Saturday, 04 November 2023 00:00

እውነተኛው እውነት

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(5 votes)

እንደሁልጊዜው በነፃነት ከህሊናችሁ ላዋህደው ያሰብኩትን ሀሳብ ያለፍርድ አድምጡኝ፡፡
እንጀምር…
ምንድን ነው ይሄ ሀይማኖት የሚባለው ነገር? በውስጡ ሰዎችን፣ መፅሀፍትን እና ህግጋቶችን ጠቅልሎ ይዟል፡፡ ግን ምንድነው? የሰው ልጅን እስከ ዐድሜው ማብቂያ ድረስ በአዕምሮው ውስጥ የማይለቅ ክታብ ሆኖ የተበየደበት ሀሳብ? ምንድን ነው የሰው ልጅ የተባለ ሁሉ የሀሳብ ቅርፁን እየቀያየረ በተለያየ ሀይማኖት ውስጥ “ራሴን እና የፈጠረኝን አገኘሁት” እያለ የሚሰብከን ነገር? እውነት ነው? ሀሳብ ብቻ ነው? የቅዠት ንግድ ነው? ሀይል ነው? የፖለቲካ አላማን ለማሳካት የተፈበረከ መንፈሳዊ ዝርፊያ ነው? የቀረበንን እውነት ማራቂያ የሀሳብ ጦርነት
ስልት ነው? ማነው የመጀመሪያው ሰውዬ/ሴትዮ ይህን ውስብስብ ሀሳብ ይዞብን የመጣው?
***
 በእርግጠኝነት ይሄን ፅሁፍ የሚያነበብ ፍጥረት ከግማሽ በላይ የሆነው ሀይማኖተኛ ነው፡፡ እሱን እርግጠኛ ሆኜ ሀሳቤን ልራመደው እና ወደ ውስጥ ልግባ፡፡ ምንም ጥያቄ የለውም- የአለም አሠራር ውስጥ ምንም ጥሩ ነገር አይታየኝም፡፡ እንስሶች በሕይወት ለመኖር አንዳቸው አንዳቸውን እያደኑ በመብላት ነውየምድር ላይ ጊዜያቸውን የሚያራዝሙት፡፡ በየትኛውም የኑሮ ጣሪያ ላይ ራሳቸውን ቢያገኙትም የሰው ልጆችም ያሰቡት አላማ ጋ ለመድረስ እየዋሹና አምሳያቸውን እየገደሉ ነው የኖሩት፡፡ አሁንም የሚኖሩት፡፡


ስጋ አንበላም የሚሉት የእንስሳት ተቆርቋሪዎችም ሕይወት ያላቸውን እፅዋት ከሥራቸው ገንጥለው ከመብላት ያዳናቸው ማንም የለም፡፡
ሁሉም ነገር መቆሚያ በሌለው ሁኔታ አንዱ አንዱን እያወደመ ነው የምድርን ሥርዓት የሚያስቀጥለው፡፡ ይህንንም የጥፋት ሰንሰለት… እንከን የሌለው ትክክለኛ የተፈጥሮ ስርዓት እንደሆነ የሚሰብኩ አሉ፡፡ ይህ መጠፋፋት መሰረታዊ የሆነ የተፈጥሮ ህግ እንደሆነ እና ይህም ሂደት ተፈጥሮ ወጓን ጠብቃ እንድትጓዝ የሚያደርጋት እንደሆነ በመላው ሀይማኖተኛ ልብ ውስጥ እንዲፃፍ ተደርጓል፡፡
ሆኖም እኔ ይህን እላለሁ…ይህ ከገሀነምም የባሰ ገሀነም ነው፡፡ የዚህም ስርዓት መፈብረክ ያመጣው ጣጣ ውስጥ፣ የሰው ልጅን ለመጫን፣ በፍርሀት ውስጥ እንዲመላለስ ለማድረግ የታሰበ አላማ ይታየኛል፡፡ አንዲት የማትገኝ ተስፋን ለማይሞላው ፍላጎት ለማስገበር የሚደረግ ጥረት አይበታለሁ፡፡ በግል ልምዴ ለማየት እንደሞከርኩት የሀይማኖት ሀሳብ… ሀሳብ መሆን እና መታመን የሚጀምረው የሰባኪውን አንደበት
ተከትለን ማመን ስንጀምር ነው፡፡ ስለዛ ሰባኪ ምናልባት ማወቅ የምንፈልገው ጥቂት ነው …ወይንም ደግሞ ማወቅ አንፈልግ ይሆናል፡፡


 ሆኖም ምንጊዜም ማሰላሰል ያለብን ነገር ከዛ የሀይማኖት ሰባኪ የሚወጡትን ቃላት በሙሉ ማመን የምንጀምርበት ቀን ይመጣል፡፡ በዛም አያቆምም፡፡ ስለዛ ሰባኪ ጀብዱ ለወዳጅ ዘመዶቻችን መስበክ እንጀምራለን፡፡ ምን ያህል ለፈጣሪ ቅርብ እውነተኛው እውነት እንደሆነ እየተናገርንለት ስሜታችንን ወደ መሰሎቻችን ለማጋባት እንተባለን፡፡ በዚህ አያበቃም…ከዚህ ቀደም ስሙን ጠርተን እንደ ቅርብ ወዳጅ ስናማክረው የነበረው ፈጣሪያችንን እረፍት ሰጥተነው ይመስል ያንን ሰባኪ እንዲፀልይልን፣ እንዲማልድልንና ከፈጣሪያችን ጋር እንዲያዋሕደን እንለምነዋለን፡፡ ሲከፋም እንከፍለዋለን፡፡ በህፃንነታችን…በሚድኸው እውቀታችን ውስጥ ሲጠብቀን እና ህይወትን ሲተነፍስልን የነበረውን ፈጣሪ እያደግን ስንመጣ በሀይማኖት ህግጋት ውስጥ እናጣዋለን፡፡ “ከናንተ በፊት ድምፁን ሰማሁት” ወደሚለን ሰባኪ መንደርደር እንጀምራለን፡፡ ውክልና ፍለጋ ፍለጋ ሩጫ ውስጥ እንገባለን፡፡ ሀይማኖት ስንይዝ የመጀመሪያው ግባችን ራሳችንን ማዳን ነው፡፡ እኔ ግን አሁንም ድረስ እጠይቃለሁ
…ከምን ለመዳን?

ይህን ስጠይቅ አንድ የምትመቸኝ አባባል አለች፡፡ የሂንዱ ሙስሊሙ እና የባህታዊው የካቢር ንግግር ትመጣብኛለች፡፡ ካቢር ለመሰሎቹ ሊሰብክ ከገዳሙ በመውጣት በየከተማው ይመላለስ ጀመር፡፡ ሆኖም መስበክ ፈልጎ ማንን ይስበክ… ግራ ገባው፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፤ “በከተማዎቹ ውስጥ ተመላለስኩ፤ ሆኖም ልሰብከው የምችለው የሰብዕ ዘር ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም በያንዳንዳቸው
ዐይኖች ውስጥ ከመለኮት እሳት ውጭ ምንም ሊታየኝ አልቻለምና ነው፡፡” ይላል፡፡ የሰው ልጅ ከነመለኮቱ እንደተፈጠረ እና መለኮታዊነቱን መልቀቅ ቢፈልግ እንኳን መሸሽ እንደማይችል ነው የካቢር ትዝብት የሚያስረዳን፡፡ ድንገት ሀይማኖት የተባለ ሰው ሰራሽ የእምነት ገበያ ውስጥ ገብቼ መለኮታዊነቴን በፍርሀት ሳጥኔ ውስጥ ቆልፌ ከሸጥኩት በኋላ እንደገና እሱኑን ለማስመለስ የመታገል ፍላጎት የለኝም፡፡ ምናልባት መዳን ካለብኝም ድህነቴ ሀይማኖታዊ አሰራር ውስጥ ተፈትኖ መፍትሄ ያገኛል ብዬ ከማስበው ሀሳብ ነው መዳን ያለብኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ሀይማኖት ታሪኮችን በመጠቀም በዘይቤ አገላለፅ “አርኪታይፒካል” ፍጥረታት በህሊናችን ውስጥ በመክተት በፍርሀታችን
አምድ ላይ ሆነን ራሳችንን ሳይሆን ምናባዊ ሂሮ (ጀግና) ኑሮ እንድንኖረው ከማድረግ ውጭ ሌላ ፅንሰ ሀሳብ አላገኘሁበትም፡፡ አስተውሉት….
ገና ራሳችንን በቅጡ ሳናውቅ የክርስቶስን መስቀል ተሸክመን እንድንሄድ ይደረጋል፡፡ የመታመምን ጥልቀት ሳንረዳው የህመሞችን ሁሉ ህመም የታመመው ክርስቶስን ካልመሰልን በገነት ስፍራ እንደሌለን ይነገረናል፡፡ ይሄ ታዲያ ምን እንድንጠይቅ ያደርገናል?
ወንጌል ማለት የመልካም ዜና ብስራት ከሆነ እንዴት አድርገን ነው የማይደረስበትን የክርስቶስን ፅናት እንድንለማመደው እንደመጀመሪያ ህግ ይዞብን የመጣው፡፡ እንድንፈራ ሆነናል፡፡ የክርስቶስ አቅም ጋ መቼም እንደማንደርስበት እናእንደማይገባንም አድረገው እነዛ ገባን ያሉት ይሰብኩናል፡፡ ይሄ ደግሞ ፍርሀት እና ተስፋ መሸጥ ነው ለኔ፡፡ ሆኖም ራሳችንን ማክበር እና የውስጣችንን ድምፅ መስማት ያቆምን እለት
ላይ በጊዜ ብዛት ውስጥ የማይገባንን እረፍት ማግኘት እንጀምራለን፡፡ እኔ ኀጥእ ነኝ ብለን ማመን ስንጀምር ማደግ እየጀመርን እንደሆነ ማመን እንጀምራለን፡፡ ለምን በመፀፀት ውስጥ ሳለን የዳንን ይመስለናል? ለምን በምድር ላይ ሳለን እየተደሰትን ያደረግናቸውን ነገሮች ለንስሀ አባቶቻችን ስንናገራቸው ፀፀት ይገርፈናል?

ፀፀታችሁ ለህሊናችሁ ተመላላሽ እንግዳ መሆን ሲጀምር ያኔ በእናንተ እና በክርስቶስ መካከል ያለው ልዩነት መረዳት ትጀምራላችሁ፡፡
ድክመታችሁን በማደመጥ ጊዜያችሁ ስለተበዘበዘ እንዴትም አድርጋችሁ ኢየሱስን መምሰል እንደማትችሉ በመረዳት በንስሀ ውስጥ ልትቀራረቡት ትሞክራላችሁ፡፡ ትልቁ ሚስጥር እዚህ ላይ ነው…ንስሀችሁን እያወረዳችሁ ባላችሁበት ወቅት ላይ፣
ከህሊናችሁ በስተጀርባ ንስሀ የገባችሁትን እያንዳንዱ ሀጥያታችሁን ደግማችሁ እንደምታደርጉት ታውቁታላችሁ፡፡ እንዲህ ስል መፅሀፍ ቅዱስን
እየተቃወምኩ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን በዛ ቅዱስ መፅሀፍ ላይ የራሴን መጠይቆች በሌላ ጊዜ ማንሳቴ ባይቀርም ቅሉ፡፡አሁን እኔ ላነሳ ያሰብኩት ሀሳብ ከእውነት ይልቅ እውነት የሚመስል ቅዠትን መለማመድ ሱስ ከሆነብን ቆይተናል ነው፡፡

ብንጠየቅ የማንመልሳቸው ብዛት ያላቸው ፍለጋዎች እና የቤት ስራዎች እንዳሉብን ብንረዳም ሮጠን የማመን እና የመስበክ ሱስ ጠምዶናል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ለመባል ብለን የብዙ ህፃናት ውስጥ ያለውን ጥልቅ የመጀሪያውን ጥበብ አውድመንባቸዋል፡፡
የገባን መስሎን፡፡ ንቁ ይሉናል፡፡ ወደየት ነው የምንነቃው?
አሁን ምን እየሆንን ነው? ሚስጥራዊ እውቀት በሚል ሰበብ የሰው ልጅ ጭንቅላት ውስጥ የሀይማኖት ፖለቲካ ይሄ ነው የማይባል ጥፋትን አድርሷል፡፡ እጅግ ሰላማዊ ከሚባለው የቁርዐን ቅዱስ መፅሀፍ ውስጥ በራሱ ስሜት የተሳለ ሰይፍ መዞ አውጥቶ መሰሉን የሚገድል እንዳለ ተመልክተናል፡፡በሀይማኖት ስም ስንት አይነት ጦርነት ተከፍቷል? በሀይማኖት ስም የስንት ህፃናት ህይወት ተበላሽቷል? ስንት ንፁሀን ከሰላማዊ ኑሯቸው ተፈናቅለዋል? የስንት ሴቶች ነፃነት ላይመለስ ተማግዶ ጠፍቷል?


በሀይማኖት ሰበብ ስንት አይነት ድግምቶች ተፈብርከዋል? በሀይማኖት ሰበብ ስንት አይነት ፈጣሪዎች ተፈጥረዋል?
አስባችሁታል ወይ? በያንዳንዱ ክርስቲያን አእምሮ ውስጥ ምን ያህል የተለያየ ሀሳብ ያለው ክርስቶስ እንደተፈጠረ፣ በያንዳንዱ ሙስሊም ውስጥ ጫፍና ጫፍ የሆኑ የነብዩ ሙሀመድ (ሰ.አ.ሁ) አስተምህሮት የተለያየ ቅርፅ እየተሰጣቸው ሰዎች እንደሚጫረሱ፡፡
 ኤዲ ግሪፈን እንዳለው የኔም ጉዳይ ከመልዕክተኞቹ አይደለም፡፡ ነገር ግን መልዕክቱ ደርሶናል ወይ? የሚለው ነው መሰረታዊው ሊሰመርበት የሚያስፈልገው ሀሳብ፡፡ ሁሉምን ሀሳብ ማባበል የግድ አይጠበቅብንም፡፡ መፈተሸ አለብን፡፡ ሁል ጊዜ የሀይማኖት ስርዓት ውስጥ ራሳችንን ከመክተታችን በፊት ሀይማኖቱን በጥልቀት ማጥናቱ የተገባ ነው፡፡ ሰባኪዎቹ እንደኛው ሰዎች እንደሆኑና እንደኛው በፈጣሪ ፊት
የእውቀት መካን እንደሆኑ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡


 ብዙ ሀይማኖቶች በየዘመናቸው ላይ ገዝፈው ይሄ ነው የማይባል ተፅዕኖ ፈጥረው በስተመጨረሻ ከነፈጣሪዎቻቸው ትዝታ ብቻ ሆነው ጠፍተዋል፡፡ የሰው ልጅ ግን ሁሌም አለ፡፡ መልስን እያሰሰ፡፡ እውቀትን እየተጠማ፡፡
የትኛውም ሀይማኖት ውስጥ ልትሆኑ ትችላላችሁ፡፡ የመረጣችሁትን ቅዱስ መፅሀፋችሁን በቅድሚያ በግላችሁ ልትመሰጥሩት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ወሳኙ የሰባኪያችሁ መረዳት አይደለም፡፡ የሀይማኖቱ ስም አይደለም፡፡ ሰባኪውም ከእለታት አንድ ቀን የያዘውን እውነት እና እምነት ሸሽቶ ሊሰወር ይችላል፡፡


በፈጣሪያችሁ ፊት የማትቀያየሩት እናንተ ናችሁ፡፡ በዘመናት ውስጥ ሀይማኖት የሚባለው ነገር ያለው የሰው ልጆች እኛ ስላለን ብቻ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል፡፡ ምናልባት በመዝሙረ ዳዊት እንዲህ ተብሎ እንደተፃፈው….”እኔ ግን ፡- አማልዕክት ናችሁ፡ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፡፡ነገር ግን እንደሰው ትሞታላችሁ፡፡ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ አልሁ፡፡ “ የዳዊት መዝሙር 82፡6-7፡፡
 ክርስቶስም በዮሀንስ ወንጌል 10፡34 ላይ እንደጠቆመው …”ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው ፡- እኔ፡- አማልዕክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ አልተፃፈምን?”
ብሎ እንደነገረን አማልክት ሆነን ይህን ማንነታችንን ሊናጠቁን በመጡት ሀሳሂ ሰባኪያን ታውረን የምድር ላይ ትቢያዎች አድርገን ራሳችንን እንድናስብም ታቅዶም ሊሆን ይችላል፡፡ ቅድም እንዳልኩት በሌላ ጊዜ የተለያዩ ቅዱስ መፅሕፍትን እየመረመርን ሚስጥራትን ገሀድ የምናወጣበት ጊዜ ይኖረናል፤ ለአሁን ግን ይህን ብዬ ሀሳቤን ልዝጋው፡፡ በህይወት እያለን ህይወትን በመፈለግ ጊዜያችንን አንብላው፡፡ መሞታችን ላይቀር ሞትን እየሸሸን የተሸከምነው እውነት በመካድ የተለየ እውነት ለማምጣት ከህሊናችን አንጋጋጥ፡፡


 የተፈጠሩት አለማትን ተመልክተን የፈጣሪን የእጅ ስራ በልበ ሙሉነት መናገር እየቻልን ሁሉንም ነገር ሚስጥር አድርገን ከማናመልጠው እውነት ጋር ድብብቆሽ አንጫወት፡፡ እርስ በእርስ እንዋደድ፡፡ እዛ እመንገዱ ላይ የምትሄደው እህትህን አክብር፡፡ ከዛ ጥጋት ስር ብቸኝነቱ የመረዘውን እና ከራሱ የተሰወረው ወንድምሽን እናት እንዲሆን በተፈጠረው ህሊናሽ አይተሸ ድረሺለት፡፡ የሀገር መሪም ቢሆን ትዝታ መሆኑ የማይቀረው የስልጣን ዘመኑ ውስጥ ሀያል ፍቅርን ከህዝቦቹ ጋር ሆኖ በመለማመድ የእጅ ስራውን ከትዝታነት ባለፈ እየደጋገሙ የሚመኙት ራዕይን ከሁላችንም ህሊና ውስጥ ከትቦ ይሰናበተን፡፡ እነዚህ ናቸው ሀይማኖቶቼ፡፡መከባበር፣ መረዳዳት፣ ማፍቀር፡፡
እነዚህን ህይወቶች ስለማመድ የፈጣሪዬ

Read 628 times