Saturday, 02 December 2023 19:36

ዶክተር ደምሱ ገመዳ

Written by  ቶማስ በቀለ
Rate this item
(1 Vote)

ዶክተር ደምሱ ገመዳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ የማቲማቲክስ ምሁር ነበሩ። የወንድሜ የዶክተር ሙሉጌታ በቀለ ጓደኛና የአርሲ ሽርካ ጎቤሳ ተወላጅ ናቸው።በዚህች አጭር ፅሁፌ የዶክተር ደምሱገመዳን ባዮግራፊ ለመፃፍ አይደለም፤በዕርግጥ ምሁሩ በህይወት ዘመናቸው ለሀገራቸው በሙያቸው ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ምሁር መሆናቸውን አውቃለሁ። ለዚህም ዕውቅና በትውልድ ሀገራቸው ጎቤሳ ከተማ መሀከል ላይ ሀውልት(Statue)ቆሞላቸዋል። ከዚህ በታች የማወጋችሁን ታሪክ ዶ/ር ደምሱ ገመዳስላጫወቱን ነው ለሳቸው ማስታወሻ ይሁን ብዬ ይህቺን አጭር ፅሁፌን በሳቸው ስም መሰየሜ።
በአንድ አጋጣሚ ወንድሜ ዶ/ር ሙሉጌታ በቀለ የድሮ የካምፓስ ጓደኞቹን ቤቱ በጋበዘበት ወቅት እኔንም ጋብዞኝ ነበር።የተጋበዙት ጓደኞቹ ዶ/ር ደምሱ ገመዳ፤በስዊድን ካምፓኒው ኤሪከሰን ውስጥ ይሰሩ የነበሩት ባለሙያ አቶ በርሔ ሐጎስ የትግራይ አዲግራት ተወላጅ እና ዶ/ር አድነው አለማየሁ የትግራይ ተወላጅ ሆነው ጎንደር ዳባት የኖሩ ሰው ናቸው። (የአሁኑን ዘመን ጓደኝነት ብዙም ባላውቅም የድሮ ጓደኝነት “ብሔር-ተኮር”ሳይሆን “ሙያ-ተኮር” መሆኑ ደስ አይልም?) በአሁኑ ወቅት አቶ በርሔ ሐጎስ በስዊድን ሐገር የሚኖሩ ምሁር፤ ዶ/ር ደምሱ ገመዳ በህይወት የሌሉ ምሁርና ዶ/ር አድነው አለማየሁ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የማቲማቲክስ ምሁር ናቸው። በዶ/ር ሙሉጌታ በቀለ ቤት ምሳ ከተጋበዝን በኋላ መጠጥ እየጠጣን እያለ ከተነሱ የድሮ ታሪኮች አንዱን እንዲህ ላወጋችሁ ወደድኩኝ።ታሪኩን ያጫወቱን ከላይ እንደገለፅኩላችሁ ዶ/ር ደምሱ ገመዳ ናቸው። ዶ/ር ደምሱ ገመዳ በ1967 ዓ.ም በአሜሪካን ሀገር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመስራት ላይ እያሉ ከአንድ ጓደኛቸው የሰሙትን ታሪክ ነው ያጫወቱን። ያጫወቱን ታሪክ መቼቱ በኛ የዘመን አቆጣጠር በ1957 ዓ.ም. በአሜሪካን ሀገር ነው። ዶ/ር ደምሱ ገመዳ ታሪኩን እንዲህ አጫወቱን።


“በ1967 ዓ.ምአሜሪካን ሀገር በትምህርት ላይ እያለሁ አንድ የትምህርት ቤት ጓደኛዬ በ1957 ዓ.ም ስለተፈፀመ አንድ ታሪክ ላጫውትህ ብሎ የነገረኝን ታሪክ ልንገራችሁ። ጉዳዩ አንድ የሶሲዮሎጂ የሶስተኛ(ዶክትሬት) ዲግሪ ተማሪ ለዶክትሬት ዲግሪውየሰራውን መመረቂያ ፅሁፍ(final paper)ይመለከታል፤ ጥናቱ የተካሄደውበሰሜን አሜሪካ(ዩኤስኤና ካናዳ) በሚገኙ የኢትዮጵያና የሶማሊያ የዘመኑ ተማሪዎች ላይ ነበር። አጥኚው ሶሲዮሎጂስት ለጥናቱ በተመደበለት በጀት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ተማሪዎችን ትምህርት በሌለበት በዕረፍት ጊዜያቸው ሰብስቦ ነበር ጥናቱን የሚያካሂደው።የወርክሾፑ ርዕስ በአፍሪካ ቀንድ በሚታዩ አብይ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መወያየት የሚል ነበር። በመሆኑም ተማሪዎቹ በስሜትና በፍላጎት ነበር የተሰባሰቡት። የሶሲዮሎጂስቱ ፍላጎት ግን ከዚያ ያለፈ ነበር። አጥኚው ተማሪዎቹ በወርክሾፑ በቆዩባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ የተለያዩ ጥናቶችን ያካሄደ ሲሆን፤ ጓደኛዬ በነገረኝ መሰረት እኔ የማጫውታችሁ በተመረጡ የተወሰኑ ጥናቶች ላይ አተኩሬ ነው።
ጥናቱ ከመጀመሩ በፊት በምዝገባ ወቅት  የተማሪዎቹ ሙሉ ስም፤ ዜግነት፤ እድሜ፤ ብሔረሳቸውን(ሶማሊያዊ ከሆነ ደግሞ ጎሳውን) የመሳሰሉ ለጥናቱ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች በሙሉ በዝርዝር ተሰበሰበ። ወርክሾፑ ሲጀመር ከላይ እንደተገለፀው ዓላማው በአፍሪካ ቀንድ የሚታዩ አብይ የፖለቲካ ችግሮች ላይ መሆኑን ሶሲዮሎጂስቱ ገልፀው ተማሪዎቹ አስተያየታቸውን እንዲናገሩ ተጋበዙ። በአፍሪካ ቀንድ የሚታዩ አብይ የፖለቲካ ችግሮች ሲባል በዋነኛነት የኢትዮጵያ ኦጋዴን አካባቢ የተመለከተ ነበር።በዚህ ጉዳይ ላይ የሶማሊያ ተወላጅ ተማሪዎች የአንድ ሰው ሀሳብ እስኪመስል ድረስ ኦጋዴን የሶማሊያ ግዛት እንጂ የኢትዮጵያ መሆን የለባትም፤ የሚል አንድ አይነት የሆነ ሀሳብ አቀረቡ። የኢትዮጵያ ተወላጅ ተማሪዎች ግን እያንዳንዱ የሚያስበውን ወይም የሚያምንበትን ሀሳብ አቀረበ። በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ከቀረቡት ሀሳቦች መሀከል ተመሳሳይ የሆኑ አሉ፤ የሚቃረኑ ሀሳቦችም ቀርበውበታል። በነገራችን ላይ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋና ባህል ያላቸው ከ80(ሰማኒያ) በላይ የሚሆኑ ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ሀገር ስትሆን፤ ሶማሊያ ግን አንድ ቋንቋ፤ ባህልና ሀይማኖት ያለው ህዝብ ቢሆንም የተለያዩ የሶማሌ ጎሳዎች የሚኖሩባት ሀገር ናት።በአፍሪካ ቀንድ ባሉት የፖለቲካ ችግሮች ላይ በሰፊው ከተወያዩ በኋላ በየመሀከሉ የሻይና የምሳ ሰዓት ዕረፍት ነበር፤ በዚሁ መሰረት የስብሰባው ጊዜ ካለቀ በኋላ የመዝናኛ ጊዜ ደረሰ። በመዝናኛ ሰዓት ላይ አዘጋጆቹ ያዘጋጁት የቤት ውስጥ ጨዋታዎች(Indoor games) ማለትም፤ የጠረዼዛ ቴኒስ፤ ቼዝ የመሳሰሉት፤ እንዲሁም የመረብ ኳስና የቅርጫት ኳስ ነበሩ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሶሲዮሎጂስቱ የራሱን ስራ በአንክሮ እየሰራ ነበር፤ ተማሪዎቹ ምን እንደሚናገሩ፤ ምን አይነት ባህርይ እንደሚያሳዩ፤ ከማን ጋር እንደሚጎዳኙ፤ እንደሚቀመጡ፤ እንደሚበሉና እንደሚጫወቱ በጥንቃቄ ይከታተል(observe ያደርግ) ነበር።
ከላይ እንደገለጵኩት በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ችግሮች ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት፤ የሶማሊያ ተወላጅ ተማሪዎች አንድ አቋም ያራመዱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ተወላጅ ተማሪዎች ግን የተለያዩ ሀሳቦችን ነበር ያቀረቡት። በጣም የሚገርመው ሌላው ጉዳይ ተማሪዎቹ ለሻይና ለምሳሰዓትዕረፍት በወጡበት ወቅት ሶማሊያዎቹ እያንዳንዱ ተማሪ የራሱ ጎሳ ከሆነው፤ ማለትም ሀወያው ከሀወያ፤ ኦጋዴኑ ከኦጋዴን፤ ይስሀቁ ከይስሀቅ ወዘተ ጋር ተፈላልገው ነበር የሚጠጡት፤ የሚበሉትም ሆነ የሚጫወቱት። የኢትዮጵያ ተማሪዎች ጋር ግን በተቃራኒው በዘር የመፈላለግ ነገር አልታየባቸውም፤ አማራው ከኦሮሞው፤ ትግሬው ከጉራጌው ወዘተ አይነት የተሰበጣጠረ ነገር ነበር የታየው። ተማሪዎቹ ይህንንበደመነፍሳቸው የሚሰሩትን፤ ነገር ግን ለሶሲየሎጂስቱ በጣም ትልቅ መረጃ የሆነን ድርጊት እየፈፀሙ ነበር፤  የሶሲዮሎጂስቱ ዋና ፍላጎት አልገባቸውም። የተነገራቸው በአፍሪካ ቀንድ ባሉ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ እንወያይ የሚል ስለነበረ በሚበሉ፤ በሚጠጡና በሚጫወቱበት ጊዜ የሚያሳዩት ባህርይና ድርጊት በልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር ነበር፤ ማለትም ሶሲዮሎጂስቱ በሚያደርጉት በእያንዳንዱ ነገር ላይ እያጠናቸው መሆኑን አላወቁም ነበረ፤ በሌላ አነጋገር ሶሲዮሎጂስቱ ጥናት እንደሚያካሂድባቸው አውቀው ለማስመሰል አርቲፊሺያል ባህርይ አልነበረም የሚያሳዩት።
ሶሲዮሎጂስቱ ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ በተማሪዎቹ ላይ የተለያዩ ጥናቶች ከአካሄደ በኋላ የጥናት ሪፖርቱን ማጠቃለያ ሲያቀርብ የሚከተሉትን ሁለት ድምዳሜዎች በሪፖርቱ ላይ አስቀመጠ። የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትላልቅ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ የራሳቸው የተለያዩ ሀሳቦች ስላላቸው ያልተግባቡ ይመስላሉ፤ አብሮ ለመኖር ግን ችግር የለባቸውም። የሶማሊያ ተማሪዎች ግን ትላልቅ በሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድ አቋም የያዙ ይመስላሉ፤ ነገር ግን አንድ ሀገር መመሰረት አይችሉም፤ “They cannot build a Nation”.
ሶሲዮሎጂስቱበሚናገሩትና በድርጊታቸውያጠና የነበረው የተማሪዎቹን ስነልቦናዊ አወቃቀር(psychological makeup)፤ ማህበራዊ መስተጋብርና አስተሳሰብ ነበር፤ የአሜሪካ መንግስት የዚህ አይነት ጥናት ፍላጎት ባለው የተለያዩ ሀገሮች ላይ አስጠንቶ መረጃ ይዟል፤ ከአንድ ሀገር ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲያደርግ ከዚያ በፊት ስለሀገሪቱ የተጠና ጥናት መሰረት አድርጎ ነው መወሰድ ያለበትን ርምጃ የሚወስደው።” ብሎ ጓደኛው የነገረውን ዶ/ር ደምሱ ገመዳ አጫወተን።
ዶክተር ደምሱ ገመዳ ይህንን ያጫወተን በ1990 ዓ.ም መባቻ ላይ ነበር። ሶሲዮሎጂስቱ በ1957 ዓ.ም ያጠናው ጥናት ድምዳሜ በተለይ ታሪኩን በሰማሁበት ወቅት በሶማሊያ የነበረውን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በኛም ሀገር ቢሆን የተለያዩ የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩንም አብሮ የመኖርና እንደ አንድ
ሀገር ህዝብ የመቀጠል ችግር የሌለብን መሆኑ የጥናቱን ድምዳሜ እውነተኛነት ያረጋግጣል።
ከቅርብ አስርት አመታት ወዲህ ግን በሀገራችን የሰፈነው የብሔር ፖለቲካ በብሔር ሳንለያይ እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ የመኖር ባህላችንን በተለያየ መልክና ደረጃ የፈተነው መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። የቋንቋዎችና የባህሎች እኩልነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ የአንድ ወይም ከዚያ በላይ ብሔረሰብ ተወላጅነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊነታችን ከፍ ያለ ዋጋ ሊሰጠውና አተኩረን ልንሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆን ይኖርበታል። አለበለዚያ እንደ አንድ ሀገር ህዝብ አብሮ የመኖር ባህላችን እየተሸረሸረ ሄዶ የማያስፈልግ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ሁላችንም ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ ነው። በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ትልቅ ባለስልጣን የነበረ በቅርብ የማውቀው አንድ ሰው በአንድ አጋጣሚ በተገናኘንበት ወቅት በጨዋታ ላይ የሶማሊያ ሀገር ጉዳይ ተነስቶ፤ ሶማሊያ አንድ ቋንቋ፤ አንድ ብሔረሰብና አንድ ሐይማኖት ያለው ህዝብ ሆኖ የስነ-ልቦና አወቃቀሩ ጎሳ-ተኮር በመሆኑ ሀገር መመስረት እንዳልቻሉ ስናወራ፤ ከሰማኒያ በላይ ብሔረሰብ ባለባት ሀገራችን ውስጥ ሶማሊያ ውስጥ እንዳለው ከብሔረሰብ ወርዶ በጎሳ የመናቆር ነገር ቢፈጠር ሊመጣ የሚችለውን ጥፋት ሳስብ ይዘገንነኛል ያለኝ ትዝ ይለኛል።
የብሔር(ጎሳ) ፖለቲካ የሰው ልጅ አፈጣጠር፤ ልዕልናና ክብር ዝቅ የሚያደርግ የወረደ አመለካከት ሲሆን፤ ውሎ አድሮ የሚያመጣው መዘዝ እጅግ ዘግናኝ መሆኑ ከተለያዩ ሀገሮች ታሪክ ከበቂ በላይ ተሞክሮ የወሰድን ቢሆንም፤ ከተሞክሮአችን ተምረን ጥሩ ግንዛቤ አግኝተናል የሚል እምነት ግን የለኝም። በዚህ ዘግናኝ ታሪክ ውስጥ ካለፉት ሀገራት መሀከል ዩጎዝላቪያ፤ ሩዋንዳና ሶማሊያን መጥቀስ በቂ ይመስለኛል። ወደሀገራችን መለስ ስንል ደግሞ እንደ ዩጎዝላቪያ፤ ሩዋንዳና ሶማሊያ ደረጃ ባይሆንም በብሔር ፖለቲካ ምክንያት ዘግናኝ የሚባሉና ከባህላችንና ከማህበራዊ መስተጋብር ማንነታችን ጋር ፍፁም ሊሄዱ በማይችሉ የቅርብ ጊዜ ታሪኮች ውስጥ አልፈናል። ይህ ሀቅ ደግሞ ከነሩዋንዳ ታሪክ አለመማራችንን ያሳያል። በትልቁ መፅሀፋችን(መፅሐፍ ቅዱስ) ውስጥ ከተጠቀሱት እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታና ዋጋ ካላቸው ምክሮች መሀከል አንዷን ምክር፤ ማለትም “በራስህ ላይ ሊደረግብህ የማትፈልገውን ነገር በሰው ላይ አታድርግ” የሚለውን መተግበር አቅቶን ከእርስ በርስ የመበላላት አባዜ ውስጥ አለመውጣታችን የሚያሳፍር ነው። ስለዚህ ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን ህልውናና ዕድገት ስንል የብሔር ፖለቲካን እንደ አረጀና የቆሸሸ ልብስ የምናወልቅበትንና ኢትዮጵያዊነታችን ብሎም ሰብአዊነታችን ጎልቶ በዕድገት የምንራመድበትን ብሩህ ጊዜ ለማየት በጉጉት እጠባበቃለሁ።
በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ እስራ በነበረበት ወቅት በኔ ስር ይሰራ የነበረ አንድ ስመ-ጥር መካኒክ በትውልድ አካባቢዬ ስራ አግኝቻለሁ በሚል የስራ መልቀቂያ አውጥቶ ወደ ትውልድ አካባቢው ሄዶ ስራ ጀመረ። ድርጅቱና ድርጅቱን የምናስተዳድር የማነጅመንት አባላት ባለሙያውን በስራው ስለምንወደው በመልቀቁ ሁላችንም አዘንን። ከዚያ ለአንድ አመት ያህል በትውልድ አካባቢው ከሰራ በኋላ ተመልሶ ወደድርጅታችን መጥቶ ወደቀድሞው ስራዬ መመለስ እፈልጋለሁ ብሎ ሲጠይቀን ልጁ በሙያው ጎበዝ በመሆኑ ምክንያት ስለምንወደው የመመለስ ጥያቄውን ሲያቀርብልን ሁለት ጊዜ ማሰብ ሳያስፈልገን ወዲያው ተቀብለነው ስራ ጀመረ። ከዚያ አንድ ቀን እኔ ቢሮ መጥቶ ስንጫወት እገሌ ብዬ በስሙ ጠራሁት፤ እሱም አቤት አለኝ። “ባለፈው በትውልድ አካባቢዬ ስራ ስላገኘሁ እዚያ ሄጄ ብሰራ ይሻለኛል ብለህ ከሄድክ በኋላ ተመልሰህ ወደድርጅታችን ለምን መጣህ? ምንድነው ምክንያቱ?” ብዬ ጠየቅሁት፤ እሱም ስለሚወደኝና ስለሚያምነኝ እውነቱን ሳይደብቅ እንዲህ ብሎ አጫወተኝ፤ “ወደትውልድ ክልሌ የተሻለ ነገር አገኛለሁ ብዬ ሄጄ ነበር፤ ነገር ግን እዚያ ያለው ሁኔታ ሰዉ ከራሱ ብሔረሰብ ወርዶ በጎሳና በወንዝ ልጅነት የሚሻኮት ስለነበረ ይህ ጉዳይ አስጠልቶኝ አዲስ አበባ ብሰራ ይሻለኛል ብዬ ነው የተመለስኩት”
ከዚህ በላይ ባለሙያው ካጫወተኝ ታሪክ ውስጥ ሁለት አንኳር ነገር መረዳት እንችላለን፤
የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ሲገባ በብሔር ብቻ አይቆምም፤ ከዚያ ወርዶ ወደ ጎሳ፤ ብሎም ወደ ወንዝ ልጅነት ዝቅ የሚል መሆኑ፤
ከብሔረሰብ ወርዶ በጎሳ የመሳሳብ ነገር በሶማሊያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን እኛም ሀገር ውስጥ በተለይ ከቅርብ አስርት አመታት ወዲህ እያደገ መምጣቱን ነው። ዶክተር ደምሱ ገመዳ ከዚህ በላይ እንዳጫወቱን በ1957 ዓ.ም በአሜሪካና በካናዳ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ምንም የብሔረሰብ ልዩነት ሳያግዳቸው የዕለት ከዕለት ኑሮአቸውን በጋራ የመከወናቸው ውጤት የኛ ሳይሆን የአባቶቻችንና የአያቶቻችን የስራ ውጤት ነው፤ እኛ ከአባቶቻችን፤ ከአያቶቻችንና ከዘመኑ ትምህርት ዕውቀትና የልምድ ጥበብወስደን ከወላጆቻችን የተሻለ አስተሳሰብ ሊኖረን ሲገባ በብሔረሰብ ተቧድነን፤ በአስተሳሰብ ዘቅጠን እርስ በዕርስ ስንራኮት አያሳዝንም? በራሳችን አናፍርም? ለነገሩ ይሔንን የመሰለ ሴራ የሚሸርቡት ቆመንለታል ለሚሉት ብሔረሰብ የአዞ እንባ እያፈሰሱ ኪሳቸውን የሚያደልቡና ሆዳቸውን የሚሞሉ በየደረጃው ላይ የሚገኙ ብልጣብልጥና ሌባ ባለስልጣናትና አክቲቪስቶች ነን የሚሉ ናቸው እንጂ የአዞ እንባ የሚፈስለት ብሔረሰብ የሴራው ጠንሳሽ እንዳልሆነና ምንም ነገር ጠብ እንዳላለለት እስኪበቃን ድረስ አይተነዋል፤ እናውቀዋለንም።
ማጠቃለያ
ከዚህ በላይ ካጫወትኳችሁ ታሪክ ውስጥ የሚከተሉትን አብይ ነገሮች መገንዘብ እንችላለን ባይ ነኝ፤፤
የአንድ ቋንቋ ተናጋሪነት፤ ወይም የአንድ ብሔር አባልነት፤ ለአንድነት፤ ለሰላምና በፍቅር ለመኖር ዋስትና(guaranty) አይሰጥም።
በብሔረሰብ መቧደን ማቆሚያ የለውም፤ ከብሔረሰብ ወርዶ ወደጎሳ፤ ከጎሳም ወርዶ ወደየወንዝ ልጅነት ወዘተ ይወርዳል፤ በመሆኑም የብሔር ፖለቲካ በጊዜ ካላጠፋነው ውሎ አድሮ በሀገራችን ላይ የሚያመጣው መዘዝ ከሶማሊያው እንደማይብስ ማረጋገጫ የለንም።
በሀገራችን የታየው የብሔር ፖለቲካ የኢትዮጵያን ህዝብ አብሮ የመኖር ስነ-ልቦና በመሸርሸር ተፈታትኗል፤ ቢሆንም ሊያፈርሰው አልቻለም፤ የሰው ልጅ እውነተኛ መለያው(በቴክኒክ ቋንቋ ስፔሲፊኬሽኑ) ሊሆን የሚገባው አስተሳሰቡ፤ ድርጊቱና ባህርይው ነው እንጂ ብሔሩ፤ ቋንቋውና አካላዊ መልኩ ሊሆን አይገባም።
በመንግስት ደረጃ እየተሰራ ያለው የሐገራዊ ምክክር ኮሚሽን አብይ አጀንዳ መሆን ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ የብሔር(የጎሳ) ፖለቲካ ለኢትዮጵያ በፍፁም እንደማይበጃትና አጥፊዋ እንደሆነ አፅንዖት ተሰጥቶበትና ህዝቡ ተወያይቶበት ለአንዴና ለመጨረሻ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲወገድ ማድረግ፤(በኔ እምነት ህዝቡ ሰሚ ካገኘ የብሔር ፖለቲካን እንደእብድ ውሻ ከቤቱ ማባረር ብቻ ሳይሆን ገድሎ እንደሚቀብረው አልጠራጠርም፤ ይህን ስል ግን ወጣቱ ትውልድ በብሔር ፖለቲካ ናላው እንዲዞር የተደረገ በመሆኑ የወጣቱን ትውልድ የአስተሳሰብ አድማስ ማስፋት እንደሚጠበቅብን ሳልረሳ ነው፤ እዚህ ላይ በተደጋጋሚ የምጠቅሰውና አንባቢ ልብ እንዲለው የምፈልገው ሌላ ዋና ነገር የብሔር ፖለቲካ ይጥፋ ስል የብሔር-ተኮር የአስተዳደር አከላለል ይጥፋ ለማለት ነው እንጂ የብሔረሰቦች፤ የቋንቋዎችና የባህሎች እኩልነት ሳይሸረሸር(ወይም “compromise” ሳይደረግ) መቀጠል እንዳለበት በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑን ነው።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የብሔር ፖለቲካን(Ethnic politics) በጣምም ሳይፈጥን፤ በጣምም ሳይዘገይ፤ በአስተዋይነት፤ የፅንፈኛ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እንዳይሆን እየተጠነቀቀ(ይህንን ስል ፅንፈኛ ፖለቲከኞች መንግስት የብሔር ፖለቲካን በሂደት ለማክሰም የሚወስደውን ርምጃ ተጠቅመው፤ ማለትም “capitalize አድርገው” ህዝቡን ውዥንብር ውስጥ እንዳይከቱት እየተጠነቀቀ ለማለት ነው)፤ ከህዝብ ጋር እየተመካከረ፤ ይህንን ኩሩ፤ ታሪካዊ፤ መንፈሳዊና ታታሪ የኢትዮጵያ ህዝብ ከብሔር(ጎሳ) ፖለቲካ በሂደት ማውጣት ይጠበቅበታል፤ ይህንን ካደረገ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ ይበልጥ እየጨመረእንደሚሄድ አልጠራጠርም፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ በፖለቲካ ባህልም ሆነ በኢኮኖሚ እንድታድግ መሰረት የመጣል አንድ አብይ ምዕራፍ መከወን ይሆናል፤ አለበለዚያ ለሀገርም ለመንግስትም አይበጅምና በጥልቀት ታስቦበት አስተዋይነት ያልጎደለው ርምጃ ሊወሰድበት ይገባልእላለሁ።

Read 1062 times