Saturday, 25 November 2023 21:02

የጥላሁን ገሠሠ ‹‹የ13 ወር ጸጋ››

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(0 votes)

‹‹በፀሐይ ብርሃን ደምቃ፣ ክረምትና በጋ፤
የትውልድ አገር ያላት፣ ያስራ ሦስት ወር ጸጋ፤…››




‹‹የ13 ወር ጸጋ›› አልበም፤ ድምጻዊ፡- ጥላሁን ገሠሠ፤ 1980 ዓ.ም.፤ ዜማ፡- ታምራት አበበ፤ ግጥም፡- ታምራት አበበ እና ክፍለእየሱስ አበበ፤ ቅንብር፡- ዳዊት ይፍሩ (ሮሃ ባንድ)።
ተቀባዮች (back vocal):- ቴዎድሮስ ታደሠ፣ ራሔል ዮሐንስ፣ ሐመልማል አባተ እና ታምራት አበበ፡፡ በዚህ አልበም ውስጥ በግጥምና በዜማ ድርሰት ረገድ፣ አየለ ማሞ፣ ታምራት አበበ፣ ክፍለእየሱስ አበበ፣ አበበ መለሠ፣ ይልማ ገ/አብ፣ ሲራክ ታደሠ፣ አስጨናቂ ከፍያለው እና ደሳለኝ ቢሻው ተሳትፈዋል፤ ‹‹ለእንባዬ ቦይ ልሥራ፣ ፍቅር ይገድላል እንዴ፣ ከረምኳታ፣ ደሜ ማሎ (ምነው ማሬ)፣ በገና መውደድ›› እና ሌሎች ዘፈኖች ተካተዋል።
አሁኔ ‹‹የ13 ወር ጸጋ›› የተሰኘ ዘፈን ነው….
…ትዝታም፣ ዓመት በዓልም፣ ልጅነትም፣ ፍቅርም፣ ትውፊትም፣ ሂደትም፣ ጅማሮም፣ ፍጻሜም፣ ዑደትም፣ ፈጽሞ - መጀመርም…. የሆነ ዘፈን! የዚህ ዘፈን መልዕክት አዲስ ዓመትን ማዕከል ያደረገ እንደሆነ ዕሙን ነው! ግና እንደ ሌሎች የዓመት በዓል ዘፈኖች ለኩበቱ ሽታ እና ለምግብና ለመጠጥ ዓይነቶች ወላ ለልባሽ ብቻ ተወስኖ እንዳልተቀነቀነ መዝግቡልኝ፤ በዓመት በዓል ድንበር ታጥሮ ወቅታዊ ብቻ ሆኖ አይቀርም፤ በአዘቦትም ውልብ ይላል፤ የስንኞቹ ማዕከል ከድግስና ግሳንግስ ያየለ ነው…
….በዚህ ዘፈን ውስጥ አገር አለች፤ ታላቅ አገር፤ ልጅነት አለ፤ በልጅነት ልባችን የጣፍናት አገር አለች፤ ስለ አገር በልጅነት የተመዘገበ አይገሥሥምና፣ ዘፈኑ ዛሬም ድረስ ትውስ ይለናል፤ ከዘፈኑ ዕኩል ደግሞ ልጅነት፤ ከልጅነት ዕኩል አገር….
…..ዘፈን የተነሳበትን ዓላማ መሳት እንደሌለበት ቢታመንም፣ ይኼ ዘፈን በዋናነት በአዲስ ዓመት ዋና፣ ዋና ክዋኔዎች ላይ መሠረት አድርጎ አይጠናቀቅም…
‹‹በፀሐይ ብርሃን ደምቃ፣ ክረምትና በጋ፤
የትውልድ አገር ያላት፣ ያስራ ሦስት ወር ጸጋ፤…››
ብሎ ይጀምራል፤ አገራችን ጸጋ ያደላት እንደሆነ እማኝ ነው ዘፈኑ፤ በእነዚህ ወራቶች ውስጥ በዓመት አንድ ጊዜ ጎብኝቶን የሚያልፍ ታላቅ በዓል አለ - እንቁጣጣሽ! የዓመቱን ማገባደጃ ተከትሎ በደስታ ባጅቶን የሚያልፍ በዓል - ጭጋጋማው ወቅት በፍካትና ጸደይ ይተካል፣ ድጥ በወካች ምድር፣ ጭፍና በፍካት ይተካል፣ ፀሐይ ኃይሏን ሳትሰስት ትለግሳለች፣ ብርሃንና ሽቶ የጥድቅ መንገድ ጠቋሚ እንዲሆኑ የጽጌያት መዓዛ በሰርናችን ይተፍናል፣ ጨረቃ እና ጸሐይ የሚያወላዳ ይሆናሉ፣ ጸዳል ይሆናል፣ ዘመን ይለወጣል…. አዲስ ዓመት - አዲስ ተስፋ!....
......ከተሰጠን በረከትና ጸጋ በመጠኑ ሸርተት ይልና ወደ ትውፊታችን ጎሬ ምስግ ይላል….
‹‹እንኳን ደረስክ ሲባባል - ወዳጅ ከጎረቤቱ፣
ትዝታው መች ይጠፋል - አቤት ማስደሰቱ፤…››
በማለት የዓመት በዓል እና የባሕላችንን አኩሪነት ጠቆም ያደርጋል፤ አንድ ክዋኔ ሕልው ከሚሆንባቸው መንገዶች አንዱ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ እና ግብረ-መልስ እንደሆነ ማሳያ ስንኝ ነው! በሕብረት ያከበርንበት ዓመት በዓል ትውስ እያለን የመጣውን በዓል እንድናከብር የሚጭር የስንኝ ቀብድ ነው ከላይ የተጠቀሰው።
ቀለስ ይልና….
‹‹አቤት ባዲሱ ዓመት - ዘመኑ ሲለወጥ፣
ያበቦቹ ሽታ - መዓዛው ሲመስጥ፤…››
ይላል፤ ከላይ ባሉ ስንኞች ወደ ተፈጥሮ ይወስደናል፤ የአዲስ ዓመትን ለማድመቅ ተፈጥሮ ምን ያክል ወገቧን ይዛ ሽር ጉድ እንደምትል ልብ እንበል! ጽጌያት ያብባሉ፣ ጥዑም ሽታ ምድርን ይባጃታል፤ መዓዛቸው ድምቀት እና ውበት ይሆናል! በአዲስ ዓመት አበባው አዲስ ነው! ለዓይንም ለልብም የሚሞላ ውበት!
ሥነ-ውበት እና ሥነ-ግጥም ዝምድናቸው እንደ ችፍርግ ዘለግ ያለ ሥር የሰደደ ነው፤ የዚህ ዘፈን ግጥም ውበት እና ወጥነትን የተላበሰ ሲሆን፣ ተፈጥሮ ውበትን የሚያጎላበትን ቀጣይ ስንኞች መልከት እናድርግማ!....
….ልከኛ ውበት ከተፈጥሮ የመጣ ነውና፣ አበቦቹ በተራቸው ኮረዶቹን ሊያስጌጡ ሲተጉ በቀጣይ ስንኞች ገላ ውስጥ እናስተውላለን….  
‹‹ኮበሌውም ሲጨፍር - ሲል መስከረም ጠባዬ፤
ኮረዳዋም ባቅሟ - ስትዞር በራሷ ቀዬ፤….››
እያለ በአበቦች ያሸበረቀውን ውበት ያትታል፤ ልጅነት አበባነት ነው - መፍካት - መዓዛን ማስረቅረቅ! የጾታ ቀዬ አለ፤ በጾታ መደብ የማጌጥ ቀዬም አለ፤ ኮረዳዋ በጉንጉን አበቦች አጊጣ እንድትፋንን ዕሙን ነው።
እንቁጣጣሽን አስኮምኩሞን ሲያበቃ….
‹‹መስቀል ሲመጣ፣ ተክሎ ደመራ፤
ሁሉም በደጁ፣ ችቦ ሲያበራ፤››
ሲል ብርሃነ መስቀሉን ጀባ ይለናል፤ በእነዚህ ስንኞች የመስቀል በዓል በአንድነት ዕውነት እና ብርሃንን የማግኘት በዓል እንደሆነ እንረዳለን!
ወደ ታኅሳስ ወር ተሻግሮ ገናን ያስቃኘንና በአዲስ ዓመት፣ በመስቀል እና በገና በዓላት ላይ ደስታና ፌሽታቸውን ያጣጣሙትን ኮበሌና ኮረዶች ላባቸውን በከንቱ አያስቀርም….
‹‹የወላጆች ሽርጉድ፣ ያጨው ጎጆ ሲወጣ፤
የሠርግ የሚዜው ጣጣ፣ ሃይሎጋው ጊዜው መጣ፤››
የሚሉ ስንኞችን እናገኛለን፤ ሐይማኖታዊ በዓላትን፣ ትውፊትን እና ባህልን ያስተዋወቀን ዘፈን ራስን የሚችል እና ቤተሰብ የሚመሠርትን ማሕበረሰብ አስተዋውቆን ያልፋል! ከሆታ፣ ከጭፈራ፣ ከፌሽታ ወዲህ ጎጆ መቀለስ፣ ኃላፊነትን መወጣት…ወዘተ. ተከተለ ማለት ነው።
ዘፈኑ ገድ ጠሪ ነውና፣ ሙሽሪትና ሙሽራ የሠርጋቸው ቀን ላብ ሳይደርቅ ሌላ ደስታ ይተካል…
‹‹በጥር ለጥምቀት በዓል፣ ሲወጣ ታቦቱ፣
አጅበውት ሲጓዙ፣ ወጣት አዛዉንቱ፤››
ይኼ ከላይ ያለ ስንኝ ደማቁን ጥምቀት ይወክላል፤ ከአደባባይ የሐይማኖታዊ በዓላት ቀለማሙና ባለመዓዛውን በዓላችንን ለመተንተን የታለመ ስንኝ ነው፤ ጥንድ ሲኮን ደግሞ ድምቀቱ ልዩ ነው!
ኢትዮጵያ በዚህ በ‹‹የ13 ወር ጸጋ›› ዘፈን ውስጥ የተድላ፣ የጸጋ እና የሐሴት አገር ሆና ተወክላለች፤ ሙሉውን ዓመት ትጋት፣ በዓል፣ ደስታ፣ ድለቃ፣ መጠያየቅ እና መተዛዘን ሲተወኑ ይኖራሉ - በኢትዮጵያዊያን! ከበዓላቱ ዕኩል መተዛዘኑ ይወሳል! ጥምቀት እንዳለፈ….
‹‹ፋሲካ ሲደርስ - ደግሞ በዓመቱ፤
ቅዳሜን ለእሁድ - ነግቶ ሌሊቱ፤››
በማለት ስለ ፍቅር የተበረከተን በዓል ጠቀስ ያደርጋል፤ ወዲያው በተከሸነ የዶሮ ወጥ የተሞላ ሌማት እፊታችን ድቅን ይላል፤ ፋሲካ የመንሳት ሳይሆን የመቸር፣ የአረንዛነት ሳይሆን የመባባት በዓል እንዲሆን ዕሙን ነው - እናም እንቸራለን! እንተዛዘናለን! ለዚህም....
‹‹ዶሮው ተሠርቶ - ቀርቦ ሌማቱ፤
ጠላው በአንኮላ - ከነገፈቱ፤
አረቄ ዳቦ - ዕኩል ላክፋይ፤
የየአቅሙን ይዞ - ወዳጅ ቤት ሲታይ፤
ከጎረቤት ጋር - በመጠራራት፤
ብሉ፣ ጠጡልኝ - ያዝማዱ ኩራት…..፤››
የሚሉ ስንኞች የቸርነት ተምሳሌቶች ናቸው! ፋሲካ አለኝታ እንዲሆን ከላይ የተጠቀሱ ስንኞች እማኝ ናቸው!!
ዘፈኑ ከአንድ ስፍራ አንስቶ አድማጩን ሜዳ ላይ አይጥልም፤ ሕይወት ሂደት መሆኑን ይመሰክራል፤ ዛሬ የተጀመረ ሕይወት የተገባደደ ቢመስልም፣ ለሌላ ሕይወት ጅማሮ እንደሆነ ያሳያል፤ አንድ 13 ወር አገባዶ ወደ ሌላኛው 13 ወር ይመስጋል - አድማጭን፤ አነሳስቶ ያደርሳል….
‹‹ግንቦት ሰኔም አለፈ፣ ደመና እያለበሰ፤
ሐምሌም በክረምት ዝናብ፣ መሬቱን እያራሰ፤
ልጆች ከእየቤታቸው፣ ለሆታ ሲጠራሩ፤
ከጅራፉ ጩኼት ጋር፣ የቡኼን በዓል ሲያከብሩ፤
ሁሉም በየደጃፉ፣ እዚህ እዚያኛው ሠፈር፤
ዳግም ሌላውን ችቦ፣ እያበራ ሲጨፍር…..፤››
በማለት ቀጣዩን አዲስ ዓመት፣ ቀጣዩን ተስፋ፣ ቀጣዩን ዕቅድ፣ ቀጣዩን ሐሴት፣ ቀጣዩን ደስታ፣ ቀጣዩን የቤተሰብ ምሥረታ፣ ቀጣዩን ባሕል፣ ቀጣዩን መጠያየቅ… እንካችሁ ብሎን ይገባደዳል - ዘፈኑ! በአጠቃላይ፣ ይኼ ዘፈን ከጥሌ ሥራዎች ተወዳጅ ሲሆን፣ ውክልናው ደግሞ በደስታ፣ በመተሳሰብ፣ በፌሽታ፣ በባሕል፣ በትውፊት፣ በልግስና…ወዘተ. የተመላችን አገር የሚያንጸባርቅ ነው።   

Read 299 times