Saturday, 02 December 2023 19:50

“የጉንዳን አፈጣጠር…”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የሆነ በቅርብ ርቀት የምናውቃቸው ‘እሱና እሷ’ ነበሩላችሁ፡፡ በቃ በፍቅር ‘እፍ’ ብለው ሰውን ሲያስቀኑት ነበር፡፡፡ ታዲያላችሁ… በቀደምለት ‘የማይታረቅ ቅራኔ’ ውስጥ ገብተው “አትድረሽብኝ” “አትድረስብኝ” ተባባሉትና አረፉት፡፡ የዘንድሮ ‘አፍ’ ያስባለ ‘ላቭ’ የአወዳደቁ ፍጥነት አይገርማችሁም! ደግሞ‘ኮ… “የጥንቱ ትዝ አለኝ..” የለ “ያሳለፍነው ዘመን…” የለ… “በጨረታው አልገደድም…” ብቻ!
እኔ የምለው … ዛሬ የተለያዩት ሮሚዮና ጁሉየት ከነገ ወዲያ… ‘ፍሬሽ’ ሮሚዩና ጁሊየት ላይ ተሰክተው ስታዩዋቸው…”መቼ ተቦክቶ መቼ ተጋግሮ ለምሳ ደረሰ!” ያሰኛችኋል፡፡
የምር ግን… ደግ ደጉን አላሳያችሁ ብሎን እንደሁ እንጃ‘ንጂ… በሥራም በሉት፣ በጾታም በሉት ‘ፍቅር’ ወይ ‘ኮማ’ ውስጥ ገብቷል ወይ ትርጉሙ ተለውጧል፡፡ እንዴ… ግርም እኮ ነው የሚለው! ይሄ “ሦስት ብር የነበረው ሀምሳ ሳንቲም!...” የሚሉት ነገር ‘ላቭ’ ውስጥም ገባ እንዴ!
ስሙኝማ… ችግሩ ምን መሰላችሁ… እርስ በእርስ እንዳንተሳሰብ እያደረገን ነው፡፡ ‘ለጋራ ጥቅም’ መባባል እየቀረ ነገርዬው ሁሉ “መጀመሪያ የመቀመጫዬን…” ሆኗል፡፡ እኔ የምለው “ጎረቤትህን እንደራስህ ውደደው…” የሚለው ነገር ትዝታ ሆኖ መቅረቱ ነው!  [እንትና… ስለፍቅር ሲወራ አሁንም ጀኔፌር ሎፔዝ ብቻ ነች ትዝ የምትልህ?]
ተስፋ ቆረጥን መሰለኝ… ‘ፍቅር ድሮ ቀረ’ እየተባባልን ነው፡፡ ለነገሩ ‘ድሮ ያልቀረ’ ምን አለ፡፡ አሀ…. ልክ ነዋ! ዘንድሮ እንደሁ ሁለትና ሶስት ዓመት “ድሮ” እየሆነብን ነው፡፡ በመቶ ብር የገዛናት ጫማ መንጋደድ ሳትጀምር… ‘አመለካከት እያለቀ’ ተቸግረናል፡፡ ደግነቱ እኔና እናንተ… እዚች ‘ዕቃ’ የሌለባት የዓለም ክፍል ስቶር ጠባቂ ሆነን ቀረ‘ንጂ… ለጥቂት ዓመት ወጣ ብለው የሚመለሱት… አለ አይደል… በአራድኛው “ጦጣ” ነው የሚሆኑት [ይኸው “ንክኪ” እንኳን ወደ ‘ተለጣፊ” ተለውጣ… ቂ….ቂ…!] የምር‘ኮ… ግራ ገባን !ድሮ ፋሺኑ የሚለወጠው ወይ ቀሚስ… ወይ የፀጉር አቆራረጥ ነው፡፡
 “አዲስ ፋሺን ቀሚስ መጥቷል…” ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ልጄ… ሴቱ ሁሉ ሱሪ ለባሽ ስለሆነ ነው መሰለኝ… ፋሺኑ የሚለወጠው… ‘ላንጉዌጁ’ ሆኖብናል፡፡
ሀሳብ አለን… ቴሌቪዥኖች ‘የሳምንቱ አበይት ዜናዎች’ እንደምታቀርቡልን ሁሉ… ‘የሳምንቱ አዳዲስ ቃላት’ የሚል ፕሮግራም ይከፈትልን፡፡ አሀ… አለበለዛ አካሄዳችን የወቅቱን አጣዳፊ ጉዳይ ያላገናዘበና ራዕይ የሌለው ሆኖ ኅብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ የጋራ አመለካከት በየደረጃው ለማስረጽ የሚደረገውን ጥረት ለጥገኝነት አስተሳሰብ አጋልጦ ይሰጠዋል፡፡
 [ተናግሬ ልቤ ውልቅ ብሎላችኋል፡፡] ስሙኝማ… የምር ግን ስለዚህ ጉዳይ ብንመክር ጥሩ ነው፡፡ አለበለዛ ነገ በ‘አዲስ ቋንቋ’ ሰላምታ የሚያቀርብልንን ሰው “ኧረ ራስህ ደደብ!” ብለን ልንመልስለት እንችላለና!
እናላችሁ… ስለ ‘ፍቅር’ አልነበር የምናወራው… ነገርዬው ሁሉ ደብልቅለቅ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ የሮሚዮና ጁሊየት ዓይነት ታሪክ እኮ… አይደለም በእውን… በቲያትርም እየቀረ ነው፡፡
የምር ግን… እንትናዬዎችም እኮ ግራ እየተጋቡ ነው፡፡ ወንዱ እንደሁ “ትናንት ምሳ ስበላ ትዝ ብለሽኝ..” “ሌሊት ደስ የሚል ሳቅሽ መጥቶብኝ…” ማለት ትቷል፡፡ ጭራሹን “ከመቼ ወዲህ ነው እስከ አንድ ሰዓት ውጪ የምታመሺው?” “ያን ያህል ጊዜ ስልኩን የያዝሽው ከማን ጋር እያወራሽ ነው፣” ምናምን ማለት ነው የሚቀናው፡፡ ምን መሰላችሁ ነገርዬው ለ‘ማርክ’ አሰጣጥም እየቸገረ ነው፡፡
ማለቴ እንትናዬዎቹም የትኛው ‘ትሩ ላቭ’… የትኛው ‘ንብረት ግዢ’ እንደሆነ ለማወቅ ቸግሯቸዋል፡፡ እንዲያው ዝም ብሎ “የዘንድሮ ሴቶች…” ማለቱ ‘ፌይር አይደለም፡፡ [“እንጀራ በአቋራጭ በምላስ በሰለ” ይሏችኋል ይሄ ነው፡፡]
እኔ የምለው… መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ዘንድሮ’ኮ በምላስ ‘ጠብ’ ማድረግ እየቀረ ነው አሉ፡፡ እነአጅሬዎች መች የዋዛ! ልጄ… ዋናው ‘ተግባር’ ሆኗል፡፡ [‘በጥሬው’ ማለትም ይቻላል!] እንደድሮ… “መኪናዬ ጋራዥ ገብታ….” ምናምን ቢባል መልሱ ምን መሰላችሁ “ውይ … አንድ ብቻ ነው ያለኝ እንዳትለኝ!” (አንዳንዱ’ኮ ‘ከመሸለሉ’ ብዛት… እግሩን እንደ እጁ በመስኮት ሊያወጣብን ምንም አይቀረው ደግነቱ የወንድ እግር ላይ ቼይን ገና አለመጀመሩ) እናችሁ…‘ፍቅር’ በገበያው ዋጋ መባል ከተጀመረ በቃ ነገር ጠፋ ማለት ነው፡፡
 አንዳንዱ ደግሞ አለ፡፡ “ሐሙስ ስደውል የት ነበርሽ?” ሲል “ሺህ ሰማኒያ ያለችው አክስቴ ጋር ሄጄ” ምናምን ሲባል ምን ይላ መሰላች… “አንቺ ስንት  አክስት ነው ያለሽ?... ደግሞ ዘመዶቼ ሁሉ ሰንጋተራ ነው ያሉት  ትይኝ አልነበር!” እኔ የምለው … ይሄ ‘ፍቅር’ ነው… ህዝብና ቤት ቆጠራ? ነገርዬውማ ሀዲዱን መሳት የጀመረው … አለ አይደል…. “እወድሻለሁ…” መባል ቀርቶ “ትመቺኛለሽ” ሲባል ነው፡፡ ‘መውደድ’ ሌላ ‘መመቸት’ ሌላ፡፡ እነእንትና ደግሞ ስለመመቸት ሲያወሩ ትዝ የሚለኝ…ፍራሽ!
ስሙኝማ… ይሄ እንትን ‘ሰፈር’ ያለው መናፈሻ በቃ እንደ ድሮው ላይሆን ነው?  ልጄ… ለስንቱ ውለታ ውሏል መሰላችሁ? ሌሎቹ መናፈሻዎች እንዳሉ ይቆዩልን፡፡ አሀ…. ልክ ነዋ! የምር’ኮ አሪፍ ፍቅር የሚገኘው መናፈሻ ውስጥ ነው፡፡ ‘ገበያ’ ቦታ የለውም፡፡ ልጄ…. ሬስቶራንት ውስጥ ጥንዶች በገቡ ቁጥር “አቤት ጉትቻዋ ደስ ሲል!” “ያውልህ በህልሜ አየሁት ያልኩህ ቀሚስ…” ምናምን መባባል የለ… “ምንድነው አሥሬ የምትዞሪው?”… “እዛ ማዶ ያለውን ሰውዬ የት ነው የምታውቂው?” የለ…. በቃ መናፈሻ ውስጥ ግፋ ቢል ስለተፈጥሮ መመራመር፡፡ ግንዱ ስር የሚርመሰመሱትን ጉንዳኖች እያዩ “የጉንዳን አፈጣጠር ግርም አይልሽም?” ማለት፡፡ አሪፍ አይደል! ሌላ ቦታ ግን “ይሄ ሀብል ደስ አይልም?” ሲል “እገዛልሻለሁ ብለኸኝ አልነበረም!” ማለት ይከተላል፡፡ መናፈሻ ውስጥ ግን “መቼ ነው ጉንዳን የምትገዛልኝ?” አይባል! በየማታው በስልክ መጨቃጨቅ የለ…
ይሄኛው “እንደ ቡና ዋጋ…” የሚዋዥቀው ‘ዘመነኛው’ ፍቅር ግን… አለ አይደል…. ሲያምርበትም፣ ሲያስጠላበትም ልክ የለውም፡፡ “በእኔ ፍቅር ልብ ድካም ይዟታል…” የተባለላት በየማታው ስልክ እየደወለች “በቅሎ ቤት ምን የመሰለ ክትፎ ቤት ተከፍቷል መሰለህ…” “ወሎ ሰፈር የበላነውን ቦዘና ሽሮ ብትቀምሰው…” ምናምን ስትል… በቃ የ‘ፍቅር’ ‘ዴፊኒሽን ‘ ተለውጧል ማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ በአፍ ገብቶ ሆድ ላይ የሚያርፍ ፍቅር ‘ኮመን ኮርስ’ የሆነ ይመስላል፡፡
ስሙኝማ… እንዲያው እግረ መንገዴን… ይሄ ወደ ዳር አገር ሲሄዱ … የሚይዘው ‘ፍቅርና ናፍቆት’ አይገርማችሁም? አጅሬ ዲሲ ገብቶ ገና የዋሺንግተን ዘጠኝ ቁጥር አውቶብስ የት እንደሚሄድ ሳያውቅ “የህዝቡ ናፍቆት አላስተኛ አለኝ…” ምናምን ይልላችኋል፡፡
 እዚህ’ኮ የሰፈር ሰው “መቼ ከዚህ ሰፈር በነቀለልን!” እያለ አቤቱታ ሲያቀርብበት የቆየ ነው፡፡ እና… አንዳንድ ‘አርቲስቶችም’ ሆነ ሌሎች… አለ አይደል… ገና ‘መሄዳቸውን’ በቅጡ ሳናውቀው እንኳን የህዝቡ ፍቅር እንቅልፍ ነሳኝ…” ሲሉ በ‘ህግ አምላክ!’ የምንልበት አጥተን እንጂ…ስሙኝማ… መቼም ‘ግሎላይዜሽን’ አይደል ‘‘እነዛኞቹ ስቴጅ ላይ ‘አይ ላቭ ዩ’ ሲሉ የሰሙት… እኛንም “እወዳችኋለሁ” ማለታቸው ክፋት የለውም፡፡ ግን አንዳንዴ… ከእነመፈጠሬም የማታውቀኝ ዘፋኝ ከህዝቡ ቀላቅላህ ‘እንደምትወደን’ ስትናገር… “ከሌሎች ሰዎች ጋር ተምታተንባት ይሆን!” ለማለት ምንም አይቀረን! ልክ ነዋ… ዘንድሮ’ኮ… እንኳን ‘የማታውቀው ድምፃዊ’… የሚያውቁንም የኬክ ቤት ሰራተኞች ‘መውደድ’ ካቆሙ ስንት ጊዜያቸው!
ሀሳብ አለን!... የዘንድሮ ፍቅር መልኩና ‘የቆይታ ጊዜው’ ግራ እየገባን ስለሆነ… የሆነ ግንዛቤ ማዳበሪያ ይዘጋጅልን!! ልጄ… ድሮ እኮ “ሼራተን የሀብታሙ ሰውዬ ነው” ሲባል “እምብዮ… ያንተ ነው!” የሚያስብል ‘ላቭ’ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን “ሞባይል’ኮ ያዝኩኝ፣” ሲባል “ይሄኔ ተውሰህ ይሆናል!” የሚል ‘ፍቅር’ መጥቷል!
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Read 2311 times