Thursday, 09 November 2023 20:26

የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የሚዲያ ትኩረት ተነፍጎታል ተባለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

*በሶማሊያ ክልል፣ ጎርፍ ብዙ ሺዎችን አፈናቅሏል፤3ሺ የቁም እንስሳትን ገድሏል

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር፣ ሳምንታዊ የቁርስ ላይ ስብሰባውን ዛሬ ጠዋት በሂልተን ሆቴል ያካሄደ ሲሆን፤ የእለቱ የውይይት ርእሰ ጉዳይም፤ "The Role of Media in Climate Change Communications፡ Why should Editors Care?" የሚል ነበር፡፡

 በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ፅሁፍ ያቀረበችው ለረዥም ዓመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የሰራችውና አሁንም በአንጋፋው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በአዘጋጅነት እየሰራች የምትገኘው ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሣዬ ናት፡፡

የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ ብክለት ጉዳይ፣ በአገራችን ሚዲያና ጋዜጠኞች እንዴት እየተዘገበ ነው የሚል ጥያቄ በማንሳት የጀመረችው ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሣዬ፤ በርካቶቹ ሚዲያዎች የአየር ንብረት ለውጥን አጀንዳ አድርገው እንደማይዘግቡና ለርዕሰ ጉዳዩ ፍላጎት እንደሌላቸው ጠቁማለች፡፡

ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት ያቀረበችው አንድም የዕውቀት ክፍተትን (እንዴት እንደሚዘገብ አለማወቅ) ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ  በቂ መረጃ ያለማግኘት ችግርን ነው።

ባለፉት ዓመታት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ በስፋት መዘገቧን የገለጸችው ጋዜጠኛ መታሰቢያ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥት ሃላፊዎች እንኳንስ በቂ መረጃ ሊሰጡ ቀርቶ በጋዜጠኛው ጥረት የተሰባሰቡ መረጃዎችና ምስሎችን ቀምተው ከአካባቢው የሚያስወጡበት ሁኔታ እንዳለ የራሷን ተሞክሮ በምሳሌነት አቅርባለች።

በአፍሪካ ባለፉት 50 ዓመታት፣ 170 የተፈጥሮ አደጋዎች መከሰታቸውንና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን በጽሁፏ የጠቀሰችው ጋዜጠኛዋ፤ ይሄ የሚያሳየው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ፣ በህይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑን ነው ብላለች። ለዚህም ነው ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት መስጠት ያለባቸው ስትልም አስረድታለች፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በቂና ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን ያገኝ ዘንድም ከሁሉም አስቀድሞ ኤዲተሮችና ሪፖርተሮች በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየመጣ ያለውን አደጋ በበቂ ሁኔታ መገንዘብ ይኖርባቸዋል ስትልም በአፅንኦት ተናግራለች፡፡

ኤዲተሮች በአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ ላይ ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ጉዳዩ የመኖርና ያለመኖር ወሳኝና አንገብጋቢ ጉዳይ እየሆነ በመምጣቱ ነው ብላለች፤ ጋዜጠኛዋ፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት አብዛኞቹ የማህበሩ አባላት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ  በቂ  የሚዲያ ሽፋን እያገኘ አይደለም የሚለውን የጋዜጠኛ መታሰቢያ ሃሳብ ይጋራሉ፡፡

አንድ የማህበሩ አባል በሰጡት አስተያየት፤ የአየር ንብረት ለውጥን ወይም የአካባቢ ብክለትን በደረቁ ከመዘገብ ይልቅ የሚያስከትለውን ወይም እያስከተለ ያለውን የጤና እክል አያይዞ መዘገብ የተሻለ ትኩረት እንዲያገኝ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ሌላዋ አስተያየት ሰጪም ተመሳሳይ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ስንዘግብ በዳታ የታጨቀ ብቻ ከሚሆን ከሰው ህይወት (ጤና) ጋር አያይዘን ብንዘግበው የበለጠ ትኩረትና ተነባቢነት ሊያገኝ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

አንድ የማህበሩ አባል ደግሞ የአቅም ግንባታ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ  ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ጋዜጠኞችና ኤዲተሮች በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ  አጫጭር ስልጠናዎች የሚያገኙበትን ዕድል መፍጠርና ማመቻቸት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል - ስልጠናው ጋዜጠኞችና ኤዲተሮች ጉዳዩን በበቂ እውቀትና ግንዛቤ እንዲዘግቡት አቅም እንደሚያስታጥቃቸው በመጠቆም፡፡

 ከሰሞኑ በሶማሊያ ክልል በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ሳቢያ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንና ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የጠቆመችው ጋዜጠኛ መታሰቢያ፤ ሆኖም ግን አብዛኛዎቹ ሚዲያዎች ክስተቱን እንዳልዘገቡት መታዘቧን ተናግራለች፡፡ ይህም ሚዲያዎች ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በቂ ትኩረትና ሽፋን እየሰጡ አይደለም የሚለውን መነሻ ሃሳቧን ያጠናክርላታል፡፡  

 ባለፈው ሳምንት፣ በሶማሌ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ፣ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ሳቢያ፣ 24 ሰዎች መሞታቸውንና 23ሺ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ የመንግሥት ሃላፊዎች የገለጹ ሲሆን፤ በተጨማሪም የጎርፍ አደጋው በአጠቃላይ 10ሺ ሄክታር የሰብል መሬት ማውደሙንና 3ሺ የቁም እንስሳትን መግደሉንም አመልክተዋል፡፡

በእርግጥም የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የሚዲያዎችን ትኩረት ማግኘት አለበት የሚባለው በህይወት የመኖርና ያለመኖር አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ ነው፤ እንደ ሰሞኑ የሶማሌ የጎርፍ አደጋ፡፡

Read 1024 times