሪክ ቅርሶች እና የማንነቱ መገለጫዎች የሆኑ ትውፊታዊ አሻራዎቹ እስከ ዛሬ ድረስ ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ ሳህሌ ከእነዚህ መካከል ጥቂት የማይባሉትን በሁለቱም ሳኖቻቸው፣ በአፈርሳታ እና በሺንጋ መንደር ውስጥ በቻሉት መጠን ለማሳየትና ለማስገንዘብ ሞክረዋል፡፡ በርግጥ በርካታልማዳዊ ድርጊቶችና ባህሎች ከትውልዶች ተቀባብለናል፡፡ በጎ ጎን ቢኖራቸውም እንኳን እንደ አገር ከሚጎዱን ጉዳዮች መካከል፤ አንዱ ሌላውን ያለበቂ ምክንያት መክሰስ እና
መካሰስ ነው፡፡ አፈርሳታ ከሶ ከማስቀጣት በፊት ወንጀለኛውን ለማውጣጣት የሚደረግ የአውጫጪኝ ስርዓት ሂደት መሆኑን ባሳለፍነው ሳምንት በአፈርሳታ የጉራጌ ብዝኃ የእሴት ስርዓትቅኝታችን ዳስሰናል፡፡ ዶ/ር መክብብ ጣሰው በቅርቡ ለንባብ ባበቃው “የስሜት ልህቀት” በተሰኘ መጽሐፉ ውስጥ፤…
መወያየት፣ መተጋገዝና አብሮ መስራት በስሜት ልህቀት ውስጥ የሚመጣ በረከት
መሆኑን በአጽንኦት አብራርቶ ሲያበቃ፤ በተቃራው ደግሞ መክሰስና መካሰስ ስሜታዊነት በእጅጉ ያመዘነበት ተግዳሮት መሆኑን በጥናቱ እንደሚከተለው አስረግጦ ገልጿል፡፡…“መካሰስ ከአቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች በጠረጴዛ ላይ ያለው የሰላም አማራጭ ሲያልቅ፣ የእርቅ ተስፋው ሲከስም መስማማት በማንችላቸው ጉዳዮች ሲሆን ግድ ነው፡፡ ነገር ግን ተወያይተን መፍታት የሚገባንን በስሜታዊነት ዘለን የምንከስና የምንካሰስ ከሆነ ከርሞ ጥጃ ነው የምንሆነው፡፡ ከ50 በመቶ በላይ ፍርድ ቤት መምጣት የማይገባቸው ጉዳዮች በስሜታዊነት የሚመጡ ናቸውና እውነትነት አላቸው ብዬ አላምንም፡፡ መካሰስን የሚያመጣው ዋነኛው ምክንያት መጠራጠር፣ ፉክክር፣ ጭፍን ጥላቻ፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ አብሮ መስራት ያለመቻል ችግር፣ የመከባበር ችግር፣ ርህራሄ የማጣት…ወዘተ ችግሮች ውጤት ነው፡፡ ይህ በቀጥታ የሚያሳየው የስሜት ብቃት ችግር እንዳለብን ነው፡፡
የስሜት ልህቀት ያለው ሰው በትንሽ በትልቁ አለቃው ጋር እየሄደ ክስ አያቀርብም፡፡ ነገር ግን የሚፈጠሩትን ችግሮች እዚያው ባለበት ይፈታል፡፡ ለአለቃው ባርኮት እንጂ እርግማን አይሆንም፡፡ ችግሮችን ከነመፍትሄው ያቀርባል እንጂ በክስ መልኩ አያቀርብም (ገጽ.146)፡፡ አንድ ኅብረተሰብ ከሚገለጽባቸው ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ ባህል ቁጥር አንድ ተጠቃሽ ነው፡፡
ባህልና ማህበረሰብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ብዝኃ ባህል ያላት እድለኛ አገር ናት፡፡ ይህን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለአገር እድገት፣ በቱሪዝም ለውጥ ለማምጣት…እጅግ ጠቃሚ አንጡራ ሀብት ነው፡፡ (ታዲያ ባህላዊ የሚመስሉ
ነገር ግን ጎጂ የሆኑትን ልማዶች በውስጡ መሰግሰጋቸውንም መርሳት የለብንም)፡፡ የጆካ! ሰባት ቤት ጉራጌ ውስጥ ህጎች የሚመነጩበት፣ የሚሻሻሉበትና ተግባራዊ የሚሆኑበት ከፍተኛ የህግ ተቋም ነበር፤ ዛሬም ነው፡፡ ተቋሙን በመመስረት፣ ህጎችን በማመንጨት፣ በማብራራትና በማስፈፀም ረገድ የሚጠቀሱ ታዋቂ የጎሳ አለቆች እና ግለሰቦች አሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የየጎሳው ነገስታት የባሮችን (የኬት ዳነ) እና የሴቶችን (ያንቂት ዳነ) መብቶች የማስከበር ስልጣን ነበራቸው፡፡ በተለይ ለወንድ ያመዘነውና የፍቺ ስርዓት እንደሆነ የሚነገረው አንቂትን አለመጥቀስ አይቻልም፡፡ ባል ሚስቱን በፈለገ ጊዜ ፈትቼሻለሁ፤ ማንንም ልታገቢ ትችያለሽ! በሚል ያለገደብ የሚያሰናብትበትና ሴቷ ላይ ገደብ የሚጥል ኢ-ፍትሀዊ ህግ ነው፡፡ ገደቡን በመጣስ ባል ካገባች አንቂት ኖርባታል፡፡ በጉራጌ ህዝብ ዘንድ ይህን የፍቺ ስርዓት በመቃወም ከተነሱ ሴቶች በዋነኝነት የምትታወቀው የቃቄ ወርድወት ነች፡፡ የቃቄ በተናጠል ከመቃወም አልፋ የሰባት ቤት ጉራጌ ሴቶችን በመቀስቀስ ለአድማ እስከ ማሰለፍ ሙከራ አድርጋለች፡፡ ይህንን የተገነዘቡት የባህላዊ አስተዳደር ተወካዮች “በአንቺ ላይ አንቂት አይኑር፤ የመረጥሽውን
አግቢ የጠላሽውን ፍቺ” በማለት ከሴቶች የተለየ መብት ለሷ በመስጠት ነገሩን ማርገብ ችለዋል፡፡ የቃቄን ዝርዝር ታሪክ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ “እምቢታ” በሚል ርዕስ ለጥራዝ አብቅቶታል፡፡( በነገራችን ላይ የቃቄን የመጀመሪያዋ የሴቶች መብት ተሟጋች፣ የተደራጀ የሴቶች የጾታ ትግል ፋና ወጊና መሪ…
በማለት የሚያሞካሿት ጥቂት አይደሉም) በአጠቃላይ በሰባት ቤት ጉራጌ ውስጥ አንቂት የተነሳላቸው ሁለት ሴቶች የቃቄ ወርድወት እና አጀት ቡቅሬት ብቻ መሆናቸውን የብሄሩ ትውፊታዊ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ከሴቶች ጎን ለጎን ከሩቅ ዘመን ከፍተኛ ዕውቅና ካገኙ ታዋቂ ወንዶች፣ የቤተ-ጉራጌ ተወላጆች መሀል ንጉስ ዳርሰሞ ኬር፣ ጌታ ጋችወ፣ አጋዝ ጋድሶ፣ ዓሊ ደነቦ፣ አሰና ማንቆርዬ፣ አንጃሞ ይመኖ… ይጠቀሳሉ፡፡ ለምሳሌ ስለ አንጃሞ መርስኤ ኃዘን “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት” በተሰኘ ማስታወሻቸው ውስጥ ታሪኩን እንዲህ ዘግበውታል፡፡…“ከቀቤና ተነስቶ የሰባት ቤት ጉራጌን በማስተባበር የአፄ ምኒልክን ጦር የተቋቋመና በአካባቢውም እምነት እንዲሰፍን ትልቅ ሚና የተጫወተ ነው፡፡ በ1880 ዓ.ም ከራስ ጎበና ጋር ባደረገው ጦርነት ቢሸነፍም ስለጦረኝነቱ እንዲህ ተብሎ ተገጥሞለታል፡፡ “አንጃሞ ደንደናው ገባር፣ ጎቤን ገጠመው ግንባር ለግንባር፡፡ (ገጽ.146) ወንዶቹ በጉራጌ ህዝብ ታሪክ ውስጥ ታዋቂ የሆኑት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት የተካሄዱት ተደጋጋሚ ወታደራዊ ዘመቻዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ዘመቻዎችና አውደ ውጊያዎች የተለያዩ የታሪክ ምሁራን በዘገቧቸው ታሪካዊ ሰነዶች ላይ ማግኘትይቻላል፡፡ “የሺንጋ ከናም” “ደራሲ የመሆን ሀሳብ አልነበረኝም - ግን ከልጅነቴ መጽሐፍ ማንበብ እወድ ነበር፡፡ ድርሰት ስራ ውስጥ እገባለሁ ብዬ ያሰብኩበት ቀን አልነበረም፡፡ ብዙ ካነበብኩ በኋላ በአጋጣሚ በሰው ጥያቄ የመጀመሪያ መጽሐፌን ጻፍኩ፡፡”
(ፈርጥ.1994) የወጣትነት የፈጠራ ድርሰታቸው ነው - የሺንጋ ቃያ፡፡ ደራሲ መሆናቸውን ያስመሰከሩበት፤ በተግባር ያሳዩበት፡፡ ይህን ስራ በጉራግኛ የጻፉት ከ59 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ አሜሪካን አገር ለህትመት ከበቃ እነሆ አምስት አስርታት አስቆጠረ፡፡ ሳህሌ ወደ አማርኛ ለመተርጎም የተነሳሱት፤ በነፃ ትርጉም መልሰው ያስነበቡት ደግሞ በቅርብ ጊዜያት ነው፡፡ ሺንጋ የመሪው ገጸ-ባህርይ
መጠሪያ ስሙ ነው፡፡ ቃያ በጉራጊኛ መንደር ማለት ሲሆን፤ ከናም ደግሞ ጉዞ ነው፡፡ ድርሰቱ የሺንጋን ከልጅነት እስከ እውቀት ያለውን የህይወቱን ጉዞ፣ የኑሮውን ውጣ ውረድ ይተርካል፡፡ ሺንጋ በራሱ አንድ ታዳጊ የጉራጌ ተወላጅ ይሁን እንጂ ገና ከአፍላነቱ፣
ከእረኝነቱ የጀመረ አስተዳደጉና አመጣጡ ሁሉ… የብዙኃኑን የጉራጌ ተወላጅ ህይወትን የሚወክል፤ ወይም ወክሎ የሚጫወት ሁለገብ ሚና ያለው ሆኖ ተስሏል፡፡ ሺንጋ ነፍስ አውቆ ሳያረፋፍድ በማሰላሰል ውስጥ ራሱን መመልከት፣ ኑሮውን በጥልቀት መፈተሽ ሲጀምር የታሪኩ ግጭት ጥንስሱ ይጀምራል፡፡ ልብ ያላለው የአገር ቤቱ ጉዝጓዙ እና አሰስ ገሰሱ፣ የሳር ፍራሽ ላይ መተኛቱ…
ይሰለቸውም ይጀምራል፡፡ ሬዲዮ ወይም ጋዜጣ የለ፣ መብራት የለ፣ ገባ የሚሉበት ቡና ቤት የለ፤ ነጋ ጠባ የሽማግሌዎችን አርቲ ቡርቲ መስማት ሲደብር…ሲል ያማርራል፡
፡ የሚያየው ሁሉ አልጥም ይለዋል፡፡ እንደ ታላላቆቹ ከተማ ሄዶ መነገድ፣ በኢኮኖሚ መመንደግ ነብሱ አብዝታ ትሻለች፡፡ እንደ አቅሙ ጥሮ ግሮም፣ በንግድ ተፍጨርጭሮም ራሱን ለመቻል ቤተሰብ ለመርዳት እና እንዲሁም የቋጠራትን ጥሪት በመላ የጉራጌ ቤተሰብ ውስጥ በየአመቱ በጉጉት በሚጠበቀውና በሚከበረው የመስቀል ክብረ በዓል ላይ ለመታደም በሚያደርጋቸው፤ ክንውኖች እንደየቅደም ተከተሉ ተዋረዱን ጠብቆ በሚወርደው የታሪኩ ጉዞ ውስጥ ይተረካሉ፡፡ ሳህሌ በሺንጋ መንደር ውስጥ የጉራጌን ባህልና አኗኗር ያነሳሉ፣ ነባር ትውፊቱን ያስታውሳሉ፣ የስራ ባህሉንና ጥበባዊ ክንዋኔውን፣ ወደ ከተማ በመሄድ በስራ የሚያደርገውን መፍጨርጨር፤ በማህበራዊ ህይወት ላይ ያለውን ጉልህ ተሳትፎ ይዘረዝራሉ፡፡ በሺንጋ፣ በኬርወጌ፣ በተሬዛ በኩል የትውልድ መንደራቸውን ህይወት ያንጸባርቃሉ፡፡
…ጉራጌ ከታሪኩ መልካም ተሞክሮዎቹ፣ ከዳበረ የባህል እሴቶቹ፣ ከትውፊታዊ ስርዓቶቹ…በርካታ ቁምነገሮችን እንማራለን፡፡ ለሀገርና ለትውልድ አካባቢ የሚሰጥ ፍቅርና አክብሮት እንዲሁም ተቆርቋሪነትና መልካም ነገሮችን ሰርቶ ቤተሰብ በማስደሰት
ምርቃትና በረከት ማግኘትን የመሳሰሉ ወዘተ… በአጠቃላይ ለታላቅ ኢትዮጰያዊ ማንነት የሚያደርገው አስተዋጽኦ አርአያነት ያለውና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት በመሆኑ ለቀጣይ ህይወት አያሌ ጠቃሚ ተሞክሮ እንካፈላለን፡፡ ደራሲና ተርጓሚ
ሳህለ ሥላሴም ብርሃነ ማርያም በሁለቱም ስራዎቻቸው ይህንኑ አጋርተውናል፡

Read 347 times