Friday, 24 November 2023 10:35

“ሌጀንድ ፎር ኦል” የማርሻል አርት ስፖርትን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

•  ስፖርቱ መስፋፋቱ በሥነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን ለማፍራት
ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሏል


የኢትዮጵያ ሌጀንድ ኢንተርናሽና ፕሮ ቴኳንዶ ፌደሬሽን፣ የቴኳንዶና የማርሻል አርት ስፖርትን በት/ቤቶችና በመዝናኛ ቦታዎች ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ከአሴቅ ዲኮርና ኢቨንት ኦርጋናይዜሽን ጋር ትላንት ተፈራረመ፡፡

የስምምነቱ ዋና ዓላማ፤ የቴኳንዶና የማርሻል አርት ስፖርትን በት/ቤቶች፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በመዝናኛ ቦታዎችና በሌሎችም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆነ ተቋማት ማስፋፋትና ማጠናከር ነው ተብሏል፡፡

የቴኳንዶና የማርሻል አርት ስፖርቱን የማስፋፋት ፕሮጀክቱ፤ በተለይም ት/ቤቶችና ታዳጊዎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤  ጤናቸው የተጠበቀ፣ በአካልና በአዕምሮ የዳበሩ እንዲሁም  በመልካም ሥነምግባር የታነፁ ብቁና አሸናፊ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም፤ የሌጀንድ ኢንተርናሽና ፕሮ ቴኳንዶ ስፖርት ውድድርን በየደረጃው በስፋት፣ በጥራትና በስርዓት በማዘጋጀት በከተማ አቀፍ፣ አገር አቀፍና ዓለማቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ምርጥ ስፖርተኞችን በማፍራት የአገርን ክብርና ዝና ከፍ ለማድረግ ታልሟል፡፡

በስምምነት ሰነዱ ላይ እንደተመለከተው፤ በከተማ ውስጥ የሚታየውን የማርሻል አርት ስፖርት ማሰልጠኛ ሥፍራ እጥረት ለመቅረፍ ከት/ቤቶች ጋር በትብብር የሚሰራ ሲሆን፤ የተለያዩ የሌጀንድ የማርሻል አርት ስፖርት ሌሎች ውድድሮችንና መዝናኛ ፕሮግራሞችን በተቀናጀ መልኩ በማዘጋጀት  ስፖርቱን ተደራሽ ለማድረግና ለህብረተሰቡ በስፋት ለማስተዋወቅ ታቅዷል፡፡

ሌጀንድ ኢንተርናሽና ፕሮ ቴኳንዶ ፌደሬሽን፣ ከ24 ዓመተ በፊት በዓለማቀፍ ደረጃ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን  በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የጠቆሙት ማስተር ሄኖክ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ላለፉት 4 ዓመታት ፈቃድ ተሰጥቶት ተደራሽነቱን ለማስፋትና ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለማበርከት  እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሌጀንድ ፎር ኦል እና በአሴቅ ዲኮርና ኤቨንት ኦርጋናይዜሽን የተደረሰው ስምምነት፣ በዋናነት ተግባራዊ የሚደረገው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ ት/ቤቶች ውስጥ ነው ተብሏል፡፡

Read 940 times