Saturday, 02 December 2023 19:53

“የአፍሮ ባሮሜትር የጥናት ውጤት የብዙኃኑ ድምፅ ነው›

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 በቅርቡ በህገመንግሥት መሻሻል፣ በጠ/ሚኒስትሩነ ሥልጣን መገደብ ና ሌሎች ተያያዥ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት አካሂዶ
ውጤቴን ይፋ ያደረገው አፍሮ ባሮሜትር ፣ የኢትዮጵያ ተወካይና ተመራማሪ፣አቶ አቶ ሙሉ ተካ፣ ተቋሙ በሚያካሂዳቸው ጥናቶች፣ በናሙና አመራረጥ ና በጥናት በሥነ ዘዴ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ እነሆ፡
          አቶ ሙሉ ተካ ፤በእኢትዮጵያ የአፍሮ ባሮሜት ተወካይና ሚስዝ ማሜ አኩየ፤ የአፍሮባሮሜትር ኮሚኒኬሽን አስተባባሪ

          • ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ላይ በወጣው የዜና ዘገባ፣ የተከበሩ አፈ ጉባኤ አገኘሁ፣ድርጅታችሁ አፍሮባሮሜትር በቅርቡ ይፋ ባደረገው የጥናት ግኝቶች ላይ አስተያየት መስጠታቸው  የሚታወቅ ሲሆን በተለይ “ህገ መንግስቱ ይሻሻል” የሚለውን የጥናት ግኝት በተመለከተ “ጊዜውን ያልጠበቀና ግልፅነት የጎደለው ነው” ሲሉ ተችተውታል፡፡  “አካታችነት የጎደለውም ነው” ብለውታልም፡፡ የእናንተ ምላሽ ምንድ ነው›?
የአፍሮ ባሮሜት የዳሰሳ ጥናት ሽፋን አገር አቀፍ ነው፡፡ የጥናቱ ናሙና cluster, stratified random sampling በተሰኘ ሳይንሳዊ ዜዴ በ3 ቅደም ተከተል ደረጃ በደረጃ የተመረጠ፤ የምልዓተ ህዝቡ አሰፋፈር፤ ብዝሃነት እና ማሕበራዊ ስብጥር የሚያንፀባርቅ አካታችና ወካይ ጥናት መሆኑን ከጥናቱ ናሙና ስርጭት መረዳት ይቻላል፡፡
1ኛ) ኢትዮጵያውን በ11 ክልልሎች እና በ2 አስተዳደሮች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) በገጠርና ከተማ የሚኖሩ በመሆናቸው የጥናቱ ናሙና (sample size) ከምልዓተ ህዝቡ ብዛት ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ (proportional to population size) ተደልድሏል፡፡ መልስ ሰጪዎች ይህንን የሕዝብ አሰፋፈር ከሚያንፀባርቅ ናሙና በተመጣጣኝ ውክልና የተገኙ በመሆናቸው ጥናቱ ቀዳሚ የውክልና መስፈርት ያሟላ ነው፡፡ 67% የሚሆኑ መልስ ሰጪዎች በገጠር፤ 33% ደግሞ በከተማ የሚኖሩ ናቸው፡፡ይህ ስብጥር ከሀገራዊው  መኖርያ ስርጭት ጋር እጅግ የተቀራረበ በመሆኑ ጥናቱ 2ኛው የአካታችነት መስፍርት ያማላ ነው፡፡ ከፆታ ስብጥር ሲመዘን 51% መልስ ሰጪዎች ወንዶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 49% ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡
መልስ ሰጪዎች ከሁለም የእድሜ ክልል የተገኙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወጣቶች በብዛት የሚኖርባት አገር ናትና በዛው ልክ በጥናቱ ተወክልላል፡፡ 63% እድሜያቸው በ18ና 35 እድሜ ክልል የሚገኑ ወጣቶች መሆናቸውን ልብ ይላል፡፡ 18% እድሜያቸው 36 45፤ 9% ከ45 55፤ ቀሪዎቹ  10% ደግሞ ከ55 በላይ ናቸው፡፡ በጥናቱ የተሳፉ ዜጎች ኃይማኖታዊ እምነት ስብጥር ስንመለት 627% ክርስትያን፡ 369% ሙዝሊም እና 04% እምነት የሌላቸው እንደሆኑ ነግረውናል፡፡
2ኛ) ክመልስ ሰጪዎች ማንነት (identity) ስብጥር አንፃር ሲመዘን ጥናቱ የኢትዮጵያን የቋንቋ እና የባህል ብዝሃነት (linguistic and cultural diversity) የተንፀባረቀበት ነው፡፡ ክጥናቱ ተሳታፊዎች 98.8% የሚሆኑት ከተለያዮ ብሔርና ብሔረሰቦችና የተገኙ ናቸው፡፡ ማንነታቸው በሚመለክት ላቀርብንላቸው ጥያቄ  ከረጅሙ ዝርዝር በከፊል ለመጥቀስ ያክል ራሳቸውን ኦሮሞ፡ አማራ፤ ሱማሊ፤ ትግራዋይ፤ አፋር፤ ሲዳማ፤ ሀረሪ፤ አገው፤ ቅማንት፤ አኝዋክ፤ ዲንቃ፤ ሽናሻ፤ በርታ፡ ወላይታ፤ ጋሞ፤ ጌድዮ፤ ቤንች፤ ደራሼ፤ ዳውሮ፤ ሀመር፤ መንቲ ወዘተርፈ እንደሆኑ ነግረውናል፡፡
 ቀሪዎቹ 12% ደግሞ “እኢትዮጵያዊ ብቻ እንደሆኑና አንዱ ወይም ሌላኛው ማንነት አለን ብለው እንዳማያስቡ ነግረውናል፡፡
በነሲብ (randomly) ተመርጠው በጥናቱ የተሳተፉ መልስ ሰጪዎች ስብጥር የምልዓተ ህዝቡን ማህበራዊ ስብጥር የሚያንፀባርቅ እና ብዝሃነትን የሚያሳይ ሆኖ ሳለ፤ እንዴት “ሁሉንም ብሔሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ያላካተተ ነው” ሊባል ይችላል? መልሱን ለአንባብያን እተዋለሁ፡፡
3ኛ) በዚህ ጥናት በመልስ ሰጪነት የተሳተፉ ዜጎች የትምህርት ዝግጅት ስንመለከት 42% መደበኛ ትምህርት የሌላቸው፡ 5% መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ያላቸው፤ 35% የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁ፤ 18% 2ኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁ ሲሆን ቀሪዎቹ 13% ድህረ 2ኛ ደረጃ ትምህርት የተማሩ ናቸው፡፡ ከዚህ ስብጥር መረዳት የምንችለው ከአጠቃላዮ መልስ ሰጪዎች ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ (87%) የሚሆኑት ተራ ኢትዮጵውን ዜጎች፤ ልሒቃኑ ደግሞ 13% ብቻ መሆናቸውን ነው፡፡ ለዚህ ነው “ሕዝቡ አስተያየቱን ይስጥ!” በሚል መሪ ቃል የሚናክወነው የአፍሮ ባሮሜትር የጥናት ውጤት የብዙኃኑ ድምፅ ነው የሚለው የምንለው፡፡ ነገር ግን ቢዚህ ጥናት የተሳተፉት ልሒቃን ብዛት አናሳ (13%) ሆኖ ሳለ፤ አፍሮ ባሮሜትር “ጥቂት ልሒቃን አነጋጋፍሮ ያቀረበው ሰነድ ነው” ሊባል ይቻላልን? አሁንም መልሱ ለአንባቢያን እተዋለሁ፡፡
•  ምናልባትም “66 በመቶ ኢትዮጵያውያን  የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር የሥልጣን ዘመን መገደብ አለበት” ብለዋል የሚለው የጥናት ውጤትም ከትችትና ከሂስ አያመልጥም የሚል ግምት አለ፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ  እንዲህ ያሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በአገራችን አወዛጋቢ በመሆናቸው ሳይሆን አናቀርም፡፡ በግላችሁ የደረሳችሁ አሰተያየት ወይም ትችት ይኖር ይሆን? በዚህ ዙሪያ--
 የአፍሮ ባሮሜትር ጥናት ይህ ብቻ ሳይሆን ልሒቃኑ በቀጣይ እያከራከቱ የሚገኙ ሌሎች የሕገ መንግስቱን ድንጋጌዎች ያካተተ ጥናት ነው፡፡ በእነዚህ አወዛጋቢ ድንጋጌዎች የተራው ዜጋ አስተሳሰብ ለመለክት የሚደረግ ጥናት ቢተችና ሂስ ቢቀርብበት ባህርያዊ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አፍሮ ባሮሜትር ዜጎች በጥናቱ ላይ እንዲወያዪ ትችትና ሂስ እንዲሰነዝሩ ያበረታታል፡፡ ይህ ጥናት በ2012 ዓም የተከናወነ ሲሆን በዛን ጊዜ ዜጎች በተለይ በማህበራዊ ሜዲያዎች ተወያይተውበታል፤ ተችተውበታል፡፡ በጥናቱ ስነዘዴ ላይ የቀረቡት ትችቶች ማብራርያ በመስጠት አስረደተናል፡፡ ዘንድሮ በተምሳሳይ ርእሶች የተከናወነው ጥናት ላይ ትችቶች እየቀረቡ ነው፡፡ እኛም የጥናቱን ስነዘዴ በማብራራት ላይ ነን፡፡
•  የጥናት ውጤታችሁን በተመለከተ በአጠቃላይ ከህብረተሰቡ ያገኛችሁት ምላሽ ምን ይመስላል?
“ህብረተሰቡ” የሚለው ቃል ጥቅል በመሆኑ ጥያቄውን ለመመለስ እቸገራለሁ፡፡ ነገር ግን የሜዲያ ሞኒቶሪንግ ስራ በመስራት ላይ በመሆናችን ምላሹ ከየትኛው የህብረተሰ ክፍል ነው? ይዙቱ ምንድ ነው? የሚሉትን ለመመለስ ጊዜው ገና ነው፡፡
•  በግጭትና ጦርነት ሳቢያ በአንዳንድ ክልሎች ጨርሶ መንቀሳቀስ የማይቻልበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ተከስቷል፡፡ ባለፉት 2 ዓመታት በትግራይ፣ ባለፈው አንድ ዓመት ደግሞ በአማራ ክልል ብዙ ቦታዎች፣ በኦሮሚያ እንዲሁ በተወሰኑ ቦታዎች የፀጥታ ችግር ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የተካሄደ ጥናት አካታች ነው ሊባል ይችላል? ጥናቱ መላ ኢትዮጵያን የሚያካትት ነው ከተባለ ማለቴ ነው?
በቅድሚያ መረጃ ለመሰብሰብ የመስክ ስራ የተክናወነው ከፕሪቶርያ ስምምነት በኃላ ሲሆን በአማራ ክልል ባሁኑ ጊዜ የሚታየው ግጭት ባልነበረበት ጊዜ ነው፡፡
 በመጀመሪያ ደረጃ የናሙና መረጣ (1st stage sample selection ) ጥናቱ የሚከናውንባቸው የቆጠራ ጣቢዎች ክየክልሉ  በነሲብ የተመረጡ ሲሆን በኦሮሚያ የፀጥታ ችግር ባለባቸው የተወሰኑ አከባቢዎች የወደቁ በጣት የሚቆጠሩ የቆጠራ ጣቢያዎች በድጋሚ በrandom drawing ከመተካታቸው በስተቀር ጥናቱ አካታች ስለመሆኑ ከካርታው ከሚታየው የናሙና ክልላዊ ስርጭት መረዳት ይቻላል፡፡  
•  ጥናቱ ሁሉንም ክልሎች ያካተተ እንደኾነ ተጠቅሷል። 2400 መጠይቆች መደረጋቸውም ተነግሯል፡፡  የተወሰዱት ናሙናዎች ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥሩ አንፃር ወካይ ናቸው  ማለት  ይቻላል ?
ለዳሰሳ ጥናቶች የናመኗ መጠን ( sample size) ስንት ይሁን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በሳይንሱ ተቀባይነት ባገኘ ቀመር ወይም ፎርሙላ እና ቁልፍ ስታቲስቲካዊ መስፈርቶች መሰረት ነው፡፡ ከመስፈርቶቹ አንዱ አስተማማኝ የርቀት መጠን (confidence interval) የሚባለው ነው፡፡ ምልዓተ ህዝቡ (population )  ሲጠና አስተማማኝነቱ መቶ በመቶ ነው፡፡ ነገር ግን ጥናቱ በናሙና የተመሰረተ ነውና 100%  አስተማማኝ  ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የመጀመርያ ጥያቄ የጥናቱ አስተማማኝነት ስንት ይሁን? 99% 97% ፣ 95%  ወይስ 90 %.? ጊዜና በጀት ታሳቢ በማድረግ፣ አፍሮ ባሮሜትር 95% የአስተማማኝ የርቀት መጠንን ታሳቢ አድርገዋል፡፡ ይሀ ከፍተኛ ከሚባሉት ርቀቶች አንዱ ሲሆን በእንደዚህ ዓይነት ማህበራዊ ጥናቶች ተመራጭ ነው፡፡
የስህተት ወይም የኅዳግ መጠን  (margin of error)  የሚባለው ነው፡፡
ማንኛውም ጥናት በናሙና የተመሰረተ ነው፡፡  ጥናቱ ናሙና እንጂ ምልዓተ ህዝቡን የማያካትት ስለሆነ ለስህተት (sampling error) የተጋለጠ ነው፡፡ ዋናው ቁምነገር ምን ያክል ስህተት እንቀበል የሚለው ነው፡፡ 1%፤ 3%፤5%፤10%. አፍሮ ባሮ ሚትር 2% የስህተት ወይም ኅዳግ መጠን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን የጥናቱን ውጤት ከመተርጎም አንፃር ጠንቃቃ (conservative ) ሊባል የሚችል ግምት ነው፡፡ በዚህ ቀመር መሰረት የጥናቱ መጠን 2400 ይሆናል፡፡ በርግጥ የናመናው መጠን ከፍ ቢል የኅዳግ መጠኑ ስለሚቀንስ የጥናቱ አስተማማኝነት ክፍ ይላል፡፡ ነገር ግን ናሙናውን በጨመርን ቁጥር በጥናቱ አሰተማማኝነትና ትክክለኛነት (precision) የሚያመጣው ለውጥ ከወጪው ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ አይደለም፡፡  የናሙናው መጠን በ10 እጥፍ ወደ 24,000 ወይም ወደ 240,000 ከፍ ቢል፣ ከዛን ያክል መልስ ሰጪ መረጃ ለመሰብሰብ ከሚወጣው ወጪ ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ በተመሳሳይ ርእስ በመንግስታዊው የፖሊስ ጥናት ኢንስቲትዩት በ2015 ዓም በተደረገው ሀገራዊ ጥናት ናሙና 1400 ነበር፡፡ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው አሜሪካውያን ብዛት ከ260 ሚልዮን በላይ ቤንም ጋልአፕ (Gallup) እና Pew Research Center የተሰኙ የአሜሪካ የጥናትና ምርምር ድርጅቶች ለሀገራዊ ጥናት የሚውስዱት የናሙና መጠን ከ1000 እስክ 1200 ነው፡፡ እንግዲህ የናሙና መጠን ሲወሰን አጠቃላይ የህዝብ መጠን ሳይሆን እነዛ ስታቲስቲካዊ መስፈቶችን ታሳቢ በማደረግ ነው፡፡
•   በተለይ በእኛ አገር ባለፈው ይፋ ያደረጋችሁት ዓይነት የጥናት ግኝቶች (ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው) ከማወዛገብም አልፈው መንግስት ጥርስ ውስጥ ሊያስገቡ ይችላሉ፡፡ እስካሁን በአጠቃላይ  የገጠሟችሁ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
አፍሮ ባሮሜትር በርእሰ ጉዮቹ ላይ ጥናት ሲያደርግ ለ2ኛ ጊዜ ሲሆን የመጀመርያው በ2012  .ዓ.ም የተከናወነ ነው፡፡ በሁለቱም ዙሮች የገጠመን ተጠቃሽ ተግዳሮት የለም፡፡
በነገራችን ላይ በአወዛጋቢ የሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ላይ በኢትዮጵያ ጥናት ሲደረግ አፍሮ ባሮሜትር ብቸኛ አይደለም፡፡በ2015.ዓ.ም መንግስታዊው የፖሊስ ጥናት ኢንስቲትዮት በነዚህ ጉዳዮች ጥናት አከናውኖ አምና ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡
•  የባሮአፍሮሜትር ቀጣይ እቅዶችና ራዕዮች ምንድን ናቸው?
የአፍሮ ባሮሜትር ቀጣይ እቅዶች፣ ጥናት የሚያካሂድባቸውን የአፍሪካ አገሮች ብዛት ከ42 ወደ 53 ከፍ በማደረግ አህጉሪቱን መሉ መሉ ማካተት ሲሆን፤ የተራ አፍሪካያውያን ዜጎች ድምጽ የፖሲና የውሳኔ አሰጣጥ አምድ ማደረግ ነው፡፡
•  አሁን የምትሰሩት ዓይነት ጥናት ብዙ ወጪ ይጠይቃል፡፡ የፋይናንስ ምንጫችሁ ምንድን ነው?
የአፍሮ ባሮሜትር ጥናቶች በበርካታ አለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች የፋይናስ ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን፤ ክብዙዎቹ በጥቂቱ ለመጥቀስ ዩኤስኤይድ፤ የስዊድን አለም አቀፍ የልማት ኤጄንሲ፤ ቢል ጌትና ሜለን ፍውንዴሽን፡ የአውሮፓ ሕብረትና አፍሪካዊው ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽኝ ይገኙበታል፡፡
•  ድርጅታችሁ የሚሰራው ዓይነት ጥናት ለአገርና ህዝብ ፋይዳው ምንድን ነው?
የአፍሮባሮሚትር ጥናቶች መንግስት፤ የልማት አጋሮች፡ የሲቪል ማህበራት፤ የፖሊሲ ወትዋቾች እና የተለያዮ ባልደርሻ አካላት የአፍሪካውያንን ዜጎች ፍላገቶችን በፓሊስ ቀረፃ፡ በፕሮግራም እና ፕሮጄክት ዲዛይን ታሳቢ እንዲያደርጉ ጥራቱን የጠበቀ አስተማማኝ መረጃ ያቀርባል፡፡

Read 1658 times