Sunday, 12 November 2023 20:09

የታካሚውና የሐኪሙ ግንኙነት…..

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 በህክምናው አለም የሚተገበሩ የስነምግባር እሴቶች፡-
የታካሚን ግለሰባዊ ማንነት ማክበር፡፡
ታካሚን የሚጠቅም ነገር ማድረግ፡፡
ታካሚን አለመጉዳት፡፡
ለታካሚ ፍትህ መስጠት፡፡
ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ የማህጸንና ጸንስ ህክምና እስፔሻሊስትና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የመካንነትና ከስነተዋልዶ ጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸው የሆርሞን ችግሮች እስፔሻሊስትነት በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የታካሚና ሐኪም ግንኙነት ምን መምሰል አለበት የሚለውን መነሻ ሀሳብ መሰረት በማድረግ ከዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ ጋር በተደረገው ቃለምልልስ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ይህንንም ለንባብ እነሆ ብለናል፡፡ ይህ አርእስት የህክምናውን ሂደት ሳይሆን የታካውንና የአካሚውን ግንኙነት ወይንም ስነምግባር መሰረት ያደረገ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሐኪሞች የህክምና ሙያውን ከመማራቸው በተጨማሪ እንዲያውም አስቀድሞ ማለት በሚያስችል ሁኔታ እንዲያውቁት ወይንም እንዲሰርጽባቸው የሚደረገው ስነምግባር ነው፡፡ የህክምናው ስነምግባር የታወቁ አሰራሮች ወይንም መለኪያዎች የአሉት ሲሆን ሁሉም የሚመነጩበት ደግሞ መሰረታዊ ሀሳቦች አሉ፡፡


አንድ ህክምናን የሚሰጥ ባለሙያ ከታካሚው ጋር ሲገናኝ እንዲያከብራቸው የሚፈለጉ መሰረተ ሀሳቦች ብዙ ቢሆኑም ዋና ዋናዎቹ ግን በአራት ይከፈላሉ ፡፡
የታካሚን ግለሰባዊ ማንነት ማክበር፡፡ (ከሁሉም የስነምግባር እሴቶች የመጀመሪያው ተደርጎ ይታሰባል፡፡)
ታካሚን የሚጠቅም ነገር ማድረግ፡፡(ሁል ጊዜ አንድ የህክምና ባለሙያ ከታካሚው ጋር በሚኖረው ግንኙነት ለመርዳት ወይንም ጥቅም ለመስጠት ተግባሩን ማከናወን ይጠበቅበታል)
አለመጉዳት፡፡(ሐኪሙ ለታካሚው ጉዳት የሚሰጥ ነገር ማድረግ የለበትም)
ፍትህ፡፡


ከላይ የተገለጹት የስነምግባር እሴቶች በሁሉም የህክምና በአለሙያዎች ወይንም የህክምና አገልግሎቱን በሚሰጡ ተቋማት ዘንድ የሚከበሩና ሁልጊዜ እየታሰቡ ከታካሚዎች ጋር ግንኙነት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች እነዚህ አራት መሰረታዊ ሀሳቦች ሊጣረሱ ይችላሉ ብለዋል ዶ/ር ገላኔ፡፡ `ምሳሌም ሲሰጡ፡-
አንዲት እናት ምጥ ላይ ሆና ለጽንሱ አደጋ ሊፈጥር ሚችል ነገር ቢከሰት እና እናትየው ግን እኔ ለጽንሱ ብዬ ምንም አይነት ቀድሞ የማዋለድ አገልግሎት እንዲደረግልኝ አልፈ ልግም ብትል በተለይም ጽንሱ ለመወለድ የደረሰ ቢሆን ይህ ነገር እንዴት ነው የሚፈታው የሚለው አነጋጋሪ ይሆናል፡፡ ልጄ ቢሞትም ይሙት እንጂ እኔ ኦፕራሲዮን መደረግ አልፈልግም ብትል ልጁ የእስዋ ነው ወይንም ልጁ ያለው እስዋ ማህጸን ውስጥ ነው ብለን እንተወዋለን ወይ የሚለው አነጋጋሪ ነው፡፡ በአንድ በኩል በእስዋ ሰውነት፤ሕይወት፤ መብት…ወዘተ ገብቶ ለመወሰን አስቸጋሪ ሁኔታ ቢኖረውም በሌላ በኩል ደግሞ ጽንሱንም ሕይወት ማዳን የሐኪሙ ስራ ነው፡፡ አንዲት እርጉዝ ሴት በመጀመሪያ ደረጃ ታካሚ ስትሆን ጽንሱ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ታካሚ መሆኑ አይካድም፡፡ ስለዚህም የአንደኛውን ታካሚ ጥቅም የሚነካ ሲሆን ምን ያስከትላል የሚለውን በደንብ መመልከት ይገባል፡፡


ሌላም ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ነገር አለ ብለዋል ዶ/ር ገላኔ፡፡ አንዲት እናት ይህንን እርግዝና ብትቀጥይ ለህይወትሽ ያሰጋል እየተባለች በጭራሽ አላቋርጥም፤እርግዝናውን እቀጥላለሁ ብትል ምንድነው መደረግ ያለበት የሚለው ነገር ሁልጊዜም አነጋጋሪዎች ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች በተከሰቱ ቁጥር ችግሮቹን ለመፍታት በቀጥታ ከታካሚ እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር መነጋገር ፤መመካከር አስፈላጊ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በተሳካ ሁኔታ በቀላሉ በመወያየት ወደመፍትሔው የሚኬድ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን በቀላሉ ውሳኔ ላይ ለመድ ረስ አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ ከአንድ ሐኪም በላይ ቦርድ ተነጋግሮ መፍትሔ ለመስጠት ይሞከራል፡፡ ከዚህም በላይ በውጭ ሐገር ወደ ፍርድ ቤትም የሚኬድበት እና በህግ ውሳ እንዲያገኝ የሚደረግበት ሁኔታም አለ፡፡
ግለሰባዊነትን ማክበር፤ጥቅም መስጠት፤ አለመጉዳት እና ፍትህ ከስነምግባር መርሆዎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱና ሁልጊዜም ስራ ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡ በሶስተኝነት ደረጃ የተቀመጠው ጉዳት አለመስጠት የሚለው ነገር በምሳሌ ሲገለጽ አንድ ታካሚ እራሱን መጉዳት ፈልጎ አደገኛ መድሀኒት እንዲሰጠው ቢጠይቅ ሐኪሙ የመድ ሀኒቱን ጎጂነት እያወቀ ለታካሚው በምንም አይነት መንገድ አይሰጠውም፡፡ ምናልባት በስህተት እንኩዋን ቢፈጸም እንደወንጀል የሚቆጠር ድርጊት ነው፡፡


ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት አንድ በጣም ሊተኮርበት የሚገባ ነገር መኖሩን ገልጸው እንደሚከተለው አብራርተውታል፡፡
ከአምስት አስርት አመታት በፊት የህክምና ስነምግባር መሰረታዊ እሴት ጥቅም መስጠት ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር፡፡ ስለዚህም አንድ ሐኪም ለታካው ይጠቅመዋል ብሎ ያመነበትን ነገር ማድረጉ እንደትልቅ ነገር ይቆጠር ነበር፡፡ በዚህ አካሄድም አንድ ሐኪም ምንም አይነት ህክምና ላይ ከታካሚው ወይንም ቤተሰቡ ፍላጎት ውጭ በራሱ እምነት የሚያስፈልገው ይሄ ነው፡፡ ይህን ብታደርጉ ነው የምትድኑት በሚል ስሜት በራሱ የሚያደርጋቸው ነገሮች ትክክል ተደርገው ይወሰዱ ነበር፡፡ በጊዜው የጤና ባለሙያዎች አመለካከት አባታዊ ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡


በአሁኑ ወቅት ከስነምግባር እሴቶች ውስጥ የግለሰብን ማንነት ወይንም ሐሳብ በቅድሚያ መቀበል እንደዋነኛ የስነምግባር እሴት ተደርጎ በመወሰድ ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህ አንድ ታካሚ ከሐኪሙ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ሁሉም ነገር ግልጽ ተደርጎ ሊነገረው ይገባል የሚል እምነት አለ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሐኪም ታካሚው በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚሞት የሚያውቅ ቢሆን በበፊቱ አሰራር ሐኪሙ ለታካሚው ….አ…አ…ይ ምንም ችግር የለም….በቃ መድሀኒት እንሰጥሀለን….ትድናለህ የሚል አይነት መልስ በቀጥታ ለታካሚው ሰጥቶ ምናልባት እንኩዋን ትንሽ ፍንጭ መስጠት ይገባኛል ቢል ቤተሰብ እንዲዘጋጅ….ብዙ እንዳይጠብቅ ይናገር ይሆናል፡፡

ታካሚው ስነልቦናው እንዳይጎዳ መደረጉ ትክክል እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ አሁን ግን ባለው ሁኔታ ሐኪሙ በእርግጥ በቀጥታ …አንተማ ከሁለት ወር በሁዋላ ትሞታለህ…..ብሎ እንዲነግረው ሳይሆን ግን ስለህመሙ በግልጽ መናገር…..ታማሚው ያለበትን ሁኔታ ….በሚቀጥለው ቀጠሮ ቤተሰብ ይዞ እንዲቀርብ……. .ወዘተ ስለህመሙ ለታካሚው ሙሉ በሙሉ እንዲነግረው ይጠበቃል፡፡ህመሙ ከባድ መሆኑን….ሊታከም የማይችል መሆኑን…የመኖር እድሉ ምን ያህል እንደሆነ መንገር የሐኪሙ ግዴታ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ በአንድ ቀን ይነገራል ማለትም አይደለም፡፡ በበፊቱ አሰራር ግን ይጠቅመዋል ተብሎ ስለሚታሰብ እስከመጨረሻው ድረስ ተደብቆ እድናለሁ እያለ እያሰበ ይሞት ነበር፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በውጭ ሀገራትም የተደረገ የውቅረ ልቦና ለውጥ ነው፡፡ በእርግጥ አስተሳሰብ በአንድ ጊዜ የማይቀየር በመሆኑ ፊት ለፊት መናገሩ ህመምተኛውን ይጎዳል ብለው የሚያስቡ ሐኪሞችም….እንዲሁም እንዴት በግልጽ ለታካሚው ጉዳቱ ይነገረዋል የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን አለም በሙሉ በተቀበለው አሰራር የግለሰብ ማንነትን ማክበር ወሳኝ ስለሆነ ይህ ይፈጸማል ብለዋል ዶ/ር ገላኔ፡፡


አራተኛው የስነ ምግባር እሴት ፍትህ በህክምናው አለም አፈጻጸሙ ምን መልክ አለው የሚለው ሌላው ለዶ/ር ገላኔ የቀረበ ጥያቄ ነበር፡፡ዶ/ር ገላኔም በሰጡት ማብራሪያ ፍትህ በሁሉም ነገር ውስጥ የሚተገበር ወይንም የሚንጸባረቅ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ በጣም የታ መመ … ለማከምም ብዙ ግብአቶችን የሚጠይቅ እና ከታከመም በሁዋላ ውጤቱ ብዙም የማያስደስት ቢሆን እንዲሁም በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ሰዎች የሚቸገሩበት ሕመም እና በቀላሉ ግብአት ሊታከም የሚችል እንዲሁም በትንሽ ወጭ ታክሞ አስደሳች ውጤት የሚያ መጣ ቢገጥም ለእነዚህ ሁለት ነገሮች ግብአት መመደብ ቢያስፈልግ ለየትኛው ቅድሚያ ይሰጣል የሚለውን መመልከት ይቻላል፡፡በሌላም በኩል ኦክስጂን የሚፈልጉ ሁለት ታካዎች ቢኖሩ እና ምናልባትም የኦክስጂን እጥረት ቢኖር ለየትኛው ቅድሚያ እንሰጣለኝ የሚለው ሁሉ ፍትሐዊ አሰራርን የሚጠይቅ ነው፡፡ ትክክለኛ የሆነ መረጃ፤ትክክለኛ የሆነ መድሀኒት መስጠት፤ይህንን መድሀኒት ግዛ ከማለት ይልቅ እዚህ መድሀኒት ቤት ግዛ፤ውጤቱን አሰርተህ ቅረብ ከማለት ይልቅ እዚህ ላቦራቶሪ አሰርተህ ቅረብ ማት ይገባል ወይ የሚለው ሁሉ ፍትሐዊ አሰራርን የሚፈልግ ነው፡፡ ፍትህ ሁሉ ነገር ውስጥ ይገባል ብለዋል ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት፡፡          

Read 2153 times