Saturday, 28 October 2023 20:32

“ዳጉሳዬ”- የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር የዓመቱ ዘፈን

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

 - የቸገረን ስንዴ ነው። የተወደደብን ዳቦ ነው። መፍትሔው መንግሥት ነው? የአገራችን ተስፋ ምን ይሆን?
      - የዳጉሳ ቂጣ እንድንበላ ይመክራሉ- ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የዳጉሳ ረሀብ ይጠፋል፤ ዓለም ይለወጣ ል ብለዋል- በልማታዊ ዘፈን።
      - ለህንድ የፓርላማ አባላትና ለውጭ አገር መሪዎች የሚቀርበው መስተንግዶ፣… ያው… የዳጉሳ ቂጣ! ሆኗል።
       
        ከምር ነው። ቅኔ አይደለም። ሰምና ወርቅ የለውም። ነገርዬው ዘፈን ነው - ለዳጉሳ የተዜመ። ዳጉሳ ምን እንደሆነ ባታውቁ  ለጊዜው ችግር የለውም። ዋናው ነገር፣  የመንግሥት ዘፈን መሆኑ ነው። የጉዳዩን ክብደት ለመገንዘብ ከፈለጋችሁ አንድ ነገር ብቻ አስታውሱ። የግጥሙ “ኮፒ ራይት” የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው።
ይህም  ብቻ አይደለም። ዝነኛውና እጅግ የተከበረው የዓለማችን ጋዜጣ ‘ዎል ስትሪት ጆርናል’፣ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በዘፈኑ ዙሪያ ሰፊ ዘገባ አቅርቧል። ለዚያውም በጋዜጣው የፊት ገጽ ላይ ነው የታተመው።  ጉዳዩ የዋዛ ባይሆን ነው። በእርግጥ መዘባበቻና ማዋዣ፣ ማላገጫና መዝናኛ አዘጋገብም ሊመስል ይችላል።
ቢሆንም ግን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘፈን፣ የኪነጥበብ ፈጠራ ነው ወይስ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ ይሆን? የሚሉ ቁም ነገሮች ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም። ከዚያ በፊት ግን፣ ጋዜጣው የጉዳን ክብደት ለማሳየት ሞክሯል። እንዲሁ በቀላሉ የተሰራ ዘፈን እንዳልሆነ በማስታወስ ዘገባው ይጀምራል።
የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሪንድራ ሞዲ፣ ለ6 ወራት በምሥጢር ያከናወኑትን አገራዊ ፕሮጀክት፣ ለአገራቸው ሕዝብና ለዓለም ይፋ ማድረጋቸውን ይገልጻል - ጋዜጣው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሥጢራዊ  ፕሮጀክት፣ ዳጉሳን የሚያሞግስ ዘፈን ነው ሲልም ጋዜጣው ማረጋገጫ ይሰጣል - ገና በመጀሪያው ዓረፍተ ነገር። ቀልድ መስሎን እንዳንጠራጠር ያሰበ ይመስላል።
Prime Minister Narendra Modi spent the first half of 2023 working on a secret project: a song about millet.
ዳጉሳ ማለት…  በአካል ባታውቁትም በወሬ በታሪክ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ። በከተሞች አካባቢ ዛሬ ዛሬ ዳጉሳ ብዙም አይታይም። ለነገሩ ድሮም ቢሆን፣ ቢቸግር እንጂ  የዳጉሳ አድናቂና አፍቃሪ ጥቂት ነው።  “አሻሮ”፣… ለቁርስ ለእራት ተመራጭ አይደለም። ዛሬ ዛሬማ፣ ዳጉሳ ከነጭራሹ እየተረሳ ይመስላል። ዋጋው ርካሽ ነው ለማለት አይደለም። ዛሬ ምን ርካሽ ነገር አለ? ርካሽ ባይሆንም ግን፣ ዳጉሳ ለጋጋሪም ለተመጋቢም አይመችም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሪንድራ ሞዲ ግን፣ በዚህ አይሰማሙም።
ዳጉሳ ብርታት ነው፤ እንደ ሙዚቃ ነፍስ ነው፤ ዳጉሳ ተአምረኛ ነው እያሉ ያወድሳሉ። እንዲያውም፣ ዳጉሳ ዓለምን  ይቀይራል ባይ ናቸው-ጠ/ሚኒስትሩ።
ዓለም የሚለወጠው፣ ረሀብ የሚያበቃው በዳጉሳ እንደሆነም ይነግሩናል።
 በአጭሩ የጠ/ሚኒስትሩ ዘፈን የዳጉሳ ትንሳኤን ይተነብያል፤ ያበስራል።  የዳጉሳን የተረሳ ስም እንደገና ለማደስ የምሥራቹን ያውጃል።
millets swaying all around
once lost now found
(ዳጉሳ በዙሪያችን በየመስኩ ይወዛወዛል
ጠፍቶ የነበረው አሁን ተመልሷል፣ የጠፋው በግ ዛሬ ተገኝቷል) በማለት ያበስራል - የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጥም።
ለማንኛውም፣ ዳጉሳ ማለት የእህል ዐይነት ነው። ከማሽላ ጋር ይቀራረባል። እንዲያውም ዘፈኑ ላይ የማሽላ ስምም ጠቅሷል። ዳጉሳ ግን ደቀቅ ጠቆር ይላል። ጠላ ለመጥመቅ ነበር የሚያገለግለው።
በነገራችን ላይ እንዲህ የተዘፈነለት የዳጉሳ እህል፣  በተለይ finger millet የተሰኘው ከኢትዮጵያ በጥንት ዘመን  ወደ ሕንድ የተስፋፋ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቅሳሉ። ቢሆንም የጠላ ጥንስስ ከመሆን ውጭ፣ እዚህ አገርም ሕንድ አገርም ያን ያህል ተፈላጊ አይደለም።
እዚህ ሁለት ተቃራኒ ሐሳቦች ሊመጡ ይችላሉ።
ዳጉሳ ተፈላጊ ባይንም ተዘፈነለት ብትሉ ትክክል ናችሁ።
ዳጉሳ ተፈላጊ ስላልሆነ ተዘመረለት ብትሉም ስህተት አይሆንም።
ተፈላጊ ቢሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ግጥም እስኪመጣ ድረስ ሳይጠብቁ አዳሜ ሊዘፍንለት ይችላልና።
በዚህም ተባለ በዚያ አዲስ የሙገሳና የፍቅር ዘፈን የተዜመው፣ ለዳጉሳ ነው።
እንዳያችሁት፣ የግጥሙ ደራሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሪንድራ ሞዲ ናቸው። ድምጻዊቷም ቀላል አይደለችም። በስፋት ትታወቃለች። አድናቂዎቿ ብዙ ናቸው። የግራሚ ተሸላሚ  ተወዳጅ ዘፋኝ ናት። ፋለጉኒ ሻህ ትባላለች። ፋሉ ብለው ያቆላምጧታል።
 ለጋዜጣው አስተያየቷን ስትናገር፣ ዳጉሳ ነፍሴ ነው  ባትልም፣ ዘፈኑ ነፍስ የሆነ ዜማ እንደሆነ ፋሉ ገልጻለች። ለእህልና ለተክል የተዘፈነ ዜማ አዲስ ሆኖ ነው? በየአገሩ ይኖራል።


“ማሽላዬ” የሚል ዘፈን ከኢትዮጵያ ሰምተው ይሆን? “የሽንብራ ጥርጥር” የሚል ዘፈንስ?
ለማንኛውም፣ ድምጻዊ፣ ፋኒ  ከጠ/ሚ ሞዲ ጋር  ቆንጆ ዘፈን ነው የሠራነው ብላለች። ጠቅላይ ሚኒስትራችን ገጣሚ መሆናቸውን አላውቅም ነበር። በጣም ነው የገረመኝ በማለትም አድንቃለች። ታዲያ፣  ጠ/ሚ ሞዲ ከገጣሚነታቸው በተጨማሪ፣ እንደ አጃቢ ሆነው ዘፈኑ ውስጥ ገብተዋል። በዜማው መሀል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ይደመጣል። ዳጉሳን የሚያወድስ ንግግር መሆኑ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። 2023 ‘የዳጉሳ ዓመት’ ተብሎ እንዲሰየም የዩኤን አጋር በመሆን ናሪንድራ ሞዲ ወስነዋል።
ምን ይሄ ብቻ!
ሕንድን የጎበኙ የዓለማችን መሪዎች የምሳና የእራት ግብዣ ላይ፣ የዳጉሳ ቂጣ እንዲቀርብላቸው ተደርጓል። በሕንድ የተካሄደው የጂ7 አገራት ስብሰባ ላይ የዳጉሳ ቂጣ፣ በየአዳራሹ ቀንም ማታም የተንበሸበሸበት አጋጣሚ ነበር ብሏል - ዎል ስትሪት ጆርናል በፊት ገጹ ላይ ባቀረበው ዘገባ።
what if we could change the world    በማለት ይጀምራል ዘፈኑ። በዳጉሳ ዓለምን ለመለወጥ ነው የዘፈኑ ራዕይ።
ወደ ኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመዝለላችን በፊት ግጥሙን እንጨርሰው።
green fields flowing grains
golden sun gentel rain
awaken and arise
looking for sunrise

millets swaying all around
once lost now found
nourishing body and soul
it is time to make us whole

cherish pearl millet and sorghum
cherish finger millets year after           year
flourishing with virtue they are              unparalleled
may millet nourish you for ages
cherish finger millets nourish by           any name
cherish finger millets year after           year
millets are a wonder
an end to hunger
what if we could change the world
what if we could change the world
one world one harmony
an ancient melody
so much that we can gain
the magic of this grain
በእርግጥ  ተአምረኛና ወርቃማ፣ የአካል ብርታት የነፍስ ሙዚቃ… ብለው ቢያሞግሱትም፣ የዳጉሳ ምርት፣ ከስንዴና ከበቆሎ ምርቶች ጋር ሲነጻጸር፣ ለቁጥር የሚገባ አይደለም።  
የዓለማችን የስንዴ ምርት፣ በየዓመት 7610 ሚሊዮን ኩንታል ነው። 7.6 ቢሊዮን ኩንታል ልንለው እንችላለን። ለአንድ ሰው በአማካይ 1 ኩንታል ገደማ ስንዴ መሆኑ ነው።
በነገራችን ላይ፣ የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ባለፉት ሀያ ዓመታት ከዕጥፍ በላይ ቢጨምርም፣ አሁንም በጣም ትንሽ ነው።
 ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በታች የነበረው የአገሪቱ የስንዴ ምርት፣ ወደ 60 ሚሊዮን ኩንታል አካባቢ ደርሷል። ወደ ሦስት ዕጥፍ ገደማ ሆኗል። ከመሬት ስፋትና ከሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ግን ገና ብዙ ይቀረዋል። በርካታ ሚሊዮን ኩንታል የዕርዳታ ስንዴ ካልመጣልን ሚሊዮኖች ይራባሉ። አደጋውን እያየን ነው።
በሌላ አነጋገር፣  ከዳጉሳ በፊት ስንዴ ይቀድማል። ሌላም አለ።
የዓለማችን የበቆሎ ምርት በዓመት 11.6 ቢሊዮን ኩንታል ነው (11,600 ሚሊዮን ኩንታል)። በምርት ብዛት፣  ከእህል ዓይነቶች ሁሉ በቆሎ ተወዳዳሪ የለውም። አንደኛ ነው። ደግነቱ ደግሞ፣ በሰላሳ በአርባ ዓመት ውስጥ ነው የዓለማችን በቆሎ ምርት በእጥፍ አድጎ እዚህ የደረሰው።
በእርግጥ፣ በኢትዮጵያም የበቆሎ ምርት በሀያ ዓመት ውስጥ ወደ ሦስት ዕጥፍ አድጓል።
በ1995 ዓ.ም የኢትዮጵያ ገበሬዎች የበቆሎ ምርት ከ30 ሚሊዮን ኩንታል በታች ነበር።
ከ2008 ዓ.ም ወዲህ ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ  በቆሎ እየተመረተ እንደሆነ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃዎች ያሳያሉ።
በ2013 ዓ.ም    117 ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ
በ2014 ዓ.ም    118 ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ
በዓመት ውስጥ የታየው ለውጥ ትንሽ ነው። ደግሞም ሰላም በደፈረሰባቸውና ግጭት በበዛባቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት፣ ያን ያህልም የምርት ዕድገት ባይታይ አይገርምም። ይልቅ እንዳይቀንስ ነው የሚያሰጋው። ሀያ ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሰን ካየን ግን ልዩነቱ ሰፊ ነው። አራት ዕጥፍ ሊሆን ምንም አልቀረውም።
እንዲያም ሆኖ፣ ገና ኢምንት ነው። ከዓለማችን የበቆሎ ምርት ጋር ሲነጻጸር፣ የኢትዮጵያ ምርት 1 በመቶ አይሆንም። ከአገሪቱ የሕዝብ ብዛት ጋር አብሮ አልተራመደም። በዚያ ላይ ብዙ ሰው ገበሬ የሆነበት አገር ውስጥ መሆናችንም መታሰብ አለበት።
ይህም ብቻ አይደለም ችግሩ። በእህል ምርት በዓለም ዙሪያ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጠው የሩዝ ምርት ላይ ፣ “ኢትዮጵያ ገና የለችበትም” ማለት ይቻላል።
በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ 7.5 ቢሊዮን ኩንታል ሩዝ ይመረታል።
 በኢትዮጵያ ግን 3 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ። ከሺ እጅ አንድ እጅ አይሞላም።
እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው  የማሽላ ጉዳይ፣ ከዚያም ቀጥሎ የዳጉሳ ነገር የሚመጣው።
ከበቆሎ፣ ከስንዴና ከሩዝ ጋር ሲነጻጸር፣ የዓለማችን የዳጉሳ ምርት በጣም ትንሽ ነው።
በዓመት 300 ሚሊዮን ኩንታል አይሞላም።  በኢትዮጵያ ደግሞ 10 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ይመረታል።በአብዛኛውም በድሀ አገራት ውስጥ የሚመረት ነው - ዳጉሳ።
እነ ስንዴና እነ በቆሎ በዓለም ዙሪያ ባለፉት ሀያ ዓመታት በሁለት በሦስት ቢሊዮን ኩንታል ምርታቸው ጨምሯል። የዳጉሳ ምርት ግን ንቅንቅ አላለም። ከ50 ዓመት በፊት ከነበረው ምርት ምንም አልጨመረም። እና አሁን በሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሙገሳ ግጥም አማካኝነት የዓለም የዳጉሳ ምርት ከእንቅልፉ ይነቃል?
ዳጉሳ ድንቅ ነው፤ ረሀብም አይኖርም… ይላል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጥም።
የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሰዎች፣  ምርታማ የዳጉሳ  ዓይነቶችን አበጥረው  ምርማ ምርጥ ዘር ግኘት ከቻሉ፣ ስኬታማና ተስማሚ የአመራረት ዘዴም ከፈጠሩለት፣ መልካም ነው። ይቅናቸው።
እስከዚያው ግን፣ ለነስንዴና ለነ በቆሎ የተፈጠሩ ምርታማ ዘዴዎችና የምርጥ ዘር ዓይነቶች ላይ ማተኮር ነው የሚበጃቸው- እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገራት።
እንግዲህ የምንለውን አልን።  ግን ለጨዋታችን ምን ስም እንስጠው?
የኢኮኖሚ ስትራቴጂ  አስተያየት ወይም የልማታዊ ዘፈን ሂስና ዳሰሳ ልንለው እንችላለን።



Read 1034 times