Saturday, 25 November 2023 20:14

አስፈሪ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ፈጠራ መጥቷል አሉ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

አንደኛውን ዓለማቀፍ ዜና አይተናል። የሮኬትና የህዋ ቴክሎጂ ነው። ሁለተኛው ዜናስ ምንድነው?  ግን ምን ዋጋ አለው? ትልቁ ዜና  እንደገና ተመልሶ ተሽሯል።
“ሳም አልትማን ተባረረ” ተብሎ ቅዳሜ ዕለት ተዘገበ።
ሮብ ዕለት ደግሞ ወደ ቦታው ተመልሷል ተብሎ እንደገና እንደ ጉድ ተወራ።
ለመሆኑ አልትማን ማለት ማን ነው?
የ “OpenAI”  ዋና መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ነው። የዓለማችን ቁጥር አንድ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ተቋም ነው-Open AI::
እንግዲህ፣ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ላይ የበላይትን የተቆጣጠረ አገር፣ የዓለማችን ገዢ ይሆናል ብለዋል- የራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን።
ቢያንስ ቢያንስ በዚህ ጉዳይ ላይ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የቻይና መንግስታትም ጭምር  በፑቲን ንግግር ይስማማሉ።አስገራሚው ነገር፣ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂ ላይ በቀዳሚነት እየመሩና እየገሰገሱ የሚገኙ ተመራማሪዎችና የፈጠራ ሰዎችም፣ ቴክኖሎጂው እጅግ ኃያል ከመሆኑ የተነሳ፣ የጥቅሙ  ያህል አደጋውም እጅግ አስፈሪ እንደሆነ ይናገራሉ።
ቴክኖሎጂው ደግሞ በከባድ ፍጥነት እየተሻሻለ እየተራቀቀ ነው።
በዚህ መሀል ነው አዲስ ተጨማሪ ግኝት፣ እጅግ የተራቀቀ አዲስ የፈጠራ ውጤት እንደተገኘ  ከሳምንት በፊት ሐሙስ ዕለት የተገለፀው። Open AI ነው የፈጠራው ባለቤት።ምን ዓይነት ፈጠራ እንደሆነ በግልፅ አልተነገረም። ነገር ግን፣ በራሱ ጊዜ የሒሳብ ስሌቶችንና ቀመሮችን መገንዘብ የሚችል ቴክኖሎጂ ባተጠበቀ ፍጥነት እንደተፈጠረ ተጠቅሷል። አዲሱ ፈጠራ ብዙዎችን እንዳስገረመና እንዳስደነገጠም በዓለማቀፍ የዜና አውታሮች ተዘግቧል።
አግራሞት፣ ድንጋጤና ፍርሀት ውስጥ ለውስጥ ሲብላሉ በማግስቱ ፈነዱ። የድርጅቱ መሪዎች ተወዛገቡ።
ከሰው ቁጥጥር ውጭ የሆነ፣ እንደ ተርሚኔተር ዓይነት ቴክኖሎጂ የሚመጣበት ጊዜ ተቃርቧል የሚል ስጋት የተፈጠረው፣ Open AI ውስጥ ጭምር፣ ቴክኖሎጂውን በሚያውቁ በባለሙያዎች ዘንድም ነው ተብሏል።
የውዝግቡ ማቀጣጠያ ይሄው ነው።…ስራ አስኪያጁ ተባረረ፤ ተመልሶ ቦታውን ያዘ የሚለው ዜና ትልቅ ዓለማቀፍ ወሬ ለመሆን የቻለውም፣ ከአዲስ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ፈጠራ ጋር በተያያዘ ሰበብ ነው። ሰውን ከምድረ-ገፅ የሚያጠፋ ቴክኖሎጂ ሊመጣ ይችላል የሚል ነው ስጋታቸው። ምን ሆነዋል እዚህ ሰዎች! ለዚያውም ባለሙያዎቹ፣ የቴክኖሎጂው ፈጣሪዎች ናቸው ይህን የሚናገሩት።
ለማመን ይከብዳል። ለክፉም ለደጉም፣ አዲስ ነገር እየመጣ እንደሆነ ግን አትጠራጠሩ።

Read 769 times