Wednesday, 29 November 2023 12:06

የገና የንግድ ትርዒት ባዛርና ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

•  ማዕከሉ በ25 ሚ. ብር ወጪ  የማስፋፊያ ስራዎችን ማከናወኑን ገለጸ


33ኛው የገና የንግድ ትርዒት ፣ ባዛርና ፌስቲቫል ከታህሳስ 6 - 27 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ሴንቸሪ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ በዛሬው ዕለት ረፋዱ ላይ  በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት  አዳራሽ  በሰጠው መግለጫ፤ በዚህ  የገና የንግድ ትርዒት፣ ባዛርና ፌስቲቫል ላይ ከ500 እስከ 600 የሚደርሱ አምራቾች የሚሳተፉ ሲሆን፤  15 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሴንቸሪ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውገ ጀማነህ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው  የገና የንግድ ትርዒት ባዛርና ፌስቲቫል ላይ  ድምፃዊ አንዱአለም ጎሳ፣ ሄለን በርሄና አረጋኸኝ ወራሽ የሙዚቃ ሥራቸውን ያቀርባሉ፡፡

በተያያዘ ዜና፤ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ግቢ በ25 ሚሊየን ብር ወጪ  የማስፋፊያ ስራዎችን ሲያከናውን እንደቆየ  የተገለፀ ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት በአዲስ መልክ በኮንከሪት አስፋልት ተሠርቷል ::  በዚህ የማስፋፊያ ስራው ለገና የንግድ ትርዒት ፣  ባዛርና ፌስቲቫል ተሣታፊዎች አመቺ ሆኖ መታደሱ ብቻ ሳይሆን፣ ተጨማሪ ተሳታፊዎችን ለማስተናገድ ምቹ እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡  

አዘጋጁ ሴንቸሪ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ፣ ይህንን ተጨማሪ ቦታ የባህል አልባሣትና ጌጣጌጦች ፣  የአነስተኛና መካከለኛ ጀማሪ አምራች ኢንዱስተሪዎች ፣  የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማስተዋወቅ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች በአቅማቸው በአነስተኛ ዋጋ ተከራይተው ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ማስተዋወቅና መሸጥ እንዲችሉ እድል መፍጠሩን አስታውቋል፡፡

የገና የንግድ ትርዒት ፣ ባዛርና ፌስቲቫል  የመግቢያ ዋጋው 100 ብር ሲሆን፤ ክፍያው የሚከናወነው በቴሌብር እንደሆነም ተነግሯል።

Read 1449 times